December 17, 2009

እኛም በበኩላችን “ይቺ ቤተ ክርስቲያን የማን ናት?” እንበል?

(ደጀ ሰላም፣ ዲሴምበር 17/2009)፦ ሰሞኑን የመገናኛ ብዙሃን (የኢትዮጵያውያኑን ማለቴ ነው) ዐቢይ ርዕስ ሆነው ከሰነበቱት ጉዳዮች አንዱ የነበረው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ መስፍን ነጋሽ ጽፏት የቆየች አንዲት ባለ 2 ገጽ ጽሑፍ (ይህ አገር የማን ነው?)“www.ethiomedia.com” ድረ ገጽ ላይ ወጥቶ ሳነበው ገና ወደ ውስጥ ሳልዘልቅ ርዕሱ ወደ ብዙ ምሥጢር ሳበኝ። ጋዜጠኛው ስለ አገር ሲያትት ቆይቶ ጽሑፉን ሲቋጭ
“አንድ ሀገር የጥቂቶች ትሁን የብዙሀን ለማሳየት እጅግ በርካታ መመዘኛዎችን መደርደር ይቻላል። ይህንን ግን ለአንባቢዎች ልተወው። ፈረንጆቹም እንዲህ ያለ ፈተና ሲገጥማቸው ዝነኛ ለመሆን የበቃ ጥያቄአቸውን ይወረውራሉ "whose country is it anyway"?”

አለ። የጽሑፉ ጭብጥ ምንም ይሁን ምን ርእሱ ግን አንድ ትልቅ ጉዳይ አጫረብኝ።

“ደጀ ሰላም” ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ በመጀመሪያ የእኔ (የዚህ ብሎግ ቆርቋሪን) ሐሳብ ቀጥሎም ሌሎች “ደጀ ሰላማውያን” ሲመጡና የጽሑፍ አበርክቷቸውን መለገስ ሲጀምሩ ደግሞ የነርሱንም በመጨመር ለቤተ ክርስቲያናችን ይበጃል የምንለውን ስታስተናግድ ከርማለች። ከጽሑፋችንም በላይ ደግሞ ኦርዶክሳውያን ማወቅ አለባቸው ብለን የምናስበውን በተረጋጋጠ እውነት ላይ የተመረኮዙ ዜናዎችንና ሐተታዎችን ስንሠራ ቆይተናል። በተለይም የጓዳችን ገበና በአዲስ መልክ ለአደባባይ ከበቃበት ከግንቦቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ወዲህ ይህንኑ ሐሳባችንን ዳር ለማድረስ ስንሞክር ቆይተናል። ልፋታችን ሜዳ ላይ ፈስሶ እንዳልቀረ የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች ቢኖሩም ከሚፈለገው ነገር አንጻር ሲታይ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ጽሑፋችን ከእንቅልፋቸው ያነቃቸውና የሚያመስግኑን ክርስቲያኖች ያሉትን ያህል “ደግሞ እነዚህ እነማን ናቸው?” በሚል ዘለፋ አዘል አስተያየት ሞታችንን የሚመኙም ሞልተዋል። (አመስጋኞቻችንን ትተን ዘላፊዎቻችን ለምን እንደሚዘልፉንና የዘለፋቸውንም መነሾ በመጠኑ እናትት።)

ቤተ ክርስቲያናችን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምእመናን (32,138,1260) እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አገልጋዮች ማለትም ጳጳሳት (??)፣ ቀሳውስት (147,114)፣ መምህራን (10,128)፣ ዲያቆናት (130,292)፣ ሰባክያነ ወንጌል (12,988)፣ መዘምራን (64,247)፣ ወዘተ ወዘተ አሏት። ታዲያ እነዚህ የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ራሳቸውን የቤተ ክርስቲያን የበኩር ልጅ ያደርጉና ሌላውን ምእመን በሁለተኛ ደረጃ ቆጥረው በተለያየ ስም ይጠሩታል። ጥቁር ራስ፣ ወዘተ ወዘተ ይሉታል። ስለ ሃይማኖቱ “ብዙም ያልተማረ (ጨዋ)” ነውና ስለ ቤተ ክርስቲያን ከእነርሱ የበለጠ ብዙም የሚገደው አይመስላቸውም። ስለ ቤተ ክርስቲያን ወሳኝ ጉዳይ ሲገጥም እንኳን እርሱም ባለቤት ነውና ያገባዋል ብለው አያስቡም።

በርግጥም ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ከሌሎቹ የሚለያት “ምእመን-መር” ሳትሆን “ቀሳውስት-መር” መሆኗ ነው። ይህም ሐዋርያዊ ትውፊት እንጂ ኢ-ዲሞክራሲያዊነት አይደለምና ትክክል ነው። ነገር ግን ይህ “ቀሳውስት-መርነት” በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ በአበው ትውፊት፣ በመጻሕፍት ቃል ያልተገራ ከሆነ ሐዋርያዊቱን ቤተ ክርስቲያን የጥቂት ካህናት ገንዘብ ያደርጋትና ምእመኑ በቤቱ የውጪ ልጅ፣ ባይተዋር ይሆናል። የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ክህነት በመቀበላቸው ብቻ የፈለጉትን እንዲያደርጉ የተፈቀደላቸው በሚመስላቸው ጥቂት ሰዎች ቁጥጥር ሥር ትገባለች። በውስጧ የሚፈጸመውም ተግባር በደሙ የመሠረታት ባለቤቷ ክርስቶስ በመስቀል የሞተለት የሰው ልጅ ድኀነት ሳይሆን ሌላ ሥጋዊ ተግባር ይሆናል።በዚህን ጊዜ ነው ታዲያ “እንዴ? ይቺ ቤተ ክርስቲያን የማን ናት? የማን ገንዘብ ናት?” ብለን ለመጠየቅ የምንገደደው።

ቤተ ክርስቲያን የቅ/ፓትርያርኩ ወይም የጥቂት አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጥቂት መነኮሳት ወይም ደባትር (ደብተሮች)፣ ዲያቆናት ወይም ሰባክያነ ወንጌል የግል ንብረት ሳትሆን የሁላችንም ናት። የክርስቶስ ናት። “እምነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ እናታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን” እንላታለንና እናትነቷ ለሁላችንም ነው። ነገር ግን ሥራችን የተለያየ እንደመሆኑ፣ ክህነትም የእግዚአብሔር ጥሪ ስላለበት፣ ሁላችን ካህናት ካልሆንን ብለን ፕሮቴስታንታዊ ጥያቄ አናነሳም። የቀደሙት ደጋጎቹ አባቶች በሠሩልን ሕግ ብንመራ ምእመኑም እንደ ምእምንነቱ፣ ካህኑም እንደ ካህንነቱ የሚያድርበት የየራሱ ተግባርና ሥፍራ አለው። ስለዚህ ያ የአበው ሕግ ይፈጸም። የዘመናችን አበውም እንደ ቀደሙቱ ሁኑ፤ ምእመኑንም እንደ ምእመንነቱና እንደ ልጅነቱ አስተዳድሩት። በመግቢያችን የጠየቅነውን ጥያቄ ስንመልሰው “ይህቺ ቤተ ክርስቲያን የሁላችንም ናት፤ የጥቂቶቹ የእናንተ ብቻ አይደለችም” እንላለን። ምእመኑም ቤተ ክርሲያኒቱ የእርሱም መሆኗን አውቆ እንደ ባለቤትነቱ የሚገባውን ያድርግ።

አንባብያንስ ምን ትላላችሁ?

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)