July 13, 2010

ለብፁዓን አበው የቅ/ሲኖዶስ አባላት የተላከ፦ "ቤተ ክርስቲያኔን ትጠብቋት ዘንድ - ለመንጋውና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ!"

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 13/2010)፦ "የሚከተለው ጽሑፍ ለብፁዓን አበው ጳጳሳት በየአድራሻቸው የተላከ ሲሆን የፀሐፊው ማንነት አልተገለጸበትም።ጽሑፉን ያደረሱንን አንድ "ደጀ ሰላማዊ" ከልብ እናመሰግናለን።
ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን
+++++++
"ቤተ ክርስቲያኔን ትጠብቋት ዘንድ - 
ለመንጋውና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ!"

ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከእስክንድሪያ ተሹሞ ከመጣው ከአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ጀምሮ ለ1600 ዓመታት የሀገራችንን ቋንቋ በማያውቁ ግብጻውያን ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት ስትመራ ቆይታለች፡፡

ይሁን እንጂ ከ1117 - 1157 ዓ/ም ነግሦ በነበረው በንጉሡ ቅዱስ ሃርቤ ገ/ማርያም ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከራሷ ልጆች በሚመረጡ ሊቃነ ጳጳሳት ትመራ የሚለው ጥያቄ በወቅቱ መልስ ሳያገኝ ከዘጠኝ መቶ ዓመታት ክርክርና ውጣ ውረድ በኋላ ውጤት አግኝቶ ግንቦት 21 ቀን 1921 ዓ/ም የመጀመሪያዎቹ አራት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት መነኰሳት መዓርገ ጵጵስናን ተቀብለዋል፡፡በኋላም ትግሉ ቀላል በማይባል መልኩ ቀጥሎ ጥር 6 ቀን 1942 ዓ/ም የሊቀ ጵጵስናው መንበር ከግብጻውያን እጅ ወጥቶ በኢትዮጵያዊ ሊቀ ጳጳስ ሊተካ ቻለ፡፡ (ዛሬ ምነው ሁሉም በቀረብን ማለታችንን አባቶቻችን አይዩ እንጂ)

የዘመናት ትግሏ ውጤታማ ሆኖ የመጀመሪያዎቹ አባቶች ጳጳሳት ሊቃነ ጳጳሳት ተብለው ከተሾሙ ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ጊዜያት ይበቃሉ ያለቻቸውን አበው እየመረጠች በመሾም ወንጌልን የማስተማር መሠረታዊ ተግባሯን ስትወጣ ቆይታለች፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ራሷን በራሷ ለማስተዳደር በፓትርያርክ ደረጃ የመተዳደር ነፃነቷን ከተቀዳጀችበት ከ1951 ዓ/ም ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በጵጵስና፣ በሊቀ ጵጵስና ከዚያም ከፍ ባለ በፓትርያርክነት ተሹመው የመረጣቸውን አምላክ በትጋት፣ በንጽሕና፣ በቅድስና ወንጌልን በማስተማር ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ተወጥተው "ሠናየ ገድለ ተጋደልኩ፤ በድርየኒ ፈጸምኩ፤ ወሃይማኖትየኒ ዐቀብኩ፤ እንከሰ ጽኑሕ ሊተ አክሊለ ጽድቅ ዘየዐስየኒ እግዚአብሔር" ማለትም "መልካም ገድል ተጋደልኩ ሩጫዬን ጨረስሁ ሃይማኖቴን ጠበቅሁ እንግዲህስ እግዚአብሔር የሚሰጠኝ የጽድቅ አክሊል ይጠብቀኛል" (ጢሞ 2ኛ 4.7) በሚል ተጋድሏቸውን ፈጽመው ብዙዎቹን ዓረፍተ ዘመን ገቷቸዋል፡፡

