April 19, 2010

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር “በበጋሻው ሥራዎች ላይ ጥናት እያደረኩ ነው” አሉ

(ደጀ ሰላም፤ ኤፕሪል 18/2010)፦ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር እና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም “አርማጌዶን” የሚለው የስብከት ሲዲን ተከትሎ በተነሣው የዲ/ን በጋሻው ደሳለኝ ሃይማኖታዊ “ሥራዎች” ዙሪያ ጥናት እንደሚያደርጉ መገለፁን “ያኔት” መጽሔት በሚያዚያ 2002 ዓ.ም እትሙ ዘግቧል። ይህ የተገለጸው ዲ/ን በጋሻው ከቅዱስ ፓትርያርኩ እና ከብፁዓን አባቶች ፊት በቀረበበት ወቅት ነው።

በጋሻውን ቅዱስ ፓትርያርኩ ፊት ቀርቦ ይዘውት የቀረቡት በቅ/ሲኖዶሱ ውዝግብ ወቅት በብዙ ሰዎች “ኤልዛቤል” እየተባሉ ስማቸው የተጠራው ወ/ሮ እጅጋየሁ መሆናቸው እየተነገረ ነው። ይህንኑ የዘገበው “ያኔት” የተባለ መጽሔት በዝርዝር እንዳነሣው ዲ/ን በጋሻው ደሳለኝ ሥጦታ ይዞ ወደ ቅዱስነታቸው መሔዱን፣ በወቅቱ በሥፍራው ከተገኙት አባቶች መካከል ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ “እኔ የግል ሲባል የማውቀው የግል ሱቅ፣ የግል ምግብ ቤት ነው እንጂ የግል ሰባኪ ሲባል ሰምቼ አላውቅም። አንተ ግን የግል ሰባኪ ነህ። ቤተ ክርስቲያኗን እየከፋፈልክ ነው። ምእመኑ ከቤተ ክርስቲያን ወጥቶ አዳራሽ መግባቱ ትክክል አይደለም። ሲኖዶሱም በዚህ ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት” ማለታቸው፣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በበኩላቸው “በዘመኑ የተነሣ ሰባኪ ነውና ልናበረታታው ይገባል” ሲሉ ሌሎችም አባቶች የተሰማቸውን መናገራቸው ተዘግቧል።
ዲ/ን በጋሻው “የመስቀሉ ስር ቁማርተኞች” በሚለው መጽሐፉ ቅዱስ ፓትርያርኩን ከቆማሪዎቹ አንዱ አድርጎ ከጠቀሳቸው ወዲህ ፓትርያርኩንና መንግሥትን በሚቃወሙ ወገኖች ዘንድ ከፍተኛ ስም ለማትረፍ መብቃቱ ይታወቃል። በዚሁ ስብሰባ ላይ በጋሻው “የመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች”ን ካሰራጩት መካከል አንደኛው ማኀበረ ቅዱሳን ነው ሲል ለቅዱስነታቸው በማስረዳት ማኅበሩን በማሳጣት እና ጥርስ ውስጥ በማስገባት ራሱን ለማትረፍ የሞከረ ሲሆን “ደጀ ሰላም” የማኀበረ ቅዱሳን ነው የሚሉት ወ/ሮ እጅጋየሁም “ማኀበረ ቅዱሳን ኤልዛቤል ብሎኛል” ሲሉ ክሳቸውን አቅርበዋል ተብሏል።

ዲ/ን በጋሻው በቅርቡ “አርማጌዶን” በሚል ርዕስ በመምህር ዘመድኩን በቀለ በተዘጋጀ ትምህርት ተቃውሞ ከቀረበበት ወዲህ የቀረበበትን ሃይማኖታዊ ክስ ከማስተባበል ይልቅ “አጥቅተውኛል” የሚላቸውን ስም በማንሣት እንዲሁም በፊት የከረረ ፀብ ያለው ይመስል ከነበሩ ሰዎች ጋር በመገናኘት እውነተኛ ማንነቱን ግልጽ በማድረግ ላይ ይገኛል። “የተነሣብህን ሃይማኖታዊ ጥያቄ ለምን መልስ አትሰጥም?” ቢባልም ከፕሮቴስታንት ሰባኪያን የወሰዳቸውን ትምህርቶች እንኳን ለምን እንደወሰደ ለማብራራት ሳይችል ቀርቷል። አሁን ደግሞ በአማላጅ ከቅዱስነታቸው ጋር በመታረቅ ከገባበት ማዕበል ራሱን በፖለቲካዊ አካሄድ ለማዳን በመሞከር ላይ ይገኛል። ከዚህ የጎን አካሄዶቹ መካከል ስለ እርሱ የሚጠይቁ ጋዜጠኞችን እና ግለሰቦችን በገንዘብ ለመደለል መሞከር ወይም በማስፈራራት ዝም ለማሰኘት መሞከር በተደጋጋሚ የሚጠቀስ ጉዳይ ሆኗል። ለምሳሌ የዲ/ን በጋሻው “ኤጀንት” (ጉዳይ አስፈጻሚ) ነው የሚባል አንድ ግለሰብ “ልጆችህን ብታሳድግ ይሻልሃል” ሲል መምህር ዘመድኩንን በስልክ ያስፈራራበትን የስልክ ልውውጥ ለመስማት የቻልን ሲሆን ጉዳዩ ወደ ፖሊስ መመራቱም ታውቋል። ዲ/ን በጋሻው አሁን በወ/ሮ እጅጋሁ በኩል የሄደው ማስፈራራቱም ሆነ በገንዘብ መደለሉ ስላላዋጣው ነው ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እያለ የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም በዲ/ን በጋሻው “ሥራዎች” ላይ ጥናት መጀመራቸው ጥሩ ዜና ሲሆን “ሥራዎቹ” የተባሉት መጻሕፍቱ፣ ስብከቶቹ እና የመዝሙር ግጥሞቹ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)