July 30, 2010

የቅዱስነታቸውን ሐውልት በማቆም የቅድስት ማርያም ስብከተ ወንጌል ማኅበር ከፍ ያለ አስተዋፅኦ አድርጓል›› (ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል)

  •  ፓትርያርኩ ቁልቢ አልሄዱም፣
(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 29/2010)፦ የብፁዕ ወቅዱስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን 18ኛ ዓመት በዓለ ሢመት ‹‹በልዩ ሁኔታ ለማክበር›› በሚል በተቋቋመው የበዓል አከባበር ኮሚቴ፣ ከ300‚000 ብር በላይ ወጪ በማድረግ በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ዐጸድ ውስጥ የቆመውን እና ሐምሌ አራት ቀን 2002 ዓ.ም ፓትርያሪኩ እና ዐሥራ አንድ ብፁዓን አባቶች (ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ፣ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም፣ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ያሬድ፣ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ስምዖን፣ ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ፣ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል) በተገኙበት የተገለጠውን የፓትርያርኩን የ‹ምስክርነት ሐውልት› ለማሠራት ‹‹የቅድስት ማርያም ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ማኅበር››  ‹‹ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ያደረገ የቤተ ክርስቲያን ማኅበር›› መሆኑን ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ተናገሩ፡፡

አቡነ ፋኑኤል ይህን የተናገሩት ሐምሌ 19 ቀን 2002 ዓ.ም ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ አለወትሯቸው በተገኙበት በአዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በተከበረው የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ነው፡፡ ‹‹ማኅበሩ በቅዱስነታቸው ዕውቅና የተሰጠው የእነ በጋሻው ማኅበር ነው፤››  ያሉት አቡነ ፋኑኤል ማኅበሩ በፓትርያርኩ ሐውልት ሥራ እና ተከላ ላይ ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ ማድረጉን ግልጽ አድርገዋል፡፡ አቡኑ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ስለነበጋሻው ቡድን የሚያሰሙትን የድፍረት መወድስ እና የምእመናኑን ሚና የሚያናንቅ አሰልቺ ንግግራቸውን የተከታተሉ በበዓሉ ላይ የተገኙ የደጀ ሰላም ምንጮች ኹኔታውን ‹‹የዐዋጁን በጆሮ›› ብለውታል፡፡

ከ‹ምስክርነት› ሐውልቱ መገለጥ በኋላ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ የሐውልቱን ሐሳብ የማመንጨት ቅድምናው የማፊያው ቡድን ‹‹ስውሩ ጸሐፊ›› ዘሪሁን ሙላቱ ሲኾን ምክንያቱ ደግሞ የዲያቆን በጋሻው ደሳለኝ ውትወታ መኾኑ እየተነገረ ነው፡፡ ይኸውም ዲያቆን በጋሻው እውነተኛ ማንነቱ በተለያዩ ቀናዒያን ምእመናን ከተጋለጠ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ እና በዋና ሥራ አስኪያጁ በወጣ ደብዳቤ ከታገደ እንዲሁም ‹መጋቤ ሐዲስ› በተሰኘው ያልተገባ ሹመቱ ሳቢያ በፓትርያርኩ ሳይቀር በጉባኤ ከተገሠጸ በኋላ የገጠመውን ክስረት በአቋራጭ ለመቀልበስ የቀድሞ ባላጋራውን ምንደኛውን ዘሪሁን ሙላቱን ‹‹ከጉድ አውጣኝ›› ይለዋል፡፡ ጥቅም ላሳዩት ሁሉ(ለመሐመዳውያን ሳይቀር) የጥፋት ብዕሩን ከመምዘዝ፣ ፓትርያርኩን እና ብፁዓን አባቶችን የሚያዋርድ ተግባር ከመፈጸም ወደ ኋላ የማይለው ይኸው ቅጥረኛ ግለሰብም ቀን እንዲሰጠው ጠይቆ ሲያስብበት ይቆያል፡፡ በመጨረሻም ዲያቆን በጋሻው የፓትርያርኩን አፍቃሬ ርእስ(መወድስ) የመኾን ከልክ ያለፈ ፈቲው ተጠቅሞ ‹ከጎጉል ጎልጉዬ አገኘኹት› ያለውን የሐውልት ሥራ ዐይነቶች በመዘርዘር ለአቡነ ጳውሎስ ‹የምስክርነት› ሐውልት እንዲሠራላቸው ሐሳብ እንዲያቀርብ፣ ለአፈጻጸሙም ራሱ ዘሪሁን ከሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ጋራ፣ ዲያቆን በጋሻው ደግሞ ከወ/ሮ እጅጋየሁ ጋራ ተመካክረው ለማስወሰን ይስማማሉ፡፡

