April 26, 2010

የቤተ ክርስቲያን ቅን መሪ ቅዱስነታቸው አባ ሽኖዳ ስለምን አለቀሱ?


(ደጀ ሰላም፤ ኤፕሪል 26/2010)፦ ቅዱስነታቸው ፖፕ ሽኖዳ 3ኛ 117ኛው የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ናቸው። እንደተለመደው ከምእመናን ለሚቀርብላቸው ጥያቄ የሚመልሱበት የተለያየ ዝግጅት አላቸው። ከዝግጅቶቻቸው መካከል በየሳምንቱ በካይሮ በመንበረ ማርቆስ የሚያደርጉት አንዱ ነው። እነዚህን የምእመናን ጥያቄዎች So Many Years With The Problems Of People” በሚል ርዕስ እየታተሙ ለንባብ በቅተዋል። ጥያቄዎቹ ዶግማን፣ ሥርዓትን፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርን የተመለከቱ ሊሆኑ ይችላሉ። በእጄ ገብተው ያነበብኳቸው እነዚህ መጻሕፍት ላይ እንደተመለከትኩት ከሆነ መልሶቻቸው የማያወላዱ፣ በአጭር አባባል ብዙ መልስ የሚሰጡ ናቸው። በቅርቡ ለተጠየቁት አንድ ጥያቄ ግን በቃላት መልስ ከመስጠት ይልቅ በእንባና በዝምታ መመለስን መርጠዋል። ከንግግራቸው በአጭሩ እንመልከት።

በቅርብ ቀናት ስለሆኑ ነገሮች ብዙ ጥያቄዎች (በጽሑፍ) መጥተውልኝ እየተመለከትኩ ነው” ሲሉ ጀመሩ ቅዱስነታቸው። በቅርብ ቀናት ሆነዋል ያሏቸው ነገሮች በአክራሪ ሙስሊሞች በተለያዩ የግብጽ አካባቢዎች በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸሙትን ጭፍጨፋዎችና ግድያዎች እንዲሁም ወጣት ክርስቲያን ሴቶችን በግድ እያገቡ ማስለም እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን ማለታቸው መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ቀጥለውም እንዲህ አሉ።

“ስሙ ወንድሞቼ፤ ልናገረው የምሻው ብዙ ነገር በአእምሮዬ ነበረኝ። በልቤም ውስጥ ከዚያ የሚበልጥ ብዙ ነገር አለ። ይሁን እንጂ ዝም ማለትን እመርጣለሁ። እኔ ዝም ማለትን የመረጥኹት (በምትኩ) እግዚአብሔር እንዲናገር ስለምፈልግ ነው። እመኑ፤ ዝምታችን ከመናገር በላይ ገላጭ ሊሆን ይችላል። እግዚአብሔር ደግሞ ዝምታችንን እያዳመጠ ነው። እግዚአብሔር ዝምታችንን ይሰማል። የዝምታችንን ትርጉምና እየደረሰብን ያለውን መከራም ያውቃል። መከራ እየተቀበልንበት ስላለው ጉዳይ ነገራችንና ችግራችንን ሁሉ ለእግዚአብሔር አሳልፈን እንሰጣለን። በእጆቹም ላይ እንተወዋለን። እናም ‘ያንተ ፈቃድ ይሁን/ ወይኩን ፈቃድከ’ እንላለን። (ጌታ ሆይ) ‘ይህንን ችግር መፍታት ከፈለግኽ ፈቃድህ ይሁን፣ የመከራን መስቀል እንድንሸከም ከፈቀድክም… (ካሉ በኋላ እንባቸውን እያፈሰሱ አለቀሱ) “…ችግራችንን ለእግዚአብሔር እንስጥ/ እንተው ያልኩበት ምክንያት እግዚአብሔር ሁሉን የሚገዛ/ የሚቆጣጠር ስለሆነ ነው። እርሱ ሁሉን ያያል። ሁሉንም ነገር ይሰማል። ሁሉንም ነገር ያውቃል።”

ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን? ስለ ቤተ ክርስቲያን ደኅንነት፣ ስለ ምእመኗ ጤንነት፣ ስለ ልጆቿ ችግር የሚያለቅስ አባት ያላት ቤተ ክርስቲያን የታደለች ናት። በፈንታው ደግሞ ስለ እርሷ ማልቀስ ሳይሆን የሚያስለቅሷት፣ ስለ እርሷ የሚያዝኑ ሳይሆን የሚያሳዝኗት፣ ልጆቿን በእንባቸውና በትምህርታቸው አጥር መከታ ሆነው ከመጠበቅ ይልቅ ከቅጽሯ የሚያባርሩ ጨካኞች ያሏት ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ሊለቀስላት ይገባል።
“ለቤተ ክርስቲያን ቅን መሪን የምትሰጥ” እንዲል ቅዳሴው ለቤተ ክርስቲያኑ የሚያለቅስ በርግጥም ቅን መሪ ነው።

አባታችን ቡራኬዎ ይድረሰን፣ ቅዱስ ጸሎትዎ ትደረግልን፣ ልጆችዎ ከመከራ ሥጋ እረፍትን አግኝተው እንባዎ እንዲታበስ እግዚአብሔር ይርዳዎ። 

ማስታወሻ፦ ቅዱስነታቸው ሲያለቅሱ የሚያሳየውን የቪዲዮ መልእክት ከዚህ (ቪዲዮ) ተመልከቱ፤ በግርድፉ የተረጎምነውን ንግግራቸውን አድምጡ።

3 comments:

nafkoteyegetalij@gmail.com said...

ልጅ ባባቱ ፊት ሆድ እንደሚብሰው ሁሉ ጻድቃንም በእግዚአብሔር ፊት ሲናገሩ ሆድ ይብሳቸዋል የልባቸውን የሚያውቅ እሱ ብቻ ነውና።
ግን አንድ ነገር ልበል

እናት እያላት የሰው እናት የምትፈልግ ምን አይነት እርጉም ልጅ ትሆን?

እናቷስ ምን አይነት ወራዳ ደሃ እናት ትሆን ወይንስ በሽተኛ ሄንን ያህል የተጠላቸው ነገር ግን አንድ ያልተረዳችሁት ነገር ቢኖር እረሱም እናት እናት ናት መቼም ሆነ መቼም በስደት ያሉት ሊቃነ ጳጳሳት ዘወትረ በመንገዳቸው ስለ ሃገራቸው ስለ ሃይማኖታቸው ደም ሲያለቅሱ እነዲሁም በሃገር ወስጥ ያሉት ሊቃነ ጳጳሳት ጠዋት ማታ ስለ አንድነት ስለ ሰላም ሲያለቅሱ
እነዲሁም በዱር በገደሉ በገዳማት ወስጥ ከሰው ተለይተው አለምን ክደው እያለቀሱ ያሉት አባቶችና እናቶች ለቅሶስ ለቅሶ አይደለም ወይ? ስንት አባቶች ናቸው ልክ እንደሳቸው ነገሮችን ሁሉ በልባቸው እንደያዙ ሳየጫውቱን ሳያማክሩን ጥለውን ያሸለቡት ለመን በሃይማኖት ካባ ስውር ደባ አይቆምም ለምን የቤታችን አይቀድምም መጀመሪያ ለምን አባቶቻችን ታረቀው ቤተ ክረስቲያን ሰላም ይምትሆንበትን መንገድ በቀኝም በግራም በላይም በታችም አንፈልግም ከዚህ ሁሉ በፊት ግን እርስ በዕርሳችን ይቅር ተባብለን እንዋደድ በሰዳደብ ይቅር እስቲ የተዋህዶ ምዕመናንም ደስ ይበላቸው አባቶቻቸንም የቀራቸውን ዘመን በፍቅርና በደስታ መርቀውን ያሳልፉ እኛም ከመርገም እንዳን።

እረ እናስተውል ወገኔ

mistire tewahedo said...

I hope our fathers will do the same having taken a lesson from his Holiness.What happened to them had happened to us in Jimma,Dessie,Harar,Gonder,Arsi,...
but we did not see a drop of tear,instead...As his Holiness said GOD knows what is in our heart.

Anonymous said...

As kiduse pawelose said enyne elete elete YmiYasasebege Yabyate kerestiyanate Gudaye newe. This is all what our holly fother weep by theway pope shinod are not only the father of Alexandria Cristian its for us to so. please lets wake up from our sleep and lets be in together to bring the required success in the church

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)