በመጀመሪያው ዘመን ለዚሁ ታላቅ ሐዋርያዊ አገልግሎተ የተመረጡት አበው በቅድስና፣ በትሕርምት፣ በትምህርት፣ በሥነ-ምግባር የተመሠከረላቸው የነበሩ ሲሆን ለግንዛቤም ግንቦት 25 ቀን 1921 ዓ/ም ጵጵስና መአረግ የተቀቡትን አባቶች የብፁዕ አቡነ አብርሃምን፣ የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን፣ የብፁዕ አቡነ ሚካኤልን፣ የብፁዕ አቡነ ይስሐቅን የሕይወት ታሪክ ማንበብ ዛሬ በእነርሱ እግር ለተተካችሁ ብፁዓን አባቶቻችን ታላቅ ትምህርት ነው፡፡ እንግዲህ ይህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የሊቃነ ጳጳሳት ችግረኛና ረሃብተኛ ሆና ከቆየች በኋላ ባገኘችው ነጻነት በሕይወት እስከሌሉት እስከ አሁን 209 ሊቃነ ጳጳሳት ተሹመውላታል (ተሹመውባታል)፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎች ሆነው የተሾሙት ሊቃነ ጳጳሳት በነበራቸው ትጋት ቤተ ክርስቲያኗ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበርን ከመሠረቱት ቀዳሚዋ እንድትሆንና እንዲሁም የመላ አፍሪካ አብያተ ክርስቲያን መሥራችና አባል አድርገዋታል፡፡

ይህንኑ አገልግሎታቸውን በትጋት በሚፈጽሙበት ወቅት የሚያጋጥማቸውን መከራ ሁሉ በአኰቴት በመቀበል አንድም የግል ሀብት ሳይኖራቸው ዘመዴ ወገኔ ብለው ሳይለዩ ሁሉን በፍቅር በመቀበል መከራውንም ደማቸው እስከማፍሰስ ደርሰው ሰማዕትነትን በመቀበል ሁሉን ታገሰው ይህችን ቤተ ክርስቲያንና ሀገሪቱን አስረክበውናል፡፡

ብፁዓን አባቶቻችን፦ ታዲያ ይህንን ስንል በብዙ ውጣ ውረድ ትለፍ እንጂ እስከ ቅርብ ጊዜ መከራው ሲመጣ የነበረው ከውጪ ነበር፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ግን ችግሩ ከውስጥ የሚመነጭ የቅድስና ጉድለት ሆኖባታል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ዘኢጾረ መስቀለ ምትየ ኢይክል ይጸመደኒ” መስቀሉንም ተሸክሞ ከኋላዬ የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም (ማቴ 3.38-10.24 ማር. 8.34) እንዳለው ቅዱስ ፓትርያርኩ ቤተ ክርስቲያኗ ላይ እያደረሱ ያለውን ችግር ታውቃላችሁ ትረዳላችሁ በሕግ ታግላችሁ ማስተካከል ባትችሉ እንኳ በጾም በጸሎት ተፀምዳችሁ ወደ እግዚአብሔር በማመልከት ማስተካከል ትችሉ ነበር፡፡

ነገር ግን በሕግ ለመታገል ትፈራላችሁ። ምክንያቱም በራሳችሁም አትተማመኑም፤ ከጥቂቶቻችሁ በቀር፡፡ አዎን ጌታ በወንጌል “ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም” (ማቴ. 5.20) ብሏል እናንተ እንኳን መብለጥ መተካከል ስላልቻላችሁ በዚህ ዓለም በወታደር አለንጋ እየተገፋችሁ እየተዋረዳችሁ ነው፡፡

ብፁዓን አባቶቻችን፦ አሁን ግን በዓለም ውስጥ ያላችሁ ኃላፊነታችሁን በጥብዐት የመወጣት አቅማችሁ የጠፋና የደከመ የዓለም ብዕል ያታለላችሁ እውነትን ተናግሮ የመሞት ዓላማችሁ የደከመ ሆናችሁ ስለምናያችሁ በአማኞች ልብ ውስጥ የሞታችሁ የሃይማኖት መሪዎች ሆናችሁ በእኛ በአገልጋዮች ልብ ውስጥ ግን መሞታችሁን ያልተገነዘባችሁ ሊቃነ ጳጳሳት ሆናችሁብናል፡፡

