July 10, 2010

በጋሻው እና ወ/ሮ እጅጋየሁ ያዘጋጁት ጉባዔ?

(ደጀ ሰላም፣ ጁላይ 10፤ 2010)፦ “ሰማዕት ዘእንበለ ደም፤ ደም ያልፈሰሳቸው ሰማዕት” በሚል ርዕስ “የቅዱስ ፓትርያርኩን 18ኛ ዓመት በዓለ ሲመት ምክንያት በማድረግ በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን” የተዘጋጀ ጉባዔ ዛሬ ቅዳሜ ጁን 10 እና እሑድ ጁን 11/2010 (ሐምሌ 3 እና 4/ 2002 ዓ.ም) እንደሚካሔድ ተገልጿል፣ ማስታወቂያውም በሪፖርተር የረቡዕ ጋዜጣ ላይ ታትሟል።  ይህ “ልዩ ጉባዔ” በብዙ መልኩ “ልዩ” ነው።


ለመሆኑ አዘጋጆቹ እነማን ናቸው? የአዘጋጆቹ ማንነትና ስብጥር ቀልብን የሚስብ ነው። በአንድ በኩል “የዘመናችን ኤልዛቤል፣ ሴቷ ፓትርያርክ” እየተባለች የምትጠራው ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ አለች። በሌላ በኩል ደግሞ “የመስቀሉ ስር ቁማርተኞች” በሚል ቅዱስነታቸውን የሚሳደብ መጽሐፍ በመጻፍ ታዋቂ የሆነውና “በዚሁ ምክንያት ታስሬያለሁ” የሚለው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከምዕመናን ተቃውሞው እየበረታበትና ተቀባይነቱ እየቀነሰ የመጣው ዲ/ን በጋሻው ደሳለኝ አለ። ሌላው ዘወትር ሽጉጥ እየታጠቀ የሚሄደውና ለምን እንዲህ ታደርጋለህ ሲባል “በቅዱሳን መላእክት ሥዕል ላይ አላየህም? ሚካኤልና ገብርኤል ጦርና ጎራዴ ታጥቀዋል” እያለ የሚዘብተው ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን አባል ነኝ የሚለው ነገር ግን እነ በጋሻውንና እነ ወ/ሮ እጅጋየሁን በድልድይነት የሚያገናኘው፣ ይህንንም ጉባዔ የጠነሰሰው ቀሲስ ሰሎሞን ሙሉጌታ የሚገኙበት ስብስብ ነው። ከዚያ ውጪ ያሉት ሌሎቹ አጫፋሪዎች ናቸው ማለት ይቻላል።
ቅዱስነታቸው እንዳይከብሩ፣ ስማቸው ከፍከፍ እንዳይል የምንመኝ ሰዎች አይደለንም። 18 ዓመት በፕትርክና ማገልገልም ሊከበርና በዓል ሊደረግለት እንደሚገባው እናምናለን። የሚደረገው ነገር ግን ከእውነት እና ስለ እውነት መሆን አለበት። መቸም ቤተ ክርስቲያኒቱ የእውነት ቤት ናት፣ ባለቤቷና መሥራቿ ኢየሱስ ክርስቶስም እውነት መሆኑን ተናግሯል። አሁን እየተደረገ ያለው ሐውልት የመሥራት ግርግር፣ “ሰማዕት ዘእንበለ ደም” የሚለው የለበጣና የሽሙጥ አነጋገር ግን የሚያዋርደው ቅዱስ ፓትርያርኩን ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱን ጭምር እንዲሁም ሁላችንንም ኦርቶዶክሳውያንን በሙሉ ነው። በእውነቱ በዚህ ዓይነቱ ዝግጅት ፓትርያርኩ የበለጠ ይዋረዳሉ፣ ከሰው ልብ ይወጣሉ እንጂ ፍቅርን አያተርፉም፣ ሰውም አያከብራቸውም። ሐውልቱም ልክ እንደ ሌኒን ሐውልት ዘመን የተቀየረ ቀን መፍረሱ አይቀርም፣ 6ኪሎ እንዳለው እንደማርክስ ሐውልት ቆሻሻ ቀለም ላዩ ላይ መደፋቱ አይቀርም።

ሌላው የሚገርመው ሁኔታ ቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኝ እጇን በግራ የምትቆርጥ መምሰሏ ነው። ባለፈው ግንቦት የዋለው የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ፈቃድ የሌላቸው የአደባባይና የመንደር ጉባዔዎች እንዲታገዱ መመሪያ ባወጣው መሠረት ጉባዔያቸው ከታገደባቸው ሰዎች መካከል ዋነኞቹ የዚህ ድግስ ደጋሾች ሆነው ብቅ ማለታቸው አስቂኝና አሳፋሪ አጋጣሚ ሆኗል። ግንባር ቀደሙ ደግሞ በጋሻው ነው። ትናንት ፓትርያርኩን መሳደብህ ሌላ ጥፋት ነበረ፣ ዛሬ ደግሞ “ስምከ ሕያው ዘኢይመውት” እያልክ መለፈፍህም ሌላ ጥፋት። ሴትየዋ እንዳለችው ተረት “ያም በዛ፣ ይኼም በዛ”። እንደፈለጉ ጉባዔ እያዘጋጁ የምእመኑን ገንዘብ መዝረፉ ሲከለከል ፓትርያርኩን “ለመሸወድ” እንዲህ ዓይነት ቆሻሻ ስራ መስራት ያሳፍራል። ምእመናን ግን ሁሉንም ያያሉ፣ ይታዘባሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አምላክ እነዚህ “ሆዳቸው አምላካቸው” የሆኑ ሰዎችን ይመለከታል። ልብ ይስጣቸው።
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)