February 16, 2010

“የት ይቀብሩ ይሆን?” - “ቤተ ክርስቲያን አሁን አንድ ትሆን ይሆን?” - ምኞት ወይስ ተስፋ?


(ከ-ዘክርስቶስ)
ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ አረፉ። በጣም አዘንኩ። በተለይ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት እውን ሆኖ ሳያዩ ወይም እውን እንዲሆን ሳያደርጉ …ብቻ እንዲሁ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት እንደተከፈለች ማረፋቸው ሐዘኔን እጥፍ ድርብ አደረገው። ከዛ ተረጋግቼ ሳስብ ደግሞ የት ይሆን የሚቀበሩት የሚለው ማሰብ ጀመርኩ።
ይህን ጥያቄ ማንሳቴ ራሱ አናደደኝ። ለምን ማንም የፓለቲካ ችግር ያለበት ሰው እንኳን በሕይወት ዘመኑ ወደ አገር ቤት መሄድ ባይችል ቢያንስ ሲያርፍ ኢትዮጵያ ሄዶ ይቀበር ይሆን ወይ የሚለው ጥያቄ እንደ ጥያቄ ራሱ አይነሳም። የብፁዕ አባታችን በምንም ዓይነት መለኪያ የፓለቲካ ችግር ካለበት ወይም ከነበረበት ሰው ጋር አይወዳደርም አይነጻጸርም። ግን ምን ላድርግ የሃይማኖት አባቶች ከፓለቲከኞች የባሰ ልብና አእምሮ በያዙበት ዘመን አፍን ሞልቶ ይህ ይሆናል ማለት አለመቻሌ ያው የጋራ ችግራችን አስከፊነት ምልክት ነው።

