July 29, 2010

በአዋሳ የምእመኑ ተቃውሞ፣ የፓትርያርኩ ምላሽ እና የብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ማስፈራሪያ

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 29/2010):- የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ለማስፈጸም እነበጋሻውንና ቡድኑን እንዳያስተምሩ የከለከሉት የአዋሳ ቅ/ገብርኤል የቀድሞ አስተዳዳሪ በፓትርያርኩ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ከቦታቸው ከተነሱ ጀምሮ ምእመኑ ይህንኑ በመቃወም የተለያዩ እርምጃዎች ወስዷል። የገዳሙ አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ ዋሕድ ወልደ ሳሙኤል ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ወደ መንበረ ፓትርያርክ  ጠቅላይ ቤተ ክህነት በመምጣት ጉዳዩን ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ አመልክተው ነበር፡፡ የምእመናኑን ማመልከቻ የተቀበሉት ብፁዕነታቸው ምእመናኑን በማስከተል ወደ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ዘንድ ቀርበው ጉዳዩን ለማስረዳት ጥረት ቢያደርጉም ምእመናኑ ከሥፍራው በማይጠበቅ መንፈሳዊነት የጎደለው አኳኋን በመገፋታቸው እና በጎ ምላሽ በማጣታቸው አዲሱን የገዳሙን አስተዳዳሪ የአባ ኀይለ ጊዮርጊስን ሹመት እንደማይቀበሉት በመግለጽ፣ ያለምንም ውጤት በከፍተኛ ኀዘን ተውጠው ወደ ሀገረ ስብከታቸው ለመመለስ ተገደዋል፡፡

የቀድሞው የገዳሙ አስተዳዳሪ ከፍተኛ የልማት ተግባራትን ያከናወኑ በመኾናቸው ከቦታቸው ያለአግባብ መነሣት እንደሌለባቸው እንዲሁም ከቦታቸው ከተነሡ በኋላ ያለምንም አገልግሎት እየደረሰባቸው ያለውን እንግልት በመቃወም ለፓትርያርኩ ባቀረቡት ጥያቄ በጎ ምላሽ ያላገኙት ተወካዮቹ፣ የበርካታ ምእመናንን ፊርማ በማሰባሰብ ሐምሌ አራት ቀን 2002 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ባለስምንት ገጽ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ በዚህ ጥያቄቸው መሠረት በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የኾኑት አቶ መረሳ ረዳ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩን ማነጋገራቸው ተመልክቷል፡፡
ሐምሌ 19 ቀን 2002 ዓ.ም በአዋሳ በተከበረው የቅዱስ ገብርኤል በዓል ላይ ከዋዜማው ጀምሮ የተገኙት ፓትርያርኩ ለዚህ የምእመናኑ ጠንካራ ግፊት ምላሽ እንደ ኾነ በተገመተው ንግግራቸው፣ ‹‹አዋሳ ብሔር ብሔረሰቦች ተቻችለው የሚኖሩበት ከተማ ነው፤ መቻቻል ያስፈልጋል፤. . . በራችን ለውይይት ክፍት ነው፤ መክሰስ መከሰስ ለማንም አይጠቅምም፤ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የሚፈታው በራሳችን እንጂ ሌላ ማንም ሊፈታው አይችልም፤ ላይ ታች ማለት ተገቢ አይደለም፤›› በማለት ኀይለ ቃል አዘል ማሳሰቢያ መስጠታቸውን በበዓሉ ላይ የተገኙ ደጀ ሰላማውያን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ሲል የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ሐምሌ ሰባት ቀን በተከበረው የቅድስት ሥላሴ በዓል በአዋሳ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ባሰሙት ተግሣጽ አዘል ንግግር፣ ‹‹የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች ለተቀመጡበት ቦታ ብቁ ኾነው ሳይገኙ ሲቀሩ እነርሱን መሻር፣ ማዘዋወር እና በምትካቸው ሌላ መሾም የሀገረ ስብከቱ ብቸኛ ሥልጣን ነው፤ ምእመናን በዚህ ውስጥ ድርሻ የላችሁም፤ በቃ፣ ለእኔ ተመችቶኛል፤ የሾምኩላችኹን ተቀብላችኹ መኖር ነው፤›› ሲሉ ተደምጠዋል።
በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እና በሥራ አስኪያጁ መካከል በቤተ ክርስቲያንን ንብረት እና ሀብት ላይ የተመሠረተ ከፍ ያለ የጥቅም ትስስር መኖሩን የሚናገሩት አንዳንድ ምእመናን ጉዳዩ ሊጋለጥ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
ውዝግቡ ያሳሰበው የክልሉ ጸጥታ ቢሮ፣ ‹‹ችግሩ ማን ጋራ እንዳለ ተረድተነዋል፡፡ ጉዳዩ የጸጥታ ጉዳይ ነው፤ ሰዎቹ ይኹነን ብለው ችግር ለመፍጠር የሚፈልጉ ናቸው፤. . . ፓትርያሪኩ ለውይይት በራችን ክፍት ነው ካሉ መንገድ መዝጋት አያስፈልግም፤ ውይይቱ ውጤት የማያመጣ ከኾነ ግን ጣልቃ ለመግባት እንገደዳለን፤›› በማለቱ የምእመናኑ ተወካዮች በዛሬው ዕለት ጠዋት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ለማነጋገር ቀጠሮ በተያዘላቸው መሠረት ማነጋገራቸውን እነዚሁ ደጀ ሰላማውያን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ፀሐይ መልአኩ ትናንትና ሐምሌ 21 ቀን 2002 ዓ.ም ከስም ማጥፋት እና ‹‹ለአዋሳ ከተማ ጸጥታ ስጋት ኾነዋል፤›› በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ማምሻውን መፈታታቸውን  የደጀ ሰላም ምንጮች አመለከቱ፡፡ የእስራቸው ምክንያት በሀገረ ስብከቱ የሚገኘው የአዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪን ያለአግባብ መነሣት እና በሕገ ወጥ ሰባክያን የሚካሄዱ ጉባኤያትን በመቃወም ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ  አቡነ ጳውሎስ አቤቱታ ያቀረቡትን ቁጥራቸው 39 የሚደርሱ ምእመናንን፣ ‹‹አሸባሪዎች እና ፀረ ሰላም ኀይሎች ናቸው፤›› ብለው በመወንጀላቸው መኾኑ ታውቋል፡፡
በሥራ አስኪያጁ ስማቸው ተጠቅሶ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እና ለክልሉ ፖሊስ ውንጀላ የቀረበባቸው ሠላሳ ዘጠኙ ምእመናን ታዋቂ ግለሰቦች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ባለሀብቶች ናቸው፡፡ በሀገረ ስብከቱ በተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተሳተፉ የሚገኙ ከመኾናቸውም በላይ፣ የሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤልን፣ በዓለ ወልድን፣ ኪዳነ ምሕረትን፣ ቅዱስ ሩፋኤልን እና የቅዱስ ጊዮርጊስ አብያተ ክርስቲያናትን በማነፅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን የደጀ ሰላም ምንጮች ይናገራሉ፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)