April 11, 2010

ጥንታዊው የሌመን ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን በአደጋ ላይ ነው

(Mahibere Kidusan)  
በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ደገም ወረዳ የሚገኘውና በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ያሠሩት የሌመን ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን በእርጅና ምክንያት በመፈራረስ ላይ ይገኛል፡፡  በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፉት ሲዘዋወሩ ካሠሩአቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ የሌመን ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን መሆኑን ከሥፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ይሁን እንጂ ይኸው ቤተክርስቲያን በ15ኛው ክፍለ ዘመን በግራኝ ወረራ ጊዜ ተቃጥሎ በ1881 ዓ.ም እንደገና በአዲስ መልክ ተሠርቷል፡፡

ቤተክርስቲያኑ ተመልሶ ከተገነባ ከአንድ መቶ ሃያ አንድ ዓመታት በላይ ዕድሜ በማስቆጠሩና እስካሁንም ባለመታደሱ በእርጅና ምክንያት በመፈራረስ ላይ ይገኛል፡፡

ስለሆነም መጋቢት 7 ቀን 2002 ዓ.ም ቤተክርስቲያኑ የደረሰበትን የጉዳት መጠን ለመመልከትና መልሶ የሚጠገንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉበኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ያሬድ፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ሓላፊዎች፣ የምሕንድስና ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኛና የአካባቢው ተወላጆች በሥፍራው ተገኝተዋል፡፡

ዙሪያው ግንቡ ተሰነጣጥቆ ሊፈርስ የደረሰው የሌመን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን

የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በዚሁ ጊዜ በሰጡት መግለጫ «የሌመን ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ትልቅ ዝና ያለው፣ ጥንታዊና በዕድሜም ተወዳዳሪ የሌለው መሆኑን ከልጅነቴ ጀምሮ ሲነገር አውቀው ነበር፡፡ ዛሬ በስፍራው ተገኝቼ በማየት እንደተረዳሁት ከአገልግሎት ዘመን ብዛት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ስለሆነም  በአባቶች ፋንታ ልጆች ተተኩ ነውና ተተኪው ትውልድ ጥገና ሊያደርግለት ይገባል» ብለዋል፡፡

«ከተቻለ የቀድሞው እንደተጠበቀ ማደስ ካልሆነም የጥንቱ ተጠብቆ እንዲቆይ በማድረግ በአዲስ መልክ መሥራት ግድ ይላል» ያሉት ብፁዕነታቸው፤ «ቤተክርስቲያኑ ጥንታዊ ከመሆኑም ባሻገር ብዙ ቅዱሳን አባቶች ያለፉበትና አጽማቸውም የረገፈበት፣ ብዙ ሊቃውንት የፈለቁበት በመሆኑ ሁላችንም ለመልሶ ግንባታ መረባረብ አለብን፡፡ «ባለቤት ካልጮኸ ጐረቤት አይረዳምና የአካባቢው ሕዝብ ተግቶ መነሣትና የውጭውም እንዲራዳ ማሳሰብ ይገባዋል» በማለት ብፁዕነታቸው ለምእመናን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ያሬድ በበኩላቸው ዋናው ዓላማ የቤተክርስቲያኑ ጥንታዊነት ባለበት ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ «እኛም እንደ አባቶቻችን ታሪክ ሠርተን ለማለፍ ዝግጁ መሆን ይገባናል፡፡

ባለሙያዎችን ይዘን ወደዚህ ታላቅ ሥፍራ የመጣነው የቤተክርስቲያኑን ይዘት ለማየትና በቀጣይ ምን መደረግ እንዳለበት ለማወቅ ከዚያም ቤተክርስቲያኑ መጠገን እንዳለበት ለአካባቢው ምእመን ለማሳሰብ ጭምር ነው» ሲሉ በዕለቱ ለተሰበሰበው የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡

በቅርቡም ቤተክርስቲያኑን ለማሠራት ኮሚቴ እንደተዋቀረ የገለጡት ብፁዕ አቡነ ያሬድ፤ ሁላችንም ከኮሚቴው ጋር በኅብረት በመሆን ጥንታዊውን ቤተክርስቲያን ሕንፃ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው  አሳስበዋል፡፡

