March 13, 2010

አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአንድነት ጉባኤያትን ማካሄድ ጀመረ

(Mahibere Kidusan):- የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓትና ደንብ በጠበቀ መልኩ ለምእመናን ሰፊ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ተከታታይና ወጥነት ያለው የአንድነት ጉባኤ ማዘጋጀት መጀመሩን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስታወቀ፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ጠብቀው በየዐውደ ምሕረቱ የሚቀርቡትን ስብከቶች በካሴት ቀርፆ ለምእመናን በነጻ የማዳረስ ዕቅድ እንዳለውም ገልጧል፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ እንደገለጡት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሀገረ ስብከቱ ፈቃድና እውቅና ውጪ በአንዳንድ ዐውደ ምሕረት እና አዳራሽ ውስጥ የሚካሄዱ ጉባኤያት የቤተ ክርስቲያንን ደንብና ሥርዓት ያልተከተሉ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለምእመናን ተገቢውን የወንጌል አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ሆነው አልተገኙም፡፡

«ይህንኑ ሁኔታ ለማስተካከል ሀገረ ስብከቱ ጠንክሮ ተነሥቷል» ያሉት ሥራ አስኪያጁ «ሕዝቤ ሆይ ና ወደ ቤትህም ግባ» በሚል መሪ ቃል በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ አንድ መቶ ስልሳ የሚደርሱ አብያት ክርስቲያናትንና ገዳማትን ያካተተ ተከታታይነትና ወጥነት ያለው የአንድነት ጉባኤ በማዘጋጀት ምእመናን ተገቢውን ቃለ እግዚአብሔር በተገቢው መምህርና በተገቢው ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ ጀምሯል ብለዋል፡፡

ይኸው ጉባኤ ካለፈው ጥር ሰባት እስከ ዘጠኝ ቀን በስድስት አብያተ ክርስቲያናት አንድነት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት መጀመሩን የገለጡት ሥራ አስኪያጁ፤ ጉባኤው የተሳካ፤ ምእመናንም የተደሰቱበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ይኸው የአንድነት ጉባኤ በሀገረ ስብከቱ ደቡብ፣ ምሥራቅ፣ ምዕራብና ሰሜን ወረዳዎች ባሉ የተመረጡ አብያተ ክርስቲያናት ዐውደ ምሕረት መቀጠሉን ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰው፤ «በዚህ ሁኔታ በሳምንት አንድ የአንድነት ጉባኤ የማዘጋጀት ዕቅድ ተግባራዊ እየተደረገ ነው» ብለዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጣ፤ ይኸው የአንድነት ጉባኤ መዘጋጀቱ በየደብሩ ያሉ አገልጋዮችን በማቀራረብ በፍቅርና በአንድነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲሁም ምእመናንን ለማገልገል የሚያስችላቸው ከመሆኑም ባሻገር በዐውደ ምሕረት እና ከዐውደ ምሕረት ውጪ በቤተ ክርስቲያን ስም የሚካሄደውን አላስፈላጊ ግላዊ ጥቅም ያስቀራል፡፡

በአንዳንድ ጉባኤያት የመግቢያ ገንዘብ እየተከፈለ በስብከተ ወንጌል ስም «ገቢ ማሰባሰቢያ» በሚል ሰበብ በየአዳራሹ የሚካሄዱ ጉባኤያት አቅም የሌላቸው ምእመናን ስብከተ ወንጌልን በተገቢው መንገድ እንዳያገኙ ማድረጉን የገለጡት ሥራ አስኪያጁ፤ ወደ ፊት ማንኛውም ዓይነት የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ከዐውደ ምሕረት ውጪ መካሄድ እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡ በዐውደ ምሕረት የሚካሄዱ ጉባኤያትም የቤተ ክርስቲያን እውቅና ባላቸው መምህራንና ዘማሪያን የሚከናወኑ ሲሆን አዘጋጆቹ ለሀገረ ስብከቱ ማሳወቅ እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የሚካሄዱ የአንድነት ጉባኤያትን ለማስተዋወቅ የሚለጠፈው ፖስተር የግለሰቦችን ስምና ዝና ሳይሆን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ክብር ለማስቀደም ሲባል የጉባኤውን ቦታ እና ጊዜ ከመግለጥ ውጪ የሰባክያንንና የዘማሪያንን ስም እና ፎቶ ግራፎች አይገልጥም፡፡

ሁሉም የአንድነት ጉባኤያት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በፊት መጠናቀቅ እንደሚኖርባቸውም ሥራ አስኪያጁ ገልጠዋል፡፡ ለዚህ የአንድነት ጉባኤ መጠናከር ሀገረ ስብከቱ መምህራንን የመመደብ ሓላፊነቱን ለመወጣት በቂ ዝግጅት ያደረገ ሲሆን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት ጠብቀው በየዐውደ ምሕረቱ የሚደረጉ ስብከቶችን ቀርፆ ለምእመናን በነጻ ለማድረስም በርትቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

«ሕዝባችንን በወንጌል ትምህርት ለማነፅ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ድምፅ ለማሰማትም የሚቻለው በዐውደ ምሕረት በምንሰጠው አገልግሎት ነው» ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ይህ ጥረት የተሳካ እንዲሆን የተጀመረው የአንድነት ጉባኤ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ለጉባኤው ስኬታማነት የየአድባራቱ አስተዳደር፣ ሰበካ ጉባኤ፣ ሰንበት ት/ቤቶች፣ ምእመናንና ሌሎችም የቤተ ክርስቲያኒቱ ወዳጆች እንዲሁም አገልጋዮች በአንድ መንፈስ እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን ሰባክያነ ወንጌል መምህራንና ዘማርያንም ከሀገረ ስብከቱ ጎን በመቆም ለአገልግሎቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል፡፡

በአንድነት ጉባኤው ዙሪያ ያነጋገርናቸው አንዳንድ በአዲስ አበባ የሚገኙ ምእመናን በሰጡት አስተያየት፤ በከተማይቱ የተለያዩ ደብሮች ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች ወጥነት ስለሌላችው የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ በአግባቡ ለመረዳት ያዳግት እንደነበረ ጠቅሰው፤ የአንድነት ጉባኤው ብዙ ችግሮችን ይቀርፉል የሚል እምነት እንደሚያሳድር ተናግረዋል፡፡

«ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት፣ ፈቃድና እውቅና ውጪ በሌሎች አዳራሾች የሚካኼድ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያን ያልተለመደ፣ እምነትና ሥርዓትን የሚሸራርፍ፣ የዐውደ ምሕረትንም ክብር የሚያሳጣ አላስፈላጊ ተግባር ነው» ያለው ወጣት ያሬድ ተሰማ ይህ ዓይነት ስሕተት እንዳይደገም ቤተ ክርስቲያኒቱ ቁርጥ አቋም ሊኖራት ይገባል ብሏል፡፡
(በደረጀ ትዕዛዙና በመንግስተአብ አበጋዝ)

2 comments:

Amehe Giyorgis said...

Egziabhair yetebalewin hulu Yakenawin

Anonymous said...

It is a good start. But, the church should have to think on financing the 'Gubaye'. The orther thing that should be considered is "assigning preachers & spritual singers" it needs a great attentin, follow up & controling system.'Hegre Sibket' has to put a great effort on it.

May God bless Ethiopia, Amen.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)