አንድ ታሪክ እናስታውሳችሁ። በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው የቁስጥንጥንያ ንጉሥ በግብጽ የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የነበረውን ቅዱስ አትናቴዎስን አባሮ የራሱን ወዳጅ በመንበረ ማርቆስ ባስቀመጠ ጊዜ ሕዝቡ አዘነ፤ ወዲያውም ሕዝቡ አዲሱን ሊቀ ጳጳስ በልቡ እንደሞተ አድርጎ በማሰብ ሕዝቡ በጸሎቱ ጊዜ አትናቴዎስን መጥራት ጀመረ። በታላላቅ በዓላት ሕዝቡ በቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባል። አዲሱ ሊቀ ጳጳስም ይመጣል፤ ሕዝቡም ሊቀ ጳጳሱ ተናግሮ እስኪጨርስ ቆይቶ ወደ ቤቱ ይሄዳል። ይህንን ወቅታዊ ታሪክ የጻፈው ግሪካዊ ታሪክ ጸሐፊ አንዱን ምዕመን ጠጋ ብሎ “ይህን ሊቀ ጳጳስ ካልተቀበላችሁት ለምን ሲያስተምር ትሰሙታላችሁ” ብሎ ቢጠይቀው “ወዳጄ እኛ በመስተዋቱ በኩል የሚታየውን እንጂ መስተዋቱን ትተነዋል” ሲል እንደመለሰለት በታሪካዊ ጽሑፉ አስፍሮታል፡፡

በዓለም ካለው ሌላም ምሳሌ ለማከል የምዕራብ አፍሪካው ኤየር አፍሪክ (የአየር መንገድ ቢሮ) ሠራተኞቹ እየጣሉት ሲሄዱ፣ ደንበኛው ሲሸሸው፣ ባለሙያዎቹን ሲነጠቅ፣ አስተዳደሩ ሲበላሽ፣ በአጠቃላይ እያሽቆለቆለ ሲሄድ ድርጅቱ እየሞተ ነበር። ነገር ግን መሞቱን የተረዳ አልነበረም። በመጨረሻም አንድ ቀን አውሮፕላኖቹ ወደየሀገሩ በረው ሳይመለሱ ሠራተኞቹም ለምሳ እንደወጡ በድንገት ሥራ ቆመ። ያኔ ነበር አመራሩ/ ማኔጅመንቱ መሞቱን የተረዱት፡፡

ብፁዓን አባቶቻችን፦ የእናንተና የዚህች ገናና ቤተ ክርስቲያንም ጉዳይ ይህንኑ እየመሰለ ነው፤ እባካችሁ ኃላፊነታችሁን ተወጡ፤ እውነት ተናገሩ እውነት ሥሩ ለእውነት ኑሩ እውነት ተናግሮና እውነት ሠርቶ ማለፍ ከሰማያዊ አባታችሁ ዋጋ ታገኛላችሁ ለሀገርና ቤተ ክርስቲያንም ለታሪክም ይጠቅማል፡፡

እስኪ መለስ ብለን ነገሮችን እናጢን። በሕገ ቤተ ክርስቲያን ምዕ. ሁለት አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 እንደተጠቀሰው ቅዱስ ሲኖዶስ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ከፍተኛ ሥልጣን ባለቤት ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም እናንተ ናችሁ። ይህም አባልነት የዕድሜ ልክ መሆኑ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 3 የተረጋገጠ ስለሆነ ሊነካችሁ የሚችል የለም፡፡

እናንተ ጠንካሮች ከሆናችሁ፣ በእግዚአብሔር የምታምኑ ከሆነ፣ የተመረጣችሁበትንም ካወቃችሁ "ቤተ ክርስቲያኔን ትጠብቋት ዘንድ እናንተን ጳጳሳት አድርጐ ለሾመባት ቤተ ክርስቲያን ለመንጋውና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ" (የሐ. 20.28) ያለውን ከሟቹ ከብፁዕ አቡነ እንድርያስ ሕይወት መማር ትችላላችሁ፡፡ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ በዚያ በአስፈሪው የደርግ ዘመን እውነትን ለመናገር ያልፈሩ፣ በመናገራቸው ግን የተዋረዱ ሳይሆን የተከበሩ አባት ነበሩ፡፡ በወቅቱ ምንም ማድረግ ስላልቻሉ ከቀሳፊ መልአክ ይሰውረን ብለው በማሳረጋቸው ጡረታ እንዲወጡ አድርገዋቸው ነበር። ግን የያዙት እውነት ስለሆነ፣ ሃይማኖት ስለነበራቸው፣ የመከራውን ዘመን በጸሎት አሳልፈው ወደ ሀገረ ስብከታቸው ተመልሰው በሰላም አርፈዋል፡፡ ዛሬ እነርሱ ሞተዋል። ስማቸው ግን ሕያው ነው።

