December 22, 2009

“በሰሜን አሜሪካ የኢ/ኦ/ተ/ቤ ካህናትና ምዕመናን ጉባኤ” መግለጫ እና ሳይገለጹ የታለፉ እውነታዎች

(ደጀ ሰላም፤ ዲሴምበር 21/2009)፦ በተለምዶ “ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ማኀበር” እየተባለ የሚጠራው “በሰሜን አሜሪካ የኢ/ኦ/ተ/ቤ ካህናትና ምዕመናን ጉባኤ” በዳላስ ቴክሳስ ደብረ ምሕረት ቅ/ሚካኤል ያደረገውን አምስተኛ ዓመታዊ ጉባዔ ሲፈጽም መግለጫ አውጥቷል። የመግለጫውን ሙሉ ቃል የምናነበው ሆኖ ዋና ዋና ሐሳቦቹን ግን እንደሚከተለው አሳጥሮ ማቅረብ ይቻላል።

1. ቤተ ክርስቲያን “በውስጧ የሚከሠቱትን የሞራልና የአስተዳደር ስሕተቶች አርማ፣ የተጣሉት ታርቀው፣ የራቁትም ቀርበው መሠረቱ የፀና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት” ሆና ማየት እንደሚፈልጉ፣
2. በኢሊባቦርና በጅማ አካባቢ ለሚገኙ ምዕመናን $53 000 ዶላር መላካቸውን፣
3. የዚህን ጉባኤ “አባላት አብያተ ክርስቲያን ካህናት በአንድ ጥላ ሥር ላማዋሐድና በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያን ውስጥም የሚፈጠረው አለመስማማት ወደ ዓለማዊ ፍርድ ቤት ከማምራቱ በፊት” መፍትሔ ለመስጠት እንደሚፈለግ፣
4. “የቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳይ ከኀሊናችን ያልጠፋና እያሳሰበን የሚገኝ ታላቅ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን በጥንቃቄና በጥልቀት ሁኔታውን ለመከታተል ጉባኤው” መወሰኑን፣
5. በአገራችን የሚገኘውን ረሀብና ቸነፈር ለመቅረፍ መፍትሔ የሚፈልግ (የሥራ ዕቅድ የሚያዘጋጅ) የምሁራን ቡድን ለማቋቋም ጉባኤው መስማማቱን
መግለጫው ይጠቁማል።

ይሁን እንጂ ይህ የካህናትን የምእመናን ጉባኤ ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ስላለችበት መሪር ሁኔታ እና መፍትሔው የተወያየበት ነገር ስለመኖሩ አልገለጠም። የሁሉ የበላይ ስለሆነውና እነርሱም “እቀበለዋለሁ፣ አይሰደድም” ስለሚለው የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ወሳኝ አካል ስለቅ/ሲኖዶስ ጉዳይም በአጭሩ “የቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳይ ከኀሊናችን ያልጠፋና እያሳሰበን የሚገኝ ታላቅ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን በጥንቃቄና በጥልቀት ሁኔታውን ለመከታተል” በሚል ግልጽ ያልሆነ ሐረግ አልፎታል። አባባሉ ራሱ ከተርታ ምእመናን የተሰነዘረ አስተያየት እንጂ የካህናት ብሒል ያለበት አገላለጽ አይመስልም።

ጉባኤው በአንድ ጥላ ሥር ለመግባት መወሰኑ አበረታች ነው። ይህ “አንድ ጥላ” ግን ራሱን “እንደ ሲኖዶስ” ለማድረግ፣ ወይም “ሀገረ ስብከት አከል” ሆኖ አሁን በመጠናከር ላይ ያሉትን አህጉረ ስብከት “ለመገዳደር” በዚያው በተለመደው “የቤተ ክህነት የምቀኝነት መንፈስ” ከሆነ “ስልቻ ቀንቀሎ፣ ቀንቀሎ ስልቻ” ይሆናል። ስለዚህ አሁንም መግለጫውን የሚያብራራ ሌላ መግለጫ ያስፈልጋቸዋል። ምን ማድረግ እንደምትፈልጉ በትክክል ተናገሩ። እንዲያው በደፈናው “ከቦርድ ባርነት ነጻ እንውጣ፣ ቦርድ ከሚገዛችሁ እኛ ካህናት እንጫወትባችሁ” ከሆነ አሁንም “ስልቻ ቀንቀሎ፣ ቀንቀሎ ስልቻ” ይሆናል። ከዚህ አዙሪት ውጡና ሌላውንም አውጡ።

የመግለጫውን ሙሉ ቃል እዚህ ያንብቡ።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)