May 27, 2010

ቤተ ክርስቲያን የሚባርከው (“የሚከፍተው”) ማን ነው? ሥልጣኑስ የማን ነው?

(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 27/2010)፦ ከዚህ መግቢያ ቀጥሎ የምናስነብባችሁ ይህ ጽሑፍ የአንዱ ደጀ ሰላማዊ የገብር ሔር ዘመ/መንግሥት ሲሆን በአስፈላጊው ጊዜ ስለደረሰን አምላካችንን እያመሰገንን ልናስነብባችሁ ወደድን። ጽሑፉ በተለይም በዳያስጶራ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ይመለከታል። በዳያስጶራው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እየተስፋፋች ቢሆንም የመስፋፋቷ ምክንያት ሥርዓትና ሕጓን በጠበቀ መልኩ ሳይሆን አንዳንዴም ፈር በለቀቀና ኢ-ኦርቶዶክሳዊ በሆነ መንገድ መሆኑን ያጠይቃል። ይህ ችግር ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በመጠኑ ጋብ ያለ፣ ቤተ ክርስቲያን በተለይም በአገረ አሜሪካ 3 ሊቃነ ጳጳሳትን ከሾመች ወዲህ መስመር እየያዘ የመጣ ቢመስልም ነገሩ አሁንም እንዳያገረሽ የሚያሰጋ እንደሆነ ፍንጮች እየታዩ ነው። ያለ ጳጳስ ፈቃድ “ራሳቸውን ጳጳስ ያደረጉ” ሰዎች አብያተ ክርስቲያናትን “ባረክን፣ ከፈትን” ሲሉ፣ ሕዝቡንም ስተው ሲያስቱ እያየን እየሰማን ነው። እኛም በበኩላችን "ኧረ እንዴት ነው ነገሩ?" ለማለት ወደድን። የአዲስ ነገር ጋዜጣ ብዕረኛ መስፍን ነጋሽ “ልብ አይሰደድም፣ ሕልም አይነጠቅም” እንዳለው ሳይሆን ከአገራችን ስንሰደድ ጊዜ “ልባችንም፣ ሃይማኖታችንም፣ ሥርዓታችንም፣ ጨዋነታችንም እኛን ጥሎ ተሰደደ” እንዴ? በሌላ ጽሑፍ በሰፊው ልንመለስበት ቀጠሮ ይዘን ወደዚህ ጽሑፍ እንግባ። መልካም ንባብ።
ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን።

“አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን ድንበር አታፍርስ” (ምሳሌ 22፤28) (ገብር ሔር ዘመ/መንግሥት):- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነችው በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙ ቀደምት አበው በደነገጉት ሕግና ሥርዓት የምትመራ መሆኑ አይደለም። በልጀችዋ በሌሎችም ዘንድ ሳይቀር የታወቀ የተመሠከረ ነው፡፡ “ሁሉ በአግባቡና በሥርዓት ይሁን”እንደተባለው ለእያንዳንዱ ድርጊት ቤተ ክርስቲያን በቃል ብቻ ያለ ሳይሆን በፊደል የተቀረጸ ህግና ስርዓት አላት ከላይ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጀምሮ አስከ ዐጻዌ ኆኅት(የቤተ ክርስቲያንን በር እሰከሚከፍተው) ድረስ ያሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ከዋክብት የሆኑት ምዕመናን ሁሉም በየድርሻው የሚፈጽመው በአግባቡ ተለይቶ ተቀምጡዋል ከሥርዓተ ቅዳሴ ጀምሮ ይበል ካህን በማለት የካህናትን ድርሻ ይበል ዲያቆን ብሎ የዲያቆኑን ድርሻ ይበል ሕዝብ በማለት የምእመናንን ድርሻ ያስቀምጣል።

