July 15, 2010

የሊቃውንቱ ማፍሪያ የበዓታ ለማርያም ገዳም እየፈረሰ ለቅንጦት መኪና እና ሐውልት ሚሊዮኖች ሊባክን ይገባዋል?

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 15/2010)፦ የሚከተለው ሪፖርታዥ የተወሰደው ከማ/ቅዱሳን ድረ ገጽ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው ታላቁ በዓታ ለማርያም ገዳም እንዴት ባለ አሳዛኝ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ያትታል። እንኳን ወደ ገጠር ሄደን እዚሁ ቤተ መንግሥቱ እና ቤተ ክህነቱ አጠገብ ያለው የአገር ቅርስ እንኳን እንዲህ ከጥቅም ውጪ እየሆነ ነው። በአንጻሩስ? ዞረን ዞረን ወደዚያው ሆነ እንጂ የሐውልቱ፣ የመኪናው እና የቅንጦቱ ነገር ውስጥ እንገባለን። ይህ ችግር እስካልተፈታ ድረስ እኛም መወትወታችን ይቀጥላል። መልካም ንባብ።

(ማ/ቅዱሳን ድረ ገጽ)፦ በአዲስ አበባ የሚገኘው የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም የመምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ ገዳም ከተመሠረተ ከ76 ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ በነዚህ የአገልግሎት ዘመናቱ ውስጥ በርካታ ታላላቅ ሊቃውንትን፣ መምህራንና ካህናትን አፍርቷል፡፡ ጥንታዊው የሀገራችን ቋንቋና ፊደል፣ ግእዝና ትምህርቱ ተጠብቆ እንዲቆይ፣ ለትውልድም እንዲተላለፍ በማድረግ በኩል ታላቅ ድርሻ አለው፡፡ ተቋሙን የሚያውቁት የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናን ሁሉ ለቤተ ክርስቲያናችን አለኝታና ቅርስ መሆኑን በኩራት ይናገሩለታል፡፡ ይህ ታላቅ ገዳምና ትምህርት ማእከል በችግር ምክንያት እየፈራረሰ ነው።


ተቋሙ በረዥም የአገልግሎት ዘመኑ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለአገር ከፍተኛ ጥቅም እንዳልሰጠ ሁሉ ዛሬ በከፍተኛ ችግር ላይ ይገኛል፡፡ ይህንን ችግር ምእመናን እንዲረዱትና ማሠልጠኛውን እንዲያውቁት ከገዳሙ አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት አባ ገብረ ክርስቶስ ስብሐት እና ከትምህርት ቤቱ ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀን እንግዳችን አድርገናል ተከታተሉን፡፡
    
የገዳሙ አመሠራረት

ዐፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ከእንጦጦ የጥቂት ጊዜ ቆይታቸው በኋላ ፍልውኃ አካባቢ አሁን ታላቁ ቤተ መንግሥት የሚባለውን ለማሠራት ሲመርጡና አዲስ አበባ ከተማን ሲቆረቁሩ ለጠዋት ማታ ጸሎታቸው ማድረሻ አነስተኛ ሥዕል ቤት ከቤተ መንግሥታቸው አጠገብ አሠሩ፡፡

ሥዕል ቤቷን የቤተ መንግሥቱ ሰዎችና የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን የኅብረት ጸሎት እያደረሱ ሲጠቀሙባት ቆዩ፡፡ ይህቺ ሥዕል ቤት ዛሬ በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ግቢ ውስጥ ስትገኝ፣ «ደብረ መንክራት ሥዕል ቤት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን» በመባል ትታወቃለች፡፡

የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ባሳተመው «የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ» ቁጥር 1፤ ነሐሴ 1992 ዓ.ም መጽሔት ላይ የገዳሙን አመሠራረት በተመለከተ የታሪክ ድርሳናትን ጠቅሶ እንዳሰፈረው፤ ዐፄ ምኒልክ በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ቅድስት ድንግል ማርያምን ዘወትር በጸሎት ይማጸኑዋት፣ ይማልዷትም ስለነበር ዕረፍታቸው ታኅሣሥ ሦስት በዕለተ ቀንዋ ሆነላቸው፡፡

ይህን ምስጢር የሚያውቁት ልጃቸው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የሕዝብ እንደራሴዎች መክረውና አጥንተው የመልካም ሥራቸው መታሰቢያ የአፅማቸው ማረፊያ እንድትሆን የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያምን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በ1910 ዓ.ም መሠረቱን ጥለው በ1920 ዓ.ም ቤተ ክርስቲያኒቷን መፈጸሙን» መጽሔቱ በገጽ 271 ላይ ገልጿል፡፡

ሐመር መጽሔት በዘጠነኛ ዓመት በቁጥር ሦስት በሐምሌ /ነሐሴ 1993 ዓ.ም እትሙ ስለ ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳምና የካህናት መምህራን ማሠልጠኛ ባወጣው ዘገባ ላይ በወቅቱ የነበሩትን የገዳሙ አስተዳዳሪ ጠቅሶ ስለገዳሙ አመሠራረት እንዲህ አስነብቦ ነበር፡፡

«ገዳሙ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ እምነት የተመሠረተ ባለ ታሪክ ገዳም ነው፡፡ የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ፣ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል፣ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እንዲሁም የሌሎችም ንጉሣውያን ቤተሰቦችና ጳጳሳት፣ አፅም ያረፈበት ጥንታውያን ንዋያተ ቅዱሳት፣ የብራና መጻሕፍት፣ ቅርሳ ቅርስ የሚገኙበት ታሪካዊ ገዳም ነው፡፡» በማለት የሚገልጸው መጽሔቱ፤ ቤተ ክርስቲያኑን በገዳምነት እንዲተዳደር ያደረጉት ነግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ለመተዳደሪያ እጅግ በርካታ ገንዘብ ርስት፣ ሀብትና ንብረት ሰጥተው በ1925 ዓ.ም ገዳሙ እንዲመሠረት አደረጉ» ይላል፡፡

