July 23, 2010

'ከቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት" ከሚል መልእክት የተገኘ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

ቀን 29/10/2002

ከቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች  
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
አዲስ አበባ
ብፁዓን አባቶች ሆይ፦
·         በቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ሲኖዶስ እየተባለ የሚታወቀውና የሃይማኖታችን ሞገስ የሆነው ቅዱስ ጉባዔ አለ ወይስ ጠፍቷል?
·         ቤተ ክርስቲያኒቱ የአቡነ ጳውሎስ የግል ንብረት ሆናለች ወይስ የጋራችን?
·         በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችን ተቆርቋሪ የሌላትና የግል ማላገጫ ስትሆን ብፁዐን አባቶች እያያችሁ ታዝኑላታላችሁ ወይስ አያገባንም ብላችሁ በግድየለሽነት እየተመለከታችሁ ነው?
የሚሉ ጥያቄዎች ስላሉን ከአባቶቻችን መልስ የምንጠብቅ መሆናችንን እየገለጽን የበኩላችንን ሐሳብ ከዚህ ቀጥሎ በመመዝገብ አቅርበናል። እናንተም ስለ ቤተ ክርስቲያናችንና ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ እስከ መጨረሻው ድረስ በጥሞና እንድታነቡት በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃል።
በመጀመሪያ ደረጃ ሃይማኖታችንና ቤተ ክርስቲያናችንን እንጠብቃለን ብላችሁ በሕዝበ ከርስቲያኑና በእግዚአብሔር ፊት ቆማችሁ ቃል ገብታችሁ፤ ምላችሁ በቤተ ክርስቲያኑ ላይ የተሾማችሁ ጳጳሳት ፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እየተባላችሁ መኖራችሁን እኛም እናውቃለን፤ እንኮራባችኋለንም። ቅዱስ ሲኖዶስ የሚባለው ጉባዔ ግን አለ ብለን በጭራሽ አናምንም፤ ቤተ ክርስቲያኒቷም ተቆርቋሪ የሌላት መሆኗንም ሙሉ በሙሉ እየተከሰቱ ካሉ ጉዳዮች በመነሳት ማረጋገጥ ችለናል። ዝርዝር ምክንያቱንም ከዚህ ቀጥለን የመዘገብነው ስለሆነ መመልከት ይቻላል።
ክፍል አንድ ሕገ ወጥ አሠራር
1.      ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና ውጭ በሆነ መንገድ በየቤተ ክርስቲያኑ ሥዕላቸውን እያቆሙ በመሆናቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንመጣ የምንሰግደው ለእግዚአብሔር ነው ወይስ ለአቡነ ጳውሎስ ሥዕል በማለት እየተሳቀቁና እያዘኑ የሚኖሩ የቤተ ክርስቲያናችን አባላት እጅግ ብዙ ከመሆናቸውም በላይ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ቃልቲ አካባቢ በምትገኘው በቁስቋም ቤተ ክርስቲያን በዐውደ ምሕረት ፊት ለፊት ማለትም ታቦት ሲቆም ሊቃውነቱ ከሚያስረግጡበት አጠገብ በአደባባዩ ላይ በልዩ ብረት ታጥሮ የአቡነ ጳውሎስ ሥዕል ቆሟል። በሥዕሉ ራስ ላይ ‘ስምከ ሕያው ዘኢይመውት’ የሚልና ከሥዕሉ በታች ‘ሰማዕት ዘእንበለ ደም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ’ የሚል ጽሑፍ አለበት። በቦሌ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ደግሞ በልዩ ሁኔታ በሲሚንቶና በአርማታ ሐውልታቸው ተሰርቶ ቆሟል። በሐውልቱ ላይ ‘ስምከ ሕያው ዘኢይመውት’ የሚለውና ‘ሰማዕት ዘእንበለ ደም’ የሚለው ቃል አለበት።
ይህንኑ ሐውልትም የሙዚቀኛው የመሐሙድ ሚስት የነበሩት ወ/ሮ እጅጋየሁ እና ‘የመስቀሉ ስር ቁማርተኞች’ የሚለውን መጽሐፍ የጻፈው ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን እንዳሰሩት እየተነገረ ነው። በመሆኑም የአቡነ ጳውሎስ ሥዕልና ሐውልት ቀኖና ቤተ ክርስቲያናችንን በእጅጉ የሚፈታተን ከመሆኑም በላይ ወ/ሮ እጅጋየሁ የተባሉት ሴት ዘፋኝ ባላቸውን ከፈቱ በኋላ የአቡነ ጳውሎስ ጉዳይ አስፈጻሚ እንዲሆኑ የሾማቸው ማነው? ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ያላቸው ግንኝነትስ ምንድነው? የሚሉ አጠራጣሪ ጥያቄዎችን የሚያስነሳና ስሙ ራሱ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር የሚነካ ስለሆነ ተገቢነት የሌለውና ቅጥ ያጣ ግኑኝነታቸው አሳፋሪ አካሄድ ነው።
እኒሁ ወ/ሮ እጅጋየሁ ከአሁን በፊትም በ2000 ዓ.ም. የሚሊኒየሙ በዓል በሚከበርበት ጊዜ በአንገት የሚጠለቅ ወርቅ ለአቡነ ጳውሎስ የግል ሽልማት ሲሰጡ “ሰማዕት ዘእንበለ ደም”’ ብዬ ሰይሜዋለሁ ብለው የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖና በመጋፋት የተናገሩ ሰው ናቸው። በመሠረቱ አንድ ቅዱስ ፓትርያርክ እንደዚህ ባለው ቅሌታዊ አካሄድ ተሰማርቶ መገኘት መረገም እንጂ የጤንነት አይመስለንም። ቤተ ክርስቲያኒቱንም የሚያሳስብ ጉዳይ ነው።

