June 19, 2010

“ሁለቱን ሲኖዶሶች” ለማስታረቅ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኘው ስብስብ ጉባዔውን አካሄደ


(ደጀ ሰላም፤ ጁን 19/2010)፦ ሁለቱን “ሲኖዶሶች” ለማስታረቅ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኘው ስብስብ ጉባዔውን አካሄደ። ከሁለቱም “ሲኖዶሶች” በጎ ምላሽ ማግኘቱ ታወቀ።

ከአምስተኛው ፓትርያርክ ማግስት ሹመት እና ከአራተኛው ፓትርያርክ ስደት ማግስት ጀምሮ በተነሣው ክፍፍል እስከ መወጋገዝ የደረሱትን አባቶች ለማስታረቅ በመሞከር ላይ የሚገኘውና ራሱን “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ” እያለ የሚጠራው ስብስብ በዋሺንግተን ዲሲ ያካኼደው ይኸው ጉባዔ ወደ አዲስ አበባ እና ኒውዮርክ የላካቸውን ልዑካን ሪፖርት ከማድመጡም ባሻገር ከሁለቱም “ሲኖዶሶች” የሚመጡ ተወካዮች ሊያደርጉት ስለሚችሉት የመጀመሪያ ስብሰባ እንዲሁም ይህ የዕርቅ ሒደት ሊገጥሙት ስለሚችላቸው ችግሮች መክሯል።
ሰኔ 8 እና 9/2002 ዓ.ም (ጁን 15 እና 16/2010) የተካሄደው ይህ ጉባዔ ሲጠናቀቅ ከሁለቱም “ሲኖዶሶች” ባገኘው በጎ ምላሽ የሁለቱም ተወካዮች ፊት ለፊት ውይይት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን አውቋል። በተያዘው ዕቅድ መሠረት ከሰመረለት በሚቀጥለው ጁላይ ወር ሁለቱ ወገኖች ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ይህንኑ በተመለከተ “ደጀ ሰላም” ያደረገችው ግምገማ እንደሚያመለክተው ከሆነ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ” በአባቶች መካከል ያለውን እና ቤተ ክርስቲያኒቱን እየጎዳ ያለውን ልዩነት ለመቅረፍ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እጅግ በጣም አስፈላጊና ሊደገፍ የሚገባው ይሁን እንጂ በምስጢራዊነትና በድብቅነት እንዲሁም ከምዕመኑ በመሰወር በጥድፊያ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሌላ ችግር እንዳይወልድ ጥንቃቄ እንዲደረግበት ማሳሰብ ያስፈልገዋል። “ዜናው ለምን ደጀ ሰላም ላይ ወጣ?” የሚለው ዓይነት አካሄድ ተገቢ አለመሆኑን ከመጠቆም ጋር ኮሚቴው እስካሁን ካቀፋቸው አባላት በተጨማሪ የሌሎች ሰዎችንም ሙያዊ እገዛ ማሰባሰብ እንዳለበት ጉዳዩን የሚከታተሉ ደጀ ሰላማውያን ጠቁመዋል። ጉዳዩን በምስጢር ለመያዝ በሚል ከማፈን ይልቅ በሰፊው ውይይት ሊደረግበት እንደሚገባ እየተጠቆመ ነው። የሁለቱ “ሲኖዶሶች” ልዩነት የአባቶች ልዩነት ብቻ ሳይሆን በጉዳዩ ውስጥ እጃቸውን ያስገቡ ብዙ አካላት እንደመኖራቸው መጠን መፍትሔውም ሰፋ ያለ መሆን እንዳለበት ደጀ ሰላማውያን ገልፀዋል። ከዚህ ባሻገር ችግሩ ከአስተዳደር እና ከፖለቲካ ልዩነት ባሻገር ቀኖናዊ ጉዳዮች ስላሉት በደፈናው “እርቅ” ብቻ ብሎ ነገረ ሃይማኖቱን መዘንጋት እንደማይገባ እንዲሁም ምዕመኑን ያላሳተፈ እና ለምዕመኑ መረጃ በመከልከል ላይ የተመሰረተ መሆን እንደማይገባው እየተነገረ ነው።

“ደጀ ሰላም” “የአባቶች እርቅ ከየት ይነሣ፣ የት ይደረስ?” በሚል ርዕስ ያዘጋችውን ሪፖርታዥ በቅርብ እንደምታቀርብ በመግለጽ ይህንን አጭር ዜና ትቋጫለች።
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)