ገዳሙ ሲመሠረት አብረው የተቋቋሙና በሥሩ የሚተዳደሩ ሦስት ተቋማት አሉ፡፡ ተቋማቱም-
1. የመምህራንና የቀሳውስት ማሠልጠኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት
2. እናት አባት የሌሏቸው ሕፃናት በእንክብካቤ ተይዘውና በትምህርት ተኮትኩተው የሚያድጉበት /እጓለ ማውታ/
3. ጠዋሪ ቀባሪ ለሌላቸው አረጋውያን መጦሪያ ናቸው፡፡

የገዳሙ መተዳደሪያ

ገዳሙን የመሠረቱት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከማይንቀሳቀሰው ንብረት እና ርስት ሌላ ሦስት መቶ ሺሕ ማርያ ቴሬዛ ብር የገዳሙ መተዳደሪያ እንዲሆን ሰጥተዋል፡፡

ገዳሙ ተጨማሪ መተዳደሪያ በጀት የሚያስፈልገው መሆኑን በመረዳት ለዘለቄታው ራሱን ችሎ ሥራውን የሚያካሒድበት በርካታ የእርሻ መሬት ርስት ጉልት፤ የከተማ ቦታና ቤት፣ ጥሬ ገንዘብ የሰጡ እንደነ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ እና ሌሎችም በጎ አድራጊዎች ነበሩ፡፡

ጠቅላላ የገዳሙን ሥራ የሚያስተባብርና መንፈሳዊውን ሥራ የሚመራው በቤተ ክርስቲያኒቱ በቂ ዕውቀት እና የቁምስና መዓርግ ያለው «ሊቀ ሊቃውንት» ተብሎ የሚሾም አባት ነው፡፡ የገዳሙን ሀብትና ንብረት እየተቆጣጠረ ለሚያስፈልገው ተግባር መዋሉን የሚከታተል፡፡ የገዳሙን የገቢ ምንጭ ለማሳደግ የሚረዱ ሁኔታዎችን የሚፈጥር፣ የገዳሙን አስተዳደር፣ የትምህርቱን፣ የፋይናንሱን ወዘተ ሥራ የሚመራ በገዳሙ ሊቀ ሊቃውንት ሰብሳቢነት የሚመራ ባለ አደራ ቦርድ ገዳሙን በበላይነት እያስተዳደረ ሥራውን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

ባለ አደራ ቦርዱ ለገዳሙ ቋሚ የገቢ ምንጭ የሚያስገኙ በአዲስ አበባ ከተማ የሚከራዩ ሕንፃዎች በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን በገዳሙ ጽ/ቤት ግቢዎች ውስጥ ለተለያየ የገዳሙ አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንፃዎች፣ የእህል ወፍጮና ዳቦ ማምረቻ ወዘተ አሠርቷል፡፡

የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም በዚህ ሁኔታ በሚያገኘው ገቢ በሥሩ ያሉትን የመምህራንና ቀሳውስት ማሰልጠኛ ት/ቤት፣ ወላጅ የሌላቸውን ሕፃናት ማሳደጊያና የአረጋውያን መጦሪያ እያስተዳደረ እንዳለ በ1967 ዓ.ም በገጠር መሬት፣ በከተማ ቦታ ትርፍ ቤቶች አዋጅ የገዳሙ የእርሻ መሬቶች፣ የከተማ ቤቶችና ሕንፃዎች በሙሉ ተወረሱ፡፡ ደርግ የገዳሙን ሀብትና ንብረት ከወረሰ በኋላ፤ ለእጓለ ማውታው ማሳደጊያ፣ ለጡረታ ቤትና ለማሠልጠኛው መተዳደሪያና ለሠራተኞች ደመወዝ የተወሰነ በጀት መደበ፡፡

የባለ አደራ ቦርዱ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ግንኙነት እያደረገ የተያዘለት በጀት በገንዘብ ሚኒስቴር እየተሰጠው ከበጎ አድራጊ ምእመናን በስጦታ ከሚያገኘው ገቢ ጋር እያቀናጀ በዚህ ዓይነት መተዳደሪያ ገዳሙ መንፈሳዊ አገልግሎቱን እያከናወነ እስከ መጋቢት 15 ቀን 1986 ዓ.ም ድረስ ቆየ፡፡

ከዚያ በኋላ ግን የባለ አደራ ቦርዱ አስተዳደር እንዲፈርስ ተወስኖ የማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚሰጠው በጀት ቀርቷል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር በቃለ ዓዋዲው መሠረት በሰበካ ጉባኤ እንዲተዳደር ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ከጠቅላይ ቤተ ክህነት በየዓመቱ ከሚሰጠው ድጎማ ጋር ከንዋዬ ቅድሳት መሸጫው፣ ከእህል ወፍጮና ዳቦ ማምረቻው እንዲሁም ከበጎ አድራጊ ምእመናን በስጦታ ከሚያገኘው ገቢ ጋር በማቀናጀት ጠቅላላ የገዳሙን መንፈሳዊ አገልግሎት የመምህራንና የቀሳውስት ትምህርት ቤቱን፣ እናት አባት የሌላቸውን ሕፃናት ማሳደጊያ እንዲሁም የአረጋውያን መጦሪያ በማስተዳደር ላይ ይገኛል፡፡

