January 19, 2010

በጠበል ከሰው ሆድ ውስጥ ከስምንት በላይ ነፍሳት ወጡ

እባብ፣ አይጥ፣ እንቁራሪት፣ እንሽላሊት፣ ሸረሪት፣ ኣባ ጨጓሬ፣ ቀንድ አውጣ፣ አልቅት፣ ጢንዚዛና ሌሎችም ምንነታቸው የማይታወቁ ነፍሳት ከሰው ልጅ ሆድ ውስጥ ወጡ ቢባል ማን ያምን ይሆን?


(በይብረሁ ይጥና)
(Mahibere-Kidusan):- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጠበል አማካኝነት ተአምራት የተደረገላቸው ብዙ የሰው ልጅ ታሪኮችን እናገኛለን፡፡ ከነዚህ መካከል አንዱ የሶርያው ንጉሥ ሠራዊት አለቃ የነበረው ንዕማን ለጌታው የቅርብ ሰውና የተከበረ ሲሆን ነገር ግን በለምጽ የተመታ ሰው ነበር፡፡ የእግዚአብሔርም ሰው ኤልሳዕ «ሂድ በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ታጠብ፣ ሥጋህም ይፈወሳል» አለው፡፡ «የእግዚአብሔር ሰው እንደተናገረው በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ፤ ሥጋውም እንደገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ሆኖ ተመለሰ ንጹሕም ሆነ» ይላል /2ነገ.5-14/፡፡ እንደዚሁም ለአሥራ ሁለት ዓመት ያህል ያለ ማቋረጥ ደም ይፈሳት የነበረችውን ሴት እግዚአብሔር እንዳነፃት በማቴዎስ ወንጌል 10-20 ላይ እንመለከታለን፡፡ ይህም የልብሱን ጫፍ ነክቼ «እድናለሁ» አለች፡፡ ኢየሱስም «ልጄ ሆይ አይዞሽ እምነትሽ አድኖሻል» አላት፡፡ ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምራ ዳነች ይላል፡፡


ልክ እንደዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ ሁሉ የእግዚአብሔር ድንቅ ተአምራት የተደረገላቸውና በጠበል የተፈወሱ ሰዎች ብዙዎች ናቸው፡፡ በዛሬም ጽሑፋችን የምንመለከተው በእግዚአብሔር ቸርነት በጠበል ተፈውሳ ከሆዷ ውስጥ ከስምንት ዓይነት በላይ ነፍሳት የወጡላትን ወጣት ይሆናል፡፡
እባብ፣ አይጥ፣ እንቁራሪት፣ እንሽላሊት፣ ሸረሪት፣ ኣባ ጨጓሬ፣ ቀንድ አውጣ፣ አልቅት፣ ጢንዚዛና ሌሎችም ምንነታቸው የማይታወቁ ነፍሳት ከሰው ልጅ ሆድ ውስጥ ወጡ ቢባል ማን ያምን ይሆን? ተሸካሚውስ ሰው እንዴት በሕይወት ሊቆይ ይችላል? የሚሉትን ሁሉ እንደ ሰው ሰውኛ ስናስብ ፈጽሞ ሊታመን የማይችል ነገር ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሁኔታው /ድርጊቱ/ ከሰው ሕሊና ውጪ በመሆኑ ማንም ሰው በቀላሉ ሊቀበለው ስለማይችል ነው፡፡

ነገር ግን ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና እውነት ሆኖ ተገኘ፡፡ የወጣቷ ቤተሰቦች፣ ጎረቤትና አጥማቂዎች በዐይናቸው አይተው አረጋግጠዋል፡፡ እኛ እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ ድንቅ ተአምሩን ያደረገላትን ጨምሮ እሷን ሲያስታምሙ፣ ሲያስጠምቁ የነበሩ ቤተሰቦችና ጎረቤት እንዲሁም ሲያጠምቋት የነበሩ አባቶችን በማነጋገር እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ በቅድሚያ ግን ከባለጉዳዩ የሚበልጥ የለምና በጠበል የተፈወሰችውን ወጣት እናስቀድማለን፡፡

