November 16, 2009

አረም የሚያስበላ ረሃብ???

(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 15/2009)፦ ይህንን የሪፖርተር ጋዜጣ ሪፖርታዥ ከማንበባችን በፊት በ2007 እዚኹ ደጀ ሰላም ላይ አውጥተነው የነበረ አንድ ግጥም ለጊዜው ተስማሚ መስሎ ተሰማን።
እጅግ በጣም ጠምቶኝ ሰግቼ ሰግቼ
እጅጉን ፈርቼ እጅጉን ፈርቼ
ሌት ዕንቅልፍ ሳላገኝ ቀን ዕረፍት አጥቼ
ጎኔ ጎኑን አጥቶ
አንጀቴ ከቦታው ሸሽቶ
ድካም በደምሥሬ ዘምቶ
አጥንቴ ለታሪክ ተጎልቶ
ዓይኔ ብቻውን ቀርቶ
ሰግቶ መዋል ፈርቶ አድሮ
አይ የሐበሻ ኑሮ፡፡
+++++

(በኃይሌ ሙሉ)
(ሪፖርተር)፦ የዘሩት በቅሎ ፍሬ ሊሆን አልቻለም፡፡ የዘሩትን አጭዶ መመገብ አልሆነላቸውም፡፡ ከችግራቸው ብዛት የተነሳ አረም መመገብ ጀምረዋል፡፡ አረም እየተመገቡ ትምህርታቸውን መከታተል ያቃታቸው ከጫፍ ደርሰው ለማቆም ተገደዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ድርቅ ገብቶባቸዋል ከሚባሉት የአገሪቱ ክፍሎች መካከል በአርሲ ነገሌ የቀራሮ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው፡፡

የቀራሮ ገበሬዎች ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የዘሩት ሰብል ሙሉ በሙሉ በመውደሙ በህይወታቸው አይተውት የማያውቁትን የስቃይ ዘመን እንዲገፉ ተገድደዋል፡፡ ድርቁን ተከትሎ የሚቀምሱት ያጡት እነኚህ ዜጎች በረሃብ ከመሞት ለመዳን የሰው ዘር ይቅርና እንስሳት እንኳን የሚፀየፉትን አረም (ሳር) ቀቅለው ለመብላት መገደዳቸውን አካባቢውን ለመጎብኘት በተጓዝንበት ወቅት ያነጋገርናቸው ገበሬዎች ይመሰክራሉ፡፡ የረሃብ ተጠቂዎቹ የሚመገቧቸው ዋነኞቹ የአረም አይነቶችም ሙጀሎ እና ሸረሌ ይባላሉ፡፡

በአርሲ ነገሌ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ 43 ቀበሌዎች ውስጥ በዘንድሮው ዓመት በአደገኛ ሁኔታ ለድርቅ የተጋለጡት ቀበሌዎች ብዛት 17 መድረሱን በአካባቢው በልማት ሥራ ላይ የተሰማሩ አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ባለሙያ ለሪፖርተር ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት በሴፍቲኔት አቅፎ የምግብ እርዳት እየሰጠ የሚገኘው ከ11 ቀበሌዎች ለተመረጡ 11ዢ400 የድርቅ ተጎጂዎች ብቻ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ለድርቅ አደጋ በሚጋለጡት በነዚህ 11 ቀበሌዎች የሚኖረው ህዝብ ብዛት 260 ሺህ ይገመታል፡፡ አብዛኞቹ የቀበሌዎቹ ገበሬዎች የዘሩት ሰብል ምርት ባለማስገኘቱ የምግብ እጥረት የገጠማቸው ቢሆንም እረዳታ የሚያገኙት ግን ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ብዙዎቹ ህይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ አረም (ሳር) ለመብላት የተገደዱት፡፡