የማሠልጠኛው አመሠራረት

በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ሥር የሚተዳደረው የመምህራንና ካህናት ማሠልጠኛ የተቋቋመው፤ ከመላ ኢትዮጵያ የሚመጡትን ተማሪዎች በልዩ ልዩ የትምህርት ዓይነቶች በሊቃውንተ ቤተ ክርስተያን አስተምሮና አሠልጥኖ በየዘርፉ ብዙ ካህናትና መምህራንን በማፍራት ቤተ ክርስቲያንን እና ሀገሪቷን እንዲያገለግሉ ለማድረግ፤

የአገራችን ኢትዮጵያ ጥንታዊ ቋንቋ ፊደል በተለይ የግእዝ ትምህርት ተጠብቆ እንዲቆይ ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፍና ማኅበረሰቡ እንዲጠቀምበት ለማስቻል፤ ትምህርት ቤቱ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለማስተማርና ለምርምር ተግባር ብቁ የሆኑ ጠበብትን ለማፍራት፤ በገዳሙ አካባቢ የሚኖሩትን ሕፃናት እየተቀበለ መሠረታዊ ትምህርት፣ ንባብና ጽሕፈት እንዲሁም አምስቱ አዕማደ ምሥጢርን በማስተማር በመልካም ሥነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ ለማድረግ ታስቦ በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያነት በ1925 ዓ.ም ተመሠርተ፡፡
  
የተለያዩ የታሪክ መዛግብት እንደ ሚያስረዱት፤ ማሠልጠኛው ተቋቁሞ መምህራንና ካህናት እያሰለጠኑ ቢቆዩም ተማሪዎች ምግብና ልብስ እየተሟላላቸው በአዳሪነት እንዲማሩና ትምህርቱ በመደበኛ ሁኔታ በጥራትና በተጠናከረ መልኩ እንዲካሔድ የተደረገው ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡

ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ በበዓታ ለማርያም ገዳም የቀሳውስትና የመምህራን ማሠልጠኛ የትምህርት ክፍል ሓላፊ /ርእሰ መምህር/ ናቸው፡፡ ስለማሰልጠኛው የትምህርት ሁኔታና የመግቢያ መሥፈርቶች የበፊቱን ከዛሬው ጋር እያነጻጸሩ ይናገራሉ፡፡

ቀደም ሲል ይሔ ቦታ ሁሉንም አስተባብሮ /አዋሕዶ/ ትምህርት ይሰጥ የነበረ ተቋም ነው፡፡ ሙዓለ ሕፃናት /መሠረተ ትምህርት/ ነበረው፡፡ እንደዚህ ዛሬ ሙዓለ ሕፃናት በየመንደሩ ሳይስፋፋ በነበረበት ሰዓት ለብቻው ቦታ አዘጋጅቶ ከሦስት መቶና ከአራት መቶ በላይ ሕፃናትን ሰብስቦ በክፍል ውስጥ መምህር ቀጥሮ ትምህርቱ ይሰጥ ነበረ፡፡

በዚህ የትምህርት ክፍል ውስጥ የንባብ መምህራን ሁለት ነበሩ፡፡ ፊደላቱን የሚያስቆጥርና በሳሎቹን ዳዊት የሚያስደግም፣ ንባብ የሚያስተምር ድርሳኑ፣ ስንክሳሩን የሚያስነብብ ወደ ፍጹምነት የንባብ ደረጀ ተማሪዎችን የሚያደርሱና የሚያስቀጽሉ መምህራን ነበሩ፡፡

አሁን ግን መምህሩ ሲሞቱ የሙዓለ ሕፃናቱ በጀት ታጠፈ ትምህርቱም ተቋረጠ /ሙዓለ ሕፃናቱም ቀረ፡፡/ በዚህ ላይ ብዙ ቅሬታ ተሰምቶ ነበር ብዙ ወላጆች ቢሮ ድረስ እየመጡ ልጆቻችንን የት እናስተምር እኛ ደሆች ነን ገዳሙ ደግሞ የድሆች መጠጊያ ነበር ለምን ትምህርቱን አስቀራችሁ ብን እያሉ ይጠይቁ ነበር መልስ ስላላገኙ ትምህርቱም በዚያው ቀረ፡፡

በማሠልጠኛው አሁን ትምህርት በመስጠት ላይ የሚገኘው ከንባብ የትምህርት ክፍል ጀምሮ ነው፡፡ ይኸውም የንባብ ትምህርት ቤቱ በመፍረሱ ትምህርቱ የሚሰጠው ሜዳ ላይ ነው፡፡ አሁን ተማሪዎቹ እየተማሩ ያሉት በዚህ ሁኔታ ነው የሚሉት ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን፤ በካህናትና መምህራን ማሠልጠኛው አሁን እየተሰጠ ያለውን የትምህርት ዓይነት በመዘርዘር የመግቢያ መሠፈርቱን ይገልጻሉ፡፡

