June 11, 2010

ያለ ኤጲስ ቆጶስ ፈቃድ ቀሳውስት ተሰባስበው የቃል ኪዳኑን ታቦት በመንበሩ መሰየም ይችላሉን?


(ወለተ አቤል፤ ከአሜሪካ)፦ እዚህ በዲያስጶራው በተለይም በሰሜን አሜሪካ በኛ ዘመን ለታቦት የሚገባውን ክብር እንዳንሰጠው አንዳንድ ካህናት ሲያቃልሉት እያየን ነው። ሰሞኑን እኔ በምኖርበት በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው “ቨርጂኒያ፣ ዉድ ብሪጅ” በሚባል ቦታ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ አብርሃም ዕውቅና ውጪ ራሳቸውን "በአስተዳደር ገለልተኛ  ነን" የሚሉ በአካባቢው የሚገኙ ካህናት ተሰባስበው ሥልጣኑ ሳይኖራቸው ቤተ ክርስቲያን “ከፍተናል”፣  “ባርከናል” ብለዋል። ታዲያ ታቦቱን ማን በመንበሩ ሰየመላቸው? ታቦቱንስ ከየት አመጡት? ይህንን ቤተ ክርስቲያን “ባርኮ የከፈተውስ ማን ነው? እነማን ናቸው? በዕለቱ በቦታው የተገኙት ካህናትስ እነማን ናቸው?” መልሱን ለራሳቸው መተው ቢገባም ምእመናን ደግሞ መጠየቅ ይገባቸዋል።
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው የታቦትን ክብር እና የት መጣ በሚገባ ጽፈው ባስቀመጡበት ሥፍራ እንዲህ ብለዋል፦

    “ታቦት ከብሉይ ኪዳንና ከእሥራኤል የነጻነት ሕይወት ጋር የተያያዘ ታሪክና የት መጣ አለው። እሥራኤል በግብጽ 430 (፬፻፴) ዓመታት ያህል በባርነት ቀንበር ሲገዙ ከኖሩ በኋላ በሙሴ መሪነት በእግዚአብሔር ተአምራት ከግብፃውያን የአገዛዝ ቀንበር ነጻ ወጡ። ወደ አገራቸውም ለመመለስ አርባ ዓመት ሙሉ በቃዴስ በረሀ ሲኳትኑ ኖሩ። በግዞት ሳሉም ሆነ አሁን በጉዟቸው ከአባቶቻቸው የወረሱትን ሃይማኖት አልረሱም። ይህን ጽኑ እምነታቸውንና በስሙ ስለተጠሩ የሚደርስባቸውን ሥቃይና ግፍ ተመልክቶ ነጻ አወጣቸው። ነጻ ካወጣቸው በኋላ በድብቅ በግዞት ያቀርቡ የነበረውን አምልኮት ነጻ ሕዝብ ሁነው በነጻ እንዲያመልኩት ራሱ ስለፈለገ በዚያው ሲጓዙበት በነበረው በረሀ ውስጥ በምትገኝ በሲና ኮረብታ ላይ ለሙሴ ተገልጦ የቃል ኪዳንና መታዘዝ ምልክት የሚሆን ዐሥር ሕግጋትና ትእዛዛት የተፃፈባቸው ሁለት የዕብነ በረድ ገበታዎችን (ሠሌዳዎችን) ሰጠው፤ ለእነሱም ማስቀመጫ ታቦትና እንደ መቅደስም የምታገለግል የምስክር ድንኳን እንዲሰራ ሙሴን አዘዘው። ታቦት የጽላቱ ማደሪያ ነው። የታቦት ትርጓሜው ማደርያ መሰወሪያ ማለት ብቻ ሳይሆን መገለጫም ነው። ንጉስ በዙፋኑ እንዲገኝ፤ እንዲገለጥ ታቦት ለእሥራኤል የአምላክ መገለጫ ነውና።…. በአጠቃላይ አነጋገር ታቦት በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለምሕረት ለሕዝቡ በሚገለጥበት ጊዜ ዙፋኑ ነው ማለት ነው። ታቦት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በልማድ ያለ አይደለም፤ ወይም አንዳንድ የዋሆች እንደሚሉት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ኦሪትን ከሥርዓተ ወንጌል ጋር በባላንጣነት የምታገለግል አይደለችም።  ከክርስትና በፊት የብሉይ ኪዳን አገር የነበረችው ኢትዮጵያ በክርስትና ጊዜም ከብሉይ ኪዳን ያገኘቻቸውን ጠቃሚ ነገሮች በክርስትና መንፈስ እየተረጎመች ትጠቀምባቸዋለች። ከብሉይ ኪዳን ከወሰደቻቸው አንዱ ጽላተ ኪዳን ታቦተ ሕግ ነው። አዲስ ቤተ ክርስቲያን በሚሰራበት ጊዜ ከዕፅ ወይም ከዕብነ በረድ ተቀርጾ በላዩ የእግዚአብሔር ምስጢራዊ ሥም (ኅቡእ ስም) አልፋና ኦሜጋ የመጀመሪያውና የመጨረሻው ማለት ነው። ይህ ቃል ከተፃፈበት በኋላ በኢጲስ ቆጶሱ እጅ ተባርኮና ሜሮን ተቀብቶ በመንበሩ ይሰየማል።  በቅዳሴም ጊዜ ኅብስቱና ወይኑ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ቄሱ ሥርዓተ ቅዳሴውን የሚያከናውነው ኅብስቱን ሥጋ መለኮት፣ ወይኑን ደመ መለኮት ወደመሆን የሚለወጠው በዚህ በታቦቱ ላይ ነው። ሥጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ እያለ ያመኑትን ሁሉ የሚጠራበት የምሕረት ምሥዋዕ ነው። ክብርና ስግደትም የሚደረግለት ስለዚህ ነው”። (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ከገጽ 93 – 94)

እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን ለታቦት ያላት ክብር ይህ ነው!!!!ይህ ሰሞኑን “የተከፈተው” ቤተ ክርስቲያን በአካባቢያችን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስም ያሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን ቁጥር ወደ ሃያ (፳) አሻቅቦታል። እስካሁን ድረስ የነበሩት አስራ ዘጠኙ አጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት የየራሳቸው የሆነ የአስተዳደር መዋቅር ያላቸው ሲሆን በባለቤትነትም በግለሰቦዎችና በቡድኖች ተመዝግበው የሚገኙ ናቸው። ብዙዎቹም ከቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውጪ ናቸው።

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)