March 27, 2010

ለዲ/ን ዳንኤል መልስ:- በሳጥኑ ውስጥ እየተርገበገብን እንኑር መልካም ነው ወይም ከሳጥኑ እንውጣ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን።
(ዲ. ኃይሌ ታከለ)
ለተወደድክ ወንድሜ ዲ. ዳንኤል ክብረት እንደምን አለህ?  ይህን ማስታዎሻ ለመጻፍ የተነሳሁት የአንተን ቃለ ምልልስ ደጀ ሰላም ስላስነበበችን በውስጡ ስለያዛቸው ቁም ነገሮች የእኔን አስተያየት ለመስጠት ነው። በኢ-ሜይል ወይም በስልክ አስተያየቴን ለአንተ ማድረስ እችል ነበር ነገር ግን በዚሁ ብሎገር ማድረጉን መርጫለሁ ለሌሎቹም መምህራን እንዲደርሳቸው አስተያየቴንም ለማጋራት። የዚህ ጽሁፍ ዋና መልዕክት በቃለ ምልልሱ ላይ በሰፈሩት አንዳንድ ቁምነገሮች ላይ ብቻ የሚያተኩር ሲሆን አስተያየቴ ግን ለሁሉም አትሮንስ ፊት ለሚቆሙ መምህራን እንዲደርስ በማሰብ ነውይቅርታ ወንበር ለዘረጉት ግን አይደለም ድፍረት እንዳይሆንብኝ በማሰብ። ጃፓኖች በባህላቸው ለአንድ ነገር ብዙ እውነት ሊኖር ይችላል ብለው ስለሚያስቡ የሚነሱትን ሃሳቦች ሁሉ ይቀበሏቸዋል ምን አልባት ይህ በሳይንስ ለደረሱበት እድገት ጠቅማቸው ይሆናል በአንድ ጊዜ ብዙ አማራጭ መንገዶችን በመፈተሽ። እኛ ግን በክርስትና እንዲሁም በክርስትናው ባህል ውስጥ በመወለዳችንና በማደጋችን ለአንድ ነገር አንድ እውነት ብቻ አለ ብለን እናስባለን ከዚህም ውጭ ሲሆን ወደተሸራረፈ እውነት አለበለዚያም ወደ ሃሰት እንወርዳለን። የዝምታን ግን ደረጃውን ለማስቀመጥ ይከብደኛል ከሳጥኑ ውስጥ ለመውጣት ላልቻሉ ሰዎች ግን የተወደደ ምርጫ ነው።
ይህን ታሳቢ በማድረግና በክርስቲያኖች መካከል ከወጣኒ አንስቶ እስከ ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ አስር የሚሆኑ የምግባር ደረጃዎችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት አስተያየቴን እሰጣለሁ።

ደጀ ሰላም፦ ውድ ወንድማችን / ዳንኤል ክብረት፣ ሰላመ እግዚአብሔር ይድረስህ። ከሁሉ አስቀድመን ይህንን ቃለ ምልልስ በጽሑፍ ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆንህ ከልብ እናመሰግናለን። / ዳንኤልኮንትሮቨርሺያል” (አወዛጋቢ) ሰው ነህ ልበል? ስለ ቤተ ክርስቲያን ውይይት በተነሣ ቁጥር ስለ አንተ አምርረው የሚናገሩ ብዙ ድምጾች ይሰማሉ። ለምን ይመስልሃል?