2.    የአቡነ ጳውሎስን የግል ታሪክ በሐሰት አጉልቶ የሚያሳይ የሚያወድስ ዶክመንተሪ ፊልም በራሳቸው ተዘጋጅቶ የአዲስ አበባ ካህናት እየተገደዱ እየገዙ ናቸው።

ከመሰረቱም ቢሆን የአቡነ ጳውሎስን ታሪክ መመስከር ያለባት ራሷ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንጂ ራሳቸውን በራሳቸው ታላቅ መንፈሳዊ አባት አስመስለው ማቅረብ ፈጽሞ ነውር ነው። ምክንያቱም የክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሕይወት የሚመራው ራስን ዝቅ በማድረግና በትሕትና ብቻ መሆኑን ምዕመናን ሁሉ የሚያውቁት ጉዳይ ነው።

እኒህ ሰው ግን መጥፎው ታሪካቸውና ጉዳቸው ራሳቸው ባዘጋጁት ፊልምና በአቆሙት ሐውልት ተደብቆ (ተሸፍኖ) ካህናቱም ትክክለኛውን እና እውነተኛውን ታሪክ ሳይሆን ተገደው የገዙትን ፊልምና የቆመውን ሐውልት ውበት እየተመለከቱ ቅዱስ ናቸው እያሉ ሲያመሰግኗቸው እንዲኖሩ የተደረገ የብልጥነት ተግባር ነውና ሙሉ በሙሉ ጥፋት ነው።

3.    በራሳቸው በአቡነ ጳውሎስ ስም የተዘጋጀው መጽሐፍም የሃይማኖታችንን አቋም የነካ ሆኖ እያለ በፁዓን አባቶች እያያችሁና እየሰማችሁ ዝም ማለታችሁ ካህናቱንም ሆነ ምዕመናኑን የሚያሳፍር ሆኗል።

4.    ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ማንኛውንም ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክሎ ወደ ውጭ የሚላክ (የሚመጣ) የቤተ ክርስቲያኒቱ አባል ሁሉ በመጀመሪያ በቅዱስ ሲኖዶስ ሊፈቀድለት እንደሚገባ በሕገ ቤተክርስቲያን መደንገጉ ይታወቃል።

አሁን ጳውሎስ ግን ከሕግ በላይ የሆኑ ወይም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግ እርሳቸውን የማያውቃቸው ይመስል ስራዬ ሙያዬ ብለው የያዙት ወደ ተለያዩ አገሮች መሄድ፣ መምጣት፣ መዞር፣ መንከራተት፣ መዝናናት ነው። በተለይ ደቡብ አፍሪካ የናት ቤት ሆኗል።

ለመሆኑ ግን አቡነ ጳውሎስ ደቡብ አፍሪካ ምን አስቀምጣል? ምን አላችው? በአጠቃላይ ነጋ ጠባ ደቡብ አፍሪካ የሚሉበት ምክንያት አጠያያቂ ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል እንላለን።