ዓላማዬ ባሕረ ጥበባት ስለሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ህግና ሥርዓት በዚህ አጭር ጽሁፍ ለማተት አይደለም። ልሞክር ብልም የባሕርን ውኃ በጭልፋ ቀድቶ በአንዲት ትንሽ ጉድጓድ ለማከማቸት እንደመሞከር ያህል ይቆጠርብኛል። ዳሩ ግን የዘመን ፍጻሜ በደረሰብን በእኛ ዘመን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በማን አለብኝነት እየተጣሰ፣ ሕጉን ጠብቀው እንዲያስጠብቁ የተሾሙት ሕግ-ጣሽ፣ ሥርዓት ደምሳሽ ሆነው ያሉበት፣ የቤተ ክርስቲያን ፈርጥ መሆን የሚገባቸው ምዕመናን ቤተ ክርስቲያንን ለግል ዝናና ጥቅም መጠቀሚያ ለማድረግ ደፋ ቀና ለሚሉት ምንደኞች የኋላ ደጀን በመሆን በማወቅም ባለማወቅም ቤተ ክርስቲያንን በማፍረስ ተልእኮ ላይ ሁሉም ተባብሮ ያለበት ጊዜ ሆኖ ስለተሰማኝ ከስሜታዊነት የመነጨ ሀሳብ ነው እንደማትሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ብዙ ጆሮን ጭው የሚያደርጉ ድርጊቶች በዙሪያችን እየተፈጸሙ መሆናቸውን ያልተገነዘበ ቢኖር የኅሊና ደጁን ምንም እንዳያስተውል የዘጋ፣ ቤተ ክርስቲያን የፈለገችውን ብትሆን የማይገደው፣ ለቤተ ክርስቲያን ምንም ተቆርቋሪነት የሌለው ብቻ ነው እላለሁ፡፡

በሰሜን አሜሪካ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የተከፈቱ በቁጥር ይህን ያህል ናቸው ብሎ ለመናገር ሥራዬ ብሎ የአብያተ ክርስቲያናቱን ብዛት ያጠና ባለመኖሩ፣ ካለም መረጃው ስላልደረሰኝ አሐዛቸውን በትክክል መናገር ባልችልም ቁጥራቸው ግን ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ ለመሆኑ ከመረጃ መረብ የምናገኛው ሀቅ ነው፡፡

የሂስ ብዕሬን እንዳነሳ ያደረገኝ የአብያተ ክርስቲያናቱ ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መምጣቱ ሳይሆን የአመሰራረቱ ወይም የአተካከሉ ጉዳይ ነው፡፡ ሁላችንም አንድ ዓይነት ግንዛቤ ኖሮን የሚተቸውን እንድንተች፣ የሚነቀፈውን እንድንነቅፍ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በመጣሱ የሚወገዝም ካለ እንዳንተባበረው ሕብረታችን ከቤተ ክርስቲያን ጋር እንዲሆን በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙት እኛና መንፈስ ቅዱስ ይህን ወስነናል በማለት ውሳኔያቸው ፈቃደ ሥጋን መሠረት ያደረገ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተወሰነ መሆኑን በመግለጽ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በቃል ብቻ ሳይሆን በጽሑፍ ጭምር የተዉልን የአባቶቻችን ውሳኔ ምን እንደሆነ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን አመንኩበት። ያላወቁ አለቁ እንዲሉ አበው ባለማወቅ ወይም በግዴለሽነት ብዙዎች የጥቅመኞች ሰለባ እየሆኑ ነውና፡፡ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሄርም እንዳለ “ሕዝቤ ካለማወቅ የተነሳ ጠፍቷልና” እንዳለ።
ቤተ ክርስቲያን ለምን ይተከላል?
“ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ትሰመይ” እንዲል ቤተ ክርስቲያን የዋዛ፣ የፈዛዛ፣ የሳቅ፣ የጨዋታ፣ የመብል የመጠጥ ቤት አይደለችም። ስለሆነም ለማሕበራዊ ግንኙነት፣ ሥጋዊ ጥቅምን ለማካበት፣ ለፖለቲካ መድረክነት ለማዋል ታስቦ የሚተከል አይደለም፡፡ “ይህ ሥፍራ እንዴት ያስፈራ፣ ይህ ስፍራ የእግዚአብሄር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም ይህም የሰማይ ደጅ ነው” (ዘፍ.22፤17) ተብሎ መነገሩን እናስተውል፡፡ ጌታም በዘመነ ሥጋዌው በመቅደስ ውስጥ ሲሸቅጡ የነበሩትን መገሰጹን ለሸቀጥነት ቀርበው የነበሩትንም የሚገለበጡትን እንደገለበጠ፣ የሚባረሩትንም በጅራፍ እየገረፈ እንዳባረረ ልብ ይሏል (ማቴ.21፤12-13)፡፡

ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች አምልኮታቸውን የሚፈጽሙባት የሚቀድሱበት የሚያስቀድሱበት ሥጋወደሙን የሚያቀብሉበት የሚቀበሉበት የአምልኮ ቦታ በመሆኗ ክርስቲያኖች እስካሉ ድረስ ቤተ ክርስቲያን መተከሉ አይቀሬ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስንዱ እመቤት እንደመሆንዋ ለሁሉ ነገር የተዘጋጀ ሥርዓትና ደንብ አላት፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደሚተከል በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙ አባቶች የወሰኑት ውሳኔ የደነገጉት ድንጋጌ አለ።

የቤተ ክርስቲያን አተካከል
እንደ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ያለ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ አይተከልም። ቅዱስ ባስልዮስ በዘጠና አራተኛው አንቀጽ “ያለ ኤጲስ ቆጶሱ ፈቃድ ቤተ ክርስቲያን አይስሩ፣ ከኤጲስ ቆጶሱ ፈቃድ አንዱ ቢሠራ ለዘላለሙ አይቁረቡባት፣ እንደ ገበያ እንደ በረት ፈት ሁና ትኑር፤ ካህን ደፍሮ በስዋ ቢቆርብባት ከሹመቱ ይሻር” ይላል (ፍትሐ ነገስት አንቀጽ 1 ቁጥር 3)፡፡ በዚህ ቃል መሠረት ከሄድን በሰሜን አሜሪካ በኤጲስ ቆጶሳት ተባርከው የተከፈቱ አብያተ ክርስቲያናት ምን ያህሎቹ ናቸው?

በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ቀደም ብለው ከተመሰረቱት ውጪ በገለልተኝነት ስም በቅርቡ የተከፈቱት “አብያተ ክርስቲያናት” ሁሉ ማለት ይቻላል በሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፈቃድና ቡራኬ ያልተመሰረቱ ናቸው፡፡ ስለሆነም በፍትሐ ነገስቱ እንደተገለጸው እነዚህ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የተከፈቱ፣ በሊቀ ጳጳስ የማይታወቁና ያልተባረኩ “አብያተ ክርስቲያናት” ሁሉ እንደ ገበያ እንደ በረት በመሆናቸው ምእመናን ሊያስቀድሱባቸውና ሊቆርቡባቸው ቀርቶ በቤተ ክርስቲያን ስምም ሊጠሩዋቸው እንደማይገባ፣ ይህን አውቆ በማናለብኝነት ግዝቱን ተላልፎ የሚገኝ ምእመንም ከቤተ ክርስቲያን አንድነት የተለየ እንደሚሆን ቃሉ ያስተምረናል፡፡