የፓትርያርኩን 18ኛ ዓመት በዓለ ሢመት ‹‹በልዩ ኹኔታ እናከብራለን፤›› በሚል ሽር ጉድ ሲሉ የነበሩት፣ በተለይም ቀደም ብሎ በወንጀል ከሚፈለጉበት የሕግ ተጠያቂነት ተሰውረው የቆዩት ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒም በሚያስተዳድሯት ቁጥጥር የሌለባት አጥቢያ ቅጽር ውስጥ የአቡነ ጳውሎስን ምስል በ170‚000 ብር (እርሳቸው 400‚000 ብር ነው ያወጣኹት ብለው ሪፖርት ቢያቀርቡም) አሠርተው በማስመረቅ መሥዋዕተ እርያ የማቅረብ ‹ልምድ› ያገኙ በመኾናቸው የፓትርያርኩን ሐውልት እስከ በዓለ ሢመቱ መዳረሻ ቀን ድረስ ሰውረው በድብቅ በማሠራት እና በዋዜማው በመግለጥ ከተጠያቂነት ለመሸሽ ተጠቅመውበታል፡፡

ዲያቆን በጋሻውም በተጋለጠው እውነተኛ ማንነቱ የተነሣ የደረሰበትን ክስረት ለመሸፈን፣ በአበው ጳጳሳት ጉባኤ ፊት ኦርቶዶክሳዊነትን በመፃረር ሲፈጽማቸው ለቆዩት ድርጊቶቹ ገሥጸው፣ ‹መጋቤ ሐዲስ› የተባለበትን ቀድሞም በአቡነ ፋኑኤል አለግባብ የተሰጠውን ማዕርግ ገፍፈው ‹አቶ› አሰኝተው ባስለቀሱት እና ባዋረዱት አቡነ ጳውሎስ ፊት ‹ሞገስ› ለማግኘት፣ ስለ ድካሙ ‹‹ፍሬም›› በበዓለ ሢመታቸው የራት ግብዣ ምሽት በበዓል አከባበር ኮሚቴ መዘጋጀቱ የተገለጸለትን የምስክር ወረቀት ከግብር አበሮቹ ጋራ መቀበሉ ይታወሳል፡፡

በተያያዘ ዜና በርእሰ አድባራት ቁሉቢ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ እየተገኙ በዓሉን የሚያከብሩት ፓትርያሪኩ የዚህን ዓመት የቅዱስ ገብርኤል በዓል ለማክበር ያመሩት ግን ወደ አዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ነበር፡፡ ቅዱስነታቸው በጉዟቸው ሻሸመኔን አልፈው ልዩ ስሙ ጥቁር ውኃ  እየተባለ በሚታወቀው የአዋሳ ከተማ መግቢያ ላይ ሲደርሱ በእነ ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ፣ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ እና በተለይም የማፊያው ቡድን ተባባሪ በመኾን የሀገረ ስብከቱን የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ በተሐድሷዊ ስልት ለመቆጣጠር እና የግለሰቦችን ኪስ ለማደለብ በሚሠራው ‹‹ማኅበረ ተስፋ ኪዳነ ምሕረት›› እየተባለ በሚጠራው አካል ተቀስቅሰው የተሰለፉ ወጣቶች ከሌላው ጊዜ በበለጠ በአቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና የተለየ ሥራ መሠራቱን የሚያወሱ መፈክሮችን በማንገብ ተቀብለዋቸዋል፡፡ ሐምሌ አራት ቀን በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በተከናወነው የፓትርያርኩ ‹የምስክርነት ሐውልት› መገለጥ ወቅት ራሱን ‹‹የቅድስት ማርያም ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ማኅበር›› እያለ የሚጠራው የእነ በጋሻው  ቡድን ባዘጋጀው መድረክ ላይ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ባቀረቡት የበዓል አከባበር ኮሚቴ ‹ሪፖርት› ተመሳሳይ ሐሳቦችን ያዘሉ የቅስቀሳ ንግግሮችን በማሰማት ፓትርያርኩን ለጉባኤ ወደ አዋሳ መጋበዛቸው ይታወሳል፡፡