5.    አምና የዛሬ ዓመት ብፁዓን ጳጳሳት በጸሎት ቤታቸው እንዳሉ ተደብድቧል። በዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ራሷ ከራሷ ጋር ስትደበደብ የመጀመሪያ ጊዜዋ መሆኑ ነው። ምንም እንኳ በአቡነ ጳውሎስ ዘመነ ስልጣን ቤተ ክርስቲያናችን ለውርደት የተጋለጠች ዘመን መሆኑ በዓለም አደባባይ የታወቀ ቢሆንም በዚሁ በብፁዓን ጳጳሳት ላይ በተፈመው የድብደባ ወንጀል የሃይማኖታችን ክብርና ታሪክ ተደፍሯል። የሕዝበ ክርስቲያኑ ሞራልም ተነክቷል።
“ይህ ጉዳይ ይጣራና ወንጀሎች ለሕግ ይቅረቡ ወደፊትም በቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ዓይነቱ አሳፋሪ ተግባር እንዳይታይ ይሁን”ተብሎ ሲጠየቅ አቡነ ጳውሎስና በወቅቱ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቡነ ይስሐቅ ጉዳዩን አፍነው አስቀርተውታል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የሚያስገርመው ደግሞ፣ ስም መጥቀስ አያስፈልግም እንጅ፣ በዚህ ወንጀል መፈጸም ምክንያት ይደሰቱ፤ ይዘፍኑ የነበሩ ግለሰቦች እየተፈለጉ በየመምሪያውና በየቁልፍ ቦታው እንደዚሁም በየታላላቅ አድባራቱ መሐይምነታቸውን እንደተጎናጸፉ እየተሾሙ የስልጣን ባለቤቶች መሆናቸው ነው። በተለይ ዱርየና ስርዓተ አልበኛ የሆኑት ባለጌዎች በመብራት እየተፈለጉ ነው ባለስልጣናት የሆኑት፤ እንዲህ አይነቱ አሰራር ደግሞ ነውረኛነት ነው። ለቤተ ክርስቲያኒቱም ከፍተኛ ውድቀት ለመሆኑ አጠራጣሪ ነገር የለውም።

ክፍል ሁለተ፡ ሕገ ወጥ ብዝበዛዎች
1.    ከዚህ በላይ በተጠቀሰው በአንቀጽ 1/4/ ላይ በገለጥነው መሰረት አቡነ ጳውሎስ ወደ ውጭ አገር እሄዳለሁ እያሉ ከአንጋቻቸውና ከአጨብጫቢዎቻቸው ጋር በተመላለሱ ቁጥር ለትራንስፖርት፤ ለአበል፣ ለክብር መጠበቂያ እየተባለ የሚጨፈጨፈው የቤተ ክርስቲያናችን ገንዘብ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው። ለቤተ ክርስቲያናችን አላችሁላት ተብሎ የሚታመንባችሁ እናንተ ብፁዓን አባቶችም ዝም ብላኋችል። ምን ይሻላል?

2.    አቡነ ጳውሎስ በደቡብ አፍሪካና በጋምቤላ ስራ እሰራለሁ በሚል ቅዱስ ሲኖዶስ የማያውቀው የገንዘብ መበዝበዣ ዘዴ ፈጥረው ቅዱስ ሲኖዶሱም በቤተ ክርስቲያኒቱ ምንም ምን እንደማያገባውና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብቸኛ አሳቢ እርሳቸው ብቻ በማስመሰል አሳምነው ከአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ያለ ታዛቢ ገንዘብ እየሰበሰቡ ናቸው። ይህ አሰራራቸውም “የነቃ የለም፣ ማንም አያውቅብኝም” በሚል የንቀት መንፈስ ተሞልቶ ጠያቂ በሌለበት ሁኔታ የተዘረጋ የብዝበዛ መረብ ስለሆነ አደገኛ ብልጥነት ነው።


3.    አቡነ ጳውሎስ “ኤልሻዳይ” የሚል አዲስ ፕሮግራም ፈጥረው ከአዲስ አበባ አድባራት ገንዘብ እየበዘበዙ መሆናቸውንም ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል ብዙዎቻችሁ እያወቃችሁ የእግዚአብሔር ገንዘብ የጠላት ገንዘብ የሆነ ይመስል በዝምታ ማየታችሁ የሚያሳዝን ጉዳይ ነው። እርሳቸው ግን በገንዘብ ብዝበዛ በኩል ክፉኛ የተመረዙና በአጠቃላይ ከመንፈሳዊ አባትነት ባህርይ አጥብቀው የራቁ አሳፋሪ ሰው ናቸው። “ተዉ አይገባም ” የሚል ተቆርቋሪም ጠፍቷል። ሁሉም ነገር ክፉውን ተግባር ለማከናወን በሚመች መልኩ ጨለማ ሆኗል። ብቻ እግዚአብሔር ይሁነን።