በማሠልጠኛው የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች

 ጉባኤያት
1/ ንባብ ከጸሎት ዘዘወትር እስከ ዳዊትና መልክአ መልክእ
2/ ዜማ
3/ አቋቋም
4/ ቅዳሴ
5/ ቅኔ
6/ ሐዲሳት /ትርጓሜ/
7/ ብሉያት
8/ መጽሐፍተ ሊቃውንት /ሃይማኖተ አበው፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቄርሎስ፣ 14 ቅዳሴያት፣ የቁጥር መጽሐፍ አቡሻክር/ ናቸው፡፡
እዚህ ቦታ ላይ ቀደም ሲል እንደነገርኩህ ከዘጠኝ በላይ ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡ ሙዓለ ሕፃናቱን ሳንቆጥር፤    ዘጠነኛ የነበረው ፍትሐ ነገሥት፣ አቡሻክር እና መጽሐፈ መነኮሳት በመምህር ንቡረእድ አብዬ ሆይ በሚባሉ አባት በጥምረት ይሰጥ ነበር፡፡ እሳቸው ሲያርፉ ጉዳዩን አስቦ ሌላ መምህር የሚተካ በመጥፋቱ በቸልተኝነት ጉባኤው ታጥፎ ይገኛል፡፡ ይላሉ ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን፡፡


የትምህርት ቤቱ የመግቢያ መስፈርት


ለንባባ ቤት፡- ንባብ ቤት የትምህርት መጀመሪያ በመሆኑ ትምህርቱ የሚጠይቀው መሥፈርት የመማር ሓላፊነትና ፍላጎት ብቻ ነው፡፡

ለዜማ፡- ንባብን በሚገባ ማወቅ አለበት፡፡ ይህም ማለት አርባዕቱ ወንጌላትን፣ መልዕክተ ጳውሎስን፣ ራእይ ዮሐንስን፤ ከቻለ ደግሞ ስንክሳሩን፣ ድርሳናቱን ያነበበ በንባብ የበሰለ ያለ ከዚሁ ጋር ዳዊትን፣ ውዳሴ ማርያምን፣ መልክአ መልኩን በቃሉ ያጠና ወደ ዜማ ቤት ይገባል፡፡


ለአቋቋም ቤት፡- የአቋቋም መስፈርቱ ዜማ ያወቀ ነው፤ ይህም ማለት ውዳሴ ማርያም ዜማ የተማረ፣ የቃል ትምህርት መስተጋብእ፣ አርያም፣ ሠለስት የጾም ምዕራፍን ያወቀ፤ በተለይ ጾመድጓ የዘለቀ፣ ድጓ የተማረ ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ መስፈርቱ እስከ ጾመ ድጓ ድረስ መማር ሲሆን ድጓውን ቢማር እጅግ ጥሩ ይሆናል፡፡


ለቅዳሴ፡- ውዳሴ ማርያምን በዜማ የዘለቀ፤ ዜማዊ የቃል ትምህርቶችን የተማረ ቢሆን ይመረጣል እነዚህን የተማረ ነው ወደዚህ የትምህርት ክፍል የሚገባው፡፡ ምክንያቱም የቅዳሴ ዜማ ረዘም ያለ ስለሆነ በውዳሴ ማርያምና በሌሎችም ዜማዎች መታሸት አለበት፡፡


ለትርጓሜዎች፡- ሐዲስ ኪዳንን መማር የሚፈልግ የግድ ቅኔ የተቀኘ መሆን አለበት፤ ቅኔ ከነአገባቡ በሚገባ የቀጸለ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ምክንያቱም የትርጓሚያት ንባባቱ ከቅኔ ትምህርት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ሰዋስው አወቃቀሩ ይያያዛል፡፡ ለምሳሌ አንድ የሐዲስ ትርጓሜ ተማሪ ንባቡ ሲነበብለት ጥሬ ትርጉሙን ማወቅ አለበት፡፡ ቅኔ የማያውቅ በኛ ት/ቤት በሐዲስም ሆነ በብሉያት ውስጥ አይገባም፡፡ ስለዚህ ቅኔ በሚገባ ማወቅ ለትርጓሜያት ሁሉ ዋና መሥፈርት ነው፡፡ የበለጠ የተመረጠ የሚሆነው ግን ዜማን በተጨማሪነት ቢያውቅ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ሁለገብ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር ነው፡፡


ለቅኔ፡- ለቅኔ መሥፈርቱ ንባብን ማወቅ ነው፡፡ በአጠቃላይ ንባብ ነክ ትምህርቶችን ያወቀ ወደቅኔ ቤት ይገባል፡፡ ትምህርት ቤቱ /ገዳሙ/ መስፈርቱን ያዘጋጀው በሁለት መንገድ ነው፡፡

1/ ለተመላላሽ ተማሪ
2/ ለአዳሪ ተማሪ ብሎ ነው ያዘጋጀው፡፡
ለአዳሪ ተማሪ ለየአንዳንዱ ጉባኤ ተመድቦለታል በመደበኛነት ገብቼ መማር እፈልጋለሁ ላለ ገዳሙ ይሔን፣ ይሔን ማወቅ አለበት ብሎ አዘጋጅቷል፡፡ ስለዚህ አሁን የተጠቀሰው መስፈርት በአጠቃላይ ትምህርቱን ለመማር የወጣ መስፈርት ነው፡፡ ትምህርቱን ለመማር መመዘኛው አንድ ዓይነት ሲሆን ለአዳሪ ተማሪዎች ግን ተጨማሪ መመዘኛዎች አሉአቸው ማለት ነው፡፡

 መታወቅ ያለበት ወደ ትምህርት ቤቱ ለመግባት በወጣው መሥፈርት ላይ እንደገና የመግቢያ ፈተና መኖሩን ነው፡፡ ጥንት ፈተናው በጣም ጠጣር ነበር፡፡ አሁን ግን የአብነቱ ትምህርት እየተዳከመ ስለሆነ ፈተናው ቢኖርም እንደጥንቱ በጣም ከባድ ፈተና አይደለም እየሰጠን ያለነው፡፡ የትምህርት ፍላጎቱ ካለውና መሥፈርቱን ካሟላ የመግቢያ ፈተናው ይሔን ያህል የከረረ አይደለም፡፡

