December 18, 2009

በአክራሪ እስልምና ቡድኖች ተቃጥሎ የነበረው የቀመቼ ቅዱስ ሚካኤል ወአቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ተከበረ


(ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ/ በሻምበል ጥላሁን):- በኢሊባቦርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት በእሳት ወድሞ የነበረው የቀመቼ ቅዱስ ሚካኤል ወአቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን በሰባት መቶ ሺህ ብር ወጪ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ጉባኤ አባላት ተገንብቶ ቅዳሴ ቤቱ ኀዳር 12 ቀን 2002 ዓ.ም ተከበረ፡፡ የድርጅቱ ሠራተኞች ለቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት እንዲረዳ በማሰብ ለአካባቢው ማኅበረሰብ አገልግሎት የሚሰጥ ወፍጮ ለማስተከልም ዝግጅት ማጠናቀቃቸው ተገልጿል፡፡


ኀዳር 12 ቀን 2002 ዓ.ም የኢሉባቦርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት የዴዴሳ ወረዳና የቀመቼ ቀበሌ ሰላም ወዳዱ ነዋሪ ሕዝብና የቅዳሴ ቤቱን ለማክበር ከየአካባቢው ለመጣው ሕዝበ ክርስቲያን እንባ ያራጨ ዕለት ነበር፡፡

መስከረም 21 ቀን 1999 ዓ.ም የጥፋት ዓላማ ባነገቡ አንዳንድ የአክራሪ እስልምና ቡድኖች ሙሉ ለሙሉ ከነንዋያተ ቅድሳቱ የተቃጠለው የቅዱስ ሚካኤል ወአቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤት በተሟላ ሁኔታ ተሠርቷል፡፡ በበዓለ ንጉሡ ላይ የነበሩት ምእመናን በእንባ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡

«ደስታም ለካ ያስለቅሳል» ያሉት የቀመቼ ቀበሌ ገበሬ ማኀበር ነዋሪ አቶ ግርማ ዋሪ፤ ዛሬ የማለቅሰው እንደያኔው በሐዘን አይደለም፤ በደስታ እንጂ፤ ይሄን ደስታ ዛሬ አይቻለሁ ነገ ብሞት አይቆጨኝም» የሚሉት አቶ ግርማ፤ «ወገን እንዳለን፣ አስታዋሽ እንዳለን ተረድተናል» በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ የያኔውን ሰቆቃ ከአሁኑ ደስታ ጋር እያነጻጸሩ የሚገልጹት የአጥቢያው ነዋሪ ወለተማርያም፤ የጥፋት ኃይሎቹ ዓላማ በመንግሥት፣ በክርስቲያኑና በሙስሊሙ ማኀበረሰብ የጋራ ርብርብ ባይበርድ ኖሮ በኢሉባቦርና በጅማ ያደረሱት የአምስት አብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎና ከሰባት በላይ ምእመናንና የካህናት ግድያ ወደ ሌሎችም ይቀጥል እንደነበር ተናግረዋል፡፡

«ያኔ ተሸብረን ነበር፣ ተፈናቅለን ነበር፣ አዝነን ነበር፣ እጅግም አምርረን አልቅስን ነበር አሁን ሰላም ነን፡፡ እግዚአብሔር በጐ ምእመናንን አስነስቶ ይሄንን የመሰለ ሕንፃ ስለተገነባልንና በምንወደው ታቦት ክብረ በዓል ላይ በመገኘታችን የሐዘኑ ለቅሶ በደሰታ ተቀይሯል» በማለት ገልጸዋል፡፡

የዴዴሳ ወረዳ ቤተክህነትን ዘገባ ያቀረቡት አቶ ዓለሙ የምእመናኑን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ አቶ ዓለሙ እንደሚሉት በአካባቢው ተከስቶ ለነበረው ችግር መፈታት መንግሥት ከፍተኛውን ድርሻ ሲይዝ የኦርቶዶክስ፣ የእስልምና፣ የካቶሊክ እና የፕሮቴስታንት የእምነት መሪዎችና ምእመናንም ርብርቦሽ የላቀ ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

መንግሥት የተለያዩ ስብሰባዎችን በማዘጋጀትና ሕዝቡ ከሃይማኖት ግጭት ሊያገኝ የሚችለው ውጤት ጥፋት ብቻ መሆኑን ይልቁንም የተለያዩ እምነት ተከታዮች ባሉበት ሀገር ያለው ብቸኛ አማራጭ ተከባብሮ መኖርን መቀበል መፍትሔ መሆኑ እንዲታመንበት ሰፊ ሥራ መሠራቱን ዘገባ አቅራቢው አስረድተዋል፡፡

