July 30, 2010

የሊ/ካህናት ጌታቸው ዶኒ እና የአባ ሰረቀ ምስጢራዊ ደብዳቤ

  • . ‹‹ወጣቱን በተሐድሶአውያን ኅብረት አዲስ ጥምቀት በማድረግ በ‹ቅን ልቦና የመንፈሳዊ የፈውስ አገልግሎት› ሥር መሰብሰብ፤››
  • . ‹‹ሐሳባችንን የሚያደናቅፉ የአቡነ ሳሙኤል ደጋፊዎችን ተቋቁመን ልንጥላቸው ይገባል፤››
  • . ‹‹ወላጅ በሌላቸው ሕፃናት ስም የገንዘብ እና አልባሳት ርዳታን ከሙሉ ወንጌል አማኞች ማኅበር በመቀበል እና የቤት ለቤት ማጥመቅ ተግባራትን በመፈጸም እንቅስቃሴውን ማጠናከር፤››
(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 30/2010)፦ ራሳቸውን ‹‹የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሕጋዊ ወኪል›› በማለት በይፋ የሚጠሩት እና የሰፋሪ ገነት አቃቂ ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ፣ ቤተ ክርስቲያንን ‹‹በተሐድሶአውያን ኅብረት›› ለማጥመቅ በሚል ያቀዱበት፣ ለዚህም እንቅስቃሴያቸው ማጠናከርያ የአቡነ ጳውሎስን ሐውልት በአጥቢያቸው ከማሠራት ጀምሮ ሌሎች የገንዘብ
ማሰባሰቢያ ስልቶችን የነደፉበት እና ይህንኑ ውጥናቸውንም በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መ ሐላፊ ከሆኑት ከአባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ጋራ በሐሳብ የተስማሙበት እና የመከሩበት መሆኑን የሚገልጽ በእጃቸው የተጻፈ ደብዳቤ ለደጀ ሰላም ደርሶ ተመልክተነዋል፡፡
በቀን 05/02/2002 ዓ.ም እንደ ተጻፈ የተመለከተበት ይኸው ደብዳቤ የሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ የግል ማኅተም እና ፊርማ ያረፈበት ነው፡፡ የደብዳቤውን ሙሉ ቃል ዳግመኛ ታይፕ በማድረግ ከእጅ ጽሑፉ ጋራ አባሪ በማድረግ ያቀረብንላችኹ ሲኾን በይዘቱ ላይ የተመሠረተ ዝርዝር ሐተታ በቀጣዮቹ ቀናት የምናስነብብ መኾኑን እንገልጻለን፡፡
                                                     ቀን፡- 05/03/2002

ለአባ ሠረቀ ብርሃን
ለሰንበት ት/ቤቶች መምሪያ ሐላፊ፤

       የማክበር ሰላምታዬን እያቀረብኹ፣ እንደሚታወቀው ባለፈው በተነጋገርነው መሠረት ጉዳዩን እየሄድኩበት እገኛለሁ፡፡
እንደሚታወቀው አንዳንድ የአቡነ ሳሙኤል ደጋፊዎች የግል ማኅደሬን ለማበላሸት የፓትርያሪኩን ሕጋዊ ወኪልነቴን ለመሻር ደብዳቤ ጽፈውብኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ሐሳባቸውን አክሽፌባቸዋለሁ፡፡ በመሆኑም አቡነ ይስሐቅ እንድነሣ ሊያደርጉኝ ቢያስቡም በአቡነ ገሪማ ጸሐፊነት ደብዳቤው እንዲመለስልኝ ተደርጓል፡፡ ምክንያቱም ጋዜጣ ላይ የጻፍኹት ራሴን ለማስተዋወቅ አይደለም፡፡ የፀረ ሰላም ኀይሎችን ምስጢር ነው ያወጣሁት፡፡ አባ ሠረቀ ብርሃን በእርስዎ በኩል ይጠበቅብዎታል፣ ምክንያቱም በርካታ ሰንበት ት/ቤቶችን በመምሪያው ሥር ማግኘት ስለምትችሉ፣ ቤተ ክርስቲያንን በወጣት ኀይል ነውና ማደስ የሚቻለው ጠንክረን መሥራት እንችላለን፡፡
እኛ ሣራ የወለደችን በመሆኑ እናታችንን ከኋላ ቀር አሠራር እና ባህል አላቀን፣ ወጣቱን በተሐድሶአውያን ኅብረት አዲስ ጥምቀት በማድረግ ‹‹ቅን ልቦና የመንፈሳዊ የፈውስ አገልግሎት›› ሥር ልንሰበስባቸው እንችላለን፡፡
የካናቴራ አልባሳት ማሠርያ ለማሠራት በጎ ፈቃደኞችን እየጠቆሙኝ ነው፡፡ ስለዚህ እኔም የማጥመቅ ሥራ በየቤቱ እየዞርኹኝ እያጠናከርኩኝ ነው፡፡ እርስዎም ይህን መንገድ በተሻለ መንገድ አጠናክረው ሊቀጥሉበት ይገባል፤ ስለ ገንዘቡ ሊጨነቁ አይገባም፡፡ 170 ሺሕ የሚያወጣ ሐውልት በእኛ ደብር ስለምናሠራ ከዚያ ላይ በሚገኘው ገንዘብ ልናጠናክረው እንችላለን፡፡ በዙሪያው ያሉ የአቡነ ሳሙኤል ደጋፊዎች ይህን ሐሳባችንን ሊያደናቅፉ ቢችሉ እንኳን ተቋቁመን ልንጥላቸው ይገባል፡፡
በመጨረሻም የሙሉ ወንጌል አማኞች ወላጅ ለሌላቸው ሕፃናት የገንዘብ እና የልብስ ድጋፍ ስለሚያደርጉልን ሕፃናትን መመዝገብ አለብን፡፡ በዚህ እኔ ባለሁበት ደብር አባ ገብረ ሥላሴ የተባሉት በስማቸው የመሠረቱት የሕፃናት ማሳደጊያ በርካታ ልጆች ስላሉ፣ በዚህ ማሳደጊያ ስም ልናገኝ እንችላለን፡፡ ስለዚህ በገንዘቡ በኩል በእንዲህ ዐይነት ኹኔታ ላይ ስለሆንን እርስዎ ወጣቱን በማነሣሣት ትልቅ ሥራ ሊሠሩ ይገባል፡፡ በተረፈ አዳዲስ ነገር ሲኖር በስልክ በመደዋወል እንጨርሰዋለን፡፡
                                       
 ‹‹ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር››
                                         ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ
                                   የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ሕጋዊ   ወኪል               
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)