 ትምህርቶቹ የሚወስዱት ጊዜያት

ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን በትምህርት ቤቱ ለሚሰጡት ትምህርቶች /ጉባኤያት/ የተመደበላቸው ጊዜ ላይ የትምህርት አስተዳደሩ ቆራጥ አቋም እንዳለው ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ጉባኤያቱ የሚፈጁት ጊዜ ተለክቶ ተቀምጧል፡፡ በተለይ ለአዳሪ ተማሪዎች እጅግ በጣም ጥብቅ ነው፡፡ በማለት ያስረዱት ሊቀ ጉባኤ፤ ምክንያቱንም እንደሚከተለው ይገልጻሉ፤ ትምህርቱን በጊዜ ገደብ መከፋፈሉ የትምህርት ጥራቱን ይጠብቃል፤ አንድ ተማሪ የተመደበለትን ጉባኤ በተመደበለት ጊዜ ካልጨረሰ ደጅ የሚጠኑ ተማሪዎችን ማለትም በአዳሪ ገብተው ለመማር ብዙ ጊዜ የሚጠብቁትን ተማሪዎች ያጉላላል፣ ስለዚህ አንድ ተማሪ በተመደበለት ጊዜ ካላጠናቀቀ በሱ ምትክ ሌላ ጎበዝ ተማሪ እንዲተካው ይደረጋል፡፡ የጉባኤው ዓመታት ውስንነት ጥብቅ የሆነው ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች ነው፡፡ በሌሎቹ ጉባኤ ቤቶች ያየን ከሆነ ግን አንድ የአብነት ተማሪ በአንድ ጉባኤ ቤት  ከ10 እስከ 15 ከዚያም በላይ በአንድ ጉባኤ ብቻ ይቆያል፤ በኛ ግን ይሔ አይታሰብም /የለም/፡፡ ከዚህ አንጻር በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም የካህናትና መምህራን ማሠልጠኛ ት/ቤት ጉባኤያቱ እንደሚከተለው የጊዜ ገደብ ተመድቦላቸዋል፡፡

- ለንባብ የተቀመጠለት ጊዜ ሁለት ዓመት፤
- ዜማ ቤት ስድስት ዓመት፤
- የአቋቋም ሰባት ዓመት፤
- የቅዳሴ አራት ዓመት፤
- የቅኔ አራት ዓመት፤
- የሐዲሳት ስድስት ዓመት፤
- ብሉያት ስድስት ዓመት፤
- የሊቃውንት ትምህርት ሰባት ዓመት ናቸው፡፡
የመደበኛ ተማሪዎች አኗኗር


የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት አባ ገብረ ክርስቶስ ስብሐት ስለ ማሠልጠኛውም ሆነ ስለመደበኛ ተማሪዎች አሁን ያለበትን ሁኔታ ከጥንቱ ጋር እያወዳደሩ ይገልጻሉ፡፡


ሊቀ ሊቃውንት «ለተማሪዎቹ የተመደበው በጀት ድሮ በነበረው ስሌት በመሆኑ አሁን ካለው ኑሮ ጋር የተመጣጠነ አይደለም፡፡ ተማሪዎቹ ቁርስ መብላት ካቆሙ ከሁለት ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡» ይላሉ፡፡ «ይህችኑ ለአንድ ተማሪ 150 ብር የሚመደበውን በጀት መሸፈን አቅቶን በትምህርት ቤቱ በአዳሪነት /በድርጎ/ መማር ከነበረባቸው 70 ተማሪዎች አሁን ተቀብለን ያለነው 60 ብቻ ነው፡፡ ለዚህም አቅማችን እየተዳከመ ነው» በማለት የተማሪዎቹ የአኗኗር ሁኔታ በችግርና በመከራ የተሞላ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን በበኩላቸው ተማሪዎቹ አሁን ያሉበትን ሁኔታ እንደ ሊቀ ሊቃውንት አባ ገብረ ክርስቶስ በማነጻጸር ጀምራሉ፤ ተማሪዎቹ በዓመት ዩኒፎርም፣ /የትምህርት ቤት ልብስ/ ብርድ ልብስ፣ አንሶላ፣ የጤና መጠበቂያና ሽፋን ነበራቸው፤ ምግባቸ ውም በመጋቢው አማካኝነት ጾም ካልሆነ በቀር በሁሉም ሰዓት የተሟላና ጥሩ ነበረ፡፡


አሁን ግን ይሔ ከስምንት ሺህ በላይ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ያፈራ ከ38 በላይ ሊቃነ ጳጳሳትን ያወጣ፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ብዙ ለሀገርም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ ምሁራንን ያስገኘው ተቋም ዛሬ ቤቱ ብቻ ሳይሆን እየፈረሰ ያለው የተማሪዎቹም ሕልውና ነው፡፡ ዛሬ የመምህራኑ ኑሮ ተጎሳቁሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የመማር ማስተማሩ ሒደት ሕንፃው መፈራረስ ሌላ ችግር ነው፤ ዛሬ በማሠልጠኛችን የትምህርት አሰጣጥ ሥር ዓቱ እየተዳከመ ነው፡፡ መምህራን ሲያልፉ የሚተኳቸው መምህራን ማጣት በጣም አስቸጋሪ እየሆነብን ነው፡፡