«ከዚህ የመንግሥት ጥረት ጐን ለጐን በወረዳችን በዞናችንና በሀገራችን የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ የሙስሊም፣ የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ እምነት ተቋማት ተከታዮቻቸውን በመምከር አጥፊዎች ደግሞ ለሕግ እንዲቀርቡ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል» ያሉት አቶ ዓለሙ፤ በተ ደረገው ሰፊ ጥረት ሕዝቡ ወደቀደመው አኗኗሩ መመለሱን ገልጸዋል፡፡

በዚያን ጊዜው ግጭት ሕይወታቸው ላለፈ፣ ንብረታቸው ለወደመና ቤታቸው ለተቃጠለ እንዲሁም ከሚኖሩበትም የመፈናቀል አደጋ የገጠማቸው ወገኖችን ለመርዳትና ወደ ነበሩበት ቦታ ለመመለስ በተደረገው ጥረት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ክርስቲያናዊ ልማት ተራድኦ ኮሚሽን፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኀበረ ቅዱሳን፣ ኅብርተሰቡን መልሶ በማቋቋም የቁሳቁስና የሞራል ድጋፍ በማድረግ የማረጋጋቱ ሥራ በሚገባ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡

በማረጋጋቱ ሥራ ወቅት የኢሊባቦር ዞን ሀገረ ስብከትና የዴዴሳ ወረዳ አስተዳደር ክርስቲያኑንና ሙስሊሙን ማኅበረሰብ በማቀናጀት የጋራ ኮሚቴ በማንቀሳቀስ ተጐጂው የየትኛውም የእምነት ተከታይ በችግሩ ተጋላጭነትን ማዕከል በማድረግ እንዲረጋጋ ጥረት ማድረጉንም አክለው ገልጸዋል፡፡

«ይሁን እንጂ እነዚህ በወረዳችን የሚገኙ የእምነት ተቋማት የጋራ ርብርብና የእምነቱ ተከታዮች ወደ ቀድሞ አንድነታቸው እንዲመለሱ ያደረጉትን ጥረት ጥላሸት በመቀባት፤ የሕዝቦች በጋራ መኖር የማያስደስታቸው ጥቂት ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው የሚንቀሳቀሱ አክራሪዎች አሁንም ያሉ በመሆኑ ከዚህ በፊት በጋራ ስንሠራ የነበረን ሰላም ወዳዶች ሁሉ ይሄን እኩይ ተግባር በጋራ እንከላከላለን» ሲሉ ዘገባ አቅራቢው የሰላም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የቀመቼ ቅዱስ ሚካኤል ወአቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ጉባኤ አባላት ሲታነጽ የኢሉባቦርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስና ሕዝቡ ከስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ እቃ በመሸከምና በማጓጓዝ ከፍተኛ ድጋፍ ስላደረጉም አመስግነዋል፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢሉባቡር ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው «ይሄ ቤተክርስቲያን በጥፋት ኃይሎች ሲቃጠል ከደቂቃዎች በኋላ ደርሼ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እንደዚህ በዘመናዊ ሁኔታ ተጠናቆ የእምነቱ ተከታዮች በተሰበሰቡት የምረቃው በዓል ላይ በመገኘቴ ተደስቻለሁ፡፡» በማለት የተሰማቸውን ስሜት ገልጸዋል፡፡

«የክርስትናውም ሆነ የሙስሊሙ የሃይማኖት መመሪያ የሆኑት መጽሐፍ ቅዱስና ቁርዓን ስለ ሰላም እንጂ ስለጠብ አይሰብኩም» ያሉት አስተዳዳሪው፤ «እግዚአብሔር ፍቅርን እንጂ ጠብን፣ መከባበርን እንጂ መገዳደልን አያስተምርም» ብለዋል፡፡

በመሆኑም በየእምነቱ ተቋማት ውስጥ ይሄን አብነት በመጣስ ድብቅ ዓላማቸውን ለማራመድ የሚጥሩ የጥፋት ኅይሎችን በመከላከልና በማጋለጥ ረገድ ምእመናን በችግሩ ወቅት ያደረጉትን ድጋፍ አሁንም እንዳያቋርጡ ጠይቀዋል፡፡