በማግሥቱ በገዳሙ በተከናወነው ሥነ በዓል ላይ ‹‹ማኅበረ ተስፋ ኪዳነ ምሕረት›› ለፓትርያርኩ የወላይታን ባህላዊ ቡሉኮ አልብሷል፡፡ ስለ ተደረገላቸው ስጦታ ምስጋና ያቀረቡት አቡነ ጳውሎስ፣ ‹‹እኛ የእንጀራ ልጅ የለንም፤ ሁላችኹም ታስፈልጉናላችኹ፤. . . ሁሉም ማኅበራት ለቤተ ክርስቲያን ይጠቅማሉ፤ የማይጠቅም የለም፡›› በማለት ለአክብሮ በዓል የተሰበሰበውን ምእመን ግራ ያጋባ ንግግር አሰምተዋል፡፡ የፓትርያርኩን አነጋገር የተከታተሉ በርካታ ምእመናን፣ ‹‹እኛ እዚህ የተገኘነው ከመልአኩ በረከት ለመካፈል እንጂ እርሳቸውን እና አጋፋሪዎቻቸውን ብለን አይደለም፤ ለምንድን ነው በዓሉን የተመለከተ ትምህርተ ወንጌል የማይሰጡት?›› በማለት በኀዘን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ከዚህ በተፃራሪ በዐውደ ምሕረቱ በፓትርያርኩ ዙሪያ የተኮለኮሉ የ‹‹ማኅበረ ተስፋ ኪዳነ ምሕረት›› ጥቂት ወጣቶች ፓትርያሪኩ በተናገሩ ቁጥጥር በኾነው ባልኾነው ቅጥ ያጣ ጭብጨባ ያሰሙ እንደ ነበር ተመልክቷል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና የአዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት፣ ሐምሌ 17 ቀን 2002 ዓ.ም፣ ‹‹የሰበካ ጉባኤውን ቃለ ዐዋዲ በመፃረር በጠቅላላ ጉባኤ የተመረጡ የሰንበት ት/ቤቱን አመራሮች ለማገድ እና ሰንበት ት/ቤቱን አላግባብ ለመቆጣጠር በማሰብ የሰንበት ት/ቤቱን ቁልፍ በመሥበር በሌላ ቁልፍ ቀይረዋል፤›› ባላቸው ሦስት ግለሰቦች ላይ ክስ መሠረተ፡፡፡-

1) በኩረ ትጉሃን ዓለምነህ ሽጉጤ - የሲዳማ ሀገረ ስብከት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር አስተባባሪ፣ ‹‹ማኅበረ ተስፋ ኪዳነ ምሕረት›› እያለ በሚጠራው ማኅበር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ፣

2) መጋቤ ሐዲስ ፍሥሓ ለማ - የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች ማ/መ ሐላፊ እንዲሁም በልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ  ኮሚሽን የሀገረ ስብከቱ ፀረ-ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠርያ አስተባባሪ፣

3) ላእከ ወንጌል ያሬድ አደመ - የፓትርያርኩን ሐውልት አወራው ‹‹የቅድስት ማርያም ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ማኅበር››  አባል ናቸው።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)