ያለ አጲስ ቆጶሱ ፈቃድ ቤተ ክርስቲያን ለከፈተስ?
በምድረ አሜሪካ ያለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ምእመናን ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ያሉትን ሌሎች ወገኖችንም ግራ ያጋባ እንደሆነ ነው የታዘብኩት። በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ባሉ ፍርድ ቤቶች በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስም የተከፈቱ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ያልቀረበበት ካለ ምናልባት በዚያ ግዛት ብዙ ኢትዮጵያውያን የሉም፣ ቤተ ክርስቲያንም አልተከፈተም፣ የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ ትችላላችሁ፡፡ ኢትየጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጉርጉርነቱን መለወጥ እንደማይችል በቅዱስ መጽሐፍ የተገለጸ ቢሆንም ዳሩ ግን አንደንዶች ምድረ ኢትዮጵያን ለቀው አትላንቲክን ተሻግረው ምድረ አሜሪካንን ሲረግጡ ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓቱን፣ ፈሪሃ እግዚአብሔሩን አሽቀንጥረው በመወርወር ወደ ቅጽረ ቤተ ክርስቲያን እንኳን መቅረብ እንደማይገባቸው ያምኑ የነበሩት ምዕመናን ቤተ ክርስቲያን ከፋች ሆነው፣ እንዴት እንደሚቀደስ ምን እንደሚሠራ “ሊቃነ ካህናት” ሆነው ካህኑን ሲመሩ፣ ሲሻኝ ጢስ ወጋኝ እንዲሉ ምክንያት ፈጥረው ከህኑን ሲያባርሩ፣ ከዓላማቸው ጋር የሚተባበረውን ለፈቃዳቸው የሚንበረከከውን ሲቀጥሩ ላስተዋለው ጉድ የሚያሰኝ ነው፡፡

አንዳንዱ ካህንም የተሾመበትንና ሥልጣነ ክህነት የተቀበለበትን ዓላማ ወደ ጎን ትቶ፣ “እስከ ዛሬ ከበላዬ በነበሩት ተጎድቼ ኖሪያለሁ፣ አሁን ግን ሁሉን ማድረግ ወደምችልበት ዓለም መጥቻለሁ” በማለት ሕገ ቤተ ክርስቲያን የማይፈቅድለት መሆኑን እያወቀ፣ አንቱ ለመባል፣ ሀብት ለማካበት፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አምዘግዝጎ በመጣል እንደ መሸቀጫ ሱቅ “ቤተ ክርስቲያን” ከፍቶ የግል ጥቅሙን ሲያጋብስ እያስተዋልን ነው፡፡

ዳሩ ግን የቤተ ክርስያናችን የሕግና የሥርዓት መጽሐፍ የሆነው ፍትሐ ነገስት ቄስ ወይም ዲያቆን በሀገሩ የተሾመውን ኤጲስ ቆጶስ ንቆ አቃሎ ለብቻው ቤተ ክርስቲያን ከሠራ ኤጲስ ቆጶሱ እስከ ሦስት ጊዜ ጠርቶት ካልመጣ እሱና እሱን የመሰሉት ከሹመታቸው ይሻራሉ ይላል(ፍትሐ ነገስት አንቀጽ ፷ ረስጠብ 19)። ቄሱ እንኳን ያለ ሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ ቤተ ክርስቲያን መክፈት ቀርቶ ያለበትን ቤተ ክርስቲያን ትቶ ወደ ሌላ ቤተ ክርስቲያን ከሄደ እንዲመለስ ተነግሮት ካልተመለሰ ከሹመቱ ይሻራል ይላል (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 6 ረስጣ 14 ኒቂያ 14)።

