October 28, 2009

ስለ ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የሪፖርተር ጋዜጣ ሪፖርታዥ:- "የቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባዔ ያለስምምነት ተበተነ"


(ደጀ ሰላም Oct 28/2009)፦ ከዚህ በታች የቀረበው የዛሬ Oct 28/2009 የሪፖርተር ጋዜጣ ሪፖርታዥ ነው። ስለ ቅ/ሲኖዶስ ጉባዔ ጥሩ ተደርጎ ማጠቃለያ የተሠራበት ከመሆኑ አንጻር “ደጀ-ሰላም” እስካሁን ሳታሰልስ ስትዘግብ ለቆየችው ማጠናከሪያ  ይሆናል። መልካም ንባብ።
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን
+++++++


የቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባዔ ያለስምምነት ተበተነ
ልዩነት የፈጠረው የአቡነ ሳሙኤል ምደባ ጉዳይ ነው

በታምሩ ጽጌ

(ሪፖርተር፤ Oct 28/2009)፦
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ጥቅምት 11 ቀን 2002 ዓ.ም. በእርቅና በጸሎት ተጀምሮ ጥቅምት 15 ቀን 2002 ዓ.ም. ያለ ስምምነት መበተኑን ከተሳታፊዎቹ አንዳንድ አባቶች በተለይ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለጹ፡፡


ጉባኤው ያለ ስምምነት የተበተነበትን ምክንያት አባቶቹ ሲያስረዱ፣ ለጉባኤው ቀርበው የነበሩት 18 አጀንዳዎች ላይ ውይይት ተደርጐ በሰላም ካጠናቀቀ በኋላ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሳሙኤልን በእጣ እንዲመደቡ፣ በእጣው ውስጥም ከተካተቱት ትንሣኤ ማተሚያ ቤት፣ የሕፃናት ጉዳይ ድርጅት፣ የልማትና ተራድዖ ኮሚሽን እና በመንበረ ፓትርያርክ ትምህርትና ማሰልጠኛ ክፍል መካከል፣ የቤተ ክርስቲያኗ የልማትና ተራድዖ ኮሚሽን በመውጣቱና ቅዱስ ፓትርያርኩ በመቃወማቸው ነው፡፡

የአቡነ ሳሙኤልን አዲስ ምደባ በተመለከተ ከጥቅምት 14 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ አዲስ አጀንዳ የቀረበ መሆኑን የገለጹት አባቶች፤ ”የት ይመደቡ” ለሚለው ጥያቄ ቅዱስ ፓትርያርኩ፤ መቀሌ እንዲመደቡ የመጀመሪያ ጥቆማ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ብሎ ከግንቦት ወር እስከ ሐምሌ 2001 ዓ.ም. በነበረው ውዝግብ የተነሣ በትግራይ ሕዝብ በኩል ተቀባይነት ሊያገኙ ስለማይችሉ፣ በልማትና ተራድኦ ኮሚሽን ቢመደቡ የተሻለ እንደሚሆን አንድ የሲኖዶሱ አባል ሌላ ጥቆማ መስጠታቸውን አባቶቹ ገልጸዋል፡፡ “እርሳቸው ረአቡነ ሣሙኤልሪ ከውጭ ይሁኑና ምደባውን በተመለከተ እኛ እንነጋገር” በሚል ሌላ አባል ሐሳብ ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሀገረ ስብከቱ ለረጅም ዓመታት መሥራታቸውን፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ትዕዛዝ ብዙ የማይረሱ ሥራዎችን መሥራታቸውንና ብዙ ፈተናዎችንም ማለፋቸውን በመግለጽ ንግግራቸውን የጀመሩት አቡነ ሳሙኤል፤ በአንድ ቤት ታምቀው ይሠሩ ለነበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ባሠሩት ሕንፃ ውስጥ በመመደብ፣ የሀገረ ስብከቱን ሥራ ቀና እንዲሆን ማድረጋቸውን ተናግረው፤ “ጥፋተኛ ተብዬ ከሀገረ ስብከቱ ብወጣም ደስተኛ ነኝ፤ አይከፋኝም” ማለታቸውን አባቶቹ ገልጸዋል፡፡

“አባቶች ባዘዙኝ ቦታ ለመሥራት ፈቃደኛ ነኝ፡፡ አባታችንና አባቶቻችን ያሳዘንኳችሁ ካለ ይቅር በሉኝ” በማለት እርቅ ወርዶ እንደነበር አንዳንድ የጉባኤው ተካፋይ አባቶች አስታውሰዋል፡፡

