October 14, 2009

“እጅ ስጡ ለእግዚአብሔር”:- የሽመልስ አበራ መዝሙር

(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 13/2009)፦ ይህ መዝሙር በተዋናዩና አክተሩ የመድረክ ሰው ሽመልስ አበራ (ጆሮ) የተዘመረ ነው። እንዲህ ሲል ይጀምራል፦
እጅ ስጡ ለእግዚአብሑር ለአምላካችሁ፣
ንስሐ ግቡ በዳጎኑ ቤት የነበራችሁ፣
ከባዕድ አልምኮ ከሬሞን ውጡ፣
በቁጣውም ሰይፍ እንዳትቀጡ።
መዝሙሩ ሽመልስ የሚያ አጋሮቹ የሆኑ ዘፋኞች፣ አርቲስቶች፣ ነጋዴዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ለጥንቆላ ተሰልፈው “ታምራት ገለታ” ለተባለ መተተኛ መገዛታቸው የመንፈስ ቅንዓት ፈጥሮበት የዘመረው መሆኑ ተገልጿል። እንዲህ ዓይነት ቅንዓት-መንፈሳዊ በእውነት ያስደስታል። ለእግዚአብሔር መቅናት ተገቢ ነው። “እኔ ማን ነኝ? ምን አገባኝ? እኔ ምን ለውጥ አመጣለሁ?” የሚል የዛሬዎቹ የእኛ ካህናት የገቡበት ዓይነት ንዝህላልነትና ለሃይማኖት አለመቆርቆር ተገቢ አይደለም። በነገራችን ላይ በyoutube ላይ ያቀናበረው ሌላ ሰው እንጂ አርቲስቱ ራሱ አልመሰለንምና “ለምን ፎቶህን ለጠፍክ” የሚለው አስያየት ትክክል አይለደለም። መቸም ሁሉም ባለው ነውና ሺመልስ እንዲህ ሲዘምር ሌላው ደግሞ “ቀልድ ቢጤ” ፈጥሮ “ጠንቋዩን ይሳለቅበታል”።
ሺመልስ፤ ዝማሬ መላእክት ያሰማልን።

ስለዚህ ጠንቋይ ባለ ከራማ ለማወቅ የሚከተለው ማንበብ ይጠቅማል።
++++
ባለ "ክራማ" ነኝ በማለት ወንጀሎችን በመፈፀሙ የተከሰሰው ታምራት ገለታ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት


ሪፖርተር ጋዜጣ :"ሐብታም አደርጋችኋለሁ፣ ከኤች አይቪ/ኤድስ በሽታ እፈውሳችኋለሁ፣ ልጅ እንድትወልዱ አደርጋለሁ . . ". በማለት "ለስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፍ፣ ለድህነትና፣ ንብረታቸውን ትተው እንዲሰደዱ አድርጓል" በሚል የተከሰሰው ታምራት ገለታ በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ወሰነ፡፡

ፍርድ ቤቱ ትናንትና በሰባት ተከሳሾች ላይ በሰጠው የቅጣት ውሳኔ አንደኛ ተከሳሽ ታምራት ገለታ በዕድሜ ልክ እስራት፣ ደረጀ ስሜ በአምስት ዓመትና በአምስት ሺህ ብር፣ አዲሱ ሱልጣንና በቀለ ገለታ [የታምራት ወንድም] እያንዳንዳቸው በአራት ዓመት እስራትና በሦስት ሺህ ብር፣ ኤልሳቤጥ አበራ [የአዳማ ዞን ዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ፀሐ]) አምስት ዓመትና ሦስት ሺህ ብር እና ፍሬገነት ማርዬ በሁለት ዓመት እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡

ታምራት ገለታ ባደረበት አፍቅሮ ነዋይ፣ በሕገወጥ መንገድ ለመበልፀግ አስቦ በተለያየ ሕመም የሚሰቃዩትን "እኔ አድናችኋለሁ"፣ ኤች. አይ. ቪ/ኤድስ ያለባቸውን ሰዎች መድኃኒት እንዳይወስዱ በመከልከል፣ በሽታ ጠንቶባቸው በግሉኮስ የነበሩ ሕሙማንን ግሉኮሱን በማስተውና ከፍተኛና አደገኛነት ያለው መድኃኒት በመስጠት በከፍተኛ ችግር ላይ እንዲወድቁ ማድረጉን ዐቃቤ ሕግ በቅጣት አስተያየቱ ላይ መጥቀሱን ፍርድ ቤቱ ለችሎቱ ታዳሚ በንባብ አሰምቷል፡፡

