August 1, 2010

ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሲዘከሩ

(በሔኖክ ያሬድ):- ሐምሌ 22 ቀን 2002 ዓ.ም. ሐሙስ በአዲስ አበባ በ"ባሕር" አቅጣጫ (በሰሜናዊ ምዕራብ አቅጣጫ) ጉለሌ አካባቢ ካንድ ዐውደ ጥናት ተገኝቼ በ10 ሰዓት አካባቢ ወደ ፒያሳ ሳመራ ቀልቤን የገዛ ክስተት ተመለከትኩ፡፡ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ራዲዮ ጣቢያ፣ የአሁኑን የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ፋኩልቲ እንዳለፍኩ፣ በርካታ ሰዎች የተሰባሰቡበት ትዕይንት እየተካሄደ መሆኑን አስተዋልኩ፡፡

የአቡነ ጴጥሮስን ሐውልት የከበቡትን ሰዎች መካከል ልብሰ ጵጵስና የለበሱ ከመሐል ኾነው በርቀት ሲናገሩ ይታየኛል፤ የሚኒባስ ታክሲ ሹፌሩን እንዲያወርደኝ አድርጌ ታዳሚውን ተቀላቀልኩ፡፡
ዕለቱ አቡነ ጴጥሮስ ከ74 ዓመታት በፊት በፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች ሰማዕት የኾኑበት ዕለት መሆኑንም አስታወሰኝ፡፡ ለካ ልብሰ ጵጵስና የለበሰው ወጣቱ ተዋናይ ነበር፡፡


ጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ከጻፉት "ጴጥሮስ ያችን ሰዓት" ከተሰኘች ተውኔት አንዷን ቃለ ተውኔት እያላት ነበር፡፡ ዱሮ ወጋየሁ ንጋቱ፣ በኋላም አብራር አብዶ የተወኑትን ወጣቱ በተራው ተረክቦ በአደባባዩ እያስተጋባ ይለው ነበር፡፡
"አዬ፣ ምነው እመብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከ መቼ ድረስ እንዲህ፣ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፣ ሰቀቀንዋን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺ እኮ ማንም የላት?"

ዝክረ አቡነ ጴጥሮስን ያዘጋጁት የአራዳ ጊዮርጊስና የጎፋ ገብርኤል አካባቢ ወጣቶች ናቸው፡፡ ወጣት ቡሩክ አበበ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ አምና በዕለቱ የጎፋ ገብርኤል ወጣቶች ጧት በጸሎትና ጉንጉን አበባ በማስቀመጥ፣ ከሰዓት ደግሞ የአራዳ ጊዮርጊስ ወጣቶች በመዝሙርና በጉንጉን አበባ አቡነ ጴጥሮስን ዘክረዋል፡፡

ዘንድሮ ግን በጋራ ዝግጅቶቻቸውን አቅርበዋል፤ ዘክረዋል፤ ከመዝሙርና ጸሎት ጉንጉን አበባም ከማስቀመጥ ባሻገር፣ የአቡኑን ታሪክና ተጋድሎ ብሎም ሰማዕትነት የሚያወሱ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች በተውኔትና በትረካ አቅርበዋል፡፡

በ1875 ዓ.ም. የተወለዱት ከኢትዮጵያ፣ የመጀመርያ ጳጳሳት አንዱ የነበሩት አቡነ ጴጥሮስ፣ "ጳጳስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ" ተብለው 21 አካባቢዎችን ያስተዳድሩ ነበር፡፡ 

የኢጣሊያ ፋሺስት በ1928 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን ባነሣ ጊዜ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከጦር ስፍራ ለመለየት ስላልሆነላቸው፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው የመርዝ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሥላሴ አርበኞች በመስበክም ይታወቃሉ፡፡

