January 4, 2010

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በዲያስጵራው ዓለም ለምትገኝበት ትርምስ ተጠያቂው ማን ይሆን?


(አቤል ቀዳማዊ qedamawi@live.com)
“የእኔ እና የእናንተ አባቶች ንጽህት ሐይማኖት ከሙሉ ሥርዓቱ ጋር እንዲሁም ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እና ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሳያፋልሱ፤ ከቀደሙት አባቶቻቸው የተረከቡትን፤ ለእኛ አስረክበውናል። ለእኔ እና ለመሰሎቼ። በመንፈስ ቅዱስ ለምንወልዳቸው ልጆቻችን እናንተ ደግሞ በሥጋ ለምትወልዱዋቸው ልጆቻችሁ በዚህ በዲያስጶራው ዓለም ምን ዓይነት ቤተ ክርስቲያን አስረክበናቸው ልናልፍ ይሆን?”።

ይህንን ቃል የወሰድኩት ብፁዕ አቡነ አብርሃም የዋሽንግተን ዲሲ እና አከባቢዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በጻድቁ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በዓለ ልደት ንግስ ላይ በምስራቀ ፀሐይ ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ውስጥ ካስተላለፉት መልዕክት ነው። እኔም ከዚህ በፊት በተለያዩ ርዕሶች በዚሁ በደጀ ሠላም አስታያየት መስጫ ቦታ ላይ ያነሳሁት ጥያቄ ስለሆነ፤ እንዲሁም ደግሞ ዛሬ እኔ የምኖርበት ሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሀሳቡን ስለደገሙት በጣም ደስ ብሎኝ ለውይይት ይሆነን ዘንድ ለደጀ ሠላማውያን ላቀርበው ተገደድኩ። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በዲያስጵራው ዓለም ለምትገኝበት ትርምስምስ ተጠያቂው ማን ይሆን? ይህ እንግዲ ብዙዎች እውነተኛ የተዋህዶ ልጆች የሚያነሱት ጥያቄ ነው። መልሱን ግን ሁላችንም ለራሳችን እንደሚመስለን ወይም እንደሰማነው ልንመልሰው እንችላለን። አንዳንዶች አቡነ ጳውሎስን ተጠያቂ ያደርጋሉ፤ ሌሎች ደግሞ አቡነ መርቆርዎስን ተጠያቂ ያደርጋሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ሁለቱን ኮሚስት መንግስታትን ማለትም ደርግ እና ኢሀዴግን ተጠያቂ ያደርጋሉ።አንዳንዶች ደግሞ እነዚህ የተጠቀሱት ሁሉንም ተጠያቂ የሚያደርጉም አሉ። የዚህ የመወያያ ሀሳቤ ዓላማ ለትርምስምሱ ተጠያቂዎች መልስ ለማግኘት አይደለም። መልሱን ለቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊዎች ሊቃውንት እተወዋለሁ።