"ህይወት አድን ምግቡ" የሚበቅለው ለአጭር ጊዜም ቢሆን ዝናብ በሚዘንብባቸው የአርሲ ነገሌ ቆላማ ቦታዎች በመሆኑ የአረሙ ተጠቃሚዎችም የቆላማ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ሙጀሎ እና ሸረሌ የተባሉት አረሞች ለአርሲ ነገሌ ቆላማ ቦታዎች የተሰጡ ፀጋዎች ናቸው፡፡

የቀራሮ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ፈይሳ በሪሳ ባለትዳርና የስድስት ልጆች አባት ናቸው፡፡ አቶ ፈይሳ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር የዘሩት በቆሎ ሳይበቅል ቀረ፡፡ ግን ተስፋ አልቆረጡም፡፡ የዝናብ ወቅት ጠብቀው ለሁለተኛ ጊዜ እድላቸውን ለመሞከር አሰቡ፡፡ እንደጠበቁትም ሐምሌ ወር ላይ ዝናብ መጣ፡፡ በቆሎውን ውጦ ያስቀረውን መሬት እንደገና አርሰውና አለስልሰው ስንዴ ዘሩበት፡፡ ይሁን እንጂ የተዘራው ስንዴ አበባ ሳያወጣ በዚያው ጠፋ፡፡ የእነ አቶ ፈይሳ ተስፋም በዚያው ከሰመ፡፡

የፈይሳ ቤተሰቦች በሴፍትኔት የታቀፉ በመሆናቸው በነፍስ ወከፍ 12.5 ኪ.ግራም በቆሎ ወይም ስንዴ በየወሩ ያገኛሉ፡፡ መንግሥት በየወሩ የሚሰጣቸው የምግብ እርዳታ ህይወትን ለማቆየት ካልሆነ በስተቀር በቂ አለመሆኑን የሚናገሩት አቶ ፈይሳ በአካባቢው ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የተከሰተው ድርቅ የቤተሰባቸውን ህይወት እንዳመሳቀለው ይናገራሉ፡፡ የዘጠነኛና የአስረኛ ክፍል ተማሪዎች የሆኑት ሁለት ሴት ልጆቻቸው በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገድደዋል፡፡

አቶ ፈይሳ እንደሚሉት ልጆቻቸው ትምህርት ባቋረጡበት ሰሞን ሲያለቅሱ ይውሉ ስለነበር ሥራ ውለው ወደ ቤቱ ሲመለሱ የእነሱን ፊት ማየት ያሳቅቃቸው ነበር፡፡ የአቶ ፈይሳ ልጆች በሚቀጥለው ዓመት ዝናብ ዘንቦ ምርት ማምረት ከተቻለ ትምህርታቸውን እንደሚቀጥሉ በአባታቸው የተነገራቸውን ማጽናኛ ተቀብለው ይሁን ተስፋ ቆርጠው አሁን ማልቀሳቸውን አቁመዋል፡፡ በልቶ ማደር በማይቻልበት አካባቢ እየኖሩ ስለ ትምህርት መቋረጥ መጨነቅ ቅንጦት ነው ብለው አስበውም ሊሆን ይችላል፡፡ አቶ ፈይሳ "ትምህርታችን ለምን እናቋርጣለን?" ከሚለው የልጆቻቸው የቀን ከቀን ጭቅጭቅና ለቅሶ መቆም ለጊዜውም እፎይታ የሰጣቸው ቢሆንም የቤተሰባቸው የወደፊት ህይወት ግን ያስጨንቀቃቸዋል፡፡ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የተከሰተው ድርቅ የእርዳታ ጥገኛ አድርጓቸዋል፡፡ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለም የቤተሰባቸውን ህይወት አደጋ ውስጥ ይከተዋል፡፡

የእነ ፈይሳ ቤተሰብ መንግሥት በሚሰጠው የምግብ እርዳታ ህይወቱን ማቆየት ችሏል፡፡ ለአሁኑ አረም መብላት አልተጠበቀበትም፡፡ ስለወደፊቱ ግን ምን እንደሚከሰት በእርግጠኝነት መናገር የሚችል የለም፡፡

