October 29, 2009

የአፍሪካ ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወወክማ) ሕብረት ጉባኤ አዲስ አበባ ውስጥ ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19 ቀን 2002 (ኢ.ዜ.አ) - ለአምስት ቀናት የሚቆይ የአፍሪካ ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ህብረት ጉባኤ አዲስ አበባ ውስጥ ዛሬ ተጀመረ፡፡ ኢትዮጵያ የወወክማን ጉባኤ ስታስተናግድ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስብሰባ ማእከል የተጀመረውን ጉባኤ በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹህ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ወጣቶች የወደፊቱ ህይወታቸው ብሩህና ተስፋ የተሞላበት እንዲሆን በመቻቻልና እርስ በእርስ በመደጋገፍ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ወጣቶች ነገ እንዲኖራቸው ለሚሹት መልካም ህይወት ዛሬ ላይ ቆም ብለው በእርጋታና በጥንቃቄ መራመድና ማሰብ እንዳለባቸው የመከሩት ብጹእነታቸው የአፍሪካ የወደፊት ተስፋዋ የተማሩና በስነ ምግባር የታነጹ ወጣት ዜጎቿ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ አስቴር ማሞ እንዳሉት በኢትዮጵያ በሚካሄዱ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የወጣቶችን አቅም ለማጎልበት እና ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል መንግስት ብሄራዊ የወጣቶች ፖሊሲ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በወጣቶች ዙሪያ የቀረጻቸውን ፖሊሲዎች ተግባራዊ ለማድረግም ፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ የወጣቶች የልማት ማእቀፍ አዘጋጅቷል፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ እንኳ በተለያዩ መስኮች ከ72 ሺህ በላይ የወጣት ድርጅቶች በመላው አገሪቱ ተመስርተዋል፡፡
እንዲያም ሆኖ ወጣቶች ያሉባቸው ሁሉን አቀፍ ችግሮች በመንግስት ጥረት ብቻ ይፈታሉ ብለው እንደማያስቡ ገልጸዋል፡፡ እናም ሚኒስትሯ የሁሉም አካላት የተባበረ ጥረት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር /ወወክማ/ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃኑ ታደሰ በበኩላቸው ማህበሩ በ1952 በቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡ ማህበሩ በንጉሱ ጊዜ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች መልካም የሚባሉ እንደነበሩ ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ የደርግ መንግስት ማህበሩን ሙሉ በሙሉ እንዳይንቀሳቀስ በማገዱ የማህበሩ እንቅሰቃሴ ተቋርጦ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ማህበሩ ዳግም ተመስርቶ መንቀሳቀስ የጀመረውም እ ኤ አ ከ1992 ጀምሮ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም 15 ሺህ አባላት እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ በአራት ክልሎች ዘጠኝ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አሉት፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የተጀመረው የአፍሪካ ወወክማ ህብረት ጉባኤ ዋነኛ አጀንዳም ወጣቱ ትውልድ የወደፊቱ አገር ተረካቢ በመሆኑ ከተመልካችነት ወደ ተዋናይነት እንዲሸጋገር ለማስቻል ሲሆን በየአገሩ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመገንዘብ መጪውን ጊዜ ለመቀየስ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ለመምከር ነው፡፡
ወወክማ በህብረተሰቡ ውስጥ ዝቅተኛ ህይወት ያላቸውንና ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ህጻናትን፣ ሴተኛ አዳሪዎችን፣ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ምንም አይነት የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የብሄር ልዩነት ሳያደርግ እገዛ በማድረግ ላይ እንደሆነም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወወክማ 124 አባል አገራት ያሉት የአለም አቀፉ ወወክማዎች ህብረት አባል ነው፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)