ወጣቷ እመቤት ሥራው ብዙ ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው በምሥራቅ ጎጃም ብቸና ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ቤተሰቦቿ የሚተዳደሩት በግብርና ሥራ በመሆኑ የተሻለ ሥራ ለመፈለግ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ታገለግላለች፡፡ ከምትሠራባቸውም ቦታዎች አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ የሚገኘው የወ/ት ወይንሸት ወልደ ሰንበት ቤት ነው፡፡ እኛም ያነጋገርናት ወደዚሁ ቤት ሄደን ነው፡፡ ምክንያቱም አንደኛ እግዚአብሔር ያደረገላትን ድንቅ ተአምር ለምእመናን ለማሳወቅ ሲሆን ሁለተኛ በአሁኑ ዘመን አንዳንድ ሰዎች ለቤት ሠራተኞቻቸው ልዩ ትኩረት በማይሰጡበት ሰዓት እሷን ግን አሠሪዎቿ እንደ ልጃቸው አድርገው እስከ መጨረሻው ድረስ በማስታመም አድነው እያስተማሯት መሆኑንም ጭምር ለማሳየት ነው፡፡ ይህ ደግሞ እግዚአብሔር የሚያዘውንና መደረግ የሚገባውን መልካም ሥራ እየሠሩ መሆኑን ለሌላው ያስተምራል ብለን ስለ አሰብን ነው፡፡

ለወጣት እመቤት ሥራው ብዙ በቅድሚያ ያነሣንላት ጥያቄ ሕመሙ የጀመረሽ መቼና እንዴት ነው? የሚል ነበር፤ እንዲህ ስትል መልሳለች፡፡ «ሕመሙ የጀመረኝ ገና የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሁን ድረስ የማያቋርጥ ከፍተኛ የራስ ምታት ያመኝ ነበር፡፡ ይበልጥ የባሰብኝ ግን በ2001 ዓ.ም በየካቲት ወር መጨረሻ ሲሆን ለአራት ወር ያህል በተከታታይ ሐኪም ቤት ስመላለስ የማኅጸን ዕጢ ነው አሉኝ፡፡ እንዲሁም እግሬ ደህና ነበር እሱንም አመመኝ፡፡ ውስጡን እየቆረጠመ ያስነክሰኛል፡፡ ከሁሉ የባሰብኝ ሕመም ማኅፀኔን ስለነበር ብዙ ጊዜ አመላልሶኛል፡፡ በሐኪሞች በማኅፀኔ ውስጥ ዕጢ ነው ተብሎ ኦፕሬሽን ትሆኛለሽ አሉኝ፤ በተባለው ጊዜ ሄጄ ስታይ «ኢንፌክሽን /Infection/ ሆኖ ከፍተኛ ደም ስለፈሰሰ አሁን ኦፕሬሽን መሆን አትችይም» ተባልኩ፡፡ በዚያ ፈንታ ሰባት መርፌ ታዞልኝ ሕክምናውን ተከታትየ ነበር አለች፡፡

እመቤት የታዘዘላትን ሰባት መርፌ ተከታትላ ብትወጋውም ሕመሙ ሳምንት ሳይቆይ ተነሣባት፡፡ እንደቀድሞው ደም መፍሰስ ጀመረ፡፡ «ከዚህ በኋላ ቃልቲ አካባቢ አዲስ የተሠራችው ቁስቋም ጠበል ሄድኩ፡፡ ትላለች እመቤት፤ «እዚያም ሄጄ ለዐሥር ቀን ያህል ደም ከፈሰሰ በኋላ ሲቆምልኝ ጠበል መጠመቅና መጠጣት ጀመርኩ፡፡ ወደ ጠበል ቦታው የሄድኩት ግንቦት 1 ቀን 2001 ዓ.ም ሲሆን ለአንድ ወር ያህል ስጠመቅ ሁለት እንቁራሪት በትውከት ወጣልኝ፡፡ ከዚህ በኋላ ዳንኩ፤ ሌላ ችግር አይገጥመኝም ብዬ ወደ ምሠራበት ቤት ተመልሼ መጣሁ» በማለት ታሪኳን ትቀጥላለች፡፡