አቶ ፈይሳ እንደሚሉት እርሱንና እርሱን የመሳሰሉት ትንሽ አቅም ያላቸው ሰዎች በአካባቢው ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት ከብቶቻቸውን ሸጠውም ቢሆን ለጊዜው የመኖር ተስፋቸውን ያለመልማሉ፡፡ እረዳታ እስከሚያገኙ ድረስም እየተንገዳገዱ ይቆያሉ፡፡ ከብቶችና ለችግር ጊዜ የሚሆን መጠባበቂያ ገንዘብ የሌላቸው ገበሬዎች ግን ብቸኛ የነፍስ አድን ምግባቸው አረም ነው፡፡ በቦታው ተገኝተን እንዳየነው ሙጀሎ የተሰኘው አረም ሰፋፊ ቅጠልና ደቃቅ ፍሬ ያለው ሲሆን በረሃብ የተጎዱት ገበሬዎች ቀቅለው የሚመገቡት ቅጠሉን ነው፡፡

ፈይሳ ከሚያሰጋው አደጋ ለመሸሽ የወጠነው እቅድ ካለ ስንጠይቀው "የምኖርበትን አካባቢ በመተው የመስኖ ወንዝ ወዳለበት ለቡ ለጲስ ወደተባለው ቦታ በመምጣት መሬት ተከራይቼ ለማረስ አስቤያለሁ፡፡ ሌላ አማራጭ የለኝም" የሚል ምላሽ ሰጥቶናል፡፡

ለመስኖ አገልግሎት የሚውለው የለጲሶ ወንዝን በመጥለፍ ግማሽ ሄክታር መሬታቸው ላይ ቲማቲም ማምረት ከጀመሩ ሁለት ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ እርሻቸው በዓመት አራት ጊዜ የሚያመርቱትን ቲማቲም ወደ ገበያ አውጥተው በመሸጥ የገቢ ምንጫቸውን ያሳደጉት አቶ ሁሴን በረሃብ ጠኔ ከሚሰቃየው አብዛኛው የአካባቢ ገበሬ በተሻለ መልኩ የተመቻቸ ኑሮ እየመሩ ይገኛሉ፡፡ ከቲማቲም ምርት ሽያጫቸው በዓመት ከሃያ ሺህ ብር በላይ ገቢ የሚያገኙት እኚህ ገበሬ እድል ብሎላቸው የለጲሶ አነስተኛ የመስኖ ወንዝ በሚያልፍበት ቦታ ላይ የእርሻ መሬት ባይኖራቸው ኖሮ የእርሳቸውና የቤተሰባቸው እጣ ፈንታ ከሌሎች የአካባቢው ገበሬዎች አይለይም ነበር፡፡ በቀራሮ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ከሚኖሩ 800 ያህል አባወራዎች መካከል የለጲስ የመስኖ ወንዝ ተጠቃሚ የሆኑት 100 ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡ እነኚህ የመስኖ ተጠቃሚዎች በማሳቸው የሚያመርቱት ሽንኩርትና ቲማቲም የእለት ጉርሳቸውን ከመሸፈን አልፎ ተቀማጭ ገንዘብ እንዲኖራቸው አስችሏቸዋል፡፡ አቶ ሁሴንም የዚህ እድል ተጠቃሚ ናቸው፡፡

በዓመት ከሶስት እስከ አራት ጊዜ በመስኖ በመጠቀም ሽንኩርትና ቲማቲም በማምረት የተሻለ ህይወት እየመሩ የሚገኙት አቶ ሁሴን በአንድ የምርት ዘመን ብቻ በአማካይ 80 ሳጥን ቲማቲም መሰብሰብ እንደሚችሉ ገልፀውልናል፡፡ በአሁኑ ሰዓት አንድ ሳጥን ቲማቲም ከ100 ብር ባላነሰ ዋጋ ይሸጣል፡፡

አቶ ሁሴን በአንድ የምርት ዘመን ከቲማቲም ምርት ሽያጭ የሚያገኙት ገቢ ከፍተኛ ቢሆንም ቲማቲሙን ለሚሰበስቡት የቀን ሰራተኞች የሚከፍሉት ገንዘብ ግን ለቁርስ መግዣ እንኳን የሚበቃ አይደለም፡፡