ቤተክርስቲያኑ በ1881 ዓ.ም በራስ ዳርጌ ልጅ በወ/ሮ ትሰሜያለሽ ሲሠራ ጣሪያው የሣር ክዳን ስለነበር በ1951 ዓ.ም ጣሪያው እንደገና በወ/ሮ ትሰሜያለሸ ልጅ በራስ ካሣ አማካኝነት ወደ ቆርቆሮ መቀየሩን አስረድተዋል፡፡ አሁን በቤተክርስቲያኑ ላይ ያለው ጉልላትም ከግራኝ ቃጠሎ የተረፈው መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የቤተክርስቲያኑን መጐዳት ከተመለከቱት የምሕንድስና ባለሙያዎች መካከል ኢንጂነር ሳሙኤል ገዛኸኝ በሰጡት አስተያየት፤ «ቤተክርስቲያኑን ተዘዋውረን እንዳየነው ሊፈርስ የሚያስችለው ባይሆንም አሁን ባለበት ሁኔታ ግን ሙሉ ለሙሉ አስቸኳይ ጥገና እንደሚያስፈልገው ለመረዳት ችለናል፡፡

ጥገናውም መደረግ የሚገባው ሕንፃ ቤተክርስቲያኑ ታሪካዊነቱን ሳይለቅ በከፍተኛ ጥንቃቄና ጥናት መሆን አለበት፡፡» ብለዋል፡፡ ባለበት ሁኔታ ለመጠገን ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

እንደዚሁም ቤተክርስቲያኑ ከተመሠረተ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረና ታሪካዊ በመሆኑ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሙያዎችም በእድሳቱ ሥራ ላይ ተገኝተው ቅርስነቱንና ጥንታዊ ውበቱን በማያበላሽ መልኩ ሥራው መከናወን እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናት የሀገር ቅርስ ጭምር በመሆናቸው ታሪካዊነታቸውንና ጥንታዊነታቸውን በሚያሳጣ መልኩ ማሻሻል የሀገርን ታሪክ እንደ ማጥፋት እንደሚቆጠርም ኢንጂነር ሳሙኤል አስገንዝበዋል፡፡

የአካባቢው ምእመናን በተወካያቸው አማካኝነት እንደገለጡት፤ ሊቃነ ጳጳሳቱና የምሕንድስና ባለሙያዎቹ በስፍራው ተገኝተው ቤተክርስቲያኑ የሚገኝበትን ሁኔታ ማየታቸው እንዳስደሰታቸው አስታውቀው፤ ለማስጠገኛ መነሻ የሚሆን ሃያ ዘጠኝ ሺሕ ብር ከአካባቢው ምእመናን ማሰበሳባቸውን ገልጽዋል፡፡

የሌመን ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያንን ጋዜጠኛው እንደተመለከተውና ከባለሙያ እንደተረዳው ጥንታዊው የቤተክርስቲያኑ ሕንፃ የዙሪያ ግንብ መሰንጠቁን ቤተክርስቲያኑን አቅፈው የያዙት ወራጅና አግዳ¥! እንጨቶች ተበልተው ሊፈርሱ መቃረባቸውን ተመልክቷል፡፡

በተለይም በሴቶች መግቢያ በኩል ያሉት የበር ጉበኖችና ቋሚዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ከአገልግሎት ውጭ ለመሆን ተቃርበዋል፡፡

በቤተክርስቲያኑ የውስጥ ግርግዳ ላይ የሚገኙት ልዩ ልዩ ቅዱሳት ሥዕላት ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኞቹ ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡

ቤተክርስቲያኑ ታሪካዊና ጥንታዊ ከመሆኑ አንጻር ምእመናንን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የቤተክርስቲያኑ የበላይ ሓላፊዎች እንዲሁም የክልሉና የፊዴራል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጡት እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡

2 comments:

Dagnu said...

May God raise the right people to get this Church saved from being once up on a time story. when you got action make sure you open the chance to partcipate for all!
Agazit Alem Silase Yirduachu!

አሐዱ said...

የባንክ አካውንት ቢከፈት ለእርዳታ ይመቻልና መላ እንበለው ‹‹ሰው ደካማ ስጋ መሆኑን አይቶ እግዚአብሔር የመዳኛ መንገዱን አበዛለት›› ብንረዳ ለበረከት ነው ባወጣነው ይተካልናልና

አሐዱ

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)