እመቤት ከሕመሜ ድኛለሁ ብላ ወደ ቤቷ ከመጣች በኋላ እንደገና አመመኝ አለችን፡፡ ደግሞ ሌላ ምን ነገር ገጥሟት ይሆን? መልሷን ለመስማት ቸኮልን፡፡ የነገረችን ነገር እጅግ በጣም የሚከብድና የሚዘገንን ነገር ነው፡፡ በራሷ አንደበት እንዲህ ትገልጸዋለች፡፡ «እንደገና አመመኝና ሐምሌ 5 ቀን ለ6 የቁስቋም ዋዜማ 2001 ዓ.ም ወ/ት ወይንሸት በታክሲ ወደ ጠበሉ ወሰደችኝ፡፡ ጠበሉን ጠጣሁ፤ ተጠመቅሁ ልክ የቁስቋም በዓል ዕለት ሁለት እባብ ከሆዴ ወጣልኝ፡፡ ለአራት ቀን ሙሉ ጉሮሮዬን አንቆ ይዞ ያስጨንቀኝ ነበር፡፡ እንቅልፍ የሚባል አላይም፤ ሲወጣልኝ ራሴን አላመንኩም፡፡ በድንጋጤ ራሴን አላውቅም ነበር፡፡ አንዱ በትውከት መልክ ሲወጣ ሁለተኛው እንደ ልጅ በማኅፀኔ ወጣ፡፡ ሁለቱም ነፍስ አላቸው፡፡ የወጡልኝ አውላላ ሜዳ ላይ በመሆኑ ከብት የሚጠብቁት ሊገድሉት ሲሯሯጡ በድንጋይና በድንጋይ መሐል ገብቶ አመለጣቸው፡፡ አሁንም ፈተናዬን ጨረስኩ ብዬ ወደ ቤቴ ተመለስኩ፤ ብዙም አልተሻለኝም፡፡ መጨረሻውን ማየት አለብኝ ብዬ በድጋሚ ወደ ጠበሉ ሄጄ ስጠመቅ ሐምሌ 19 ቀን የቅዱስ ገብርኤል ዕለት ሁለት ትናንሽ እባቦች ወጡልኝ፡፡ ጠበሉን ተጠምቄ ከወጣሁ በኋላ ነው ሁለቱም በትውከት ከሆዴ የወጡልኝ፡፡ ሊጠመቁ የመጡና አጥማቂዎች ያዩት ሲሆን ቤተሰቦችሽ ማየት አለባቸው ብለውኝ በዕቃ አድርጌ ወደ ቤት በማምጣት ጎረቤት ሳይቀር አይተውታል» ስትል የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ተናግራለች፡፡