ክፍል 3 ቤተ ክርስቲያናችን የቤተሰብ ብቻ መጠቀሚያ ስለመሆኗ
አቡነ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሀብቷ፣ በንብረቷና በቀኖናዋ ላይ ሁሉ ከንቀት ጋር እየተጫወቱበትና እየረገጧት ከመሆናችውም በላይ ለቤተሰብ መጠቀሚያ እያደረጓት እንደሆነ በተደጋጋሚ የገለጥነውና የታወቀ ጉዳይ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ እየተደረገ ያለውን ብቻ ጥቂቶቹን ለመጠቆም እንሞክራለን።
1.    የአንጋቻቸው የሙሉጌታ በቀለ ወንድም አሰፋ በቀለ የተባለ ሰው ያለምንም ውድድር የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ቁጭ ብለው እየተመለከቱ በከፍተኛ ደመወዝ በልማት መምሪያ እንዲቀጠር አደርገዋል፤
2.    አሁንም ሊቃውንቱ ተመልካቾች ሆነው እየሳሱና እየጓጉ አቡነ ጳውሎስ አንድ ዘመዳቸውን አምጥተው ያለምንም ውድድር በከፍተኛ ደመወዝ በልማት መምሪያው እንዲቀጠር አድርገዋል፤
3.    ተክሉ የተባለው የቅርብ ዘመዳቸውና አንጋቻቸው በልማት መምሪያው እየሰራ ያለ ቢሆንም ከማንም ጋር ሳይወዳደር ከፍተኛ እድገትና ከፍተኛ ደመወዝ እንዲያገኝ ተደርጓል፤
4.    በልዩ ጽ/ቤት አካባቢ የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር በማያውቀው ሁኔታ አንዱ ተርጓሚ፣ አንዱ አጥኚ ወዘተ በሚል የውሸት የስራ መደብ እየተፈጠረ ምንም ነገር ሳይሰሩ አራት ሺ፤ ስድስት ሺ ፤ ስምንት ሺ፤ የሚከፈላቸው ዘመዶቻቸውም እየተፈለፈሉ ናቸው። በአጠቃላይ ግን ስለ ቤተ ክርስቲያናቸን ጉዳይ መልስ ያላገኘንላቸው ብዙ ቢሆንም መሰረታዊ የሆኑ ሁለት ጥያቄዎችም አሉን። ማለትም፦
ሀ.  እግዚአብሔር ይችን ቤተ ክርስቲያን በእኒህ ሰው አማካይነት እየቀጣ ነው?   ወይስ ሰውየው ከሌላ የተሰጣቸውን ተልዕኮ እያከናወኑ ነው?
ለ. ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደዚህ ባለ በከፋ ውድቀት ላይ እያለች መሆኗን ብፁዓን አባቶች እያዩ ምንም አያገባንም ብለው ዝም እንዲሉ እግዚአብሔር ልቦናቸውን አደነደነው ወይስ የግል ችግር ያለባቸው አባቶች በዙ
የሚሉ ናቸው።

በበኩላችን ግን በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያለው ጭካኔ ስላሳዘነን ለዋናው ዳኛ ለእግዚአብሔር አቤቱታችንን እያቀረብን መሆናችንን እየገለጥን ምናልባት ብፁዐን አባቶቻችን የቤተ ክርስቲያኒቱን ጉዳይ ለማየትና ለመዳኘት የምትፈቅዱ ከሆነ ሊፈጸም ይገባል ብለን ያቀረብነውን የማጠቃለያ ሀሳባችንን ከዚህ ቀጥለን መዝግበነዋል።