ተማሪው በሦስት፣ በአስራ ስድስት እና የሰንበት ዕለታት በቤተ ክርስቲያን እንደንብ ተሰግስጎ ገብቶ እንዲያገለግል ይደረግ ነበር፤ ዛሬ ግን ከስብሐተ ነግህ በስተቀር ማኅሌቱንም ቅዳሴውንም እንደ ጥንቱ ተማሪው እንዲቆም ማድረግ አልቻልንም፡፡ ለምን ቢባል ተማሪው ሌሊት ሲያገለግል አድሮ ጠዋት የሚቀምሰው የሚልሰው ባለመኖሩ ይሔን ሳናሟላ ሐደህ አገልግል፤  ማኅሌቱንም ቁም ብሎ ለማስገደድ የሞራል ብቃቱ አንሶናል፡፡


ተማሪው ቁርስ የለውም፣ ምሳና እራቱም ቢሆን አጥጋቢ አይደለም፡፡ በዓመት የሚሰጠው ዩኒፎርም ቀርቷል፡፡ ብርድ ልብስም ሆነ ዩኒፎርሙ ከቆመ ሰባት ዓመታት አልፎታል፡፡ በቅርቡ ማኅበረ ቅዱሳን ከበጎ አድራጊዎች ጋር በመተባበር ለ70 ተማሪዎች ብርድ ልብስ፣ አንሶላና ጫማ ባይሰጥልን ኖሮ ተማሪው በሌሊት ልብስ ተራቁቶ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የተማሪው የኑሮ ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ የተማሪው መኝታው በላዩ ላይ እየፈራረሰ ነው፤ አልጋዎቹ ወላልቀው በጧፍና በገመድ ተጠፍረው ነው ያሉት፤ ከዚህ አንጻር የተማሪው መብት በመጓደሉ ግዴታውን እንዲወጣ ለማድረግ እያቃተን ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን ማታ ሰርክ ጸሎት፣ መሐረነ አብ፣ እግዚኦታ ይደርሳል፣ ይሔ አገልግሎት ከዓመት ዓመት አይቋረጥም፡፡ ሌሊት ደግሞ ስብሐተ ነግሕ ሌሊቱን ሳይቆም በምንም ሁኔታ አይታደርም 365 ቀናት አይቋረጥም በዚህ ለየት ያለ ነው ትምህርት ቤታችን፡፡


ይህ ሁሉ ችግር እያለም ቢሆን ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ስምንቱን ጉባኤ የሚማሩ ከ60 በላይ የአዳሪና ከ240 በላይ ተመላላሽ ተማሪዎች አሉ፡፡ አኗኗራቸውም በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሥርዓት መሠረት ነው፤ በየዓመቱም በአማካይ ከ30 በላይ እጩ መምህር እናወጣለን /እናስመርቃለን/

 ትምህርት ከመደበኛው ጊዜ ውጪ

የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም መምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ ቀንና ሌሊት /24 ሰዓት/ በጋና ክረምት ጉባኤው ሳይቋርጥ የሚካሔድበት ትምህርት ቤት ነው፡፡


ከተለያዩ አድባራት በሥራ ላይ ሆነው ሞያቸውን /ዕውቀታቸውን/ ለማሻሻል የሚመጡትን ሁሉ ያስተምራል፡፡ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ሥራ ላይ ያሉትንም የሥራ ሰዓታቸውን በማይነካ መልኩ ከመምህራቸው ጋር በመነጋገር አመቺ ሰዓት መርጠው በትርፍ ጊዜአቸው ይማራሉ፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችም /የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች/ በመምጣት እየተማሩ ነው፡፡ በደጅ ጥናት አዳሪ ትምህርት ቤት ለመግባት የሚጠባበቁትም ተመላላሽ ሆነው ሙሉ ቀን ይማራሉ፡፡


ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን መደበኛ ከሆነው ትምህርት ውጪ ማሠልጠኛው ብዙዎችን ለማስተማር የሚረዱ ሥርዓተ ትምህርት ዘመኑን በዋጀ መልኩ በመቅረጽ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡ በቀጣይም ሥርዓተ ትምህርቱን ለሁሉም በሚመች መልኩ ለመቅረጽ የሰው ኃይል፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማፈላለግ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ለመጀመር ብለን በቀረጽነው ሥርዓተ ትምህርት ብዙ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች ተቀብለን እየስተማርን ነው፡፡ በዚህ ትምህርት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤ የሚማሩ ልጆችም ተካተው እየተማሩ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የቤተ ክርስቲያኒቱን የአብነት ትምህርት ለመማር የሚፈልጉ ሁሉ ወደ ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም የካህናትና መምህራን ማሠልጠኛ ገብቶ መማር እንደሚቻል ለመግለጽ እንወዳለን ይላሉ ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ፡፡


ማሠልጠኛው ከሌሎች ተቋማት ጋር ያለው ግንኙነት

ማሠልጠኛው ከሌሎች ተቋማት ጋር የመመረቂያ ልብስ ውሰት በቀር ይህ ነው የሚባል ድጋፍ እንደሌለው ሊቀ ጉባኤ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ከቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ የአብነቱን ትምህርት በአጭር ጊዜ ለመማር የሚፈልጉ ደቀ መዛሙርት ከኮሌጁ አጽፈው ሲመጡ ለሦስት ወርም ሆነ ባላቸው ትርፍ ጊዜ ሁሉ እናስተምራለን ይላሉ፡፡


ማሠልጠኛውን ከሌሎች የሚለየው ነገር

የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም የካህናትና መምህራን ማሠልጠኛ ከሌሎች ጉባኤ ቤቶች የሚለየው ሁሉም ጉባኤ በተጠናከረ መልኩ በአንድ ቦታ በመሰጠቱ ነው፡፡