በአጠቃላይ በቃልቲ ቁስቋም ለሁለት ወር ያህል እየተጠመቀች ቆይታ ከሁለት ወር በኋላ ግን በዚያው መቀጠል አልቻለችም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ በመሐል «የአተት /የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት/ በሽታ ገብቷል» ተብሎ ጠበሉ ሲዘጋ ቦሌ ቡልቡላ መድኃኔዓለምና አባ ሳሙኤል ጠበል መጀመሯን አስረድታለች፡፡ በዚያም ስትጠመቅ በየቀኑ ብዛት ያላቸው አባ ጨጓሬ እንደወጡላት ታስረዳለች፡፡ «የሚወጣልኝ ነገር ሁሉ አላልቅ ብሎ ከእኔም አልፎ ያለሁባቸውን ሰዎች እያስደነቀ መጨረሻውን ይናፍቁ ነበር፡፡ ቶሎ ቢያልቅልኝ ብዬ በአቅራቢያው እዚያው ቦሌ ቡልቡላ በሚገኘው የተክለ ሃይማኖትና የእመቤታችን ጠበል ጀመርኩ፡፡ ይህ ቦታ ቅርሶች በቅርብ ጊዜ የተገኘበትና ጠበል የፈለቀበት ነው፡፡ በዚህ ቦታ ምንነቱን የማላውቀው ነገር ወጣልኝ፡፡ ትልልቅና መልኩ ጥቁር ሲሆን የወጣልኝ ደግሞ ወደ ገደል አካባቢ አስሩጦ ከወሰደኝ በኋላ ነው፡፡ በዚያን ዕለት በተጨማሪ እንሽላሊትና ሁለት የቄብ ዶሮ እንቁላል የሚያክል ከድፍርስ ውኃ ጋር ተቀላቅሎ ወጣልኝ፡፡ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ አሁን ሙሉ ጤነኛ ነኝ፡፡ ራስ ምታቱም ሆነ ደም መፍሰሱ ቆሞልኛል» አለችን፡፡

ወጣት እመቤት ሥራውብዙ ንግግሯን ብትጨርስም የሕመሙ መነሻ ምን እንደነበር ጠየቅናት፡፡ «እኔ በመጀመሪያ ቃሊቲ ቁስቋም ጠበል ስጀምር አጋንንት፣ መተትና ቡዳ ነኝ ብሎ እንደጮኸ አስታማሚዎች ነግረውኛል፡፡ ከዚህ ውጭ ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ የአስታመሙኝ ሰዎች ሁኔታውን ስለሚያውቁ እነሱን መጠየቅ ይቻላል፡፡ እኔን ግን እግዚአብሔር አድኖኛል፤ አመሰግነዋለሁ፡፡

በመቀጠል ለታመመ ሰው አስታማሚ ያስፈልጋልና ያስታመሙኝን አሠሪዎቼን አመስግኑልኝ፡፡ ከዚህ በፊት በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ወፍ የወጣላት እኅት አለች የሚለውን ወሬ ስሰማ ከዚህ የባሰ የእኔን ቢሰሙ ምን ሊሉ ነው? ብዬ የእግዚአብሔርን ቸርነት ሰው እንዲያውቀውና አስታማሚዎቼን እንድታመሰግኑልኝ በማሰብ ነው፡፡ አሠሪዎቼ ቤት እየዘጉና እየከፈቱ ምግብ አመላልሰው አስታመውኛል፡፡ ሌላ ሰው ሳይቀጥሩና የእኔን ሥራ እየሠሩ ሲያስታምሙ ማንም ዘመድ የማያደርገውን ሥራ ሠርተዋል» ብላ ከልቧ አለቀሰች፡፡ ቃላት ቢያጥራት በዕንባዋ ጭምር ከልብ የመነጨ ምስጋናዋን ገለጸች፡፡ እሷን አጽናንተን በቀጥታ ጥያቄያችንን ያስከተልነው አስታመውኛል ወደአለቻቸው አሠሪዎቿ ነው፡፡