እስኪ እያንዳንዳችሁ ሕይወታችሁን ከእነዚህ አባቶች ጋር አነጻጽሩ፡፡ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ሲኖዶስ የወሰነውን የሻረው የለም። እነርሱም "እኛና መንፈስ ቅዱስ ወስነናል" እያሉ ውሳኔያቸውን ያፀኑ ነበር። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በቤተሰብና በአድርባዮች የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና ኃላፊነት የማይሰማቸው፣ ማን እንደጠራቸው የማይታወቁ መንደርተኞች ተሰባስበው ቅዱስ ሲኖዶስ የመረጠውንና የሾመውን የቅዱስ ሲኖዶስን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሻሩት፡፡ ከሁሉ በላይ የሚገርመው የቅዱስ ሲኖዶስም፣ የዚህ የጥፋት ግሩፕም ሊቀ መንበሩ ፓትርያሪኩ መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ የሆነውንና የሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀስ 13 ላይ የሰፈረውን ደንብ በመተላለፍ የአንድን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አገዱ፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን "ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነውን ውሳኔ ማንም ሊሽር አይገባውም፤ መጀመሪያ ሕጉ ይከበርና ከዚያ በኋላ ነው የምንወያየው" ብሎ የጠየቀ፣ የተከራከረ ያለ አይመስለንም። ቢኖርማ ኖሮ ውሳኔውና ሕጉ ይፀና ነበር፡፡ በእርግጥ ጥቂቶቹ አባቶች መናገራቸውን እናውቃለን። ነገር ግን ሌላውስ ሊቀ ጳጳስ አይደለም? የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አይደለም? የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አያሳስበውም? ሃይማኖታዊ ዓላማ የለውም? "ዝም ብል የሾመኝ እግዚአብሔር ይታዘበኛል" ብሎ አያስብም? ወይስ ሁሉ ቤተሰብ አለውና ለቤተሰቡ ያስባል እንበል? ወይስ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚለው ሥም ተሠርዟል?

ሌላው ደግሞ የተወሰናችሁ አባቶች ቅዱስ ፓትርያርኩ ምንም ቢያጠፉ ላለመናገር ከቅዱስነታቸው ጋር ቃል ኪዳን ተጋብታችኋል ይባላል። ይህስ ተገቢ ነው? ቤተ ክርስቲያን ስትጠፋ አልናገርም ተብሎ ቃል ይሰጣል? የሊቀ ካህናቱ የዔሊን ውድቀት አያስከትልም? እያንዳንዳችሁስ በሊቀ ጳጳስነታችሁ ብቻ በቤተ ክርስቲያኗ ጉዳይ ተጠያቂ እንደምትሆኑ አታስቡም? ነገ ቅዱስ ፓትርያርኩ በሞት ሲለዩ ሁሉ እንደሚገለጽና ተዳፍኖ የሚቀር ነገር እንደማይኖር አታስቡም? ከእናንተ በላይስ ለቤተ ክርስቲያን የመከራ ቀን ደራሽ ሌላ ይኖር ይሆን? የአንድ ሰንበት ት/ቤት ተማሪ ያህል እንኳ አትቆረቆሩም? ዝምታ ያዋጣል? እኔን አይመለከተኝም ማለትስ ይቻላል? የወንድማችሁ የአቡነ መልከ ጸዴቅ ሞት ሞታችሁ አይደለም? ወይንስ ወንድም አታውቁም? እናንተስ ቋሚ ናችሁ? ባለፈው ዓመትስ ወንድሞቻችሁ ተደብድበው እናንተ መሰብሰብና ውሳኔ መስጠት ነበረባችሁ?  ወንድማችሁስ ታግተው እናንተ የት ሄዱ ማለት አልነበረባችሁም? ወንድሞቻችሁን የደፈረ፣ የደበደበ፣ ማን እንደሆነስ ማወቅ አልነበረባችሁም? እናንተስ አትሞቱም? አትደፈሩም? ነገ በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊትስ አትቀርቡም? መልስስ አላችሁ? ቤተ ክርስቲያኗ ራቁቷን ቀርታ የቤተሰብና የሌቦች መናሐርያ መጫወቻ መሆኗ አይገዳችሁም?

“የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘለዓለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና የሚታየው የጊዜው ነውና የማይታየው ግን የዘለዓለም ነው” (2. ቆሮ.4.16)፡፡

ምን ስሕተት አለ ለምትሉ እስኪ የምታውቁትንና የቅርብ ጊዜውን እናስታውሳችሁ፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ከመስመር መውጣት ችግር ምንድን ነው? ጥፋቱ በግልጽ ተቀምጦ የሊቀ ጳጳሱ ጉዳይ ለምን ውሳኔ አላገኘም? ለምንስ ያለ ሊቀ ጳጳስ እንዲቀመጥ አስፈለገ? የሀገረ ስብከቱ ገንዘብ በአሁኑ ወቅት በነበረበት ሁኔታ አለ? ዛሬ በሀገረ ስብከቱ ምን እየተሠራ ነው? እንዲያጣራ የተመደበው ኮሚቴ ምን እያደረገ ነው? በደመወዝ ተቀጣሪ አልሆነም? ያለጨረታ ቤት አልተሰጠውም?  ይህ ሁሉ ምን ተፈልጐ ነው? የድራፍት (የመጠጥ) ቡድን ማደራጀት ለምን አስፈለገ? ዛሬ ገንዘብ የሌለው የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ይቀጠራል? እናንተስ በአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት እንዳትሳለሙ እንዳታስተምሩ እገዳ አልተጣለባችሁም?

ሌላው የቅዱስ ፓትርያርኩ ስዕል (ሐውልታቸው ሲተከል) በየደብሩ በግድ ሲቆሞ ምዕመናንን ግራ አላጋባም? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደምናነበው በሕይወት እያለ በአምባገነንነት ሐውልቱን አቁሞ ስገዱልኝ ያለ የባቢሎኑ ንጉስ ናቡከደነፆር ነው፡፡ ለመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ዝም ብሎ ሊመለከት ይገባዋልን? አዎ አታፍሩም ሄዳችሁ ትመርቁ ይሆናል? (በርግጥም ሄደው መርቀዋል)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዙሪያዋ ለሚደረገው፤ እየተደረገ ላለውና ለሚሆነው ሁሉ የራሷ የሆነ ሕግ፣ ሥርዓትና ትውፊት አላት፡፡ ይኸ ባሕርይዋ የሚመነጨው ተቋማዊ አደረጃጀትዋ መንፈሳዊ ተልእኮ ያነገበ በመሆኑ ነው፡፡ የትኛውም ዓለማዊ ተቋም (Secular Institution) ለሆነው እና እየሆነ ላለው ፍጹም ባይሆንም ጉድለት ያለበትን ሕግና ሥርዐት ሊያበጅ ይችላል፡፡ ለሚሆነውም ከሆነውና እየሆነ ካለው በመነሣት መላምታዊ ማዕቀፍ (Frame) ሊያስቀምጥ ይችል ይሆናል እንጂ ፍጹም ሆኖ ሊያስቀምጥ አይችልም፡፡ ሁሉን ሊመረምርበት የሚያስችለው መንፈሳዊነት እና ሐዋርያዊነት ስለሚጎድለው ነው፡፡

 ከሆነው፣ እየሆነ ካለውና ከሚሆነው ውስጥ ሕግ፣ ሥርዐት፣ ከተሠራላቸው አንዱ ሐውልት ማቆም ነው፡፡ በቤተክርስቲያኗ ሥርዓት መሠረት እንኳን በሕይወት ላለ ሰው ይቅርና ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየ ሰው ሐውልት እንዲሠራለት የሚያዝዝ ድንጋጌ የለም፡፡ በአጸደ ነፍስ ላሉት ቅዱሳን መታሰቢያነት ገድል ይጻፋል፣ መልክ ይደረሰል፣ ሥዕል ይሳላል፣ ጽላት ይቀረስላቸዋል እንጂ ሐውልት አይቆምላቸውም፡፡ እንደ ጣዖት ማምለክ ስለሚያስቆጥር ነው፡፡ ይኸ ዓይነቱ ሥርዐት ከምዕራባውያነ የጣዖት አምልኮ የተወረሰ፣ በቤተክርስቲያን ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ፣ የአርጤምስስ ጣዖት በኢትዮጵያ ቆመ እንዴ የሚያሰኝ ነው ምንም እንኳን በተለምዶ ከጣሊያን ወረራ ወዲህ አብሮ የገባው ሐውልት ማቆም የተለመደ ቢሆንም በቤተክርስቲያን አጸድ ውስጥ እንደ ሐውልት ያለ የተቀረጸ ምስል ማቆም የተከለከለ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ቅዱስ ሲኖዶስም ጳጳሳት ከዚህ አለም በሞት ቢለዩ እንኳን ሀውልት ሊቆምላቸው እንደማይገባ መወሰኑ ይታወቃል፡፡