ችግሩን ያባባሰውና የት እንደሚቀበሩ ጥያቄ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ “አገር ቤት ያሉት አባቶች እንዴት ነው የሚያዩት?” የሚለው በአንድ ወገን “ከዛም ውጪ ያሉት አባቶችስ ምን ይሆን የሚወስኑት?” የሚለው በሌላ በኩል እየተጨነቅን እያለ አገር ቤት ያሉት አባቶች የነበረው ውግዘት አንስቶ የአባታችን ቀብርም በኢትዮጵያ እንዲሆን መወሰኑን ሰማን። በጣም ደስ አለኝ። አዲስ ተስፋ ታየን ወይም አማረን። እኝህ አባት ተወዳጅ ሰለነበሩ “ምናልባት በሕይወታቸው ሲመኙት የነበረውን አንድነት ዕረፍታቸው ምክንያት ሆኖ ቤተ ክርስቲያን አንድ ትሆን ይሆን?” የሚለው ተስፋዬ ለመለመ - እንደሌላው ሰው ሁሉ ማለት ነው።
የእሳቸው ተዋድጅነትና ወቅቱ “የትና እንዴት ይቀበሩ?” ይሆን የሚለው “አሁን ቤተ ክርስቲያን አንድ ትሆን ይሆን?” ከሚለው ጋር ተያያዘ። እናም “ውጭ ያሉት አባቶች ምን ይሉ ይሆን?” እያልን ምንስ ማድረግ አለብን እያልን መጨነቅ ያዝን። ከዛም ውጭ ባሉት አባቶች የአባታችንን ዕረፍት በተመለከተ የወጣ መርሐ ግብር ላይ “ወደ ተዘጋጀላቸው ማረፊያ” ይሄዳሉ የሚል አነበብን። መርሐ ግብሩ የቀብር ሥነ ሥርዓት አይልም። “ወደ ተዘጋጀላቸው ማረፊያ” ማለት ምን ማለትና የት ይሆን ስንል አሰብን። ያው አገር ቤት ካሉት አባቶች ጋር ገና እየተነጋገሩ ስለሆነና ስላልወሰኑ ይሆናል ብዬ አሰብኩ ወይም ማሰብ ፈለግኩ።
በቅርብ የምናውቀው ሰውን ሞት መስማት የሆነ በጎ የማሳሰብ፣ ልብን የማለስለስ ነገር ስለሚያመጣ በዛ ላይ የሃይማኖት አባትነታቸው ተጨምሮ ኧረ እኛም እኮ ነገ እንደዚሁ ነን እና እስቲ ይህን አጋጣሚ ለአንድነት እንጠቀምበት ይላሉ ከሚለው ምኞትና ተስፋ ጋር በዛ ላይ ደግሞ በባህላችንም በሥርአታችንም እንኳን አቡነ ዜና ማርቆስን ለመሰለ ሊቀጳጳስ ቀርቶ ለሌላውም ለቀብር በቦታውና በጊዜ መፈጸም ከምንሰጠው ትኩረት አንጻር ከአሁን አሁን አንድ ጥሩ ነገር እንሰማለን እያልን ጓጓን። እሳቸው አገር ቤት ሊቀበሩ ሲሄዱ ውጭ ያሉት እነ አቡነ መልከጺዴቅ አቡነ ኤልያስ እና ፓትርያርኩ አቡነ መርቆርዮስ አብረው ይሄዱና በዛው መነጋገር ይጀምራሉ የሚል ጉጉት ማለት ነው።
በዚህ ጉጉት ላይ እያለሁ ውሸት እንዲሆን የምመኘው አስደንጋጭ ነገር ውጭ ከሚኖሩት አባቶች አካባቢ ሰማሁ። አሁንም ውሸት እንዲሆን የምመኘው ቢሆንም እውነት እንዳይሆን እነዚህን አባቶች መለመን እንድንችልን የምንጓጓለት ነገር እንዲሳካ ለማድረግ የሰማሁትን ነገር ላስቀምጥ።
ያሰቡት የትም እንዲቀበሩ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ (ለዓመታት) አስከሬን ማስቀመጥ የሚቻልበት ቦታ ለማቆየት ነው(እንደ ማቀዝቀዣ ቢጤ)። ይህንን ስሰማ መርሐ ግብሩ ላይ ለካ “ቀብር” የሚል ቃል ሳይኖር “ወደ ተዘጋጀላቸው ማረፊያ” በሚል የተገለጸው ለዚህ ነው አልኩኝ። እናም እንደገና እጅግ አዘንኩ። ብዙ ጥያቄዎች መጡብኝ ምን ለማለት ተፈልጎ ይሆን? ማንን ለመጥቀም? ማንን ለማስደሰት? ማንን ለመጉዳት? በየትኛው ልማድ መሠረት ተወሰነ? ማን ወሰነው? እጅግ አፋጣኝና ወሳኝ መልስ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች።
እነ አቡነ መልከ ጼዴቅና እነ አቡነ ኤልያስ ለራቸው ይህን ነው የሚመኙት? አይመሰለኝም። ወይም እንዲመኙ አልፈልግም። ታዲያ ምን ነካቸው? የምንመኘው የቤተ ክርስቲያንስ አንድነት እሺ ይቅር ብፁዕ አባታችን በሕይወት ዘመናችን ሳሉ ሲረዷቸው የነበሩት የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት ቢያንስ በክብር መቅበር አለባቸው እኮ። አረፉ ግን አልተቀበሩም? ካረፉ በኋላ ታገቱ ዓይነት አሠራር ምን ማለት ነው? ከላይ እንደተባለው መቼም ቢሆን አገር ቤት መግባት አይችሉም የሚባሉ ፓለቲከኞች ላይ እንኳን መድረስ የሌለበት ብቻ ሳይሆን ደርሶም የማያውቅ ነገር ብፁዕ አባታችን ላይ መድረስ የለበትም።
ውሸት በሆነ የሚለው ምኞቴ እንዳለ ሆኖ ይህንን ነገር ማጣራት እና እንዳይደረግም ማድረግ የሁላችንም ማለትም የቤተ ክርስቲያን አንድነት ይገደናል የምንል ወገኖች ኃላፊነት ነው፤ ጥረታችንም በሚቀጥሉት ሰዓታት ይጥበቅብናል።
የአባታችንን ነፍስ ከደጋጎቹ አበው ጋር ያቁምልን።
መንፈሳዊ ልብ ይስጠን።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)