July 25, 2010

የአራቱ ጉባኤያት ሊቅ ዐረፉ

(ማኅበረ ቅዱሳን):- የአራቱ ጉባኤያት አብነት መልአከ ገነት ገብረ ሥላሴ አወቀ በተወለዱ በአንድ መቶ ሁለት ዓመታቸው ግንቦት 28 ቀን 2002 ዓ.ም ለ29 አጥቢያ ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም በትውልድ ሀገራቸው ባሠሩት ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

መልአከ ገነት ገብረ ሥላሴ እንዳረፉ አስከሬናቸው ወደ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን ተወስዶ ጸሎተ ቅዳሴ ከተደረገበት በኋላ በትምህርት ቤቱ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ሙሉ ጸሎተ ፍትሐትና አደራረስ ሲደረግበት ውሏል፡፡
አስከሬናቸው ጉባኤ ዘርግተው ያስተምሩበት ከነበረው ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በዓታቸው ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተወስዷል፡፡

በካቴድራሉም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአዲስ አበባ አድባራት አስተዳዳሪዎችና የገዳማት አበ ምኔቶች፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሹማምንትና የየመምሪያው ሓላፊዎች በተገኙበት ጸሎተ ፍትሐት ተደርጎላቸዋል፡፡

በዚህም ወቅት የሕይወት ታሪካቸው ከተነበበ በኋላ ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት ቃለ በረከተ፤ «በሊቁ በመምህር ገብረ ሥላሴ ሞት ቅድስት ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ሐዘንና ጉዳት የደረሰባት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይሁን እንጂ እንደ ሊቁ መምህር ገብረሥላሴ ያሉት የትምህርት አብነቶች አያሌ ተተኪ መምህራንንና ደቀመዛሙርትን በማፍራት ራሳቸውን ተክተው ያለፉ በመሆናቸው እንደሞቱ አይቆጠርም፡፡ ቸር አምላክ በቸርነቱ ለኒህ ታላቅ ሊቅ ለነፍሳቸው ዕረፍት መንግሥተ ሰማያትን እንዲሰጥና ለቤተክርስቲያናችን እንደሳቸው ያለ ሊቅ እንዲተካ እንጸልያለን በማለት ጸሎተ ቡራኬ አድርገዋል፡፡

የመምህር ገብረ ሥላሴ አስከሬን ወደ ጎጃም ተወስዶ በትውልድ ሀገራቸው ራሳቸው ባሠሩት በሞጣ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳቱ በተገኙበት ሥርዓተ ፍትሐት ተከናውኖ ሰኔ 1 ቀን 2002 ዓ.ም ሥርዓተ ቀብራቸው ተከናውኗል፡፡

በሥርዓተ ቀብራቸው ላይ ሊቃነ ጳጳሳት የአካባቢው አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የገዳማት አበምኔቶች፣ በርካታ ካህናትና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ተገኝተዋል፡፡

የመምህር ገብረ ሥላሴ አጭር የሕይወት ታሪክ

የኔታ ገብረ ሥላሴ አወቀ በቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ በደጋ ዳሞት ወረዳ ወይም ፈረስ ቤት ልዩ ስሙ ወገም ቅዱስ ጊዮርጊስ በተባለው ታሪካዊ ቤተክርስቲያን ጳጉሜ 3 ቀን በ1900 ዓ.ም ከአቶ ደርሰህ ወንድሁነኝና ከወ/ሮ ማዘንጊያ ገብረ ሰንበት ተወልደዋል፡፡

ታላቁ ሊቅ የኔታ ገብረ ሥላሴ አወቀ የትውልድ ሐረጋቸው ከቤተ ሌዊ /ቤተክህነት/ የተያያዘ እንደ ነበረ ታሪካዊ አመጣጣቸው ይገልጣል፡፡ በዚህም መሠረት የኔታ ገብረ ሥላሴ አወቀ ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ ወደ አብነቱ ትምህርት ቤት ገብተው ድጓና ጸዋትወ ዜማ ወገም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሪጌታ ገላው ደስታና ከመሪጌታ ተገኝ የቁም ዜማ ተምረዋል፡፡

