March 31, 2010

"በታላቁ በረሃ፣ በሚያስፈራ ማዕበል የተፈተነ ሰውነት":- በሊቢያ በኩል ጣሊያን ስለሚገቡ ኦርቶዶክሳውያን ስደተኞች እውነተኛ ታሪክ ክፍል አንድ

ውድ ደጀ ሰላሞች እንደምን ከረማችሁ? እንኳን ለሕማማት በሰላም አደረሳችሁ ። ከዚህ በታች ያለውን ጽሑፍ አንብቡትና እንደ መነሻ ሃሳብ ተጠቅማችሁ የረቀቀውን አጉላታችሁ፣ የተሳሳትኩትን አርማችሁ እና አስፍታችሁ በሊቢያ በኩል ጣሊያን ስለሚገቡ ስደተኞች የመወያያ ርዕስ ብትከፍቱ የሀገራችንን ሕዝብ ግንዛቤ ይጨምራል ብዬ አስባለሁኝ።
ታናሽ ወንድማችሁ
በፈቃዱ ንጉሴ ዓለሙ
ቸር ስንብቱ
++++
ቀኑ መጋቢት 26/ 2002 ዓ.ም፡፡ እለቱ ቅዳሜ ነው ከሚላኖ ቸንትራሌ ስቴሽን ተነስቼ ጉዞዬን ወደ ደቡብ አቅጣጫ አድርጌ በይሮ ስታር ባቡር ጉዞዬን ተያያዝኩት። ባቡራችን በሚያስደንቅ ፍጥነት ይሄዳል እኔም በሃሳብ ነጎድኩኝ። ከሚላኖ ወደ ፓርማ፤ ሞደና፤ ቦለኛ፤ ርሚኒ፤ አንኮና... ወዘተ ጉዟችንን ቀጠልን። አሁን ደቡብ ጣሊያን አካባቢ እንገኛለን ከ9 ሰዓታት ጉዞ በኋላ ማለትም ከ558 ማይልስ (898.32 ኪ.ሜ) በኋላ ባሪ ከተማ ገባሁኝ። ባሪ በደቡብ ጣሊያን ከ ሮማ 229 ማይልስ (370 ኪ.ሜ) ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ነች። ባሪ ከባህር አጠገብ የምትገኝ ከተማ ነች። ከሰሜን ጣሊያን ወደ ደቡብ ጣሊያን ባሪ የመጣሁበትም ዓላማ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን (የክርስቲያኖችን ስብስብ ማለቴ ነው) እንዳለ ሰምቼ ከነርሱ ጋር የሆሳዕናን በዓል ለማክበር ነው። በርግጥ ከወንድሞቼና ከእህቶቼ የሰማሁትን ነገር የቤተ ክርስቲያኑን ታሪክና አጀማመር እንዲህ አቀርበዋለሁኝ።


ቤተክርስቲያኑ በርግጥ ታቦት የለውም። የሚሰባሰቡበትም ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን በተሰጣቸው አዳራሽ ነው። ታዲያ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ተባለ የሚል ጥያቄ ቢነሳ የምዕመናን ስብስቡ ቤተ ክርስቲያን አሰኘው እንጂ በሌላም በኩል እነኚህ ወጣቶች የራሳቸው የሆነ ቤተ ክርስቲያን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ በመሆኑና እግዚአብሔር ቢፈቅድ ወደ ፊት እንደሚያገኙ በማመን ነው። ይህ በጣሊያን የተለመደ ሂደት ነውና። አጀማመራቸው እንዲህ ነው፡-