መልእክት በአሜሪካ ለከተማችሁ ሰባክያነ ወንጌል
“በኃይል ጩህ አትቆጥብ፣ ድምጽህን እንደመለከት አንሣ” እንደተባለው ነቢይ የተማሩትንና የተረዱትን ላልተማረውና ላላወቀው እንዲያሳውቁ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰባክያነ ወንጌል “ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ” ብለው ቤተ ክርስቲያንን የስብከታቸው ማእከል ማድረግ ሲገባቸው በላያቸው ላይ ያነገሱዋቸውን ሰዎች ፈቃድ በመፈጸም ምንደኛነታቸውን በስውር አይደለም በገሃድ ያለምንም እፍረት እየገለጡ ያሉበት ጊዜ ነው፡፡ እንዲህ ስል እግዚአብሄር የሚያውቃቸው ራሳቸውን ቀብረው ከቤተ ክርስቲያን መድረክ ተገፍትረውም ሆነ ተከልክለው በሚሆነው ነገር ሁሉ እያዘኑ በበዓታቸው ተወስነው ያሉ መኖራቸውን ባለመዘንጋት ነው:: መንጋውን የመጠበቅና የማሰማራት እንዲሁም እውነትን የማስተማር ተልዕኮ ተቀብላችሁ በቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ የቆማችሁ ካህናትና ሰባኪያነ ወንጌል ማሩን አምርሮ ወተቱን አጥቁሮ በማቅረብ የምዕመኑን ኅሊና በሀሰተኛ ምላስ በማደንዘዝ የህገወጦችና የጥቅመኞች አጋፋሪነታችሁን ትታችሁ ነገ ፍርድ ከእግዚአብሄር ቤት የሚጀምርበት ጊዜ እንደሚመጣ ከወዲሁ ተገንዝባችሁ ወደ ኅሊናችሁ በመመለስ ከአፈ ቀላጤነት ወደ ወንጌል አርበኝነት ትለወጡ ዘንድ ምክሬ ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ እውነትን ለመናገር መቆማችሁን አትዘንጉ። ዖዝያንን ፈርቶ የእግዚአብሄርን መልእክት ሳያስተላልፍ በመቅረቱ ለምጽ በከንፈሩ ላይ የወጣውን ታላቁን ነቢይ አስቡ። እናንተም ልታስተምሩት ልትመሰክሩት የሚገባውን እውነት ልባችሁ እያወቀ ዳሩ ግን ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ብላችሁ እውነቱን ሰውራችሁ በስራችሁ ያለውን ምእመን ወደ ጥፋት የምትመሩት ከሆነ እግዚአብሄር ሓላፊነታችሁን በአግባቡ ባለመወጣታችሁ የበጎቹን ደም ከእናንተ እንደሚጠይቅ ለእናንተ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ይሆንብኛል። ዳሩ ግን ዕውቀት ሳይሆን እምነትና ተግባር ስለሆነ የሚያጸድቀው የእምነትና የተግባር ሰው ሁኑ፡፡

በምዕመናን በኩል
“ተቀባይ ከሌለ ሌባ አይኖርም” እንደሚባለው ለሕገ ቤተ ክርስቲያን መጣስ የምዕመናንም አስተዋጽኦ እንዳለበት መገንዘብ ያስፈልጋል። በምዕመንነት ደረጃ ቀርቶ በቅስና ደረጃ ያለ እንኳን ቤተ ክርስቲያን ባርኮ እንደማይከፍት እየታወቀ “ማንም ይክፈት ማንም ቤተ ክርስቲያን መኖሩን ብቻ ነው የምንፈልገው፤ ሌላው እኛን አይመለከተንም” የሚል ከአንድ ምዕመን መደመጥ የማይገባውን አስተያየት እየሠጡ ጉዳዩ እንደማይመለከታቸው አድርገው የሚናገሩ እንዲሁም ግብረ በላ በሆኑ ሰባክያን ልቦናቸው የደነደነና የቆሙበት መንገድ ትክክል እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩ እንዲሁም ቤተሰባዊነትን ከሃይማኖት በላይ አድርገው የያዙ ምእመናን የጥፋቱ መሪ ፊት አውራሪ ለሆኑት ወገኖች አጥር ሆኖ መገኘት ችግሩ መፍትሄ እንዳያገኝ አድርጎታል። ከእኔ ይልቅ ሴት ልጁን ወይም ወንድ ልጁን የሚወድ ቢኖር ለእኔ ሊሆን አይችልም እንዳለ ጌታ ምርጫችንን ቤተ ክርስቲያን አድርገን ቤተ ክርስቲያንን ተጣብተዋት ያሉትን መዥገሮች ለመንቀል በቁርጠኝነት መነሳት ያስፈልጋል። ቤተ ሰባዊነት ይሉኝታ ግዴለሽነት እነዚህ ሁሉ አንቀው ይዘውን ተዘልለን ብንቀመጥ የቤተ ክርስቲያን አምላክ አንድ ቀን ቤተ ክርስቲያኒቱን ይታደጋታል። በዚያን ጊዜ ግን እናንተ ወዮታ እንዳለባችሁ እወቁ።

ይቅር ይበለን፣
አሜን
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)