/ ዳንኤል፦ በመጀመርያ ይህንን ዕድል ስለሰጣችሁኝ እንደ ሀገሬ ክርስቲያናዊ ባህል እግዚአብሔር ይስጥልኝ እላለሁ፡፡ ይህንን ጥያቄ ስትጠይቁኝም «ኮንትሮቨርሻል» የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል የተጠቀማችሁት ምናልባት ተመሳሳዩን አማርኛ አጥታችሁ ይሆን? ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔም ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ይህ ነገር እያስገረመኝ መጥቷል፡፡ እንዴት ሊሆን ቻለ? ብዬም ደጋግሜ አስቤያለሁ፡፡ እስካሁን ግን መልስ መስለው የታዩኝ ሦስት ነገሮች ናቸው፡፡ ወደፊት ሌሎች ደግሞ ይታዩኝ ይሆናል፡፡

በአንደኛው ላይ ጥያቄም አስተያየትም የለኝም እንዳለ ስለምቀበለው።

ሁለተኛው (የእኔ ስም ተደጋግሞ የሚነሣበት) ምክንያት ደግሞ ከኔ ጠባይ የመነጨ ይመስለኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያኔን የተመለከተ ጥያቄ እና ክስ ከተነሣ እረፍ እረፍ አይለኝም፡፡ ይህኮ የእነ እገሌ ሥራ ነው ብዬ ዝም ማለት አልችልበትም፡፡ አጠናለሁ፡፡ አስብበታለሁ፡፡ መረጃዎችን አሰባስባለሁ፡፡ በሰበሰብኳቸው መረጃዎች፣ ዕውቀቶች እና ትምህርቶች ራሴ ካመንኩ፤ ከዚያ በኋላ ለሌሎች ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ለማካፈል እሞክራለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች ይህንን ጠባዬን ያውቃሉ፡፡

አስተያየትበዚህ ጥያቄና መልስ ውስጥ ብዙ ቁም ነገሮችን አግኝቻለሁ በተለይም ዲን. ዳንኤል በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎችና ክሶች እረፍ እረፍ እንደማይለው፤ ይህ የእኔ እገሌ ሥራ ነው እንደማይልና ከመናገር ወደ ኋላ እንደማይል፤ ለሚናገረው ነገር ግን አስቀድሞ ጥናት የሚያደርግ ሰው መሆኑን ለዚህም በአሁኑ ወቅት ያለውን የአባቶቻችን መከፋፈል እንደምሳሌ በመጥቀስ ያሰፈረው ነው።

«የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፡- ከአቡነ ባስልዮስ እስከ አቡነ ጳውሎስ» የሚል የጥናት ፕሮጀክት ከፈትኩና መረጃዎችን ማሰባሰብ ጀመረኩ፡፡ አምስቱም አባቶች እንዴት ተሾሙ? ሂደቱ ምን ይመስል ነበር? የዓይን ምስክሮች ምን ይላሉ? በወቅቱ የነበሩ ጋዜጦችስ? ሌሎች ተጓዳኝ መረጃዎችስ? ቃለ ጉባኤዎችስ? ወዘተ እያልኩ ማጥናት ጀመርኩ፡፡ አያሌ የቀድሞ ጋዜጦችን ሰበሰብኩ፡፡ በወቅቱ የነበሩ ምስክሮችን አነጋገርኩ፡፡ የተጻፉ ደብዳቤዎችን ቪዲዮዎችን አየሁ፡፡ ፎቶዎችን ሰበሰብኩ፡፡ የሌሎችን ሀገሮች ታሪክ አየሁና አንድ ድምዳሜ ላይ ደረስኩ፡፡