በሌሎች የአብነት ትምህርት ቤቶች ጥቂት ካልሆኑ በቀር እንዲህ ተጠናክረው ጉባኤያቱን በአንድ ላይ የሚሰጡ ብዙ ጉባኤ ቤቶች የሉም፡፡ በዚህ ግን አንድ ተማሪ ሁሉንም ጉባኤ የመማር አቅምና ጊዜ አለኝ ካለ ስምንቱንም ጉባኤ መማር ይችላል፡፡


የተማሪው አቤቱታ

በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም የካህናትና መምህራን ማሠልጠኛ ተማሪዎች፤ በትምህርት ቤቱ ካለባቸው ችግር በላይ የሚያሳስባቸው እና ሁልጊዜ በጭንቀት እንዲወጠሩ የሚያደርጋቸው ነገር አለ፡፡ ይኸውም በብዙ ድካምና ችግር ተምረው ካጠናቀቁ በኋላ ተመደበው ሥራ ያለማግኘታቸው ጉዳይ ነው፡፡


ከማሠልጠኛው ተምረው የሚወጡ ደቀ መዛሙርት እንደሌሎቹ ማለትም እንደቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ እንደ ሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤትና እንደሌሎችም መንፈሳዊ ኮሌጆች ተመራቂ ደቀመዛሙርት ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ተመድበው ሥራ አይዙም፡፡ በዚህ ምክንያት ለቤተ ክርስቲያን እንደ መብራት ሆነው የሚያገለግሉ ሊቃውንት በየቀን ሥራው፣ በየሰው ቤት በዘበኝነት ተቀጥረው እያገለገሉ እንደሚገኙና አንዳንዶቹም፣ ዕድሉን አግኝተው ተቀጥረው ቤተ ክርስቲያንና ምእመናኑን እያገለገሉ እንደሚገኙ ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ ይገልጻሉ፡፡

ሊቀ ጉባኤ እንደገለጹልን ችግሩን ለመቅረፍ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሣሙኤል ጊዜ ተማሪዎቹ ተመርቀው ሲወጡ በየደብሩ በየሙያቸው የመመደብ ሥራ ተጀምሮ እንደነበር ጠቅሰውልናል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት እየሰፋ ነው የሚሉት ሊቀ ጉባኤ፤ ይሔን እየሰፋ ያለውን አገልግሎት በትክክለኛው አገልጋይ እንዲሸፈን ለማድረግ በየጉባኤ ቤቱ እየሠለጠኑ የሚወጡ ደቀ መዛሙርትን በአገልግሎት ቦታ መመደብ ቤተ ክርስቲያን ጊዜ ልትሰጠው የማይገባ ጉዳይ ነው በማለት ማሠልጠኛው ያሳስባሉ፡፡

 ትምህርት ቤቱ አሁን የሚገኝበት ሁኔታ

የገዳሙ አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት ገብረ ክርስቶስ ትምህርት ቤቱ የሚገኝበትን የአሁኑን ሁኔታ የሚገልጹት ከዚህ በፊት ለቤተ ክርስቲያን ከሠራው ውለታና ካፈራቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ብዛት አንጻር ነው፡፡

 የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም የካህናትና መምህራን ማሠልጠኛ ከ38 በላይ ሊቃነ ጳጳሳትን፣ በርካታ ስለቤተ ክርስቲያን ሊጠየቁ የሚችሉ ሊቃውንትን፣ ለሀገርም በርካታ ውለታ የሠሩ ዶክተሮችንና ፕሮፌሰሮችን አፍርቷል ይላሉ፡፡ ሊቀ ሊቃውንት ገብረ ክርስቶስ፡፡

ዛሬ ግን ይሔ በርካታ ሊቃውንትን ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን ያበረከተው ማሠልጠኛ በመፈራረስ ዛሬና ነገ በላያችን ወደቀ እያልን በመሥጋት ላይ ነን፡፡ ግድግዳው የተመረገበት ጭቃ ረግፎ ማገሩ የተያያዘበት የሣር ገመድ በመበጣጠስ ላይ ይገኛል፡፡ የንባብና ሙዓለ ሕፃናት መማሪያ የነበሩት ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ፈርሰዋል፡፡

 በዚህ ምክንያት ሙዓለ ሕፃናት ክፍሉን የማስተማር ሥራውን ስንተወው የንባብ ትምህርቱን ግን መምህራኑ በሜዳ ላይ ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡ ያልፈረሱት የመምህራኑና የተማሪዎቹ መማርያና መኖሪያ ክፍሎች ጣሪያዎችና ግድግዳው ክፍት በመሆኑ በፀሐይና በዝናብ እየተፈራረቀባቸው ይገኛል፡፡ መምህራኑም ሆኑ ተማሪዎቹ በችግር ላይ ናቸው፡፡ በክረምት ወቅት ቤቶቹ በማፍሰሳቸው ተማሪዎቹም ሆኑ መምህራኑ ክረምቱን የሚያሳልፉት በሠቀቀን ነው፡፡ በድርጎው በኩል ለተማሪዎቹ የምንደጉማት ገንዘብ አሁን ካለው የኑሮ ሁኔታ ጋር ባለመጣጣሟ ተማሪዎቹ ቁርስ እንዲያቆሙ ተደርጓል፡፡ በችግሩ ምክንያት የመቀበል አቅማችንን በአሥር ሰው ቀንሰናል፡፡ ጾም ሳይሆን የሚበሏት ምሣና አራትም ብትሆን ይሔን ያህል የምትበቃ አይደለችም፡፡ እንዲያው ለስም የሆነች ናት የሚሉት ሊቀ ሊቃውንት የማሠልጠኛው ችግር ከቃላት በላይ ነው ይላሉ፡፡