     በመሆኑም እየተሻረ ያለው የራሳችሁ ውሳኔ አይደለም ወይ? እየሆነ ላለው ሁሉ ሥርዐት ያላትን ሐዋርያዊትና መንፈሳዊት ቤተክርስቲያን ከቀኖና ቤተክርስቲያንና ከሥርዐተ አበው ውጭ ሐውልት ለማቆም መነሣት የቤተክርስቲያኗን ክብር መዳፈር ብቻ ሳይሆን የፓትርያርኩ - ፕትርክና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባው ነው ለፓትርያርኩ ሐውልት እናቁም ብለው የተነሡት ሰዎችስ ይኸን ያጡታል? እነዚህ ሰዎችም ለፓትርያርኩ ሐውልት ለማቆም የተነሡት እርሳቸውን ከመውደድ ወይም ቅድስናቸውን ለማረጋገጥ አይደለም፡፡ ቀኖና እና ሕገ ቤተክርስቲያን በመጣስ የሚገኝ ቅድስና እና ፍቅር የለምና፡፡ ምን ይሆን ተልዕኳቸው?

ከሁሉ አስፈሪው ደግሞ የፕሮቴስታንት እምነት ከፍተኛ አራማጅ ለሆነና በይገባኛል ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር ለብዙ ዓመታት ተከራክሮ በፍርድ በተሸነፈው የቀድሞው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ተሰጥቶ በአሁኑ ወቅት የእምነቱ ማራመጃ ሆኖ ይገኛል። ይህ አያሳዝናችሁም? ይህ እንግዲህ የሃይማኖት ጉዳይ ነውና ቅ/ሲኖዶስ ምን ይላል? ኧረ ለመሆኑ እናንተ ስታስተምሩን "ድንኳን የሆነውን ምድራዊ መኖርያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እንዳለን እናውቃለን" ብላችሁን የለ? ታዲያ ይህንን ሕንፃ እናንተን አያካትትም ማለት ነው? (2.ቆሮ.5.1)

ቤተ ክርስቲያኗ የበላይ ሆና የምትመራው የኢየሩሳሌም ድርጅት ለወ/ሮዋ ሲባል ፈርሶ ለሦስት እንዲከፈል ተደርጎ ቀራንዮ በሚል ለተሰየመው ቅዱስ ፓትርያርኩ ቢሮ ሰጥተው የበላይ ኃላፊ በመሆን መገነጣጠላቸው ቤተ ክርስቲያኗን አያዋርድም?

በደቡብ አፍሪካ ለገዳም ምሥረታ፣ በጋምቤላ ለመንፈሳዊ ት/ቤት በሚል በሚሊዮኖች የተሰበሰበው ገንዘብ የደረሰበት ታውቋል? ጉዳዩን በቅዱስ ሲኖዶስ ሊወሰን አይገባውም ነበር? ገንዘብ አሰባሰቡና አቀማመጡስ ሕጋዊ ሊሆን አይገባውም?

በየአድባራቱ ካህናት ተገደው የሚገዙት የፓትርያርኩ ዶክመንተሪ ፊልም ሁኔታው ተገቢ ነው ብሎ ቅዱስ ሲኖዶስ ያምናል? አስፈላጊ ከሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ሊያዝና ሊወሰን አይገባውም ነበር? በአሁኑ ጊዜ የአብነት ትምሕርት ቤቶች፣ ገዳማት፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት፣ የከፍተኛ ትምሕርት ቤት ምሩቃን ደቀ መዛሙርት በበጀት እጥረት በመዘጋትና በመበተን እንዲሁም በረሐብ አለንጋ እየተገረፉ ባሉበት ለፓትርያርኩ የ3.3 ሚሊዮን ብር መኪና ከአድባራት በማስገደድ ገዝታችሁ ሸልሙኝ ማለት ምን ይሆን? አባቶች ግን ሐዋርያው እንዳስተማረን የምናውቀው “ጻድቃንስ ዔሉ ገዳማተ በዘብድወ ጠሊ ወበ ሐሜላት” ጻድቃንስ ሁሉን እያጡ ወይም ትተው የበግና የፍየል ለምድ ለብሰው ዞሩ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በከርሰ ምድር ተቅበዘበዙ (ዕብ. 1.31-38)

በአጠቃላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣን የተሰበረ ሸንበቆ መሆኑ አያሳፍራችሁም? ቅዱስ ሲኖዶስ በእናንተ ዘመን ተራ መሆኑ አይቆጫችሁም? እስከመቼስ ትፈራላችሁ? በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ ተንቃችሁ መጨረሻችሁ አይናፍቃችሁም? ወይስ ሌላ ዓላማ አላችሁ?

ጉዳዩን ከሥሩ በማጣራት ችግሯን ለመቅረፍ ጥረት እንድታደርጉ ቢሆን፣ ካልሆነ ግን በሰውም፣ በእግዚአብሔርም፣ በታሪክም ተወቃሽና ተጠያቂ ከምትሆኑ ዛሬውን በራሳችሁ እንድትወስኑ ዝቅ ብለን በትሕትና ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

7 comments:

ማህበረ፡ክርስቲያን said...

ጤና፡ይስጥልኝ፡ወገኖቼ፡ሰላም፡ከሁላችሁ፡ጋር፡ይሁን
በመሰረቱ፡ሁሉንም፡በጥሩ፡አገላለፅ፡አስቀምጣችሁታል፡የምጨምረው፡የለም፡፡አንድ፡ለአባቶች፡የምመክረው፡ነገር፡ቢኖር(መካሪ፡የመሆን፡ብቃት፡ኖሮኝ፡ወይም፡አባቶች፡አያውቁትም፡ብዬ፡ሳይሆን፡ምናልባት፡ዘንግታችሁት፡ከሆነ፡ብዬ፡ነው)በቤተ፡ክርስቲያናችን፡መንገደ፡ሰማይ፡የሚባል፡ፅሁፍ፡አለ፡አንብቡት፡፡
ፈጣሪ፡ለሁላችንም፡መልካም፡ልቡና፡ይስጠን፣ይሄን፡
የከፋ፡ጊዜ፡ያሳጥርልን፣የቤተክርስትያንን፡ትንሳኤ፡
ያሳየን፣
የአምላክ፡ቸርነት፡የእመቤታችን፡አማላጅነት፡
አይለየን!!!

Addisu said...

አባታቸን ትግሎት በስማይም በምድርም የማይረሳ ነው። ለበተ ክርስትያን ያላት ግን አርስዎ ብቻ መሆኑ ይገርማል። ለሎቹ ጳጳሳት የፈሩት ምን ይሆን?? ስልጣናቸወ ወይሰ ደሞዛችወ አንዳይገፈፍ። ማፈሪያዎቸ መሆናቸወን የተረዱ አይመስልም። ሀዝቡ ግን ምን ያህል አንቅሮ አንደተፋቸው ያውቁ ይሆን።ብተ ክርስትያንን ክመዋረድ ካላዳኑ ለሆዳቸው ይሆን ጵጵስናን የተቀበሉት?? አርስዎ ግን ይበርቱ። ኧንድ ቢሆኑም ብዙ ኖት። ትውልድና ታሪክ ሲያስታውሶት ይኖራል።

awudemihiret said...

egzioooooooooooo.yehualegnaw zemen min ayinet gud talebin?yeminikorabachew sayihon yeminafribachew abatoch yifeteru?Abetu maren!!!!!!!!!!1

Anonymous said...

አባታችን እግዚአብሔር እድሜዎትን ያርዝምልን፡ ምንም አንድ ብቻዎትን እንኳን ቢሆኑም ብዙ ነዎት፡ ከብዙ ዉሸት ጥቅቷ እውነት ትበልጣለች እና እባከዎትን ይበርቱ እግዚያብሔር ከእርሶ ጋር ነው።

paulos Yenager said...