አሜሪካ ስመጣ «ስደተኛ የሚባል ሲኖዶስ የለም፡፡ 1983/84 በነበረው የቤተ ክርስቲ ያን ታሪክ ትክክለኛው ሥዕል አሁን በአሜሪካ የሚባለው አይደለም፡፡ ሌላ ያላወቅነ ውም አለ፡፡ጥፋት ጠፋም ከተባለ በዋናነት ተጠያቂዎቹ እዚህ ነው ያሉት፡፡ ጥያቄው የቀኖና ሳይሆን ሌላ ነው» እያልኩ ማስረዳት ቀጠልኩ፡፡ የማይነካው ነገር ተነካ፣ የማይነሣው ጥያቄ ተነሣ፣ የማይደፈረው ጉዳይ ተደፈረ፤ እናም መነጋገርያ ሆነ፡፡ በወቅቱ እንዲያውም ወደፊት ለሚደረገው የቤተ ክርስቲያን አንድነት ብዬ የተውኳቸው መረጃዎች አሉ፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሲሾሙእንኳን አደረሰዎ፣ ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ እንደዚህ ዓይነት ፓትርያርክ አግኝታ አታውቅም» ብለው የጻፉ አባት ዛሬ ተቃዋሚ ነኝ ይላሉ፡፡ ደብዳቤው ከነፊርማ እና ማኅተማቸው አለ፡፡ ቅዱስነ ታቸው ሲሾሙ፣ በበዓለ ሲመታቸው ጊዜ «ይደልዎ ይደልዎ በሉ» ሲሉ የነበሩ አባት እዚህ መጥተው የስደተኛ ሲኖዶስ አቋቋሚ እና አስተባባሪ ሆኑ፡፡ ቪዲዮውኮ ምስል እና ድምፃቸውን ቀርፆ አስቀምጦታል፡፡ ታዲያ አብዛኛው ሰው ዝም ባለበት በዚያ ጊዜ በምድረ አሜሪካ ባለማቋረጥ ተጉዤ ተናግሬያለሁ፡፡ እንዲህ ዛሬ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ተመልሰው ጳጳስ ሊሆኑ፤ በወቅቱ በቤታቸው ያሳረፉኝ አባት እንኳን ፈርተው «ይህንን ቤት ለቅቀህልኝ ብትወጣ» እስከ ማለት ደርሰው ነበር፡፡ የተከፈለው ሁሉ መሥዋዕትነት ተከፍሎ ግን በአባቶች ብርታት፣ በወጣቶች ትጋት የአሜሪካ መልክዐ ምድር ተለወጠ፡፡ በዚህ ቂም የያዙ ብዙ እንጀራ ፈላጊዎች አሉ፡፡ ስለዚህም ማንኛውም ነገር ሲከሰት ዳንኤል አለበት ማለትን የዘወትር ጸሎታቸው አድርገውታ።

አስተያየትበዚህ መልስ ውስጥ ለእኔ ያስደሰተኝ ነገር ቢያንስ “ከአቡነ ባስልዮስ እስከ አቡነ ጳውሎስ” የሚል የጥናት ፕሮጀክት በዲ. ዳንኤል ተሰርቶ ያለቀ መሆኑ ነው። ከዚህ አስቀድሞ በሁሉም አባቶቻችን ጳጳሳት መንፈሳዊ ህይዎትና አስተምሮታቸውን በዲን. መርሻ አለኸኝ እንዲሁም ፍሬ ሊቃውንት የተሰኘ የአበው ሊቃውንት ታሪክና ስብከቶቻቸውን የሚዘክር (በማህበረ ቅዱሳን የመጻሕፍት ክፍል የተዘጋጀ) መጻሕፍትን ለማንበብ እድሉን አግኝተናል። ይህን የዲን. ዳንኤልን ጥናት ስገምተው ግን በአምስቱ ፓትርያርክ አባቶች ላይ ጥልቅ የሆነ ጥናት እንዳከናወነና የቤተ ክህነቱን ፖለቲካም የመረመር ይመስለኛል። በማጠቃለያውም ከሳጥኑ ለመውጣት በማሰብ!!! ነገር ግን በጥናቱ ፍጻሜ አንድ ድምዳሜ ላይ መድረሱን ከዚያም በኋላ ወደ አሜሪካ ምድር በመዝለቅ የስደት ሲኖዶስ ስለሚባለው ቀልድ ይናገራል ለጥፋቱም ተባባሪ ስለሆኑ አባቶች ያነሳል። የማይነካው ነገር ተነካ፣ የማይነሣው ጥያቄ ተነሣ፣ የማይደፈረው ጉዳይ ተደፈረ፤ እናም መነጋገርያ ሆነ ይለናል።