አንድ ሳጥን ቲማቲም በመቶ ብር የሚሸጥ አንድ ገበሬ አንድ ሳጥን ቲማቲም ለሰበሰበ የቀን ሰራተኛ 10 ብር ቢከፍል ያን ያህል የሚጎዳ አይሆንም፡፡ በቀራሮ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ግን የሚታሰብ አይደለም፡፡

እድሜያቸው ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰ ሁለት ሕፃናት ረሀብ በጎዳው አንጀታቸው ድክ ድክ እያሉ በሌሎች ሰዎች ተቀጥፎ መሬት ላይ የተቀመጠ ቲማቲም እየሰበሰቡ በሳጥን ውስጥ ያጠራቅማሉ፡፡ እነሱ ቲማቲም የሚሰበስቡበትን የአቶ ሁሴንን እርሻ ለመጎብኘት ወደ አካባበው የተጓዝነው ሰዎች በቁጥር በርከት ያልንና ለአካባቢው እንግዶች በመሆናችን የብዙዎችን ትኩረት የሳብን ቢሆንም ሕፃናቱ ግን የማወቅ ጉጉታቸው በረሃብ ተቆልፎ ሳይሆን አይቀርም ቀና ብለው እንኳን አላዩንም፡፡ አንገታቸውን አቀርቅረው ከአንዱ የቲማቲም ተክል ወደ ሌላ ተክል በባዶ እግራቸው እየተዘዋወሩ ቲማቲም ይሰበስባሉ፡፡ ሕፃናቱ በለጋ እድሜያቸው በጠራራ ፀሐይ እንዲያ ሲንከራተቱ የተመለከተ በሙሉ አንጀቱ መላወሱ የማይቀር ነው፡፡ የልጆቹን ሁኔታ አስከፊ የሚያደርገው ግን ከአቅማቸው በላይ በሆነ የጉልበት ሥራ መድከማቸው አይደለም፡፡ አልሆነም እንጂ ደክመውም ቢሆን በልተው ለማደር የሚያስችላቸው ክፍያ ቢያገኙ ባልከፋ ነበር፡፡ አቶ ሁሴን እንደነገሩን ሁለቱ ሕፃናት በቀን አራት ሳጥን ቲማቲም ይሰበስባሉ፡፡ ሕፃናቱ አንድ ሳጥን ቲማቲም ሲሰበስቡ ሁለት ብር ይከፈላቸዋል፡፡ አራት ሳጥን ቲማቲም ለመሰብሰብ ቀኑን ሙሉ ሲባክኑ የዋሉት ሁለቱ ሕፃናት እያንዳንዳቸው የሚያገኙት ክፍያ 4 ብር ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ይህ እውነታ እንደኔ ላለ አዲስ ሰው የሚያስደነግጥ ቢሆንም ለእነ አቶ ሁሴን እና ለጓደኞቻቸው ግን ብዙም የማያስገርም የተለመደ ክስተት ነው፡፡

እንዲያውም አቶ ሁሴን ከሌሎች ገበሬዎች በተለየ መልኩ የቀን ሰራተኞችን ቀጥረው ምርታቸውን ማሰባሰባቸው ሌሎቹን ለመርዳት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ የሚገኙ ሞዴል ገበሬ ሆነው እንዲታዩ አድርጓቸዋል፡፡ ቁም ነገር ተደርጎ የተወሰደው ሰራተኛ መቅጠራቸው እንጂ ተቀጣሪዎቹ የሚያገኙት ገንዘብ አይደለም፡፡ "እንደዚህ ሠራተኛ ቀጥሮ የሚያሰራ የለም" ይላሉ የአካባቢው ነዋሪዎች፡፡ ኢትዮጵያ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ከሚካሄድባቸው የአለም አገራት በመጀመሪያዎቹ ተርታ የምትሰልፍ መሆኗ ብዙዎቻችን የምናውቀው ሀቅ ቢሆንም የጉልበት ብዝበዛ የሚካሄድባቸው ህፃናት ቢያንስ የምግብ ወጪያቸውን የሚሸፍን ክፍያ አለማግኘታቸውን ማወቅ ግን ለህሊና ይከብዳል፡፡