ከዚያም ጾመ ድጓ፣ ድጓ፣ ምዕራፍ ከዘለቁ በኋላ ወደ ቅኔ ቤት አምርተዋል፡፡

የኔታ ገብረ ሥላሴ አወቀን ቅኔ ያስተማሯቸው መምህራን መምህር ገብረ ሥላሴ ዘደብረ ኤልያስ፤ መምህር ማዕበል ፈንቴ ዘዋሸራ፤ መምህር ገሠሠ ዘአቸፈር ናቸው፡፡

በቅኔ ቤት ደግሞ አራት ዓመት ቆይተው ለአንድ ዓመት የቅኔ ዘረፋ ከተቀበሉ በኋላ ተመልሰው ወደ ድጓ ቤት ገብተዋል፡፡ ድጓን ከዘለቁ በኋላ የተክሌ አቋቋምን ተምረው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡ በመቀጠልም ለሦስት ዓመታት ቅኔ ቤት ቆይተው የቅኔ አገባብን በመቀጸል ወደ ጌቴ ገሞራ አዴት ሰበካ የቅኔ አገባብን ከነ እርባ ቅምሩ ለሁለት ዓመታት ተምረዋል፤ አስመርቀዋልም፡፡

በአጠቃላይ የኔታ ገብረ ሥላሴ አወቀ በቅኔ ትምህርት ብቻ ለዐሥር ዓመታት ከደከሙ በኋላ የቅኔ ጉባኤ ዘርግተው አስተምረዋል፤ ብዙ መምህራንንም አፍርተዋል፡፡

የኔታ ገብረ ሥላሴ መጀመሪያ ጣሊያን ኢትዮጵያን ሳይወር አዲስ አበባ መጥተው ከእነ አለቃ አየለና አለቃ ኅሩይ በደብረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስና በታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም በእግር ጉዞ እየተመላለሱ መጻሕፍተ ሐዲሳቱን ዘልቀዋል፡፡

የኔታ ገብረ ሥላሴ አወቀ በመማር ብቻ የተወሰኑ ሳይሆን እየተማሩም አስተማሪ እና አገልጋይ ነበሩ፡፡ የኔታ በዚህ ሁኔታ አዲስ አበባ ለዐሥር ዓመታት እንደቆዩ ጣሊያን በ1928 ዓ.ም ሀገሪቱን ሲወር ከአዲስ አበባ ተነሥተው መምህር አባ ጽሕማ ዘጐንድ ተክለሃይማኖት ጋር በጎሐ ጽዮን አድርገው ጉዟቸውን ቀጠሉ፤ በዚያን ጊዜ ጣሊያንን ሊወጉ በአርበኝነት የተሰለፉት አበበ አረጋይ በኋላ ራስ አበበ የዓባይን ወንዝ በዋና አሻግረዋቸው ወደ ሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሔደዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ የኔታ ገብረ ሥላሴ አወቀ የትምህርት ጥማታቸው ገና ስላልረካ ከአለቃ ጌታሁን የላይ ቤቱን መጻሕፍተ ሐዲሳት ትርጓሜ፣ ከመምህር ጽሕማ ዘጐንድ ተክለሃይማኖት ደግሞ ፍትሐ ነገሥቱን፣ ትርጓሜ ዳዊቱን፣ መጽሐፈ አስቴርን፣ መጽሐፈ ኢሳይያስን፣ መጽሐፈ ኤርምያስን አሂደዋል፡፡

በመቀጠልም በ1933 ዓ.ም የድሮ መምህራቸው አለቃ አየለ ዓለሙ ወደ ጎንደር መመለሳቸውን ሰምተው መጻሕፍተ ብሉያቱንና መጻሕፍተ ሊቃውንቱን አጠናቅቀዋል፡፡