ትንሽ ቀልድ ሆነብኝ ምክንያቱም የጥፋቱ ተባባሪዎች በየትኛውም ስፍራ ይሁኑ መኖራቸው የታወቀ በመሆኑ ይህን መግለጽ የጥናቱ ዋና ዓላማ እንደሆነ ከቃለ ምልልሱ አላገኘሁትም እንደዚህም አልተረዳኝምና። በ1983/84 በነበረው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ትክክለኛው ሥዕል አሁን በአሜሪካ የሚባለው አይደለም ይልና በቀጥታ በዚያን ጊዜ የተውኔቱ አካል ወደ ነበሩ በስም ስላልተጠቀሱ አባቶች ነገር ግን የአሰላለፍ ለውጣቸውን ወደ ማሳየት ይወርዳል። ለእኔ ግን ይህ ቁም ነገር አይደለም በተለይም የማይደፈረውን ለመድፈር ከተነሳ ሰው በጉዳዩ ጠለቅ ያለ ጥናትም ከአደረገ ሰው። የምጠብቀው እውነትን በወርዷና በቁመቷ ልክ ሳትጠብና ሳትሰፋ፣ ሳትረዝም ሳታጥር፣ ሳትቀድድ ተለብጣም ሳትሰፋ ለመስማት ነበር። ለመናገር ከደፈርን እውነትም እራሷ እረፍ እረፍ የማታሰኘን ከሆነ የ2003/2004 ዓ.ም የቤተክነቱ ፖለቲካ እንዴት ነበር? እውነት ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ የፓትርያርክ መንበሩን ወደውና ፈቅደው ወይም በህመም ምክንያት ስለሚባለው ቀልድ የጥናቱ ውጤት ምን ያሳያል? የመንግስት ወይም በግለሰብ ደረጃ ባለስልጣናት፤ የሲኖዶሱ አባላት አባቶች ጳጳሳት፤ ካህናትና ምዕመናን ድርሻችን ምንድር ነበር? ብዙ መረጃዎችን ያሰባሰበ በአሉባልታ ላይ ሳይሆን በመረጃ ላይ የተመሰርተ ጥናት ያደረገ ሰው ከጥናቱ በኃላ ጥፋት አለ ካልንም ሳይሆን ጥፋት ነበር ወይም አልነበረም ብሎ በማስረጃ ማሳየት ያስፈልጋል!!! ከዚያም አምስቱም አባቶች እንዴት ተሾሙ? ሂደቱ ምን ይመስል ነበር? ስለሚለው መተንተን ነው። መቸም ይች ነገር ቀልድ አይደለችምና የማይደደፈረው ተደፈረ ተረተረት ከዚህ ላይ ይፈጸማል። ከላይ የማይደፈረው የተባለው ግን በትክክል ሊደፈር የማይቻል አይደለም ያለመረጃም ያለአድካሚ ጥናት ልንደፍራቸው የምንችላቸው ሰዎች ጥርስ የሌላቸው በመሆኑ። ያማ ከሆነ እኔም በዚህ ጽሁፍ የማይደፈረውን ዲን. ዳንኤልን ደፈርኩት ብል ምን ይባላል አስቂ ነው።
በዚህ ጽሁፍ ስለ ስደተኛ ሲኖዶስ ልከራከር አይደለም ወይም የማይደፈረውን (እውነተኛውን ማለቴ ነው) እንድትደፍር ልገዳደርህ አይደለም። በመኖርህ በአገልግሎትህ የምንጠቀም ክርስቲያኖች እጅግ ብዙ ነንና። በዚህች ማስታዎሻ ግን ለወንጌል መምህራን ከፍርደ ገምድል መዝገብ ውስጥ እንዳትመዘገቡ በጥንቃቄም እንድትጓዙ ለመጠቆም ነው። ለዚህም በቅድሚያ ደረጃዎቻችሁን በትክክል ማወቅ እንዳለባችሁ ይታየኛል የቀደሙትን ሳናነሳ ከባድ በመሆኑ በዘመናችን እንኳ «እኔ በአለቃ አያሌው ታምሩ ወንበር መቀመጥ እችላለሁ?» ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል እውቀታቸውን ብቻ አይደለም ልበ ሙሉነታቸውን የእምነታቸውን ልክ ማሰብ ያስፈልጋል። ቀሲስ አስተራኤ ጽጌንም ላነሳ ወድጀ ነበር መደፈር ያለበትን በመድፈር ወደ ኃላ ሲሉ አይቻቸው አላውቅም ነገር ግን የሚደፍሩት እውነት ሊያመጣባቸው ከሚችለው እዳ እራቅ በማለታቸው በሁለተኛው ደረጃ ከአድናቆት ጋር መጥቀሱን መረጥኩ። ከዚህ በመለስ ዝቅ ባለው ወንበር በልካችሁ ለመቀመጥ ለምታስቡና ለምትመኙ ወንድሞችና እህቶች ከሳጥኑ ሳትወጡ የምትሰሩት ብዙ የአግልግሎት ድርሻ ቤተ ክርስቲያን አላትና በዚያ ላይ ብንሰማራ።
በማህበረ ቅዱሳን የመጀመሪያ ዘመናት የነበሩ ወንድሞችና እህቶች በአወጡት የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ የቤተ መንግስቱን ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የቤተ ክህነቱን አስተዳደር ላለመንካት ያዝ ነበር። ይህም ብልህነት ነው ከሳጥኑ ሳይወጣ በአቅም የሚሰራውን ብቻ የጎደለውን ለመሙላት። ለምሳሌ በዚህ ሰሞን በተለያዩ ድረ ገጻች የአቡነ ዜና ማርቆስ እረፍተ ሞት ሲነገር የቤተ ክርስቲያን ነገር በሚነገርበት በማህበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ እንደ ዜናም አለመነገሩ ማህበሩ ወደልቡ እንደተመለሰና ድርሻውን እንዳወቀ የተረዳሁበት ነው። ያውም ውግዘቱም ከተነሳ በኃላ መሆኑ ደግሞ እጅግ አስደንቆኛል። ይህም ይበል የሚያሰኝ ነው በሳጥኑ ውስጥ ሁኖ የሚሰራ ብዙ ድርሻ አለና።(አይ አመስግኘ ሳልጨርስ የአርባ ቀን መታሰቢ የሚሆን ዜና ተለጥፎ አይቻለሁ ግን የጻፍኩትን አልሰርዝም።)
ከሳጥኑ ውስጥ ወጥተን ለማገልገል እንችላለን ዝም አንልም እውነትን በቁመቷና በወርዷ ልክ እንሰፍራታለን ለምትሉ ግን የሃገር ጉዳዩን ትተን በቤተ ክህነቱ ፖለቲካ ዙሪያ ብቻ ብዙ ልንገዳደራችሁ የምንችልበት ነጥብ ይኖራልና አቤት ወዴት ማለትን ይጠይቃል። ከዚ በፊት ግን አንድ ነገር ላጫውታችሁ በአለፈው ጦርነት የቅርቡን ትውስታችን ማለቴ ነው ወታደር በየአካባቢው ሲመለመል በአንድ ወረዳ በስብሰባ ነበር። መልማዮቹም የአካባቢውን የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች ለስብሰባ ከጠሩ በኋላ አንዳንዶቹን በስም በመጥቀስ ፈቃደኝነታቸውን ይጠይቋቸዋል ፈቃደኛ ያልሆነ ሰው ፈሪ ነው ከሚል መልክት ጋር። በአካባቢው ሰዎች ዘንድ ፈሪ መባል ነውር በመሆኑ ብዙዎቹ ከፉከራና ቀረርቶ ጋር ጥያቄውን በደስታ ተቀበሉት አንዱ ግን ገና ስሙ ሲጠራ “እኔን በፈሪ ያዘኝ” በማለቱ እኔን በፈሪ ያዘኝ አለ እገሌ እየተባለ እስከ አሁን ይተረታል።
