November 17, 2009

ኮሚኒስታዊው ኢትዮጵያዊ ትውልድ እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን


(አቤል ቀዳማዊ ወለቴ)
(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 16/2009):- “የራሱን ሀብትና ማንነት የማያከብር ሕዝብና ተቋም በቁሙ የሞተ ነው” በሚል በነመራ ዋቀዮ ቶላ የቀረበውን ጽሑፍ ሳነብ ልቤ እጅጉን ተነክቷል። ይህንኑ የደጀ ሠላም ጦማሪ ሀሳብ መነሻ በማድረግ እኔም መጦመር እንኳ ባልችልም ስሜቴን ግን ለመግለጽ ብዕሬን ለማንሳት ተገድጃለሁ። ባለፉት 40 ዓመታት ቤተ ክርስቲያናችን የአስኳላውን ትምህርት ተምሬያለሁ በሚለው በማርክሳዊና በሌኒናዊ ትውልድ እጅጉን ተፈትናለች። እንዲሁም አሁንም ‘በተረፈ’ ኮሚኒስቶች እየተፈተነችም ትገኛለች።

ማርክሳዊ እና ሌኒናዊ ፍልስፍና ምንም እንኳ በየክፍለ ዓለማት የሚገኙት የእምነት ተቋማት በሙሉ (ከእስልምና በስተቀር) ፈተና ቢሆንም፤ እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግን የተፈተነ የለም። ሌኒን ተወልዶ ያደጉባት እንዲሁም ለዚሁ ፍልስፍና መሠረት የሆነችው ሀገር ሩሲያ ወይም ‘የሩሲያ ቤተ ክርቲያን’ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አልተፈተነችም ቢባል ማጋነን አይሆንም። እንግዲህትውልዱን ለመውቀስ አቅሙም ችሎታውም የለኝም፤ ነገር ግን ታሪክ በራሱ ጊዜ ይወቅሳቸው ይሆናል። የዚሁ ጽሑፌ ዋና ዓላማ ግን ‘ተረፈ’ ኮሚኒስቶች ከቤተ ክርስቲያናችን ላይ በትራቸውን እንዲያነሱ ለማስገንዘብ ነው። ቤተ ክርስቲያን ይህንን ትውልድ በማጣቷ ለሁላችንም የእግር እሳት ቢሆንብንም አሁንም በዚሁ ዘመንም ቤተ ክርስቲያኒቱን ማሳደድ አለማቆማችውና እንዲሁም ደግሞ ሁለተኛ ትውልድ እንድናጣ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ግን የበለጠ ያበሳጨኛል።

ለመሆኑ ኮሚኒስቱ ትውልድ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሰው ጥፋት ሳያንሰው አሁንስ ቢሆን ምን እያደረሰ ነው? እስቲ ከብዙ በጥቂቱ፦

1. በማርክሳዊና ሌኒናዊ ፍልስፍና የተዋጠው ትውልድ የቤተ ክርስቲያኒቱን ፓትርያርክ ጨምሮ አያሌ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን በግፍ ገድሏል፤ አስሯል፤ አሳዷል። በዚህም ብቻ አላበቃም። ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ዘመናት ያፈራችውን ንብረትና ሀብት ወርሷል፤ በብዙ በገንዘብ የማይተኩ ንዋያተ ቅድሳት ዘርፏል።

2. የቀድሞው የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከመንበራቸው እንዲወርዱና እንዲሁም ከወረዱ በኋላም ከሀገር እንዲሰደዱ አድርጓል። የመጀመሪያው ኮሚኒስት የደርግ መንግሥት ፓትርያርኳን በግፍ ገደለ፤ሁለተኛውና ወይም አሁን ያለው ኮሚኒስቱ መንግሥት ደግሞ ፓትርያርኳን ከመንበራቸው እንዲወርዱ አደረገ። እንግዲህ ቅዱስ ፓትርያርኩ ከመንበራቸው ከወረዱ በኋላም ተቀማጭነቱ ሀገረ አሜሪካን ያደረገው ሌላኛው ኮሚኒስት ቡድን ደግሞ ቅድስት ሀገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል። ከተሰደዱ በኋላም የራሳቸው ሲኖዶስ እንዲያቋቁሙና ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሁለት እንድትከፈል እዚሁ አሜሪካን ሀገር ያሉት ‘ተረፈ’ ኮሚኒስቶች በአማካሪነትና በዋና ተዋናይነት አስተዋፅዖ አድርገዋል።

3. አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ‘ተረፈ’ ኮሚኒስት ቡድን ቤተ ክርስቲያንን ማሳደድ አላቆመም። ባለሥልጣናቱ ቤተ ክርስቲያን የሌላትን ተቀጽላ ስም እየሰጡ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የነፍጠኞች ዋሻ ናት” በማለት ሲያንቋሽሹ ሰምተናቸዋል። እንዲሁም ልጆቿዋ በተለያዩ አካባቢዎች በአክራሪው የእስልምና ቡድን በግፍ ሲታረዱባት ተገቢውን ፍርድ ሳያገኙ ቤተ ክርስቲያንን “ምንም አታደርገንም” ብለው በዝምታ አልፈውታል። እነዚህ ኮሚኒስት ባለሥልጣናት በዚህ ብቻ አላቆሙም። ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ያበረከተችውን በርካታ አስተዋጽዖ ወደ ኋላ በመተው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለኢትዮጵያ ድህነት ቤተ ክርስቲያንን ተጠያቂ ሲያደርጉ እንሰማቸዋለን።

4. ይኸው ኮሚኒስቱ ትውልድ በውጪው ዓለም በተለይም በአሜሪካን ሀገር ቤተ ክርስቲያን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ እንድትመራ አድርጓል። ቤተ ክርስቲያን ያስቀመጠችውን ከራሷ ቀኖና ወይም ‘ከሰበካ ጉባዓኤ አስተዳድር’ ውጪ ቦርድ የሚል ስያሜ በመስጠትና እንዲሁም ገለልተኛ አስተዳደር በሚል ተቀጽላ ቤተ ክርስቲያን እንዲቋቋም አድርጓል። ይህም ብቻ አይደለም ኮሚኒስቶቹ በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት የግላቸው ቤተክርስቲያንም አቋቁመዋል።

ከላይ እንደጠቀስኩት አሁንም በድጋሚ መጥቀስ የምፈልገው የዚህ ጽሑፍ ዓላማ እነሱን ለመውቀስ አይደለም። ነገር ግን የዚሁ ፍልስፍና ተዋናዮች እያወቁም ሆነ ሳያውቁ እያደረጉት ያለውን ጥፋት እንዲያቆሙ ለመማፀን ነው። በስደት ላይ የሚገኙትም ‘ተረፈ-’ኮሚኒስቶች ጥንታዊቷንና ሐዋርያዊቷን ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን በይበልጥ እንድታስፋፋ እንቅፋት ከመሆን እንዲቆጠቡ እለምናችኋለሁ።
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)