አቡነ ሳሙኤል ተናግረው ሲያበቁ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ “መቀሌ መድቤዎታለሁ” ሲሉ ሌሎቹ ሁለት የሲኖዶሱ አባሎች ደግሞ የሀገረ ስብከቱን ፋይናንስ በሚያጣራው ኮሚቴ በየጊዜው ለቃለ ምልልስ ስለሚፈለጉ አሰበ ተፈሪ ወይም በአዲስ አበባ ዙሪያ ቢመደቡ የተሻለ እንደሚሆን ሐሳብ አቅርበው እንደነበር ተሳታፊ አባቶች ተናግረዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ ስለተባሉትም ሆነ ስለተጠቆሙት ቦታዎች ምንም ምላሽ ባለመስጠታቸው፤ የሲኖዶሱ አባላት የተለያዩና ጠንካራ አስተያየቶች መሰንዘራቸውን ተሳታፊ አባቶች ገልጸዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ እንደሚያዘው፣ አንድ አባት የሚመደቡት በፈቃዳቸው እንጂ በግድ መሆን እንደሌለበት በመግለፅ ተጽዕኖ መደረግ እንደሌለበት የጉባኤው አባላት አስተያየት መስጠታቸውን ተሳታፊ አባቶች ተናግረዋል፡፡

“እኔ እዚህ የመጣሁበትንና የተወለድኩበትን ዕለት ረግሜዋለሁ” በማለት አስተያየት በሰጡት አንድ አባት በሰጡት አስተያየት፣ ሦስት አባቶች ተመርጠው ቦታውን አጥንተው እንዲያቀርቡ ሐሳብ ማቅረባቸውን ታውቋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ ስብሰባው በአግባብና በስርዓት እንዲመራ እንዲያደርጉ አባላቱ መጠየቃቸውንና አንዳንዶቹም ይቅርታ በመጠየቅ አቋርጠው በመውጣት፣ ከሰዓትም ሳይመለሱ መቅረታቸውን ተሳታፊ አባቶች ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ የሲኖዶሱ አባላት በሰጡት አስተያየት፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ለማኝና ተለማኝ መሆን እንደሌለበት ተናግረው፣ “የሰላም ሲኖዶስ ከሆነ ለምን በሰላም አንፈታውም” ሲሉ ቅዱስ ፓትርያርኩ “ያላለቀ ጉዳይ አለ፡፡ ከአንድ ወር በኋላ ቅዱስ ሲኖዶሱ ይሰበሰባል፤ ወይም ይደርና እንነጋገር” በማለታቸው ለጥቅምት 15 ቀን 2002 ዓ.ም. መቀጠሩን ተሳታፊ አባቶች ተናግረዋል፡፡

ለጥቅምት 16 ቀን 2002 ዓ.ም. በይደር የተቀጠረው ጉባኤ በጸሎት ከተከፈተ በኋላ የአቡነ ሳሙኤል ጉዳይ ሦስት ሰዎች ተመርጠውና አጥንተው እንዲመጡ እንዲደረግ የሚል አስተያየት ሲነሳ፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ “ወደመረጥኩት ሀገረ ስብከት ቢሄዱ የተመረጠ ነው” ማለታቸውን ተሳታፊ አባቶች ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉዳይንና የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርት እንዲያቀርብ የተሰየመው ኮሚቴ፤ ..የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርት እንዳልደረሰለትና ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ አስተዳደርን በተመለከተ ባቀረበው ሪፖርት ችግሩ የቤተ ክርስቲያኗ መሆኑን በመናገር የምትመራበት ስርዓት እንደሌላትና ሕግም ቢኖር እርስ በርሱ የሚጋጭ መሆኑን በገለጸው መሠረት አቡነ ሳሙኤል አስተያየት መስጠታቸውን ተሳታፊ አባቶች ተናግረዋል፡፡

አቡነ ሳሙኤል በሰጡት አስተያየት፤ አጣሪ ኮሚቴው ስለ ሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉዳይ ባደረገው ሪፖርት ችግሩ በሙሉ የቤተ ክርስቲያኗ መሆኑን እንጂ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ችግር ባለመሆኑና ጥፋተኛ ስላልሆኑ ወደ ሥራቸው እንዲመልሷቸው በድጋሚ መጠየቃቸውን ተሳታፊ አባቶች ገልጸዋል፡፡