እኔም በዲን. ዳንኤልና በሌሎች መምህራን ያለኝ ቅሬታ መደፈር በሚችሉ ላይ አብዝተን ስንጮህና ለመደፈር በሚከብዱት ላይ ምላሳችን በማጠሩ ሚዛኑን አስተካክለን ሳንይዘው የቀረን ስለመሰለኝ ነው። ካልቻልን ግን ፈጽሞ ሚዛኑን ባለማንሳት በስብከተ ወንጌሉ ላይ ብቻ ብንሰማራ እኔን በፈሪ ያዘኝ ያለው ሰው ካመለጠው ነገር ለማምለጥ ማንንም ሳንነካ ይቻለናል።

ደጀ ሰላም፦ በተለይም በአሜሪካ ባለው የቤተ ክርስቲያን መከፋፈል ውስጥወጣቶችን አክራሪ አድርጓቸዋልትባላለህ።
አንዳንዶች «አባቶች የሚሉትን ስሙ» ይላሉ፡፡ ንግግሩ በራሱ ስሕተት የለውም፡፡ ግን አባቶች እነማን ናቸው? አባቶች የሌሏት ሲኖዶስ እና ሲኖዶስ የሌላቸው አባቶች ሊኖሩ አይችሉም፡፡ እስቲ በቀላሉ ያለንበትን አገር እንይ፡፡ አንድ ሴናተር ብቻውን በሴኔት ሳይሰበሰብ፣ ራሱን ከሴኔቱ ለይቶ፣ ቤቱ ቁጭ ብሎ ሴናተር ሊሆን ይችላል እንዴ? አንድ ሊቀ ጳጳስ ራሱን ከሲኖዶስ ለይቶ ጳጳስ ነኝ ማለት አይችልም፡፡ የሾማቸውን ሲኖዶስ እየናቁ እኛን አክብሩን ቢባል አያስኬድም፡፡ የሾማቸውን ሲኖዶስ ሕግ እየጣሱ የኛን ሕግ አክብሩ ቢባል አይሆንም፡፡ ልጅ እንድንሆናቸው አባቶች ይሁኑ፡፡ የቀድሞ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እንኳን ዚምባቡዌ ገብተው አርፈው ተቀመጡ እንጂ ስደተኛ መንግሥት መሠረትኩ አላሉም፡፡

አስተያየትይህም በጣም አከራካሪ አባባል ነው አባቶች የሌላት ሲኖዶስ ሊኖር አይችልም የሚለውን በደንብ ብረዳውም ሲኖዶስ የሌላቸው አባቶች ሊኖሩ አይችሉም ካልን ግን አባቶች አይደሉም ካላልን በቀር ወይም አለመሆናቸውን በመረጃ ካላሳየን በቀር ሁለትም ከዚያም በላይ የሆኑ አባቶች የግድ ሲኖዶስ ሳይኖራቸው እንዳይቀመጡ አባባሉ ይደግፋልና። ስለዚህ እነዚህ አባቶች ስደተኛ ከሚለው ቅጥል ውጭ ሲኖዶስ መመስረታቸው አግባብነት ሊኖረው ነው። አለበለዚያ ይህ ሲኖዶስ መቀመጫው አዲስ አበባ ላይ ብቻ መሆን እንዲገባው በደንብ አብራርተን ማስረዳት ሊጠበቅብን ነው። አባቶች ሁሉ አባቶች አይደሉም በሚል ከቀጠልን ግን ሲኖዶስ ሁሉ ሲኖዶስ አይደለም ለሚሉን መልስ እንዳያጥረን እሰጋለሁ። ይልቁንም ሲኖዶስ ለምን ከሚለው ተነስተን የተሻለ መልስ መስጠት የምንችል ይመስለኛል። የቀድሞ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም ከሚኒስተሮቻቸው መካከል ዚምባቡዌ ላይ ቢያገኙና መሪያችን የሚላቸው ይህን ያህል ሰው ቢያገኙ ስደተኛ መንግሥት ላለመመስረታቸው በጣም እጠራጠራለሁ።

ደጀ ሰላም፦ ወደጥያቄያችን ስንመለስ አንተ ሰባኬ ወንጌል እንደሆንክ ይታወቃል። አሁን ደግሞ በየጋዜጣው ላይ ስለ ፖለቲካ ትጽፋለህ፣ፖለቲከኛ ሆነኻልትባላለህ።