ጊዜ ያመጣዉን ጊዜ ይመልሰዉ።

መቼም ጊዜ የእገዚአብሔር ገንዘብ ቢሆንም ዘመነኞች ጊዜ በሰጣቸዉ ዕድል መጠቀማቸዉ አይቀሬ ነዉ። ጊዜ ያነሳዉን ጊዜ ይጥለዋልና የጊዜ ቁማርተኞችን ለጊዜ መተዉ ብልህነት ነዉ። ጊዜ የሾመዉን ጊዜ እስኪጥለዉ ተብሎ የሚተዉ ታሪክ ባይኖርም እነ ዺ/ን በጋሻዉንና ወ/ሮ እጅጋየሁን በአባታቸዉ በአቡነ ጳዉሎስ ጥላ ሥር አሰባስቦ ቤተ ክርስቲያንን ሲያዋርዱ ለማየት መብቃትጊዜ ያመጣዉ ነዉና ለጊዜዉ ለቀቅ ማድረግ ያሻል። ጊዜ ነዉና ያነሳቸዉ ጊዜ ያሰያናልና እንረጋጋ ። ለእነርሱ ከንቱ የልጅ ጨዋታ መላ ስንሻ ለቤተ ክርሰትያናችን መሥራት የሚገባንን መልካም ነገር እንዳንተዉና እንዳንዘናጋ። የሚያሳዝነዉ ግን የዓለም አብያተ ክርስቲያን ፕረዜደንትፓትሪያርካችን አደግን የሚሏትን እናት ቤተ ክርስቲያንና ያፈራቻቸዉን ቅዱሳን ናቅ አድርገዉ መተዋቸዉ ነዉ። ያ ሁሉ ባይሆን ኖሮ አቦ አቦ ባሏቸዉ ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሲጣስ ዝም ባላሉም ነበር። "በመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች" ጸጋቸዉን የተገፈፉት ብጹዕነታቸዉ ገና ቁስላቸዉ ሳይሽር በሐዉልት ምረቃ ለሙት መታሰቢያነት ባልበቁም ነበር። ይቆየኝ። ብዕሩ ይናገር

Anonymous said...

ጊዜ ያመጣዉን ጊዜ ይመልሰዉ።

መቼም ጊዜ የእገዚአብሔር ገንዘብ ቢሆንም ዘመነኞች ጊዜ በሰጣቸዉ ዕድል መጠቀማቸዉ አይቀሬ ነዉ። ጊዜ ያነሳዉን ጊዜ ይጥለዋልና የጊዜ ቁማርተኞችን ለጊዜ መተዉ ብልህነት ነዉ። ጊዜ የሾመዉን ጊዜ እስኪጥለዉ ተብሎ የሚተዉ ታሪክ ባይኖርም እነ ዺ/ን በጋሻዉንና ወ/ሮ እጅጋየሁን በአባታቸዉ በአቡነ ጳዉሎስ ጥላ ሥር አሰባስቦ ቤተ ክርስቲያንን ሲያዋርዱ ለማየት መብቃትጊዜ ያመጣዉ ነዉና ለጊዜዉ ለቀቅ ማድረግ ያሻል። ጊዜ ነዉና ያነሳቸዉ ጊዜ ያሰያናልና እንረጋጋ ። ለእነርሱ ከንቱ የልጅ ጨዋታ መላ ስንሻ ለቤተ ክርሰትያናችን መሥራት የሚገባንን መልካም ነገር እንዳንተዉና እንዳንዘናጋ። የሚያሳዝነዉ ግን የዓለም አብያተ ክርስቲያን ፕረዜደንትፓትሪያርካችን አደግን የሚሏትን እናት ቤተ ክርስቲያንና ያፈራቻቸዉን ቅዱሳን ናቅ አድርገዉ መተዋቸዉ ነዉ። ያ ሁሉ ባይሆን ኖሮ አቦ አቦ ባሏቸዉ ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሲጣስ ዝም ባላሉም ነበር። "በመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች" ጸጋቸዉን የተገፈፉት ብጹዕነታቸዉ ገና ቁስላቸዉ ሳይሽር በሐዉልት ምረቃ ለሙት መታሰቢያነት ባልበቁም ነበር። ይቆየኝ። ብዕሩ ይናገር

Anonymous said...

'mane tekel fares'

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)