የኔታ ገብረ ሥላሴ የተማሩትን ትምህርት ለማስተማር ወደ ደንበጫ ለመሔድ በዝግጅት ላይ እንዳሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በአስቸኳይ አዲስ አበባ እንዲመጡ ላኩባቸው፡፡ እሳቸውም ጥሪውን አክብረው አዲስ አበባ እንደመጡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከግርማዊነታቸው ዘንድ አቅርበው የሞጣ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ መልአከ ገነት ሆነው እንዲያስተምሩ ተሹመዋል፡፡

ታላቁ ሊቅ መልአከ ገነት ገብረ ሥላሴ አወቀ የሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ አስተዳዳሪ ሆነው ለ15 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በማስተማር ብቻ ተወስነው እያሉ ብፁዕ አቡነ ተክለሃይማኖት የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የአራቱ ጉባኤያት መምህር ሆነው እንዲያስተምሩ በቅዱስ ሲኖዶስ አስወስነዋል፡፡

በውሳኔውም መሠረት በ1979 ዓ.ም ከወርኃ ኅዳር እስከ ግንቦት 4 ቀን 2002 ዓ.ም ድረስ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ኮሌጅ ለ24 ዓመታት ደከመኝ ስለቸኝ ሳይሉ እስከ መጨረሻ የእስትንፋስ ሕቅታ ድረስ ቃለ እግዚአብሔር በመናገር በልማደ ሰብእ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

6 comments:

Anonymous said...

RIP ye'ene Abat!!!a great role model for the those young students in ye'abenet school.Hey...those bad public figures and HODAM hula please learn from this person history

Anonymous said...

ደጀ ሰላም ሌላ ወሬ ቢሆን ኖሮ በዕለቱ ታወሩ ነበር የኒህ ታልቅ ሊቅ ዕረፍት ግን በግንቦት ያረፉ
እስከዛሬ ቆይታችሁ እንደ አዲስ ዜና አድርጋችሁ ጻፋችሁ ለመሆኑ የትከርማችሁ ነው?
የታላቁን ሊቅ የኔታ ገብረሥላሴን ነፍስ ከቅዱሳኑ ጋር ይደምርልን ፡፡

Unknown said...

ውድ አስተያየት ሰጪ፣
ስለ አስተያየቶ በጣም እናመሰግናለን። አስተያየቶ "ሌላ ወሬ ቢሆን ኖሮ" ከሚለው አግቦ በስተቀር፣ ትክክል ነው። እናሻሽላለን።
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

Dan said...

መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ።ምዕራፍ 18።

17፤ አክዓብም ኤልያስን ባየው ጊዜ። እስራኤልን የምትገለባብጥ አንተ ነህን? አለው።

18፤ ኤልያስም። እስራኤልን የምትገለባብጡ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ በኣሊምን የተከተላችሁ፥ አንተና የአባትህ ቤት ናችሁ እንጂ እኔ አይደለሁም።
========
ዛሬ ቤተ ክርስቲያንን የሚገለባብጣት

1. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ
2. ፓትርያርክ
3. ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
4. ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
5. ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
6. የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና
7. የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት፤

ይህን ሁሉ ሥልጣን የተሽከመው ነው??

Anonymous said...

I knew Melake genet Gebreselasse Awoqe in person since my childhood. Then he replaced yeneta Gete, a well known metshaf memhir of Motta giworgis church. Yenet Gete was a blind small man with an incredible talent. I still remember his theological thaughts very well. He was very tough!!! If my childhood recollection permits me Melake Genet Gebre Selasse speaks little, but my father used to say that Melake genet Gebre Sellase is one of the best well educated child of the Ethiopian Orthodox church. He was long, measured when he speaks. Let the Almighty God put his soul next to Abraham!!!

Sebatu Warka

hiwot said...

May God rest his soul in peace

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)