በየጊዜው በሚያጋጥማቸው ድርቅና ረሃብ ምክንያት አረም ለመብላት የሚገደዱት አብዛኛዎቹ የቀራሮ እና የሌሎች አጎራባች ቀበሌ ማህበራት ነዋሪዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት ከደጋው ነዋሪ ጋር የትዳር ዝምድና መመስረታቸው ሳይጠቅማቸው አልቀረም፡፡

ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አንድ የግብርና ባለሙያ እንደተናገሩት የቆላው ነዋሪ ህይወቱን ማትረፍ የቻለው በደጋው አካባቢ ከሚኖሩት ዘመዶቻቸው በሚደረግላቸው እርዳታ ነው፡፡ የቆላው ነዋሪ በድርቅ ተመትቶ በተቸገረ ቁጥር በደጋው የሚኖሩ ዘመድ አዝማዶች ያላቸውን አካፍለው ከሞት ይታደጓቸዋል፡፡ ችግሩ ባስ ሲልም የቆላው ነዋሪዎች ከነከብቶታቸውና ከነልጆቻቸው ተያይዘው ደጋ ወደሚኖሩት ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ለወራት ይቆያሉ፡፡ በዚያም በደጋው ነዋሪ የሆኑ ዘመዶቻቸው ያመረቱትን በጋራ እየተቃመሱ የረሃቡን ጊዜ ያሳልፋሉ፡፡ ታዛቢዎች እንደሚሉት ይህ መተባበር ባይኖር ኖሮ በአርሲ ነገሌ ቆላማ ገበሬ ማህበራት የሚኖሩ ገበሬዎች ህይወት ከዚህ በከፋ መልኩ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችል ነበር፡፡

በአንድ በጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ አንድ ኃላፊ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት በዘንድሮው ድርቅ የተመታው አብዛኛው የአርሲ ነገሌ ወረዳ ህዝብ ከአንድ ወይም ከሁለት ወር በኋላ ረሃብን ሽሽት ወደ ደጋው አካባቢ ማምራቱ አይቀርም፡፡ አብዛኛዎቹ የድርቁ ተጎጂዎችም ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው የሚመለሱትም በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ መሆኑን እኚሁ ኃላፊ ይናገራሉ፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ባጋጠማቸው ድርቅ ለአረም መብላትና አካባቢያቸውን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱት የአርሲ ነገሌ ቆላማ ነዋሪዎች አሁን የገጠማቸው አስከፊ ህይወት መቼ እንደሚሻሻል አያውቁትም፡፡ ከተስፋ ይልቅ ጨለምተኝነት ይታይባቸዋል፡፡ በሴፍትኔት የታቀፉ ተጎጂዎች ከመንግሥት በሚሰጣቸው እርዳታ ቢያንስ ህይወታቸውን ማቆየት ይችላሉ፡፡ በእርዳታው ያልተካተቱ በርካታ ገበሬዎች ግን ነገ በህይወት ስለመኖራቸው በርግጠኝነት መናገር ይቸገራሉ፡፡ በቀራሮ ቀበሌ ገበሬ ማህበር በረሃብ ጠኔ የሚሰቃዩ ገበሬዎች ተፈጥሮ ፊቷን አዙራላቸው የዘሩት ፍሬ የሚያፈራበትን ቀን በናፍቆት እየተጠባበቁ ነው፡፡ የመንግሥት ግብርና ፖሊሲ ከተፈጥሮ ቀድሞ ከአረም መብላትና ከስደት ይታደጋቸው ይሆን?


1 comment:

Anonymous said...

It is so sad to hear such thing again.Is it possible to organize some sort of fund raising for those who did not get support from the government?

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)