መንግሥት የጥፋት ኃይሎችን የመከታተልና ተገቢውን ቅጣት የመስጠት ሂደቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው፤ ለአካባቢው ሰላም ከኀብረተሰቡ ጋር ተባብሮ እንደሚሠራም አስረድተዋል፡፡

ቤተክርስቲያኑ በዘመናዊ ሁኔታ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲዘጋጅ ያደረጉትን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ጉባኤ በማደራጀትና በማስተማር ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ያበቁት ቀሲስ ሰሎሞን ሙሉጌታ የቤተክርስቲያኑን አሠራር ሂደት አስመልክተው እንደተናገሩት፤ ቤተ ክርስቲያኑን በሁለት ዓመት ከአምስት ወር ውስጥ በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በተባበሩት መንግስታት ሠራተኞች ጉባኤ አባላት ጥረትና በአካባቢው ምእመናን ድጋፍ ለዚህ መብቃቱን ተናግረዋል፡፡

ለቤተክርስቲያኑ ማሠሪያ ከሕንፃ ግንባታው በተጨማሪ ለአገልግሎት የሚያስፈልጉ ንዋየተ ቅዱሳት፣ ጄኔሬተርና ማይክረፎን የተሟላለት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለቤተክርስቲያኑ ግንባታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኛ ጉባኤ አባላትንና አንዳንድ በጎ አድራጊ ምእመናንን አመስግነው ሠራተኞቹ ከዚህ በተጨማሪም ለቤተክርስቲያኑ ገቢ የሚፈጥር ከ180 - 200ሺሕ ብር በሚገመት ወጪ ወፍጮ ለመትከል ዝግጅት ማጠናቀቃቸውንም ገልጸዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በበዓሉ ላይ ለመገኘት አስበው የነበረ ቢሆንም በሥራ መደራረብ ምክንያት መገኘት ስላልቻሉ፤ የተሰማቸውን ደስታ የሚገልጽ ለምእመናን ቃለ ቡራኬ በጽሑፍ ልከዋል፡፡

በመጨረሻም ቃል ምእዳንና ቡራኬ ያስተላለፉት የአሉባቡርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የመንበረ ፓ-ትርያርክ ወመዘክርና የትንሳኤ ማተሚያ ቤት የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ፤ ይሄንን የተቀደሰ ተግባር በመፈጸም የአካባቢው ምእመናን እንዲያገለግል ቤተክርስቲያን ያሳነጹትን፣ ቤተክርስቲያኑ ሲታነጽ በጐልበት በእውቀት በሁሉ ነገር የተራዱትን የአካባቢው ምእመናንና ነዋሪዎች ሁሉ አመስግነዋል፡፡

«እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነውና ሰላም ይወዳል፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና ፍቅር ይወዳል፡፡ ይሄንን አርአያነት ይዛችሁ የአካባቢው ሰላምና ፍቅር እንዲመለስ ጥረት ያደረጋቹሁ የአካባቢው አስተዳደርና ምእመናን እንዲሁም ሕዝቦች ሁላችሁም እግዚአብሔር ዋጋችሁን ይክፈላችኹ» በማለት አባታዊ ቡራኪያቸውን ሰጥተዋል፡፡

በበዓሉ ማጠቃለያ ላይም በአካባቢው ለሚተከለው ወፍጮ በበዓሉ ላይ የታደሙት ምእመናን በጉልበት ለመርዳት ቃል ከመግባት ጀምሮ ከ15 ሺሕ ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ አዋጥተዋል፡፡ የኢሉባቦር ዞን አስተዳዳሪ ወፍጮ ቤቱን የቆርቆሮ ወጪ ለመሸፈን ቃል የገቡ ሲሆን፤ የካቢኔው አባላት በበኩላቸው ሁለት ሺሕ ብር እንደሚለግሱ ተናግረዋል፡፡

የዴዴሳ ወረዳ በኢሊባቦር ዞን ከሚገኙት 24 ወረዳዎች አንዱ ሲሆን በአጠቃላይ 85 ሺሕ 520በላይ ነዋሪዎች ይገኙበታል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 5 በመቶው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታይ ነው፡፡ በወረዳው ከ1921 እስከ 2001 ዓ.ም የተመሠረቱ 11 አብያተ ክርስቲያናት እንደሚገኙም ለማውቅ ተችሏል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

1 comment:

kalehawaryat said...

May the blessing of Almighty God always be with those who built this Church and may God bless our nation.

Kalehawayat AA

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)