«በየጋዜጣው ስለ ፖለቲካ ትጽፋለህ» ያላችሁትን በተመለከተ ግን ከመሠረቱ ማብራራት እፈልጋለሁ፡፡ መሆኑ ፖለቲካ ምንድን ነው? አፍሪካ ውስጥ ይህ ቃል ሌላ ትርጉም አለው፡፡ ፖለቲካ ዓለምን የምታይበት መነጽር ነው፡፡ ፖለቲካ ብዙ መልክ አለው፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ (partisian politics) አለ። ፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ገብተህ፣ ፖለቲካን የመታገያ መንገድ አድርገህ መሥራት ነው፡፡ እኔ እዚህ ውስጥ የለሁበትም፡፡ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ (politcal thinking) አለ፡፡ የፖለቲካ ዕውቀት፣ ነገሮችን፣ ፖለቲካውን መረዳት እና መተንተን ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የሚሆን ሰው የለም፡፡ እያንዳንዱ ሰው ዓለምን የሚያይበት መነጽር አለው፡፡ ነገሮችን በዚያ ነው የሚተነትነው፡፡ እኔም ሰው እንደ መሆኔ ዓለምን የማይበት መነጽር አለኝ፡፡ ይህ ግን ፖለቲከኛነት አይደለም፡፡ ስለ ሃይማኖት ያወቀ ሁሉ ሃይማኖተኛ አይባልም። ስለ ግብርና ያወቀ ሁሉ ገበሬ አይደለም፡፡ በኮምፒውተር የሚጠቀም ሁሉ የኮምፒውተር ኤክስፐርት አይደለም፡፡ እንደዚሁም ስለ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ያወቀ እና ያነሣ ሁሉ ፖለቲከኛ አይባልም፡፡ ሌላ በኩል ደግሞ መንፈሳዊ ከሚባሉ ጋዜጦች ውጭ መጻፍ ኃጢአት ነው ብሎ ማሰብም በራሱ ኃጢአት ነው፡፡ ምንድን ነው የምትጽፈው? ነው ጉዳዩ፡፡ ምነው የኢትዮጵያ ፕሬስ ጀማሪዎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ሰዎች መሆናቸው ተረሳ እንዴ? «ኤዲቶርያል» የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ርእሰ ዐንቀጽ ብለው ስም ያወጡለት እነ አፈ ሊቅ አክሊሉ መሆናቸው ተረሳ እንዴ? እኔ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሀገሬን፣ ባህሌን፣ ታሪኬን እና አመለካከቴን የሚያንጸባርቁ ጽሑፎች በአንዳንድ የግል እና የመንግሥት ፕሬሶች አወጣለሁ፡፡ አሁን ከኅትመት ውጭ በሆነችውአዲስ ነገርጋዜጣ ቋሚ ዐምደኛ ሆኜ በተከታታይ ጽፌያለሁ፡፡ ዋሽንግተን፣ ሲያትል እና አትላንታ የሚታተሙ የኢትዮጵያውያን ኅትመቶች ጽሑፎቹን በድጋሚ ያወጧቸው ነበር፡፡ ስለዚህም እዚህ አሜሪካም ብዙ ሰው ሊያነባቸው ችሏል፡፡ ሮዝመጽሔትም በመጠኑ እጽፍ ነበር፡፡ በእነዚህ ጽሑፎች የእኔ ትኩረት ማኅበራዊ ሂስ “social critique” ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ራሱን እንዲያይ ያደርጋሉ ያልኳቸውን ጽሑፎች አወጣለሁ፡፡ አንዳንዶችወደ ዓላማ ዊነት ገባህ ወይ?” ብለውኛል፡፡ ለመሆኑ ዓለማዊነት ምንድን ነው? በቴሌቭዥን፣ በሬዲዮ፣ በዌብ ሳይት አገራዊ ጉዳዮችን የሚሠሩ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ ዓለማውያን ናቸው ማለት ነው?