ወ/ሪት ወይንሸት ወልደ ሰንበት ይባላሉ፡፡ የእመቤት አሠሪ ሲሆኑ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ወ/ሪት ወይንሸትን ስለእመቤት ሥራው ብዙ ምን የሚነግሩን ነገር አለ? አልናቸው፡፡ እሳቸውም «እመቤት ወደእኔ የመጣችው የዛሬ ዓመት ነው፤ እኔ ቤት ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ ለአራት ወር ያህል ብቻ ነው በሰላም /በጤና/ የኖረችው፡፡ ከባድ የራስ ምታት ነበረባት፡፡ በዚህ የተነሣ የሠራችበትን ይዛ በመሄድ ትታከማለች፡፡ ለሁለት ቀን ያህል ደህና ሆና እንደገና ይመለስባታል፡፡ በመጨረሻ ደህና ሐኪም ቤት ሂጂና ታከሚ ብዬ ከዘመድ ጋር አያይዤ ላክኋት፡፡ ሄዳ ስትመረመር የማኅፀን ዕጢ ነው አሏት፡፡ ኦፕሬሽን ለማድረግ ቀነ ቀጠሮ ሰጥተዋት በተባለው ጊዜ ሲታይ «ዕጢው ማሙቶ ብዙ ደም ፈሷልና አደጋ አለው» ብለው ወደ ካንሰር እንደተቀየረ ነገሯት፡፡ ማስታገሻ ብለው እያንዳንዱ አንድ መቶ ሰባ ብር የሚገዛ ሰባት መርፌ አዘዙላት፡፡ መርፌውንም ተወግታ መዳን አልቻለችም፤ በመጨረሻ ተስፋ ቆርጣ «በቃ ወደ ሀገሬ ላኪኝ፤ ዶክተሩ ካንሰር ነው ሲል ስለ ሰማሁት ካንሰር ደግሞ ይገድላልና አልድንም ልሂድ፤» አለችኝ» ነበር ያሉት፡፡

እመቤት የመዳኗ ተስፋ ተሟጦ ወደ ሀገሬ ልሂድ ብትልም ወ/ሪት ወይንሸት ግን ሌላ መፍትሔ ከመሻት በቀር ወደ አገሯ ለመላክ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ እንዲህ ነበር ያሏት፤ «ወደ ሀገርሽ ከመሄድሽ በፊት ለሰባት ቀን ጻድቃኔ ማርያም ሄደሽ ጠበል ትጠመቂያለሽ» እያሏት ሳለ በአጋጣሚ አዲስ አበባ ቃልቲ ቁስቋም ጠበል መጀመሩን ሰምተው ወደዚያው ወስደዋት ሁለት ወር እንደተጠመቀች አመልክተዋል፡፡ «ሁለት ወር ስትጠመቅ የማይወጣ ነገር የለም፡፡ ሁሉንም እንኳን መጥቀስ ባልችል ሁለት እባብ፣ እንቁራሪት፣ ሁለት ሸረሪት፣ አባ ጨጓሬ ሌላ ደግሞ አባ ጨጓሬ አይሉት ረጅም ነገር ወጥቶላታል፡፡ የሚወጡት ደግሞ ከነ ሕይወታቸው ሆኖ ትንሽ ሲቆዩ ይሞታሉ፡፡ የሚገርመው ነገር ቃሊቲ ቁስቋም፣ አባ ሳሙኤልና ተክለ ሃይማኖትም ስትጠመቅ ወጥቶላታል፡፡ በተለይ የቁስቋም፣ የኪዳነ ምሕረት፣ የገብርኤልና በሃያ አንድ የእመቤታችን በዓል ዕለት የሆነ ነገር ከሆዷ ሳይወጣ አይውልም፡፡ ሲወጣ ደግሞ በቀላሉ አይወጣም ጉሮሮዋን አስጨንቆና አታግሎ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ እቤት ጠበል አምጥታ ሞቅ ሲል ትጠጣና ወዲያው ይወጣል፤ የሚወጣው ነገር እንዳይታይ መጸዳጃ ቤት ቶሎ ሄዳ ታስወጣዋለች፡፡ አንድ ጊዜ እኛ ተሰብስበን በጓሮ በኩል ትጮሃለች፤ ምንድን ነው? ብለን ስንወጣ ትልቅ አይጥ በአፏ ሲወጣ ጅራቱ ብቻ ቀርቶ ያሠቃያታል፡፡ እኔ አላይም! ብዬ ደንግጬ ልትሞትብኝ ነው በሚል ፍርሃት ጎረቤቴን ስልክ ደውዬ ድረስልኝ አልኩት፤ እሱ መጥቶ በዕቃ አድርጎ ለሦስት ቀን ያህል አስቀመጠው፡፡ መጥፎ ጠረን ሲያመጣና እሷም አታሳዩኝ ስትል አውጥቶ ጣለው፡፡ ከዚያ በፊት ሁለት እባብ ይዛ አምጥታ አሳይታናለች፡፡ በጆሮዋና በአፍንጫዋ ሳይቀር ሙልጭ ሙልጭ የሚል አልቅት ሲወጣ አይቻለሁ፡፡ በመጨረሻ ጥቅምት 30 ቀን 2002 ዓ.ም ሁለት እንቁላል ሁለት ሸረሪት ወጣላት፡፡ ይህ እንግዲህ መርዙን ነቅሎ ሲወጣ ነው» ሲሉ ድርጊቱን በአግራሞት ተርከውታል፡፡

