November 16, 2009

የራሱን ሀብትና ማንነት የማያከብር ሕዝብና ተቋም በቁሙ የሞተ ነው

እሰቲ በመጀመሪያ ይኽንን ይመልከቱ።፡ከዚያ ወደ ጽሑፉ …

ነመራ ዋቀዮ ቶላ
(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 15/2009)፦ “የደጀ ሰላምን የፌስ ቡክ ገጽ” ስጎበኝ እዚህ ለውይይት ያቀረብኹትን ዘፈን አየኹት። ከያኒው ሞገስ ተካ ሲሆን የሚያጠነጥነው በቅዱስ ያሬድ ዙሪያ ነው። ሞገስ ዓለማዊ የሙዚቃ ሰው እንጂ ዘማሪ ስላልሆነ መዝሙር ይሆናል ብዬ አልጠብቅኹም። ምናልባት ቢሆንስ? ባለፈው ወንድማችን ሺመልስ አበራ ጥሩ መዝሙር አስደምጦን የለ? ታዲያ ሞገስስ ቢደግመን? ነገሩ ከላይ እንዳያችሁት ቅ/ያሬድን ያመሰገነበት ዘፈን ነው። እናም ሞገስን አንድ ሁለት ልልበት ፈለግኹ።


ብዙ እንደሚባለው/ እንደምንለው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና ሀገራችን ኢትዮጵያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። አይለያዩም አይነጣጠሉም። ሀገሪቱን ስናነሣ ቤተ ክርስቲያኒቱን፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ስናነሣ ደግሞ ሀገሪቱ ይነሣሉ። ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላት ነገር በሙሉ የሀገሪቱና የሕዝቦቿ በሙሉ ነው። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት የሆነው ቅ/ያሬድ የሀገሪቱም ነው። እናም ቤተ ክርስቲያኒቱ በመዝሙሯ ስታመሰግነው የሀገሪቱ የኪነጥበብ ሰዎች ደግሞ በዘፈናቸው ማመስገን ይገባቸዋል። ስለዚህም “ሞገስ ቅ/ያሬድን አስታውሰኽ በዜማ በማንሣትህ ተገቢ ነገር አድርገኻል” ባይ ነኝ(ከበሮ አመታቱ ድቤ መስሎ ሳቄን ቢያመጣውም፣ ወይም ዜማውን ያሬዳዊ ለማስመሰል ጉት…..ት ማድረጉ ፈገግ ቢያሰኘኝም)።

በቅርቡ “አዲስ ራዕይ” (የሐምሌ-ነሐሴ 2001 እትም) የተባለ መንግሥታዊ መጽሔት ሳነብ በገጽ 40-41 ላይ ስለ ፀበል ብዙ ነገር አትቶ ተመለከትኩ። ጭብጡ በአጭሩ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ተከሥቶ የነበረው አጣዳፊ ተቅማጥና ተውከት (አተት) መነሻ የፀበል ቦታዎች መሆናቸው፣ በኋላ በሐኪሞችና በሃይማኖት አባቶች ቦታዎቹና ውሃው በበሽታ መበከላቸው ሲታወቅ እንደተዘጉ፤ ሰዎች የሕክምና እጦችና ችግር ሲገጥማቸውና ሌላ አማራጭ ሲያጡ ያላቸው የመጨረሻ መፍትሔ ፀበል መሆኑን መጽሔቱ ያትታል። ይህ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለእምነቷ ያላትን አስተምህሮና ክብር ያላገናዘበ “ክብረ-ነክ” ጽሑፍ ታላላቅ የመንግሥቱ ባለሥልጣናት በብዕር ስም ይጽፉበታል በሚባለው መጽሔት ላይ መስተናገዱ ይህ በማርክሳዊ ሌኒናዊ ፀረ ሃይማኖት ዝንባሌ የተባላሸ ትውልድ ለሀገር በቀል እውቀትና ልምድ ያለውን ብኩን አስተያየቱን አሁንም አለመለወጡን ያመለክታል።