በሰላማዊ መንገድ ቅዱስ ሲኖዶሱ በፈለገው ቦታ እንዲመድባቸው በድጋሚ አስታውሰው፤ “በቀድሞ ቦታዬም ቢሆን ችግር ስለሌለብኝ በሕግም ቢሆን እገባለሁ” ብለው ከተናገሩ በኋላ፣ በሁሉም የሲኖዶሱ አባላት ዘንድ ለጥቂት ደቂቃዎች ያህል ዝምታ ሰፍኖ እንደነበር ተሳታፊ አባቶች ተናግረዋል፡፡

እሑድ ጥቅምት 15 ቀን 2002 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ባደረጉት ስብሰባ ቅዱስ ፓትርያርኩ ስብሰባውን ሲጀምሩ እንደተናገሩት፤ በግንቦት 2001 ዓ.ም. ስብሰባ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአምስት ይከፈል ሲባሉ ረአቡነ ሳሙኤልሪ አሻፈረኝ ማለታቸውን ነገር ግን ከቦታቸው ይነሱ አለማለታቸውን፤ እራሳቸው ባመጡት ጣጣ እዚህ መድረሳቸውን፣ በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ (ቪ.ኦ.ኤ) “ፓትርያርኩ ለ17 ዓመታት ምንም አልሰሩም” በማለት ስም የሚያጠፉ አንዳንድ አባቶች መኖራቸውን በመግለጽ “አታስፈራሩኝ፤ ዛቻ ለማንም አይጠቅምም” በማለት መናገራቸውን ተሳታፊ አባቶች ተናግረዋል፡፡

ከብዙ ልመናና አስተያየት በኋላ ሦስት አባቶች (አቡነ ኤልሳዕ፣ አቡነ አትናቴዎስና አቡነ ፊልጶስ) ተመርጠው አቡነ ሳሙኤል ሊመደቡ ይችላሉ ያሏቸው ቦታዎችን መምረጣቸውን የተናገሩት ተሳታፊ አባቶች፤ አራት ቦታዎች (ትንሣኤ ማተሚያ ቤት፣ የሕፃናት ጉዳይ ድርጅት፣ የልማት ኮሚሽንና የመንበረ ፓትርያርክ ትምርትና ስልጠና ክፍልን) መምረጣቸውን ተናግረዋል፡፡

ከቃለ አዋዲ ውጭ በእጣ እንዲመደቡ ቢደረግም ዕጣው ሲወጣ “ልማት ኮሚሽን” የሚለው በመውጣቱ ቅዱስ ፓትርያርኩ “በፊትም ብያለሁ፤ አሁንም አልስማማም” በማለታቸው፣ የተወሰኑ የሲኖዶሱ አባላት ጉባኤውን ጥለው በመውጣታቸው ጉባኤው ያለ ውጤት መበተኑንና ድርጊቱም ብዙ አባቶችን ያሳዘነ መሆኑን ተሳታፊ አባቶች ገልጸዋል፡፡

ለቅዳሜ ጥቅምት 14 ቀን 2002 ዓ.ም. 5፡00 ሰዓት ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል በሚል ጋዜጠኞቹ ተጠርተው የነበረ ቢሆንም “ይቅርታ ልጆቼ ስብሰባው ስላላለቀልን ለነገ (እሑድ) 9፡00 ሰዓት ተመለሱ” በማለት ቅዱስ ፓትርያርኩ አሰናብተው፣ በማግስቱ ጋዜጠኞች በተባሉበት ሰዓት ደርሰው እስከ 11፡30 ከቆዩ በኋላ “ይቅርታ ስብሰባው ለረቡዕ ስለሚቀጥል ሐሙስ ጥቅምት 19 ቀን 2002 ዓ.ም. መግለጫው ይሰጣል” በሚል አቡነ ገሪማ (የተራድኦ ልማት ኮሚሽኑ የበላይ ጠባቂ ሊቀ ጳጳስ) ጋዜጠኞቹን በድጋሚ አሰናብተዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሰ ያቋረጠውን ስብሰባ በዛሬው ዕለት ይቀጥላል ተብሎ እንደሚገመት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች አረጋግጠዋል፡፡
+++++++++

ደጀ ሰላም
በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ዜናዎችን፣ አስተያየቶችን፣ ጥያቄዎችን፣ መልሶችን የምታወጣ የጡመራ-መድረክ ናት። ግለሰቦች ለሚጽፏቸው ጽሑፎች “ደጀ-ሰላም” ኃላፊነቱን አትወስድም። ደጀ-ሰላም ራሷ ያዘጋጀቻቸውን ጽሑፎች “ደጀ-ሰላም” ብላ ትጠቅሳለች። ኃላፊነቱን የምትወስደው ለነዚያ ጽሑፎች ብቻ ነው።
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)