ወ/ሪት ወይንሸት እንደገለጹት የሚወጡት ነፍሳት አቅሟን ስለሚያደክሙት ምንም ዓይነት ምግብ እንደማትወስድ ተናግረዋል፡፡ «በአፍ የምትመጠጥ ግሉኮስ እየገዛሁ ነበር የምትወስደው እንጂ ምግብ የሚባል ገና ሲሸታት አታሳዩኝ ትላለች፡፡ የተባበሩት ነፍሳት በሆዷ ውስጥ ጎጆ ሠርተው ደሟን እየመጠጧት ኖረው ነበር» በማለት ተናግረዋል፡፡

እመቤትን ያማት የነበረው በሽታ መነሻ ምን እንደሆነ የሚያውቁት /የሰሙት/ ነገር ይኖር ይሆን ማለታችን አልቀረም፡፡ ወ/ሪት ወይንሸት መልስ አላቸው፡፡ «አጀማመሩን በተመለከተ ጠበል ቦታ ለፍልፋለች፡፡ ትውልድ ሀገሯ ነው፤ መነሻውን፤ /ድርጊቱን/ ስሰማው የተቀናበረ ነገር ነው፡፡ ስለ መዳኗ እንጂ ሌላውን ብንተወው መልካም ነው» ብለዋል፡፡