በሕጋዊ መንገድ የመጡት ወንድሞችና እህቶች በቤታቸው ውስጥ ስብከቶችን በማስመጣትና በመስማት ሐመር መጽሔቶችን በማንበብ በቤት ውስጥ ያካሂዱ ነበር ።ከአንድ ዓመት እና ከተወሰኑ ወራት በኋላ በወንድሞችና በእህቶች ጥረት አጠቃላይ በከተማው ማኅበር አቋቁመው መማማር እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ይደርሳሉ። በስደት የመጡት በበኩላቸው በባሪ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ ያሉት ኦርቶዶክሳውያን (ኢትዮጲያውያንና ኤርትራውያን) ተሰባስበው ባዶ ሜዳ ላይ ጸሎት ያደርሱ ነበር። ይህ በሊቢያ ቆይታቸውም የተለመደ ነበርና። በቤታቸው ጉባዔ የጀመሩት ይህን ሲሰሙ ደስ ብሏቸው ምእመናንን አሰባስበው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ የመጀመሪያ ጉባኤቸውን አደረጉ። በይበልጥ ተጠናክረው ኮሚቴ በማዋቀር መምህራንን ከሮማ፤ ከፓርማ እንዲሁም ከሚላኖ አስመጥተው መማማር ጀመሩ። በዚህ ብቻ ሳያቆሙ በባሕር ያሻገራቸውን ተስፋቸውን እግዚአብሔርን በሰንበት ትምህርት ቤት በማዋቀር አገልግሎታቸውን ቀጠሉ። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ይሄው ለዚህ በቃን ብለው ከተሳታፊዎቹ አንዱ አጫወተኝ።


በዚህ ጉባኤ ውስጥ ኢትዮያውያን እና ኤርትራውያን እንደሚካፈሉ አየሁኝ። በጣም ተደሰትኩኝ። ምክንያቱም እንኳን ሁለት የተለያዩ ሀገራት በአንድ ሀገር አንድ ሃይማኖት ሆነው በፓለቲካ የሚከፋፈሉ አሉና። ይህን ሳስብ ድንገት የቅ/ጳውሎስ መልእክት ትዝ አለኝ። "አንዱ እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ ሁለተኛውም እኔ የአጵሎስ ነኝ ቢል ሰዎች ብቻ መሆናችሁ አይደለምን? አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደ ሰጣቸው ያገለግላሉ።እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም። የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፥ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል።የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና።............ ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው።" ብሎ መከፍፈል እንደሌለብን አስረግጦ የተናገረውን ክፍል። እኔም በልቤም እግዚአብሔር ያጽናችሁ አልኩኝ። ከነሱ እኛ በጣም ብዙ ነገር መማር አለብን። ለኔ ብዙ ነገር አስተምረውኛል።


ዕለተ ቅዳሜ ተገባዶ እለተ እሁድ መጣ:: ድንገት በሐሳብ ወደ ኋላ ነጎድኩ። በ1997 ዓ.ም ትዝ አለኝ ከግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የዝዋይ ሐመረ ብረሐን ቅ/ገብርኤልና አምስቱ ደሴቶች የተደረገ ጉዞ በአጋጣሚ ሆኖ የ ሆሳእና ቀን በዝዋይ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በአብነ ጎርጎርዮስ ሳልሳይ (የሰ/ሸዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ) ቀድሰው በበዓሉ ላይ የታደምነውን የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችም ባርከው ደስ በሚል ሁኔታ ነበር። ያሳለፍነውን ሁልጊዜ አልረሳውም። በጣም ረክቼበት ስለነበር። ዛሬ ደግሞ በጣሊያን ሀገር በባሪ ከተማ ላይ ነኝ። ምእመኑ ግጥም ብሏል፤ አዳራሹን ሞልተውታል። በአብዛኛው በባሕር የመጣ ስደተኛ እንደሆነ ነግረውኛል። ከሽማግሌ እስከ ሕፃን ልጅ ድረስ መጥተዋል። ጉባኤያችን በጸሎት ተከፈተ። በአካባቢው ምንም ካህናት ስለሌሉ የቅዳሴ ነገር የማይታሰብ ነው።


