May 12, 2010

የሃይማኖት መሪዎች ምርጫውን በማስመልከት ፓርቲዎችን ሊያነጋግሩ ነው

- ፓርቲዎቹ የተለያዩ አስተያየቶች ሰጥተዋል፤
(ሪፖርተር ጋዜጣ) :- የሃይማኖት መሪዎች የ2002 ምርጫን አስመልክቶ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ነገ በምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት እንደሚያነጋግሯቸው ታወቀ፡፡

የሃይማኖት አባቶች ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚነጋገሩ ሲሆን፤ የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ፣ የፕሮቴስታንትና የእስልምና እምነት መሪዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ 

የሃይማኖት መሪዎች የጠሩትን ስብሰባ አስመልክተን ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተለያየ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡(Pictures: Courtesy of Addis Fortune).

የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ፓርቲ (መኢዴፓ) ሊቀመንበር አቶ ዘለሌ ፀጋ ሥላሴ እንደሚሉት፤ "የሃይማኖት አባቶች እኛን ከመሰብሰባቸው በፊት የፖለቲካ እስረኞችን አስፈትተው መምጣት አለባቸው፡፡
ባይሆን ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን አስፈትተው ይዘው መምጣት አለባቸው፡፡ ሰው በየሜዳው ላይ እየሞተ፣ እጅግ በጣም የከፉ ችግሮች እያሉ፤ የእኛ ኃይማኖት አባቶች አሁን ምርጫው በኢሕአዴግ በደልና ጭቆና ሲጠናቀቅ፣ ቡራኬ ማምጣታቸው ተገቢ አይደለም የሚል አቋም አለን" ብለዋል፡፡

አቶ ዘለሌ እንደሚሉት፣ ስብሰባው ላይ የሃይማኖት አባቶች ቢያንስ ብርቱካንን ይዘው መምጣት አለባቸው፡፡ ይሄንን ካላደረጉ ግን በጠሩት ስብሰባ ላይ ለመገኘት ፓርቲያቸው ፈቃደኛ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ "አድበስብሶ ለማለፍ ቡራኬ አንቀበልም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ አስፋው ጌታቸው በበኩላቸው፤ "ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ ሁላችንም መቻቻል አለብን፡፡ ምርጫው በሰላም እንዲያልፍ ሁላችንም የጥረቱ አካል እስከሆንን ድረስ ወደ ኋላ የምንልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ሌላ ተልዕኮ እስከሌለው ድረስ" ብለዋል፡፡

አቶ አሰፋ "ሁላችንም ዕምነት ያለን ሰዎች ነን፡፡ አንዳንድ ጌዜም እኮ ሞራላዊም ሆኑ መንፈሳዊ ነገሮች ያስፈልጋሉ የሚል ዕምነት አለን" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት) ሊቀመንበር አቶ አየለ ጫሚሶ በበኩላቸው፤ የሀይማኖት አባቶች ዘግይተው ለሰላማዊ ጥሪ ከመጡ በሩ ክፍት ነው በማለት፣ "ትልቁ የምንፈልገው ነገር ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ነው፡፡ በሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን ጫና፣ ሁከትና ደም መፋሰስ እንዲሁም ሌሎች ሁኔታዎች እንዲፈጸሙ አንፈልግም፡፡" በዚህ ሁኔታ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን፣ "የሃይማኖት አባቶች ከመጀመርያው ጠንክረው መቆም ሲገባቸው፣ ያንን ሳያደርጉ ዘግይተው በመጨረሻ ቢመጡም አይወቀሱም" ሲሉ አክለዋል፡፡ ትልቁ ነገር ዓላማው በማንኛውም ሰዓት ተፈጻሚ እንዲሆን ጥረት መደረጉ አግባብነት ስላለው አባቶች ያስተላለፉት ጥሪ ይደገፋል ብለዋል፡፡

አቶ አየለ፣ ቀደም ብሎ የምርጫ እንቅስቃሴ ሲጀመር የምርጫው መግቢያ አድርገው መዘጋጀት ነበረባቸው፡፡ የሃይማኖት አባቶች መጨረሻ ሰዓት ላይ መምጣታቸው የዘገየ አቀራረብ ቢሆንም እሰይ የሚያሰኝ እንጂ የሚያስወቅስ አይደለም ሲሉ አክለዋል፡፡

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ያዕቆብ ልኬ እንደተናገሩት፤ "የሃይማኖት አባቶች እስካሁን ድረስ አልጠሩንም፣ የሰማሁት ነገር የለም፡፡ ወሬ ካልሆነ በስተቀር በጽሑፍ ጥሪ የተደረገልን ነገር የለም" ብለዋል፡፡

"በድርጅት ስም ጥሪ ሊደርሰን" ይገባል ያሉት ኃላፊው፣ ከዚህ አንጻር ምንም የደረሳቸው የጽሑፍ ጥሪ ስለሌለ በጥሪው ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ አባልና ከፍተኛ አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ "በ97 ምርጫ በሃይማኖት አባቶች ላይ ተስፋ ቆርጫለሁ፡፡ በ97ቱ ምርጫ ወቅት በጳጳሱ ቤት ሁሉም የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት የኢትዮጵያን ሕዝብ አድኑ በሚል፣ የሃይማኖት አባትነታቸሁን ተወጡ በሚል ጠይቀናቸው ነበር፡፡ የአንዳንዶቹ መልስ እጅግ በጣም አሳዛኝ ነበር" ብለው "ወደ ምድራዊው ዓለም ያዳሉ ስለነበር የረዱን ነገር አልነበረም፡፡ ሕዝቡ ሲያልቅ ዝም ስላሉ፤ በእነሱ ላይ ተስፋ የማደርገው ነገር" የለም ብለዋል፡፡

ዶ/ር መረራ የመድረኩን ሐሳብ ሳይሆን የግላቸውን ሐሳብ መናገራቸውን ጠቁመው፣ ከካቶሊኩ ጳጳስ በስተቀር በሌሎቹ ሙሉ በሙሉ ተስፋ እንደቆረጡ ተናግረዋል፡፡

(በሰብለወንጌል ሀብታሙ)
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)