ሌላው ያነጋገርነው የወ/ሪት ወይንሸትን ወንድም አቶ ብንያም ወልደ ሰንበትን ነው፡፡ እሱም ያየውንና የተገነዘበውን እንዲህ ገልጾታል፡፡ «እኔ የምናገረው ያየሁትን ሲሆን በወሬ ደረጃ የሚታመን አይደለም፡፡ እኔ እንዳውም ይሄ ምን ተብሎ ይነገራል፤ ዋናው መዳኗ ነው ብዬ ነበር፡፡ እመቤት ግን «እግዚአብሔር ያደረገልኝን ቸርነት ድንቅ ተአምሩን ሰው እንዲያውቅልኝ መመስከር አለብህ» ብላ ስለጠየቀችኝ ነው፡፡ ስለወጣላት ነገር ብዙ ተብሏል፤ እኔ ለመጨመር የምፈልገው ያልተጠቀሰውን ሲሆን ሌሎች የወጡላት እንዳሉ ሆነው ቀንድ አውጣና የኩሬ ውኃ የሚመስል ወጥቶላታል፡፡ እንደዚሁም የአባ ሳሙኤል ንግሥ ዕለት እምነት ይዘንላት መጥተን እሱን ወስዳ ጢንዚዛና ደም አይሉት ውኃ የእንቁላል አስኳል የሚመስል ነገር ወጥቶላታል፡፡ ነገሩ ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ በሰው ሆድ ውስጥ ይህ ሁሉ ይቻላል? የሚለውን ሳስብ ይከብደኛል፡፡ ጠበል ምን ያህል ኃይል እንዳለው ያየሁትም በዚህች ልጅ ላይ ነው፡፡ እኔ ከዚህ በፊት ለጠበል የጠበቀ ዕውቀት የለኝም፤ በጠበል ሰው ተፈወሰ ሲባል ትኩረት አልሰጥም ነበር፡፡ አሁን ግን በማየቴ ለሌላውም እየመሰከርኩ ነው፡፡ የእሷን መዳን ሳይ እንደገና የመፈጠር ያህል ነው የምቆጥረው» በማለት አቶ ቢንያም አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ወጣት እመቤት ሥራው ብዙንና አሠሪዎቿን ካነጋገርን በኋላ «ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ» እንዲሉ ያመራነው ወደ አቶ ንጉሤ ዐምደማርያም ቤት ነው፡፡ እሳቸውም የተገነዘቡትን በእንዲህ መልኩ ነበር የገለጹት፡፡ «እመቤት ሲያማት እየተጠራሁ እመጣለሁ፤ ከእመቤት ሆድ ብዙ ነገር ይወጣል፡፡ ለምሳሌ አይጥ ሲወጣላት በተግባር አይቻለሁ፤ አንስቼም በዕቃ ያስቀመጥኩት እኔ ነኝ፡፡ የተጨቀጨቀ ግራዋ የሚመስል ነገር ሲወጣም አይቼያለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ያማታል፤ መድኃኒት ግዛላት በሚሉኝ ጊዜም የምገዛላት እኔ ነበርኩ፡፡ በተለይ በአፍ የሚመጠጠውን ግሉኮስ የምገዛላት እኔ ነኝ፡፡ እናም ልነግርህ የምፈልገው እኔ ክርስቲያን ነኝ፤ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ ሰው ተፈወሰ ሲባል ከምሰማው ውጭ በዐይኔ አላየሁም ነበር፡፡ አሁን ግን በዐይኔ ስላየሁ ከሰው ሆድ ውስጥ አንድ ነገር አይደለም መቶ ነገር ወጣለት ቢሉኝ አምናለሁ፡፡ ሰው ደግሞ ሲነገረው ማመንና መቀበል አለበት፡፡ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ቸርነቱ የጠበልን ኃይል እንደሚገልጥ መታመን አለበት፡፡ የእግዚአብሔርን ኃይልና ተአምሩን ደግሞ ሳይደበቅ መነገር፤ መመስከር እንዳለበት እምነታችን ግድ ይላል» ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

እመቤትን ጠበል ካጠመቋት አባቶች መካከል በፍኖተ ሕይወት ቅድስት ማርያምና ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ቦሌ ቡልቡላ የሚያጠምቁት አባ ገብረ ጻድቅ ክፍለ ዮሐንስ እና በአባ ሳሙኤል ቤተ ክርስቲያን አባ ወልደ ማርያም ኅብስቴ ምን ይላሉ? ብለን ጠይቀናቸው ነበር፡፡ እነሱም «በእኅታችን ላይ የታየው የእግዚአብሔር ተአምር በሰው ሰውኛ ስንመለከተው ይከብዳል፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ እንደተናገረው ለሰው የማይቻለው ለእግዚአብሔር ይቻለዋል፤ ስለሚል እውነት ሆነ፡፡ ከሰው ሆድ እባብ፣ አይጥ፣ እንቁራሪትና ሌሎች ነገሮች ወጡ ሲባል ግን ለሰው ሕሊና በጣም ከባድ ነው፡፡ ሰው እነዚህን ሁሉ ተሸክሞ ይሄዳል ወይ? የሚለውን ስናስብ መንፈሳዊ ሕሊና ካልሆነ በቀር ሥጋዊ ሕሊና ሊቀበለው የማይችል ነው፡፡ እኛ ስናጠምቅም ያየነው ነገር እንዳለ ሆኖ ያላየነውም ነገር አለ፡፡ በተለይ አባ ገብረ ጻድቅ ሰይጣኑ በላይዋ ላይ ስላለ እንዳይታይበት እያባረረ ወደ ወንዝ ወስዶ ከሆዷ ውስጥ ፍንቅል ብሎ ወጥቶ ውኃውን ሲመታው ያዩ አሉ፡፡ እኔ እያጠመቅሁ ስለነበር ለመያዝ ተከተሏት ስል ወዲያውኑ አስመልሷት ተወርውሮ ወንዝ ገባ አሉኝ፡፡ እኔ ሳጠምቃት አጋንንቱ ጮኋል፤ መተት ነኝ፤ ቡዳ ነኝ እያለ ሲለፈልፍ የያዛትም ትውልድ ሀገሯ እንደሆነ ነው፡፡ እኔ እንዳውም አእምሮዋን መልስላት የሚል ነው የጠየቅኩት፤ ለምን? አፍዝዟት ራሷን አታውቅም፤ ለሦስት አራት ቀን ራሷን ሳታውቅ ጠበል ቦታ ትተኛለች» ብለዋል፡፡

