October 29, 2009

ደጀ ሰላማችን ሰላም እንድትሆን!


(ከብርሃኑ አ.)
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትኩረቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሆነ፣ ባለቤቷንና ማንነቷን ለመግለጽ አይን አፋር የሆነች ነገር ግን ከቤተክርስቲያኒቷ የውስጥ አዋቂዎች መረጃ የምታገኝ መሆኑ የማይጠረጠር ደጀ ሰላም የተሰኘች ብሎግ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበች መጥታለች። ፈጥኖ ደራሽነቷና የሰማችውን ሳትደብቅ እንደወረደ ማቅረቧ በብዙዎች ዘንድ ተነባቢ አድርጓታል። ደጀ ሰላም የምትዘግበው ሁሉ እውነት ነው ለማለት ባያስደፍርም የቤተክርስቲያኒቷን ወቅታዊ ሁኔታዎች ለመረዳት ከየትኛውም ይልቅ ጥሩ የመረጃ ምንጭ መሆኗ አሌ የማይባል ሀቅ ነው። የሚገርመው መጽሐፍ “…ባለበት አሞሮች በዚያ ይሰበሰባሉ።” እንዲል ደጀ ሰላምን የሚከታተሉት የቤተክርስቲያኒቷ ልጆች ብቻ ሳይሆኑ መናፍቃን ጭምር መሆናቸው ነው። በተለይም መናፍቃኑ የሚያነሷቸውን ሃሳቦችና ቤተክርስቲያንን የሚነቅፉበትን ሁኔታ በሚገባ ለተመለከተ ቤተክርስቲያን ምን ያህል ጠላቶች እንደከበቧት ለመረዳት ይቻላል። ለዚህም ነው ለብዙ ዓመታት በዚህች ብሎግ ላይ “በአስተያየት” መልክ በተደጋጋሚ እየተሰጡ ያሉ ሀሳቦችን ስከታተል ቆይቼ ጥቂት ለማለት የፈለኩት።

