December 31, 2009

ቤተ ክህነት ከአምስት እጥፍ በላይ የቤት ኪራይ ጭማሪ አደረገች


(ሪፖርተር ጋዜጣ/ፍሬው አበበ):- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በሚያስተዳድራቸው ቤቶችና ሕንፃዎች ላይ ከ500 ፐርሰንት በላይ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ አደረገ፡፡ ተከራዮች ጭማሪው አቅማችንን ያላገናዘበ ነው በማለት ሲቃወሙ ቤተክህነት በበኩሏ በጥናት ላይ የተመሰረተ እርምጃ መወሰዱን ገልፃለች፡፡ ድርጅቱ ታህሳስ 8 ቀን 2002 ዓ.ም. ለተከራዮች በበተነው ደብዳቤ ወቅቱን ያገናዘበ፣ ፍትሀዊና በጥናት ላይ የተመሰረተ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ ከኅዳር 1 ቀን 2002 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2003 ዓ.ም ድረስ ለአንድ ዓመት የሚቆይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ በተጨማሪም ተከራዮች ለአንድ ዓመት የሚቆይ አዲስ ውል እንዲፈርሙ፣ በአዲሱ የዋጋ ተመን መሠረት የሶስት ወራት ኪራይ መያዣ ገንዘብ ገቢ እንዲያደርጉ አዟል፡፡

ተከራዮቹ ቀደም ሲል የቤት ኪራይ በቁርጥ ክፍያ ይከፍሉ እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት ፒያሳ አካባቢ የሚገኙ ቤቶች 1ኛ ፎቅ በካሬ ሜትር 35 ብር፣ ከዚያ በላይ ያሉ በየፎቅ ብዛቱ አምስት ብር እየጨመረ በሚሄድ ስሌት እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል፡፡ በዚሁ መሠረት በወር 220 ብር ሲከፈልበት ለነበረ ቤት 1"095 ብር፣ 213 ሲከፈልበት የነበረ ቤት በወር 1,288 ብር እንዲከፍሉ መወሰኑን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ተከራዮቹ ገልፀው፣ ይህ በተለይ የጡረተኞችንና የተቀጣሪ ሠራተኞችን አቅም ያላገናዘበ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

ተከራዮቹ ቤተክህነት አስጠናሁት ባለችው ጥናት መሠረት የኪራይ ሒሳቡ በየዓመቱ እየጨመረ የሚሄድ መሆኑን መገንዘባቸውን ገልፀው፣ ሁኔታው በተለይ ለትርፍ ባልተቋቋመች ቤተክርስቲያን መፈፀሙ አሳዝኖናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሲያን ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ይስሐቅ ስለ ጉዳዩ ከሪፖርተር ጋዜጣ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ የኪራይ ዋጋ ጭማሪው ሥራ ላይ እንዲውል የተደረገው በቅድሚያ ጥናት ተካሂዶ ነው፡፡ የኪራይ ጭማሪ የተደረገውም ቤተክህነት በየገጠሩ ያሏትን አብያተ ክርስቲያናት ለመደጎም ገንዘብ ስለሚያስፈልጋትና የኑሮ ውድነት እየጨመረ በመምጣቱ መሆኑን ጠቁመው፣ ጭማሪው የኅብረተሰቡን አቅም እንዳይጎዳ በብርቱ ታስቦበት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቤተክህነት በጭቃ የተሰሩ አንዳንድ ቤቶች ወርሃዊ የኪራይ ዋጋ 0.75 ሳንቲም ሆኖ መገኘቱን አቡነ ይስሐቅ ጠቁመው ይህን በወር ወደ 15 ብር ከፍ ሲደረግ ቅሬታ መጥቷል ብለዋል፡፡

አንዳንድ ተከራዮች ሁለት መቶ ብር የተከራዩትን ቤት ከሁለት ሺህ ብር በላይ አከራይተው ሌላ ቤት ተከራይተው እንደሚኖሩ ያስታወሱት አቡነ ይስሐቅ "እኛ ግን ይህን ያህል የተጋነነ ጭማሪ አላደረግንም" ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ቤተክህነት በደርግ መንግሥት ተወርሰው የነበሩ በጠቅላላው ወደ 800 ያህል ቤቶች እንዲመለሱላት ቢወሰንም በተለያዩ ምክንያቶች በአሁኑ ወቅት ተረክባ በማስተዳደር ላይ የምትገኘው ግማሽ ያህሉን ብቻ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)