አስተያየት፡ በዚህ ላይ ከነሙሉ ማብራሪያው ጥሞኛል። በርታ ጥሩ ነገር ነው። እንዲህ ያለውን ማኅበራዊ ሂስ ከመንፈሳዊነት ጋር በማያያዝ ቤተ ክርስቲያንን የፍርሃታችን መደበቂያ ላደረግን ሰዎች አርአያነቱ ትልቅ ነው።

ደጀ ሰላም፦ ቤተ ክርስቲያን ያላወገዘችውን ቀድመህ ታወግዛለህ ስለሚባለውስ?
/ ዳንኤል፦ ወይ በአንድ ፊቱ ውግዘት ምንድን ነው ብለን እንነጋገር እንጂ ጎበዝ፡፡ ሃሳብ መስጠት፣ የተሳሳተ አስተምህሮን መቃወም ሁሉ ውግዘት መሆን የጀመረው መቼ ነው? ቤተ ክርስቲያን አርዮስን ስታወግዝ የአርዮስን ትምህርትም አውግዛለች፡፡ ስለዚሀም በአርዮስ መንገድ የመጣ ሁሉ «የውሾን ነገር ያነሣ ውሾ» ነው፡፡ ያለበለዚያማ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ መዓት ትራክት ተሸክመው በየቤታችን የሚያንኳኩትን የጅሆቫ ተከታዮች ቅዱስ ሲኖዶስ በየራሳችሁ አላወገዛችሁም እያልን ዝም ልንላቸው ነው? ቅዱስ ሲኖዶስኮ ሥራ አልፈታም በየሥርቻው እየተነሣ የሚዘባርቀውን ሁሉ ሲያወግዝ የሚውል፡፡ «ሰዎች የሚያሳዝኑኝ መሳደባቸው ሳይሆን ደረጃዬን የጠበቀ ስድብ ሰድበውኝ አለማወቃቸው ነው» ብሏል ባለቅኔው ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዕብዱን ሁሉ መናፍቅ እያልን ባናከብረው ጥሩ ነው፡፡ ክብሪት በነደደ ቁጥር እሳት አደጋ መከላከያ አይጠራም፡፡ እፍ ማለት ይበቃዋል፡፡ከዚህ ውጭ ግን ከቤተ ክርስቲያን ሕግ እና ቀኖና፣ ከአባቶቻችን አስተምህሮ የተለየውን ሁሉ ትክክል አይደለም፤ ከዚህ እና ከዚያ ነባር አስተምህሮ ጋር ይጣረሳል ማለት ማውገዝ ሆኖ ከተቆጠረ የተርጓሚው ስሕተት ነው፡፡ አርዮስን ሊቃውንት የተቃወሙት ኑፋቄውን እንደጀመረ ነው፡፡ የተወገዘው ግን ምናልባትም ከዐሥር ዓመታት በኋላ ነው፡፡ ስለዚሀም ኑፋቄ የሚከሰትበትና የሚወገዝበት ጊዜ ሊለያይ ይችላል፡፡ ተገንጥለን ሲኖዶስ መሠረትን ያሉት ሰዎች የተወገዙትኮ ከስንት ክርክር በኋላ ነው፡፡

አስተያየት፡ ይህም በመሰረታዊ ሃሳቡ የሚደገፍ ነው ነገር ግን በችኮላ አይሁን እንደ “ለመናፍቁ ስልጣነ ክህነት የሰጠ እራሱ………ነው” አይነትና “ይሁዳ የቀረውን እዳ ለማወራረድ…………..።” እስኪ ማን ነው የአባቶችን መደብደብ በግልጽና በግል በስብከተ ወንጌሉ በጉባኤ ላይ ያስተማረ? በVOA እንጅ እስከ አሁን ከእናንተ የሰማ ነው ነገር የለም ግን አልፈርድም አልጠብቅምም ይች የማይደፈረው ተደፈረ አይደለችምና። እንግዲያውስ ለበጎ እንኳ ዝም አልኩ ይለናል ቅዱስ ዳዊት።ነገራችን ሁሉ ያለማዳላት ይሁን።
እግዚአብሔር አግልግሎታችሁን ይባርክ።

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)