አርበኞች አዲስ አበባን በሁለት አቅጣጫዎች ከሰሜናዊ ምዕራብ (ባሕር) እና በደቡባዊ ምሥራቅ (ሊባ) አቅጣጫ ለመቆጣጠር ውጊያ በከፈቱበት ጊዜ የተማረኩት አቡነ ጴጥሮስ፣ ለፋሺሽት እንዲገዙ የኢጣሊያ መንግሥት ገዢነትንም አምነው አሜን ብለው እንዲቀበሉ ግፊት ቢያደርጉባቸውም፤ እምቢኝ ለሀገሬና ለሃይማኖቴ ብለው ለሰማዕትነት ያበቃቸውን የሞት ጽዋ ተቀብለዋል፡፡

ባለፈው ሐሙስ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና በኅብረ ቀለማት ጥብጣቦች ደምቆ በነበረው የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ዙርያ የነበረው ታዳሚም በመታሰቢያ ዝግጅቱ ባየው ትዕይንት ደስታውን ከመግለጽ አልተቆጠበም፡፡
ወጣቱ ተዋናይ፣ "አዬ፣ ምነው እመ ብርሃን?
ኢትዮጵያ ጨከንሽባት?"
እያለ ያቀረበው መነባንብን ሳዳምጠው የታወሱኝ፣ የተውኔቱንና የግጥሙን አንጓዎች እየከፋፈሉ አንድም እያለ የተረጐሙት፣ (የፈከሩት"፣ በመጽሐፋቸውም ያሰፈሩት በቅርቡ ያረፉት አቶ ብርሃኑ ገበየሁ ነበር፡፡

የሥነ ግጥም መምህርና ፈካሪ የነበሩት ነፍስ ኄር (ዘ ሌት) ብርሃኑ ገበየሁ፣ በቀለም አበባ ይዘከሩና "የጴጥሮስ ያቺን ሰዓት" ያዩበትን መነጽር በዚህች አጋጣሚ ማንሣት ወደድኩ፡፡ በ"የአማርኛ ሥነ ግጥም" መጽሐፋቸው ከላይ የተጠቀሰውን አንጓ እንዲህ ፈክረውታል፡፡

"ንባበ አእምሮ በተለይ ትራጀዲ ተብሎ በሚታወቀው የተውኔት ዘውግ የትራጀዲ ጀግና በመከራና በስቃይ ተወጥሮ ባለበት አፋፍ የሚያስበውንና የሚያሰላስለውን በተደራስያኑ ይሰማ ዘንድ በራሱ አንደበት እንዲናገር የሚያደርግ የተውኔት ብልሃት ነው፡፡

በእነዚህም ከላይ የተጠቀሱት ስንኞች ትራይጀዲያዊው ጀግና ሐዋርያው ጴጥሮስ ምሬታቸውን የሚያሰሙት፣ ልመናቸውን የሚያቀርቡት ለእመ ብርሃን ነው፡፡ የልባቸውን የሚነግሯት የአምላክ እናት በቅርብ፣ እንዲሁም በአካል ባትኖርም ተናጋሪው በእርሳቸውና ለእርዳታ በሚጠሯት ጻድቅ መካከል መንፈሳዊ ወዳጅነት እንዳለ እርግጠኛ ናቸው፡፡ እንቶኔ ዘይቤ እንደዚህ ሰማዕታትን፣ ጻድቃንን ወይም በሕይወት የሌሉ ጀግኖችን በሚጠቅስበት ጊዜ፣ አንባቢውና ገጣሚው በጋራ የሚያውቁት ነገር እንዳለ በመቁጠር ነው፡፡"

"ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት" የግጥም እውነታም ሃይማኖታዊ ትውፊትን ይጠቅሳል፡፡ የትውፊቱ ጭብጥ እመ ብርሃን ኢትዮጵያን ትጠብቅና ስለ ኢትዮጵያ ታማልድ ዘንድ፣ ኢትዮጵያ ከልጅዋ ከኢየሱስ የተሰጠቻት የአስራት አገሯ ናት የሚል ነው፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)