July 16, 2010

ቅን የተዋሕዶ መሪ

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 15/2010)፦
አንተ ኖላዊ ሰው ትጉሁ እረኛ
በበር የገባኸው ያልሆንከው ቀማኛ
እግዚአብሔር የላከህ አንተ ደግ እረኛ
እውነተኛ ፈራጅ አንት የፍቅር ዳኛ፤
ከበረት ለወጡት ለጠፉት በጎችህ
ፈጥነህ ድረስልን ታደገን በበትርህ።

አንተ ደግ ዳኛ ባለ ቀጭን ዘንጉ
ዘመንህ መቼ ይሆን የምትመጣበቱ
እግዚአብሔር የላከህ አንተ ደግ እረኛ
እውነተኛ ፈራጅ አንት የፍቅር ዳኛ?

ላክልን ጌታችን ተክለ ሃይማኖትን
በወንጌሉ ያጽናን በጸሎት ያድነን፤
ላክልን ጌታችን አባ ጊዮርጊስን
ሰዓሊ ለነ ብሎ ከጌታ ያስታርቀን፤
ላክልን ጌታችን ቅዱስ ያሬድን
“ፍቅር ሰሐቦ” ብሎ እንዲያስተምረን፤
ላክልን ጌታችን ፍሬምናጦስን
የሰላሙን አባት ከሳቴ ብርሃን፤
ላክልን ጌታችን ተክለ ሃይማኖትን
ቀጭኑን ፓትርያርክ ጫማ ‘ማያውቀውን፤
ላክልን ጌታችን ጎርጎርዮስ ካልዕን
የዝዋዩን መናኝ ባህታዊ ምሁሩን፤
ተዋሕዶ ተጣራች ተጋልጣ እርቃኗን
ልጇ ቢቀድባት ቀሚስ ነጠላዋን፤
አትናቴዎስ ተነሥ ቁም ተሟገትላት
ቄርሎስም ተነሣ ጥብቅና ቁምላት፤
ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳኑን ጻፍላት
ዲዮስቆሮስ ተነሥ ጥርስህ ይርገፍላት፤
ጊዮርጊስ ተቀበል ሰማዕትነቱን
በመጋዝ መሰንጠቅ በጦር መወጋቱን፤
ባስልዮስም ጥራው ቅዱስ ኤፍሬምን
ለተዋሕዶ ያልቅስ ይዝጋ በዓቱን፤
ማኅበረ ሥላሴ ዋልድባም ተናገር
ጣና ቂርቆስ ፈክር የተዋሕዶን ነገር፤
አክሊላችን ወድቋል ከራሳችን ወርዶ
ክብርም ሸሽታለች ከጽድቅ ወዲያ ማዶ፤
ያን ደግ ኖላዊ ቅን የተዋሕዶ መሪ
ያን ደግ እረኛ ላክልን ፈጣሪ።

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)