የቤተክርስቲያናችን አብዛኛዎቹ አገልጋዮች ዘመናዊ ሥልጠና የሌላቸው በመሆኑና “የተማሩት” የቤተክርስቲያኒቷ ልጆች ደግሞ “ብእረ-አፈር” መሆናቸው በቤተክርስቲያናችን ላይ የተከፈተውን የሳይበር ጦርነት የዳዊትና የጐልያድ ግጥሚያ አስመስሎታል (ምንም እንኳን ውጊያው የእግዚአብሔር ቢሆንም)። ይኸንን ለማለት ያስደፈረኝ በደጀ ሰላም ላይ በመናፍቃኑ እየተሰራ ያለውን ሸፍጥ በመረዳቴ ነው።
የቤተክርስቲያን ጠላቶች ደጀ ሰላም ላይ ምን እየሰሩ ነው?
እውነተኛ ጠላትም የሚታወቀው በክፉ ቀን ነው። እውነትም በተፋፋመ ጦርነት መካከል ለወገን ጦር በሚዋጋው ወታደር ላይ ከኋላ አድብቶ ከሚተኩስ የበለጠ ምን ዓይነት ጠላት ይኖራል? በአሁኑ ወቅት መናፍቃን ይልቁንም በተሐድሶ ስም የተደራጁት እያደረጉ ያሉት ይኸንን ነው። ቤተክርስቲያናችን በተለያዩ ውስጣዊና ውስጣዊ ችግሮች በተጠመደችበት በዚህ ወቅት ካለማሰለስ የቤተክርስቲያንን የውስጥ ድክመት ሽፋን በማድረግ አላማቸውን በማስፈጸም ላይ ይገኛሉ። ደጀ ሰላም ላይ በያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ሳያሰልሱ ሰፋ እና ዘርዘር ያለ “አስተያየት” የሚሰጡት እነዚህ መናፍቃን ሲያሻቸው የቤተክርስቲያኒቷን ትምህርት አጣመው የሚያቀርቡ፣ ሲያሻቸው ለእነሱ መሰሪ አላማ እንቅፋት የሆኑባቸውን እንደ ማህበረ ቅዱሳን ያሉ ስብስቦችን መልካም ተግባር ጥላሸት እየቀቡ በምእመናን ልቡና ጥርጣሬ በመዝራት፣ ጊዜያዊውን አስተዳደራዊ ችግሮች በማጋነን ምእመናንን በአባቶች ላይ ያላቸው አመለካከት እንዲቀየር የተለያዩ ፈጠራዎችን በመጨመር የሚጽፉ ብዙ መናፍቃንን አይተናል። አንዳንድ የቤተክርስቲያኒቷ ልጆች መናፍቃኑ ለሚያነሷቸው ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት የሚያደርጉት ጥረት የሚደነቅና መንፈሳዊ ተግባር ቢሆንም እነርሱ አውቀውና አልመው የሚያደርጉት ከመሆኑ አንጻር አደብ የሚያስገዛቸው አይመስልም። ምክንያቱም እነርሱ የተላኩበት አላማ ለማስፈጸም እንጂ የተሳሳቱት ነገር ካለ ተረድተው ለመመለስ የተዘጋጀ ልቡና የላቸውም። ይልቁንም ብዙዎች የዋሃንን ግራ ሊያጋባ የሚችል የተዛባ አስተያየታቸውን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይዘራሉ። አላማቸው አንድና አንድ ሲሆን ይኸውም የቤተክርስቲያኒቷን ትምህርትና ሥርዓት መቃወም፣ ቤተክርስቲያናችንን ታሪክ አልባና ቅርስ አልባ በማድረግ ባለማዊነት አስተሳሰብ የተጠለፈች ቤተክርስቲያን እንድትሆንና በስተመጨረሻም እንደ ምእራባዊያኑ ሀገራችንን እምነት አልባ ማድረግ ነው።
ምን ማድረግ ይቻላል?
የቤተክርስቲያናችን ወቅታዊ ሁኔታዎች ልንረዳበትና ችግሮች ሲኖሩ ጠቃሚ ውይይቶች ልናደርግበት የምንችልባቸው እንደ ደጀ ሰላም ያሉ የውይይት መድረኮች በመናፍቃኑ የጥፋት አጀንዳ መጠለፍ የለባቸው። በመሆኑም ፦
1. የቤተክርስቲያንን መሠረታዊ ትምህርት ለማዛባት የሚሞክሩ አስተያየቶች በብሎጓ ላይ እንዳይስተናገዱ በአዘጋጆቹ ጥረት ቢደረግ፤ ይህንንም በማድረግ መናፍቃኑ ለሚሰጡት አስተያየት ወይም የተዛባ መረጃ ማስተባበያ ለመስጠት የሚባክነውን የውይይት ጊዜአችንንና ሃሳባችንን ስለ ቤተክርስቲያናችን ጉዳይ ተገቢ ውይይት ለማድረግ እንጠቀምበታለን፤
2. ምንም እንኳን የቤተክርስቲያኒቷ አስተዳደራዊ ችግሮች በአደባባይ ጭምር ውይይት ሊደረግባቸው ቢገባም ተጨባጭ መረጃዎች ላይ ያልተመሰረቱ አሉቧልታዎችን በአስተያየት ሰጪዎች ሲሰጡ ማገድ፤
3. ስለቤተክርስቲያናችን ችግሮች ስንወያይ ግለሰቦች ላይ ከማተኮር ይልቅ የችግሩ ምንጭ እና መፍትሔዎች ላይ የሚያተኩር ውይይቶችን ማበረታታት፤
4. በብሎጉ ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ሰበብ እየፈለግንና እየተነቃቀፍን እርስ በእርስ የምንለያይበት ሳይሆን ሁሉንም የቤተክርስቲያን ልጆች በአንድነት የሚያሳትፍ እንዲሆን ጥረት ማድረግ፤ ለዚህም ማንኛውንም ዓይነት አባቶችንም ሆነ ምእመናንን ለመከፋፈል የሚሞክሩ ዘገባዎችን፣ አስተያየቶችን ያለመቀበል፤
በአጠቃላይ ደጀ ሰላማችን ሰላም እንድትሆንና የመናፍቃን መጠቀሚያ እንዳትሆን ሁላችንም በንቃት ልንጠብቃት ይገባል።

++++++++++
ደጀ ሰላም
ግለሰቦች ለሚጽፏቸው ጽሑፎች “ደጀ-ሰላም” ኃላፊነቱን አትወስድም። ደጀ-ሰላም ራሷ ያዘጋጀቻቸውን ጽሑፎች “ደጀ-ሰላም” ብላ ትጠቅሳለች። ኃላፊነቱን የምትወስደው ለነዚያ ጽሑፎች ብቻ ነው።
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)