October 29, 2009

የአቡነ ሳሙኤል ልማት ኮሚሽን ላይ መሾም ምን አንድምታ አለው?

(ደጀ ሰላም Oct 28/2009)፦

የዛሬ ረቡዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሎ ምን ይመስላል? ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬው ውሎው በዐቢይነት በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ምደባ ዙሪያ የተጀመረውንና በእንጥጥል የተላለፈውን አጀንዳ ከዳር በማድረስ ብፁዕነታቸውን ለልማት ኮሚሽን ኃላፊ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። እስካሁን ቦታውን ይዘው የነበሩት የፓትርያርኩ የረዥም ጊዜ ቀኝ-እጅ አቡነ ገሪማ ነበሩ።

የጥቅምት የቅ/ሲኖዶስ ጉባዔን አብዛኛ ሰዓት በወሰደው የአቡነ ሳሙኤል ምደጋ ጉዳይ ቅዱስ ፓትርያርኩ ለብቻቸው፣ ሌሎች አባቶች በአንድነት የቆሙ ሲሆን ፓትርያርኩ ግን በደፈናው “አይሆንም፣ አይቻልም፤ አይቻልም ብያለኹ” በማለታቸው ብቻ ውሳኔ ሳያርፍበት ቆይቷል። ቅዱስ ፓትርያርኩ በመጨረሻ አንስተዋል እንደተባለው ከሆነ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል መቐለ ካልሄዱ የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ኃላፊ እንዲሆኑ ሐሳብ አቅርበው ነበር። በአዲስ አበባ ዛሬ እስከ 10 ሰዓት (4ፒ.ኤም) ድረስ በተካሄደው ስብሰባ ማጠቃለያ አቡነ ሳሙኤል የልማት ኮሚሽንን ቦታ መያዛቸው ተረጋግጧል። ልማት ኮሚሽን ከ1972 እ.ኤ.አ ጀምሮ የተለያዩ ምግባረ ሰናይ ተግባሮች የሚፈጸም የቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ተቋም ነው። ገጠር ልማት፣ ውሃ ማውጣት፣ በግል ንጽሕና፣ በኤች.አይ.ቪ ኤይድስ፣ በስደተኞች፣ በጾታና ዕድገት፣ በሰላም ዙሪያ እንዲሁም አህጉረ ስብከትና አጥቢያዎች ዙሪያ ፕሮጄክቶችን በመቅረጽ የሚሠራ ትልቅ ድርጅት ነው። ልማት ኮሚሽን ይህንን ሁሉ ሥራ የሚሠራ ይሁን እንጂ የሚታማበትና የሚወቀስበት ብዙ ጉዳዮች አሉ።

የመጀመሪያው ሠራተኞቹ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚቃወሙ ፕሮቴስታንቶች ጭምር መሆናቸው ነው። ስለዚህ ጉዳይ በተለያዩ ጊዜያት የተጠየቁ ኮሚሽነሮች “ዋናው ሥራቸው ነው” እያሉ ኢመልሱ ነበር። የቤተ ክርስቲያኒቱን ደሞዝ እየበሉ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚሰድቡት እነዚህ ሰዎች ለምን እንደዚያ እንዲያደርጉ እንደሚፈቀድላቸው ለብዙ ኦርቶዶክሳውያን የሚገርም ጉዳይ ነበር።

ሁለተኛው የልማት ኮሚሽን ችግር ገንዘቡ በጥንቃቄ ለታለመለት ሥራ ብቻ እንደማይውል መታማቱ ነው። በዚህ ጉዳይ ከሚታሙት ሰዎች መካከል ደግሞ ቅዱስ ፓትርያርኩ አንደኛው ናቸው። ፓትርያርኩ ለገንዘብ ብክነቱ አስተዋጽዖ አድርገዋል የሚባሉት “የሥጋ ዘመዶቻቸውን” ያለ ብቃታቸው በመመደባቸው ነው። ለዚህ ዓይነቱ ሕገ ወጥነት ሌላው አስተዋጽዖ የሚያደርጉት በበላይ ጠባቂነት የሚሾሙ እንደ አቡነ ገሪማ ያሉ ጳጳሳት ናቸው። የአቡነ ሳሙኤል በቦታው መሾም ትልቅ አንድምታ የሚኖረው ከዚህ አንጻር ነው። በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ላይ እንደታዩት ከሆነ ለዚህ ዓይነቱ የሙስና ተግባር አይመቹም፣ የሥራ ሰውም ናቸው፣ ለቤተ ክርስቲያናቸውም ፍቅር አላቸው።

ቅ/ሲኖዶስ በዚህ የጥቅምት ጉባዔው 17 አጀንዳዎች ላይ የተወያየ ሲሆን ነገ ማጠቃለያ ተደርጎ ለጋዜጠኞች መግለጫ ከመሰጠቱ በፊትም ሌሎች “ጥቃቅን” ጉዳዮች ላይ ሊወያይ ይችላል።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)