ክርክሬ ስለ ፀበሉ ቦታ አይደለም። መበከል አለመከሉን ማጣራት ይቻላል። ነገር አንድና አንድ መረጃ ያውም በትክክል ስለመመርመሩ ብዙ ምርምር ሳይደረግበት “ፀበል” በሙሉ የድሆችና ያልተማሩ ችግረኞች መሰብሰቢያ አድርጎ ማቅረብ የሌላውን ክብር መንካት ነው”። ለዚህ አባባላቸው “አዲስ ራዕይ”፣ አሳታሚና የጽሑፉ አዘጋጅ ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባ ነበር። (ደግሞ እንዲህ ማለቴ ወደ ፖለቲካ ይተረጎብኝ ይሆን?) ለዚህ ነው ሞገስ ተካን ዓይነት ሰዎች ማመስገን ያስፈልገናል የምለው። የራሱን ባሕል፣ ሀብትና ቅርስ በማወቁና በማክበሩ ማመስገን ይገባናል። ሌላውማ ፀበል የድሆች ነው እያለን ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለቤተ ክርስቲያናችን ውስጣዊ ንቀት ያላቸው ይመስለኛል። ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋሞቻችን፣ የየዘመኑ መንግሥታትና ባለሥልጣናቱ በንቀት የተያዙ ይመስላሉ። ይህንን ደግሞ በያጋጣሚው ያሳዩናል፤ አሳይተውናል። በ”ደርጉ ዘመን” እንኳን አደረሳችሁ ማለት ተከልክሎ “እንኳን ደረሳችሁ” ይባል ነበር። “አደረሳችሁ” ከተባለ “ማነው ያደረሰን?” የሚል ጥያቄ ተነሥቶ “እግዚአብሔር” የሚል መልስ እንዳያመጣ መሆኑ ነው። ታላቁ የሙዚቃ ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ (አፈር ይቅለለውና) በአንድ ወቅት ለእሑድ ጠዋት ቃለ ምልልስ ከመስጠቱ በፊት እንዲህ ብሎ ዘፈነ፦
ጤና ይስጥልኝ፣
እንደምናችሁ፣
እንኳን ለእሑዱ፣
ደረሳችሁ፣
ጤና ይስጥልኝ፣
እንደምናችሁ፣
እንኳን ለእሑዱ፣
ደረሳች…..ሁ ….
እንግዲህ “ደረሳችሁ” እንዲል ያስገደዱት “አደረሳችሁ” ወንጀል ስለሆነ ነበር። ይህ ፀረ ሃይማኖት አመለካከት ዛሬም ይታያል። በቅርቡ ቃለ ምልልስ የሰጡት የአንድነት ፓርቲ መሪ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም እንዲህ ያሉት ጥሩ ማስረጃ ይሆናል።
“ከጀርባችን በማርክሲዝም ሌኒንዝም ታንፀን የመጣን፣ ቅራኔዎች በውይይት ሳይሆን በመጠፋፋት መፈታት አለባቸው የሚል እምነት ይዘን የመጣን ሰዎች ነበርን …ገዢው ፓርቲ ይበልጥ አክራሪና አናቋሪ ፓርቲ ነው፡፡ ከሁሉም የበለጠ ገዢው ፓርቲ የድሮ ማርክሲስቶችን አስወግዶ ወጣቶችን መተካት አለበት፡፡ … ለሀገሪቱ ሰላምና እድገት አስተማማኝነት ከተፈለገ በማርክሲዝም ሌኒንዝም ታንፀው ስር ሰደው የመጡ ሰዎች በሙሉ ከየትኛውም የፖለቲካ አመራር መውጣት አለባቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ራሳቸው መጀመሪያ ከሁሉ ሰው በፊት ሥልጣናቸውን መልቀቅ አለባቸው፡፡ እሳቸው የማርክሲስት ሌኒኒስት አደገኛ አክራሪ የነበሩ ናቸው፡፡ አሁን ከማየው አንፃር ሙሉ በሙሉ ተቀይረዋል፡፡ የሚል እምነት የለኝም፡፡ የሀገሪቱ ፖሊሲ በአብዛኛው የሶሻሊስት ፖሊሲ አቀንቃኝ ነው፡፡ የንብረት አያያዝ፣ የመሬት ባለቤትነት ከተመለከትን የኮሚኒስት ሥርዓት ነው፡፡ ብዙ ድርጅቶች በመንግሥት እጅ ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ የኮሚኒስት ሥርዓት ገፅታ ነው፡፡ ዴሞክራሲን ማፈን፣ የንግግር ነፃነትን ማፈን፣ የኮሚኒስት ሥርዓት መመሪያ ነው፡፡ በሀገራችን እነዚህ ሁሉ አሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ሀገራችን በብዙም ባይሆን በከፊል ሶሻሊስት ናት ማለት ይቻላል፡፡”

በርግጥ ከኮሚኒስቶች “ቤተ ክርስቲያንን የሚያወድስ ቃል” መጠበቅ አይቻልም። ስለዚህ ሞገስ ተካን ብራቮ ሞገስ እንለዋለን። ሌሎች ባለሙያዎችም ያንተን ፈለግ ተከትለው እናት ቤተ ክርስቲያናቸውንና ለሀገሪቱ ያበረከተችውን ታላቅ ጸጋ እንዲያውቁና እንዲያከብሩ ዓይነ(ዕዝነ) ልቡናቸው እንዲበራ እንመኝላቸዋለን።
ፈያ ተኢ አቤ!!!
ገለቶሚ!!!

ቸር ወሬ ያሰማን
አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)