በተለያዩ የመወያያ ርዕሶች በዚሁ በደጀ ሠላም እንደገለጽኩት እዚህ አካባቢ በኢ/ኦ/ተ/ቤ ሥም የሚጠሩ 18 (አስራ ስምንት) አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ። ከነዚህ 18ቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አንዱ የምስራቀ ፀሐይ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ከተቋቋመ ገና ሰባተኛ ወሩ መሆኑን በበዓሉ ላይ ተገልፆልናል። ዛሬ በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የምዕመናን ብዛት እና የበዓሉ ድምቀት ሲታይ ግን የሰባት ወር ዕድሜ ያለው አጥቢያ አይመስልም። ይህ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በመቃኞነት በኪራይ ቤት እንኳ ቢቋቋምም ነገር ግን የኢ/ት/ኦ/ተ/ቤ ቀኖና እና ቃለ ዓዋዲ እንደሚያዘው ለመጀመሪያ ግዜ በዚህ አካባቢ በኢ/ኦ/ተ/ቤ ስም እና ባለቤነት የተመዘገበ መሆኑንና በሀገረ ስብከት መተዳደሩ ከሌሎቹ አጥቢያ ልዩ ያደርገዋል። በዚህ አካባቢ ቆይታዬ የታዘብኩት ነገር ቢኖር በየ ዓመቱ የጥምቀት እና የመስቀል በዓል ሲደርሱ የአንዳንድ አጥቢያ አብያተ ከርስቲያናት አስተዳዳሪዎች እየተሰባሰቡ በዓሉን ለማክበር ብቻ ብለው ምዕመናንን ተታርቀናል፣ ሠላም ሰፍኖዋል፣ አንድ ሆነናል፣ አጨብጭቡ፣ እልል በሉ የተለመደ ሆኖዋል። ነገር ግን አንድነቱ ሲዘልቅ አናየውም። ዛሬም ከላይ በገለጽኩት ደብር ክብረ በዓል ላይም ሌሎች አጥቢያ አብያተክርስቲያናት እንደሚያደርጉት ሊቀ ጳጳሱ በዚሁ በዓል የተገኙት የተለያዩ አጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት ሰንበት ት/ት ቤት እየዘረዘሩ ተናግረው ሳይጨርሱ እልልታውና ጭብጨባው ቀደመ። የየደብሩ ሰንበት ት/ት ቤት አባላት ተገናኝተው በአንድ ላይ መዘመራቸው ባልቃወምም ለአንድነታችን መሰረት ሊሆን ግን በፍፁ የሚችል አይመስለኝም። የአድነታችን መሰረት ሊሆን የሚችለው እያንዳንዱ ምዕመን እንዲሁም አገልጋዮች የጥንታዊቷ እና ሐዋርያዊቷ የኢ/ኦ/ተ/ቤ የቀደሙት አባቶች ያስረከቡንን አስተተዳደራዊ መዋቅር ጠንቅቀ ስናውቀው እና ስንተገብረው ብቻ ነው። አንድነታችን የሚመጣው በችግሮቻችን ተነጋግረን በተቀመጠልን መዋቅር ሥር ስንጠለል ነው። አለበደዚያ ግን የተወሳሰበ እና የተበጣጠሰ የፕሮቴስታንቱን ዓይነት ቤ/ክ በግለሶቦች እና በድርጅቶ ስም እንዲሁም ባለቤት ለልጆቻችን አስተላልፈንላቸው እናልፋለን። እኛ የፈጠርነው ችግር ልጆቻችንስ ይፈቱት ይሆን?። ወይስ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የሚለውን አባባል እየተገበርነው ያለው ተግባር ከቀጠለ፤ ይኼኛውም ዳግም አጥፊው ትውልድ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከወቀሳም ከውገዛም የሚያልፍ አይመስለኝም።

ይህ የቤተ ክርስቲያናችን የአስተዳደር መዋቅር ት/ት የተለያዩ ሰባኪያን ወንጌል እዚህ እኔ የምኖርበት አካባቢ አያነሱትም፤ እንዲሁም እንደ ጦር የሚፈሩትም ይመስለኛል። ግን አስከ መቼ ፈርተነው ልንኖር?። እንግዲህ ይህ በማለቴ አንዳንዶች እንደተለመደው ቅጥያ ስም በማውጣት “ወያኔ የአባ ጳውሎስ ደጋፊ” እንደሚሉኝ አልጠራጠርም ምክንያቱም እዚህ ሀገር ስለ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እንዲሁም ስለ ቀኖና ቤተክርስቲያን መናገር “የወያኔነት” ተቀጽላ ስም ማግኘት የተለመደ ሆኖዋል። እንዲሁ በተመሳሳይ በሀገራችን በኢዮጵያም በቤተ ክርቲያኒቱ ላይ እየተፈፀሙ ያሉት በደሎች መናገር ደግሞ “ጽንፈኛ ተቃዋሚ” የሚል ቅጥያ ሥም ከማስገኘትም አልፎ በወንጀል ያስፈርዳልም። ስለዚህ ወገኖቼ ዓይናችን ወደ እውነት ያለመሸነጋገል እየተያየን ከመጥፎ ታሪክ ተጠያቂነትም እንድንድን የእውነቱን መሰረት ይዘን ብንወያይበት መልካም ይመስለኛል።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)