ታምራት ገለታ በተለያየ መንገድ ወደ እርሱ የተጠጉትንና የተታለሉትን በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ ችግር ከዳረገ በኋላ አቅም አጥተው ሲወድቁ በማባረር፣ በመድፈር፣ በሴተኛ አዳሪነት ተሰማርተው ያገኙትን ገንዘብ ሳይቀር በመውሰድ፣ የባለሥልጣናትን ስም በመጥራትና በማስፈራራት ከፍተኛ ወንጀል መፈፀሙን በመግለፅ ፍርዱ ከብዶ በሞት እንዲቀጣ ዐቃቤ ሕግ መጠየቁን ፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡

የተከሳሾች ጠበቃ በበኩላቸው ባቀረቡት የቅጣት ማቅለያ፤ ተከሳሾቹ በቂ ዕውቀት የሌላቸው መሆኑን፣ አቶ ታምራት ገለታ የበርካታ ቤተሰቦች አስተዳዳሪ መሆኑንና ተከሳሾቹ ከዚህ ቀደም የሰሩትና የተመዘገቡበት የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው በመሆኑ [ዐቃቤ ሕግም አረጋግጧል] ቅጣቱ ቀሎ እንዲወሰንላቸው መጠየቃቸውን ፍርድ ቤቱ በንባብ አሰምቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገኖች የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ ሀሳቦች ከሕጉ ጋር በማገናዘብ ከመረመረ በኋላ፣ ታምራት ገለታ ባለ "አውሊያ" እና ባለ "ክራማ" ነኝ በማለት ወንጀሎች መፈፀሙን በቀረበበት የሰነድና የሰዎች ምስክርነት ቃል መረጋገጡን ተናግሯል፡፡

ታምራት ገለታ ወንጀሉን የፈፀመው አደገኛ በሆነ ሁኔታ መሆኑን፣ አደገኛነታቸው የታወቀ መድኃኒት በመስጠት፣ መድኃኒት ወስደው የደከሙትን አውጥቶ በመጣልና በመድፈር፣ የባለሥልጣናትን ስም በመጥራት ዘመዶቻቸው እንዳይጠይቁት በማባረር፣ ለዓመታት በሕብረተሰቡ ዘንድ አስነዋሪ ድርጊት መፈፀሙን ፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡

በመሆኑም ዐቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ የሞት ቅጣት እንዲፈረድበት የጠየቀ ቢሆንም፤ ከዚህ ቀደም ሌላ ወንጀል ባለመፈፀሙና ሪከርድ የሌለበት መሆኑን ፍርድ ቤቱ በመረዳቱ እንደ ቅጣት ማቅለያ በመውሰድ የሞት ቅጣቱን በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን አሳውቋል፡፡

ሁለተኛው ተከሳሽ[ደረጀ ስሜ] ለበርካታ ዓመታት ሲተባበር መቆየቱን፣ አዲሱ ሱልጣንና በቀለ ገለታ፣ ታምራት ገለታን በመተባበር የማታለል ድርጊት የፈፀሙ መሆናቸውን፣ ኤልሳቤጥ አበራ ምንም ገንዘብ ያላወጣበትን ቦታ የሱ በማስመሰል የተሰማራችበትን የመንግሥት ሥራ ወደ ጎን በመተው በአዳማ ከተማ ቦታ እንዲያገኝ በማድረጓና፣ ፍሬገነት ማርዬ ከታምራት ጋር ያላትን ዝምድና በመጠቀም ከ1989 ዓ.ም. ጀምሮ ስትተባበር በመቆየቷ፤ ሁሉም ጥፋተኛ በተባሉበት የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ቁጥሮች መሠረት የቅጣት ውሳኔውን ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡

ደረጀ ስሜ አዲሱ ሱልጣን፣ በቀለ ገለታ እና ኤልሳቤጥ አበራ የእስራት ጊዜአቸውን ጨርሰው ሲለቀቁ፣ ለሁለት ዓመት ማንኛውም ሕዝባዊ መብታቸው መሻሩን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ በመጨረሻም ሁለቱም ወገኖች የይግባኝ መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን በመግለፅ ችሎቱ ተጠናቋል፡፡


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)