በመጨረሻ ይህ ሁሉ አውሬ በሆዷ እንዴት ሊቀመጥ ይችላል? እርስ በርሱስ ተስማምቶ ሊኖር ይችላል ወይ? የሚልም ጥያቄ አንሥተንላቸው ለዚህም ምላሽ አላቸው፡፡ «አውሬዎቹን እኮ የሚቀያይራቸው እርኩሱ መንፈስ ሰይጣን ነው፤ ሰይጣን ለሰይጣን መልእክተኛ ስለሆኑ ደሟን እየመጠጡ ተስማምተው ይኖራሉ፡፡ ሰይጣን በምትሃት ሆዷ ውስጥ በተለያየ ነገር እየተመሰለ የሚወጣው ሆዷን ቤት አድርጎ በመሥራት ነው» ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ጽሑፋችንን የምንቋጨው አባ ገብረ ጻድቅ ባስተላለፉት መልእክት ነው፡፡ እመቤትን ያስታመሟት ሰዎች እግዚአብሔር የሚያዘውን ትልቅ ሥራ ሠርተዋል፡፡ የሠሩት መልካም ሥራ ደግሞ ለሁሉም ሰው ትምህርት የሚሆን ነው፡፡ ስለዚህ ሌሎችም ሊማሩበት ይገባል፤ እያልን እግዚአብሔር ይባርካቸው፤ እሷንም ሞልቶ ይማራት እንላለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
6 comments:

Anonymous said...

Egziabher Yimesgen enji min enilalen!!!

Libona yisten esti Medhanealem

Anonymous said...

I encourage the faithful Orthodox christian to mark the anniversary of the Roe v. Wade Supreme Court decision with prayers, volunteer work with local pro-life ministries, and participation where possible in the Washington D.C. March for Life.
O Most Holy Trinity our God, accept the prayers of Thy Saints who shone forth from the African lands for our renewal and regeneration in Thy divine likeness.
Amen.

Orthodox Unit said...

Please visit the blog for basic frequent questions.

ልሳን ምንድን ነው?

ድህነት/መዳን ምንድን ነው? ሰው እንዴት ይድናል?

http://wongelforall.wordpress.com/category/frequent-questions/

Anonymous said...

+++
Beliwo Le Egiziabiher Groum Gibrik.

Egiziabiher Yehulachinim dewuye siga ena dewuye nefise Yifewusilin.

Ze Zewaye

Anonymous said...

+++
ለእግዚአብሔር ምን ይሳነዋል፤

ነገር ግን በብዛት ከጠበል ቦታ የምንሰማቸዉ ህመሞች ሰዎች በሰዎች ላይ ያመጡባቸዉ በሽታዎች (ችግሮች)ናቸዉ፤
ከአንድ አረማዊ በከፋ ሁኔታ ክርስቲያን ለክርስቲያን ክፉ ሲሰራ ይታያልና የሕዝባችን የክርስትና ደረጃ ጥያቄ ያስነሳብናል፤

በዚህ ዘመንም ቸርነቱን ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን! አሜን

tsegereda said...

eijeg betam yasazenal endezi mehonachu lemenafikan menged eyekefetachu mehonun atwkum egzabhar yeker yeblachu

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)