 የመፍትሔ እርምጃ

አስተዳዳሪው እንደሚሉት፤ የተማሪውን የድርጐ ሁኔታ ለማሻሻል የገዳሟ ገቢ አነሥተኛ በመሆኑ ለማስተካከል እየጨነቀን ቢሆንም፤ ትምህርት በቱን  መልሶ ለመጠገን ግን ምእመናንን ተስፋ አድርገን ቆርጠን ተነሥተናል፡፡ ከዚህ በፊት ይሔን ትምህርት ቤት ለማደስ ያልተቋቋመ ኮሚቴ ያልተደረገ ጥረት እንዳልነበረ ሰምቼያለሁ፤ ነገር ግን በተለያየ ምክንያት አልተሳካም፡፡ አሁነ ግን ቅዱስነታቸው በታኅሣሥ 3 ቀን 2002 ዓ.ም. የበዓታ ክብረ በዓል ላይ ለእድሳቱ ሃምሣ ሺሕ ብር ለመስጠት ቃል በመግባታቸውና ሥራው እንዲጀመር መመሪያ በመስጠታቸው የዲዛይን ኮሚቴ አቋቁመን እንቅስቃሴ ጀምረናል ይላሉ፡፡


መልእክት ለሕዝበ ክርስቲያኑ

ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መፋጠን ደከመኝ ሰለቸኝ የማይለው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመን፣ መንፈሳዊ ማኅበራት፣ ለሀገር ታሪክ የሚቆረቆሩ የሀገር ወዳጆችና መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለዚህ ታሪካዊ ትምህርት ቤት በጋራ በመቆም ድጋፍ እንዲያደርጉ ሊቀ ሊቃውንት ገብረ ክርስቶስና ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ ተማጽነዋል፡፡

7 comments:

Anonymous said...

Hey,Who will have the control over the finance that's going to be collected for maintainance of the building? If it's again ye'abune paulos Mafia group I will so NOOOOOOOOOO TO MY $$$.If there is a mechanism of transparency with direct implementation to the work ,ofcourse that's my christian responsibility!!!

Anonymous said...

yeabiyate betekiristiant megodat yehiliwuna guday new. enegnih sewock haimanotachinin knemeteleyawu eyatefubin enidehone gilits new. neger gin leman new eridatawun yeminisetew zare beadiss ababa yetejemerewun hawulit degimo betigiray enidiketilu eniridachew? 3.4 milion birr mekina enichemirilachew? esikahun yesebesebutin mejemeria tifitew yicherisut. enebegashaw eko zare yaleminim efiret 100,000 birr yesetubet gubaea sisera wenigelin lemasifafat bilew betesalew anidebetachew bemechoh kekisachin bawetut genizeb new. ene fanitahun moche 3.4million bir awutitew mekina yegezut bedihawa mebelet santim eko new. ere enasitewul. gidelachihum egiziyabiher dehina ken siyameta hulu yisitekakelal mejemeria enezihin yezemenachinin yihubdawoch amilak befekedew meniged bota enidisetilin hulachinim beanidinet entseliye. balefut yesera yegeta eji zarem yiseral. zare lebetekiristian genizeb ayasifeligatim egiziota yikidem. libona yalew eregna sigegne lelaw yiketelal

awudemihiret said...

dejeselam...yihe yetetsafew mechee new?keziyas behuala lewut ale wey?yetebalew 50,000 birr teseto tadisual wey?asteyayet lemestet endyamech new.

new generation said...

WENDIMOCHE ENA EHITOCHE YIH YE EPRDF POLICY NEW.
AHUN TIYAKEW ANDI ENA ANDI NEW MENGIST BETECHRISITANIN MADAKEM YIFELIGAL.SILEZIH BE MENGIST LAY TESINO MAMTAT MECHAL ENA HUNETAWOCHIN MASTEKAKEL NEW. SINODOS SIBSEBA LAY ABAY TSEAHYEN LIKO TERENBEZA EYEDEBEDEBE YEMIASFERARA MENGIST NEW YALEN.
TIYAKEW WEY BETEMENGIST MEGBAT WEYIM BETEKIHNET MEGBAT NEW AHUN MEFTIHEW BETEMENGISTU SIKEYER BETE KIHNETU YIKEYERAL ENA MINIM MAMOKASHET AYASFELIGIM YE ETHIOPIA KURT KEN LIJOCH TESEBASEBU HULU EJACHIHU LAY ALE.
NEW GENERATION

Anonymous said...

dear aba paulos,

i want to ask u one short question Are u christian????????????????????!!!!!!!!!!!!!!!

Anonymous said...

I am very sorry about some enemy of Patrialic Abune Pawlos. Because he is a true christian.

Please leave them alone. let them do thair job. Who are you to guge? Please dont give the mony to call them self MK mafia group again. Thank you.

Anonymous said...

አባታችና አብራሀም ጣዎት ተሸክሞ ቤቱ ያረፈውን ሰው ለአንድቀን መታገስ አቅቶት እንደነበር ና አምላኩን እንዳስቆጣ መጽሀፍ ቅዱሳችን ይነግረናል ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላክ ያንን ሰው ለረጅ ጊዜ ተሸክሞት ስለ ነበር ፡፡ እግዚያብሔር የዘገየ ቢመስልም እንኳን ከሁሉም ይቀድማል እና “ ብትዘገይም የሚቀድምህ የለም” እያልን በጸሎት እንትጋ፡፡ ረድኤተ እግዚ አብሔርአየለየን

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)