March 22, 2010

ቤተ ክርስቲያን ኤድስን ለመከላከል የሚያስችሉ መጻሕፍትን ይፋ አደረገች


(ሔኖክ ያሬድ/Reporter):- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኤድስ የተባለውን መድኀኒት የለሽ በሽታ፣ ሁሉም ሰው አስከፊነቱን አውቆና ተረድቶ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ወገኖቹን መርዳት እንዲችል የሚያደርጉ ሁለት መጻሕፍትን መጋቢት 7 ቀን 2002 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሒልተን አስመረቀች፡፡


ከተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ እና ከፖፑሌሽን ካውንስል ጋር በመተባበር በሁለት ቅጽ የታተሙት መጻሕፍት፣ "የልማት ወንጌል (Developmental Bible) የሚባሉ ሲሆን፣ ከመስከረም አንድ እስከ ጳጉሜን አምስት እና በ52 ሳምንታት ባሉት በዓላት ዙርያ ያተኮሩ ናቸው፡፡

መጻሕፍቱን ያዘጋጀው የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድዖ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አርጋው ጥሩነህ እንደተናገሩት፣ የመጻሕፍቱ መውጣት ቤተ ክርስቲያኒቱ እስካሁን እየሰጠችው ካለው መንፈሳዊ ጠቀሜታ ባሻገር፣ ማኅበራዊ ችግሮችን የሚፈታና ስለ ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ሌሎች ጤና ነክ ጉዳዮችን እንዲዳስስ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል፡፡

ኮሚሽነሩ አያይዘውም፣ ማንኛውም ካህን በፈለገው ዕለት ከኤድስና ከሌሎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማንሳት ልስበክ ቢል መነሻ ሐሳብ በማፈላለግ እንዳይደክም ይረዳል ብለዋል፡፡

የመንግሥታቱ ማኅበር የሥነ ሕዝብ ፈንድ የአፍሪካ ዳይሬክተር ሚስተር ቡንሚ ማኪንዋ ባደረጉት ንግግር፣ ከሕዝቡ 70 ከመቶ ያህሉ ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ተቋማት ጋር ትስስር ስላለው፣ ኅብረተሰቡን ከኤች አይ ቪ ኤድስ ለመጠበቅ የሚያስፈልገው ትምህርታዊ መግለጫ ለማድረስ አመቺ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቷ ከሺሕ ዓመታት በላይ ዕለት ተዕለት ለማስተማርያነት ከምትጠቀምበት መጽሐፈ ግጻዌ ጋር ኤች አይ ቪ ኤድስን፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት ትምህርታዊ መግለጫዎች መካተታቸው ውጤታማ ያደርጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ አማካይነት ሚሊዮኖችን በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ መድረስ ያስችላል ብለዋል፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሰው ዘር አጥፊ የሆነው በሽታ፣ ከተከሰተበትና ዜናውም ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ፣ ባሉት የትምህርት አውታሮችና የአሠራር መዋቅሮች ሁሉ የማስተማር ጥረቷን ቀጥላለች፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ አያይዘውም፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ኤድስ ያስከተለውን ማኅበራዊ ቀውስ ለመቋቋም የሚያስችለውን አቅጣጫ የቀየሰበትን ማስተማርያ መጽሐፍ (ማኑዋል) ቤተ ክርስቲያኒቱ በ1973 ዓ.ም. አስተርጉማ ለሕዝብ ማሰራጨቷን አስታውሰዋል፡፡

መጻሕፍቱን የመረቁት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትና የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡

የቅዱስ ፓትርያርኩ መልእክት እንደሚለው፣ ቤተ ክርስቲያኗ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል መሠረት በማድረግ ይህን ግዙፍ የትምህርት መጽሐፍ ለማዘጋጀት የተነሳሳችውም፣ የዘመኑ ትውልድ ሊያደርገው ከሚገባው ጥንቃቄ ጉድለት የተነሣ፣ በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጅ ሕይወት ፀር ለሆነው የኤድስ ቫይረስ በመጋለጡ ሲሆን፤ ይህንኑ ክስተት ዝም ብሎ መመልከት ከቤተ ክርስቲያን የማይጠበቅ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡

የኤድስ ቫይረስ፣ በተለይ የሰውን ዘር ለይቶ የሚያጠቃ አደገኛ ወረርሽኝ መሆኑ በተግባር እየታየ ነው፡፡ ሆኖም መተላለፊያውም ሆነ መከላከያው ግልጽ ስለሆነ ራስን ከዚህ ቫይረስ አደጋ ለመከላከል ያለው ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ይህም በዚህ መጽሐፍ በሰፊው ተገልጧል፡፡ ቫይረሱ በአብዛኛው ከአንዱ ወደ አንዱ የሚተላለፈው ከጋብቻ ውጭ በሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ ማለትም በግብረ ዝሙት ስለሆነ የሚያስከትለውም መንፈሳዊ ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡

ከዚህም ጋር በኤድስ ሕሙማን ላይ የሚፈጸመው አድልዎና ማግለል ኢ- ክርስቲያናዊም፣ ኢ - ሰብዓዊም ስለሆነ ድርጊቱ የሃይማኖትን ሕግ ሳይቀር እየተፈታተነ ነው፡፡ ሕሙማንን ማግለል በክርስትና እምነት ክርስቶስን እንደማግለል የሚቆጠር ድርጊት ስለሆነ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዚህ መስክ እስካሁን ስታበረክታቸው የቆየችውን አገልግሎት በበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠል፣ በዓይነቱ የመጀመርያ የሆነውን ይህን የትምህርት መጽሐፍ ባሁኑ ጊዜ አዘጋጅታ ለሕትመት ማብቃቷን የገለጹት ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ "መጽሐፉን ልዩ የሚያደርገው ፣መጽሐፈ ግጻዌ፣ በመባል በሚታወቀው የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ተቀነባብሮ የሚገኘውን የሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀናት (የዓመት) የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብን፣ መሠረት በማድረግ የተዘጋጀና የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ትምህርትና ስብከትን የያዘ በመሆኑ ነው" ብለዋል፡፡ መጽሐፉ የተዘጋጀው ከከተማ እስከ ገጠር ለእያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በማዳረስ ከሞላ ጎደል በመካሄድ ላይ ያለውን የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ትምህርት ስርጭት ለሁሉም ኅብረተሰብ እኩል ለማዳረስ ታስቦ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡

የየአጥቢያው አብያተ ክርስቲያናት ካህናትና ምድብ ሰባክያንም፣ በዚህ የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ትምህርት መድበል በሆነ መጽሐፍ፣ ኅብረተሰቡ ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ከሚያጋልጥ ድርጊት በመጠንቀቅ ራሱን እንዲጠብቅ፣ ኅብረተሰቡም ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ወገኖችን ማግለልና አድልዎ እንዳይፈጽም በርትቶ በማስተማር ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን የመንጋ ጥበቃ ተግባር በኀላፊነትና በታማኝነት እንዲወጡ ከአደራ ጋር ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

አንደኛው ቅጽ፣ በ13ቱ ወሮች በ365 ቀኖች የሚተላለፉ መልዕክቶች የያዘ ሲሆን፣ ሁለተኛው ቅጽ በዓመት ውስጥ በሚኖሩት 52 እሑዶችና ፋሲካን መሰል ተዘዋዋሪ በዓሎች በሚውሉበት ዕለት ምክር የሚሰጡ ኃይለ ቃላት ተካትተውበታል፡፡

ለምሳሌ ዛሬ እሑድ መጋቢት 12 ቀን 2002 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን "ዘኒቆዲሞስ" ተብሎ ይታወቃል፡፡ በዕለቱም ሆነ ዕለቱ በየዓመቱ በሚመጣበት ጊዜ የሚከተለው መልእክት ለምዕመናኑ ይተላለፋል፡፡

"ስለዚህ አንዲት ሴት ባልዋ እያለ እርሱን ፈትታ ሌላ ብታገባ፣ ወይም በባልዋ ላይ ከሌላ ወንድ ጋር ብትተኛ፣ አመንዝራ ተብላ የሚፈረድባት ከመሆኑም በላይ፣ ባሏንም በሽታ ታስተላልፍበታለች፡፡ ባሏ ከሞተ በኋላ ግን ሌላ ላግባ ብትል ስለሚፈቀድላት፣ እርሷና እርሱ ከበሽታው ነጻ ለመሆናቸው የጋራ ምርመራ አድርገው፣ ንስሐ ገብተው በጸሎተ ንስሐና በቁርባን ሊጋቡ ይችላሉ፡፡ ይህ ግዴታ በሴቶች ብቻ የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ በወንዶችም ተግባራዊ ሊሆን ይገባል፡፡

በተለይ ባል በሕይወት እያለ፣ ሚስትም በሕይወት እያለች፣ አለመግባባትንና ፍችን ከሚያመጡት ምክንያቶች ሌሎች ቢጠቀሱ፣ አንዱ ያለ ዕድሜ ጋብቻ ነው፡፡ ሁለቱ ተጋቢዎች በአብዛኛው በአካልና በአእምሮ ያልበሰሉ በመሆናቸው፣ ተሳስበው ለመኖር ከፍተኛ ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ትዳራቸው ይፈርስና ይለያያሉ፡፡ ይህም ሁኔታ የሴቶቹን የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በመቀስቀስ፣ በአቅራቢያ ወደሚገኙ ከተሞች ፍልሰትን ያስከትላል፡፡ ሴቶቹም ጥሩ ሥራ ለማግኘት የሚያስችል በቂ ዕውቀት ስለሌላቸው፣ ከቤት ሠራተኝነት ጀምሮ እስከ ሴተኛ አዳሪነት ድረስ ያሉ ማናቸውንም ዓይነት ሥራ ለመሥራት ይገደዳሉ፡፡ ይህም ሁኔታ በራሱ ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እና ለሌሎች የአባለ ዘር በሽታዎች መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም የጋብቻ ቃል ኪዳንን አክብሮ በመተማመን መኖር ከዚህ ሁሉ ችግር ራስን ለመጠበቅ ያስችላል"

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)