ታዲያ ምን ያደርጋል ካህናት የሉ...በድጋሚ ሁሌ የማስባት ወደ ህገሬ በሃሳብ ና በትካዜ ወደ ሀገር ቤት ተጓዝኩ ብዙ ካህናት በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ እንደ ምእመን ቆመው ሲያስቀድሱ እዚህ ግን ካህን ጠፍቶ ሕዝቡ ምስጋና ሲጠማ... አስተዋልኩኝ በጣም ያሳዝናል።ሌላው ደግሞ ትናንት ስመጣ የነገሩኝ ነገር በሃሳቤ ድቅን አለብኝ። እንዲህም ብለውኝ ነበርና ይህ ጉባኤ ከመጀመሩ በፊት እዚህ የነበሩ ኦሮቶዶክሳውያን ልጆቻቸውን የሚያስጠምቁበት ቤተ ክርስቲያን ስለሌለ ካቶሊኮቹ ቤተ ክርስቲያን ጋር እየሄዱ እንደሚያስጠምቁ፣ ጸሎት እንደሚያደርጉም እንደነገሩኝ አስብኩና እዚህ ደረጃ ላይ ማለትም ሕዝቡን ስብስበው በቤቱ እንዲጸልዩ በተለይም ደግሞ ከ1 ወር በፊት ብፁዕ አባታችን አቡነ ዮሴፍ የምስራቅ አውሮፓ ሊቀጳጳስ በዚሁ ቦታ ተገኝተው ብዙ ሕፃናትን አዋቂዎችንም ሳይቀር እንዳጠመቁ፣ ቀድሰውም ሥጋና ደሙን እንዳቀበሉ ሳስብ እዚህ ደረጃ መድረሱ በራሱ ትልቅ ነገር ነው በዚህ አጭር ጊዜ አልኩ።በተጨማሪም ባለፈው የገና ዕለት ሰንበት ተማሪዎቹ የስደተኞች ካምፕ ድረስ ሄደው ምሳ ለስደተኞቹ አብልተው የወገን መከታ ሆነዋል። ይህ ደግሞ ታላቅ ጅማሬ ነውና በዚህኛውም ተደሰትኩኝ።


የዘወትር ጸሎት የዕለቱን ውዳሴ ማርያም፣ ይዌድስዋ መላእክት አደረስንና በማሳረጊያ ጸሎት ዘጋን። በልቤ ጌታ ሆይ በዚች ሰዓት በየቤተ ክርስቲያናት የሚደገመው የቁም ፍታት ለኛም ይሁን ብዬ በልቤ አሰብኩኝ። ፕሮግራሙ ቀጥሏል። እነኝህ ወጣቶች ሁልጊዜ መዝሙር እያጠኑ ያቀርቡ ነበርና ዛሬም እንደተለመደው መዝሙር አቀረቡ፤ ሆሳእና በአርያም......። ዘማርያኑ እንደ ጨረሱ የእለቱን ትምህርት ሆሳእና በአርያም በሚል ርዕስ መምህሩ እግዚአብሔር ያቀበለውን አስተማረ። ሕዝቡም በጸጥታ ይሰሙ ነበር። በጣም የገረመኝ ነገር ግን ከአጠገቤ የተቀመጠው የአንድ ጣሊያናዊ ሁኔታ ነው።ይህ ሰው ጸሎት ሲጸለይ፤ መዝሙር ሲዘመር ልክ አማርኛ እንደሚሰማ ሰው በደንብ እየተካታተለ ሲሰማ ነበር። ልክ ትምህርቱ ሲጀመር የራሱን መጽሐፍ ቅዱሱን አውጥቶ ማንበብ ጀመረ። ይህ ሰው አማርኛ ሳይሰማ ፍፁም እንደሚሰማ ሲሰማ ሆኖ ይከታተል ነበርና(እባክዎን ከታች ፎቶ ይመልከቱት)። እኛ እንኳን በሌላ ቋንቋ በቋንቋቸን ተነግረን እንሰማ ይሆን???


ትምህርቱ ተጋባዶ በ አንድ ወንድም ጥያቄና መልስ ተካሄደ:: መልሱን ለመለሱ ምዕመናን ለማበረተቻ የአንገት መስቀል ተሸለሙ። በመጨረሻ የሆሳዕና ወረብ በአንድ ዲ/ን መሪነትአማካኝነት ከወረብን በኋላ የዕለቱ ፕሮግራም ፍፃሜ ሆነ።
++++


ከፕሮግራም በኋላ በባህር የመጡትን ወንድሞችና እህቶች ማነጋገር ፈልጌ አንዲት እህትን ጠየኳት። እሷም በባህር ከመጡ ልጆች ጋር አገናኘችኝ። በርግጥ ብዙ ቢሆኑም ከብዙ 4 ብቻ ለማቅረብ ወደድሁኝ።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)