March 26, 2010

አለቃ አያሌው ታምሩ እና ትምህርታቸው፦ ለትውስታ


(ደጀ ሰላም፤ ማርች 26/2010)፦ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ዘመናት እንደ ሰማይ ኮከብ፣ እንደ ምድር አሸዋ የሚበዙ ሊቃውንት አፍርታለች። ከነዚህ ሊቃውንት መካከል ደግሞ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አለቃ አያሌው ታምሩ አንዱ ናቸው። ስለ ሕይወት ታሪካቸው፣ ሥራዎቻቸውና ተያያዥ ጉዳዮች በስማቸው የተሰየመውን ድረ ገጽ እንድትመለከቱ እየጋበዝን ስለ ትምህርታቸው የሚናገረውን ክፍል ቀንጭበን ለማቅረብ ወደድን።
ምናልባት “የሥነ መለኮት ሊቅ”፣ የቤተ ክርስቲያን መምህር፣ መጋቤ ብሉይ፣ መጋቤ ሐዲስነት እንዴት እንደነበር ለመረዳት ይጠቅመን ይሆናል። ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን
“… ታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ በተወለዱበት አካባቢ ባሳለፉአቸው ዓመታት የቀሰሙአቸው ዋና ዋና የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶችና ያስተማሩአቸው መምህራን እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል።
ሀ፤ መሪጌታ ከበበው፣ መሪጌታ እውነቴ፣ መሪጌታ ክንፉና መሪጌታ አልማው ከተባሉት መምህራን ጸዋትወ ዜማን ከጣዕመ ዝማሬው ጋር፤
ለ፤ አለቃ ማርቆስ፣ መሪጌታ ወልደ ኪዳን፣ መሪጌታ ያሬድ ከተባሉት መምህራን የግእዝን ቋንቋ ከጠቅላላ ሙያው ጋር፤
ሐ፤ አባ አካሉ፣ መምህር እጅጉ (ዘወልደ ማርያም) ከተባሉት መምህራን የሐዲሳትን ጣዕመ ትርጓሜ፤ ከብሉያት አራቱን ብሔረ ነገሥት፤ ትርጓሜ ዳዊት ከነቢያትና ከሰሎሞን ጋራ፤ የውዳሴ ማርያምና የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ።
ከላይ የተጠቀሱት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፤ ከዚህ ያልተጠቀሱትንም ሌሎች ትምህርቶች ሰንቀው ሰፊ አገልግሎት ወደሚሰጡበት ወደ አዲስ አበባ ከተማ በ፲፱፻፴፱ ዓመተ ምሕረት አጎታቸውን ታላቁን ሊቅ ክቡር መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬን ተከትለው መጡ።
ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ ከዕውቀት ወደ ዕውቀት እያደጉ ከመሄዳቸውም በላይ ያወቅሁት ይበቃኛል ሳይሉ፤ ወደ አዲስ አበባም ከመጡ በኋላ፤
ሀ፤ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ መልካም ፈቃድ በጊዜው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት ከስመ ጥሩው መምህር ፊላታዎስ መጽሐፈ ኢሳይያስን፣ መጽሐፈ ዐሠርቱ ወክልኤቱ ደቂቀ ነቢያትን፣ መጽሐፈ አስቴርን፣ መጽሐፈ ዮዲትንና መጽሐፈ ጦቢትን ከነ ሙሉ ትርጓሜአቸው፤
ለ፤ በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ትምህርት ቤት ከመጋቤ ምስጢር ጌራ ስምንቱን ብሔረ ኦሪትና መጽሐፈ ዳንኤልን ከነ ትርጓሜአቸው፤
ሐ፤ ከመምህር ጽጌ (ኋላ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ዘጎጃም) የአርባዕቱን ወንጌል ትርጓሜ፤
መ፤ ከመምህር ገብረ ማርያም መጽሐፈ ኪዳንንና ትምህርተ ኅቡዓትን ተምረዋል።
አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ የቅድስት ተዋሕዶ ሃይማኖታቸውን ዕውቀት ካደላደሉ በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በሌሎች አብያተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ፤ እንዲሁም ባለ ማወቅ የተሳሳቱትን ለመመለስ፤ የእምነታቸውን መሠረትና የእንግሊዝኛ ቋንቋ፣ እንዲሁም ለዐይነ ሥዉራን የተዘጋጀውን የብሬል ጽሑፍ ለመማር ወደ እንጦጦ ወንጌላዊት ሚስዮን ትምህርት ቤት ገቡ። በዚያም የፈለጉትን ያህል መቀጠል ባይችሉም የብሬል ጽሑፍና መጠነኛ የሆነ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተምረው ወጥተዋል።
ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ ስለ ትምህርታቸው በአጠቃላይ፤ «የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት፤» በተባለው መጽሐፋቸው ገጽ ፲፭ ላይ የገለጹትን እንጠቅሳለን። «ትምህርቴ እንደ መምህሮቼና እንደ ትምህርት ቤቶቹም ብዛት ሙሉ አይደለም። ዕውቀቴም አነስተኛ ነው። ይህንኑ ከመምህራኑ ከሞላ ጎደል የሰማሁትን የትምህርት ጣዕም በጥቂቱ እንዳውቀውና እንዳስተውለኝ ያደረገኝ፤ ምሬቱንም ያጠነከረብኝ ዐዲሱ ዘመን ብዙ የትምህርት ዐይነቶችን ስላስገኘና በወንጌላዊት ሚሲዮን ትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና በሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ልዩነት በደንብ ለማጥናት ስላገዘኝ፤ ከዚያ ወዲህ ራሴን መቆጣጠር ስጀምር ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በሎንዶን ያሳተሙትን መጽሐፍ ቅዱስ በቤተ መጻሕፍት ወመዘክር አዘውትሬ መመልከቴ፣ ከመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬና ከመምህር ይኄይስ ወርቄ ጋር በጥብቅ መነጋገሬ ነው። ሆኖም ዕውቀቴ በዚህ ሁሉ ፍጹም ሊሆን አልቻለም። ግን ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፤ ስለ ቀናችው ሃይማኖቷና ስለ ተቀደሰው ምግባሯ፤ በእግዚአብሔርና በሷ መካከልም ስላለው ጥሩ ፍቅር በሕሊናዬ የሚወጣው የሚወርደው ሐሳብ እንደ እሳት ያቃጥለኛል። ቆሜ ተቀምጨ፣ ተኝቼ ተነሥቼ በምሄድበትና በማርፍበት፣ በምበላበትና በምጠጣበት ጊዜ ሁሉ ትሩር አድርጌ የምመለከተው እሱን ብቻ ነው። በዚህ ምክንያት በመኝታዬ ጊዜ እንኳ የጤና ዕንቅልፍ አጥቼ ሕልም ይሆንብኝና፤ «ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር፤» «አሐዱ ነገሩ ለኲሉ ዓለም፤» ያመጽኡ እምሳባ ወርቀ ወስኂነ፤» «ቃል ወልድ እኁየ ናሁ ውእቱ መጽአ፤» «ንግሥተ አዜብ ትትነሣእ አመ ዕለተ ደይን፤» «ናሁ መሰግላን መጽኡ እምብሔረ ጽባሕ፤» «ሁር ትልዎ ለዝንቱ ሠረገላ፤» «ቃል ሥጋ ኮነ፤» «ተሣሃለነ በሞተ ወልዱ፤» ስለሚሉትና እነሱንም ስለ መሳሰሉት ቃላት ሙሴን፣ ዳዊትን፣ ኢሳይያስን፣ ንግሥተ ሳባን፣ ማቴዎስን፣ ዮሐንስን፣ ሉቃስን፣ ፊልጶስንና ጳውሎስን ስጠይቅ አድራለሁ። ይሁን እንጂ፤ «ጥበብን የሚሻ ሰው ቢኖር ሳያወላውል ሳይጠራጠር ከእግዚአብሔር ይለምን፤ እግዚአብሔርም ንፍገት የሌለው አምላክ ነውና ይሰጠዋል፤» (ያዕ፤ ፩፣ ፭።) ብሎ ሐዋርያው ያዕቆብ እንደ ተናገረው፤ እግዚአብሔር አምላኬ የለመንኩትን ስላልነሣኝ፤ በዕውቀቴ ሳይሆን በቸርነቱ እየተረዳሁ ይህን መጽሐፍ ሳዘጋጅ ምስጋናዬን ለሱ አስቀድማለሁ፤» በማለት ገልጸዋል። . . .”