ክፍል አራት የውሳኔ ሐሳብ
1.    ‘ስምከ ሕያው ዘኢይመውት’ እየተባለ እግዚአብሔር የሚከብርበትና የሚቀደስበትን ቅዱስ ቃል አቡነ ጳውሎስ ዘርፈው ወስደው ለራሳቸው ማድረጋቸውና በስለት ወይም በእሳት ወይም በውግረተ ዕብን ወይም በሌላ ሁኔታ መከራና ስቃይ ሳይቀበሉ ደምም ሳይፈሳቸው፣ የሰማዕትነት ማዕረግም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሳይፈቀድላቸው እንዲሁ በንጥቂያ እና በጉልበት ሰማዕት ሆኛለሁ ማለታቸው የቀኖና ጥሰት ስለሆን ራሳቸውም ተባባሪዎቻቸውም ሊቀጡ ሊወገዙ ይገባል እንላለን። ምክንያቱም ጤናማ እና የተደላደለ አእምሮ ያለው መንፈሳዊ ነኝ ባይ ሰው ያልሆነውን ነገር ሆኛለሁ በማለት ሰውን ግራ ለማጋባት እና ሥርዓትን ለማፋለስ ሙከራ ካደረገ የተሟላ ጥፋት ፈጽሟል ማለት ነውና ይህ ከግምት ገብቶ ሐውልቱም ጭምር መፍረስ እንዳለበት እናሳስባለን። በየቤተ ክርስቲያኒቱ የቆሙ ፎቶዎቻቸውችም ተነስተው መውረድ አለባቸው እንላለን፤

2.    ታሪካቸውን በውሸት የሚያንጸባርቀውና በአዲስ አበባ ካህናት እንዲገዙት የሚገደዱት ፊልም እንዲታገድ፤


3.    ቅዱስ ሲኖዶስ በማያውቀው ሁኔታ በደቡብ አፍሪካ እና በጋምቤላ ሥራ እሰራለሁ እያሉ የሚያካሂዱት የገንዘብ ዘረፋ እንዲቆም፣

4.    በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር ኃላፊ ተብሎ ከተሾመው ከአቶ ያሬድ ጀምሮ በልዩ ጽ/ቤትም ሆነ በልማት መምሪያው ያለ አግባብ የተሾሙትና አዲስ ተቀጣሪዎችም እንዲታገዱና እንዲጣራ፤


5.    ከአሁን በፊት ሚያዝያ 19 እና ሰኔ 24 ቀን 2002 ዓ.ም. ጽፈን በአቀረብነው መግለጫ መሰረት ብፁዕ አቡነ ይስሐቅም በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ከፍተኛ የአስተዳደር በደልና የገንዘብ ብዝበዛ የፈጸሙ ስለሆን የአቡነ ጳውሎስንና የአቡነ ይስሐቅን ጥፋት የሚያጣራ ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቋቋምና የኮሚቴው ውጤት እስኪገለጥ ድረስም አቡነ ጳውሎስ በአስተዳደር ሥራ እንዳይገቡ እንዲታገዱ እየጠየቅን ከዚህ ጋር የምንገልጠው ከአሁን በፊት ቅዱስ ሲኖዶሱ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጉዳይ ማጣራት አይችልም፤ በገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴ ነው መታየት ያለበት በሚል ሐሳብ ስራ ተከናውኖ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖና የማያውቁ ግለሰቦች በኮሚቴ ደረጃ ተቋቁመው በቤ ተክርስቲያኒቱ ሀብት ያለ አግባብ የተጠቀሙ መሆናቸውን ማንም ሰው ያውቃል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በተለያዩ የሀገር መንግስታት መካከል የተፈጠረ የድንበር ጥያቄ ወይም ጦርነት ቢሆን ኖሮ ወይም በአንድ ሀገር መንግስትና የፖለቲካ ድርጅት መካከል የሚፈጠር የአገዛዝ ጥያቄ ያለበት ቢሆን በእርግጥ ገለልተኛ ያጣራ ማለት ይገባ ነበር። ከዚህ ውጭ ግን አንድ መንግስት የራሱ አስተዳደርና የሀገሩን ሀብት መቆጣጠርና ማጣራት አይችልም? ቤተ ክርስቲያኗም በበኩሏ ቀኖናዋን፣ ሃይማኖቷን፣ የቤተ መቅደሷን አሰራርን፣ ሀብቷን፣ ንብረቷን መቆጣጠርና ማጣራት አትችልም ተብሎ የተደነገገ ሕግ በሀገራችን በጭራሽ የለም። ብቻ ‘ያይዘጌን ቤት ውሻ ታውቀዋለች’ እንደሚባለው ሁሉ የተለያየ ምክንያት ተፈጥሮላቸው ግለሰቦች እናጣራለን ብለው ገብተው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት ተረዳጅተውበታል። የሆነ ይሁንና ያለፈው እንደ ታሪክ ተቆጥሮ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ከእናንተ ከብፁዓን አባቶች የሚቀርባት የለምና እባካችሁ ዳኝነት እዩላት፤ ፍትህም ስጡ በማለት በቤተ ክርስቲያን ስም እንማጸናችኋለን።

ከቤተክርስቲያኒቱ ልጆች
 

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)