7 comments:

Anonymous said...

We just lost a great father and respectful person in Ethiopia. It is a sad day for any Ethiopian Orthodox Tewahedo Church families. Especially in This highly and critical period of Ethiopia when all kind of Religion the so called born again Christians are running around with a false and misleading statements.

May the Father of Abraham, Jacob and Isak be
with the People of Ethiopia, Israel and America.

Anonymous said...

ያለቃን ነፍስ ይማር? ምንም እንኳን በማህበረ ቅዱሳን በሽምግልናቸው ጊዜ ሊያስታቸው ቢጥርም በእግዚአብሔር ጥሪ እና ቤተሰባቸው ጸሎት ከውሾች አናደበት ተርፈዋል። አንደበተ ርቱዕ ሊቅ ነበሩ። መጽሀፎቻቸውንም እወዳቸዋለሁ።
ሳለ እግዜር

Anonymous said...

ያለቃን ነፍስ ይማር? ምንም እንኳን በማህበረ ቅዱሳን በሽምግልናቸው ጊዜ ሊያስታቸው ቢጥርም በእግዚአብሔር ጥሪ እና ቤተሰባቸው ጸሎት ከውሾች አናደበት ተርፈዋል። አንደበተ ርቱዕ ሊቅ ነበሩ። መጽሀፎቻቸውንም እወዳቸዋለሁ።
ሳለ እግዜር

ሰይፈ ሚካኤል said...

ይገርማል!
የዛሬዎቹን መጋቤ ሓዲሳት ታዲያ ምን እንበላቸው????
አይገባኝም እስኪሉ እንጠብቅ ይሆን?

Unknown said...

Dear Deje Selam,
Thank you for remembering one of the best EOC fathers Likelikawent Aleka Ayalew Tamiru. You remembered him on the right time. His birthday was Megabit 23 which was Sunday coincided with "Hossena". I very much impressed how he expressed the coincidence in his golden words. Any one interested about this can read what I mentioned about his birthday and "Beale Hossana" on his short biography posted on the web sit open in his name.
Our church lost her indispensable son. Let me add one poem transmitted following his death on VOA
" Errii beye Orthodox chuhi beye ageru:
Ewnet ketefama Ayalew Tamiru"
It would be helpful to us and to our church to ask the help of God to give us a true father like Aleka Ayalew Tamiru.
May the Almighty God bless Ethiopia!

Anonymous said...

Dear Deje Selam,
Thank you for remembering one of the best EOC fathers Likelikawent Aleka Ayalew Tamiru. You remembered him on the right time. His birthday was Megabit 23 which was Sunday coincided with "Hossena". I very much impressed how he expressed the coincidence in his golden words. Any one interested about this can read what I mentioned about his birthday and "Beale Hossana" on his short biography posted on the web sit open in his name.
Our church lost her indispensable son. Let me add one poem transmitted following his death on VOA
" Errii beye Orthodox chuhi beye ageru:
Ewnet ketefama Ayalew Tamiru"
It would be helpful to us and to our church to ask the help of God to give us a true father like Aleka Ayalew Tamiru.
May the Almighty God bless Ethiopia!

Anonymous said...

Dear Dejeselam,
We really apprciate what you are doing specialy remembering our great EOTC son Aleka Ayalew. Even though he is away from us phisicaly I believe he is always with us and EOTC in spirit. And I hope there will be millions of Aleka Ayalew will raise soon.
May his soul rest in peace always.
God bless us all.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)