October 21, 2009

የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ነገ ይጀመራል፣ አባቶች ምንም እንዳይናገሩ እየተነገራቸው ነው፤

• የመንግሥት ባለሥልጣናት ብፁዓን አባቶችን ለብቻ ለማነጋገር ሞክረዋል


(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 21/2009)፦ በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ነገ ሐሙስ ጥቅምት 12/2002 ዓ.ም (10.22.2009) እንደሚጀመር ሲጠበቅ ዓመታዊው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ በበኩሉ በትናንትናው ዕለት ተፈጽሟል። ዛሬ በዋዜማው ጸሎት ይደረጋል። በዚህ ጉባዔ ለመገኘት አባቶች የተሰባሰቡ ሲሆን ያለፈውን ተቃውሞ የመሩት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ግን መታመማቸው ታውቋል። ከሕመማቸው አገግመው ከስብሰባው ይገኙ አይገኙ እንደሆነ አላወቅንም።

በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከናወነው የቅ/ሲኖዶስ ጉባዔ በጉጉት እንዲጠበቅ ያደረገው በቅዱስ ፓትርያርኩና በቅ/ሲኖዶስ አባላት መካከል በተነሣው የሕገ ቤተ ክርስቲያንና የአስተዳደር ጉዳይ ልዩነት መሆኑ ሲታወስ በዚሁ ሰበብ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከሥልጣናቸው መታገዳቸው አይዘነጋም።

ባለፈው ግንቦት በጀመረውና እስከ ሐምሌ አጋማሽ በዘለቀው ልዩነት ቅዱስ ፓትርያርኩ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን አልቀበልም በማለት ሲገፉ፣ የእርሳቸውን ሐሳብ እንደግፋለን የሚሉ ወገኖች ደግሞ የርሳቸውን ተቃዋሚ አባቶች ቤት በመሰባበር፣ አባቶችን በማፈንና ዛቻና ማስፈራሪያ በማድረስ ታሪካዊ ስሕተት ፈጽመዋል። እስካሁን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ባልዋሉት በነዚህ ወንበዴዎች ድርጊት የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በእጅጉ ያፈሩ ሲሆን ድርጊቱ በየአቅጣጫው ሲወገዝ መቆየቱ ይታወሳል። የድርጊቱን ፈጻሚዎች ማንነት ለማጣራት በተደረገው ግላዊ አሰሳ ነገሩ ከፓትርያርኩ አቡነ ቀሲስ (የቅርብ ረዳት) የወጣ ትዕዛዝ መሆኑ ላይ የደረሰ ሲሆን የመንግሥት የደህንነት ክፍል እጅም እንዳለበት አሳማኝ ፍንጮች አሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ እሸመግላለሁ በማለት ላይ የሚገኙት የመንግሥት የደህንነት መሥሪያ ቤት ሃላፊ አቶ አባይ ፀሐዬ በትግራይ አህጉረ ስብከት የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳትንና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሰዎች በመሰብሰብ ልዩ ምክክር ማድረጋቸው ታውቋል። በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አባቶች አነሳሽነት የተንቀሳቀሰውንና ቤተ ክርስቲያኒቱን ከፓትርያርክ ጳውሎስና ከዘመዶቻቸው አስነዋሪ አስተዳደር ለመታደግ በተጀመረው እንቅስቃሴ እረፍት ያጣው መንግሥት የትግራይን ጳጳሳት በመሰብሰብ “አረጋጉ” ማለቱ ታውቋል። ማረጋጋት ማለት አቡነ ጳውሎስን አትናገሩ፣ ፀጥ እረጭ ብላችሁ ተገዙላቸው፣ ቤተ ክርስቲያናችሁ ስትጠፋ ተመልከቱ ማለት እንደሆነ ለጊዜው አልታወቀም።
በሌላም በኩል ሰሞኑን የደረሱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ የመንግሥት ተወካዮች በቀጥታ በቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ በመግባት አባቶች ስለ ፓትርያርኩ ምንም እንዳያነሡ መመሪያ ቢጤ በመስጠት ላይ ናቸው። “እርሳቸው ተሻሽለዋል፤ ችግሩ ይፈታል” በሚል ማግባቢያ በመደለል ላይ ያሉት እነዚሁ ባለሥልጣናት በቤተ ክህነቱ ያለው ሙስናና የዘር አሠራር “ተሻሽሏል” ለማስባል የተወሰኑ የፓትርያርኩ ዘመዶች ከቦታቸው እንዲነሡ ተደርገዋል። በዚህም መሠረት የፓትርያርኩ ረዳት አቶ ሙሉጌታና ፀሐፊያቸውና የምታስሾመው የምታስሽረው አፀደ የተባለች ዘመዳቸው የተቀየሩ ሲሆን እነዚህን ሰዎች ማንሣታቸው “የቤተ ክርስቲያንን ችግር እንደቀረፉ” ተደርጎ እንዲቆጠርላቸው ያደረጉት መሆኑ ታውቋል።
ከዚህ ባሻገር የተቃውሞ በሮችን ሁሉ ለመዝጋት “ይናገራሉ” ተብለው የሚታሰቡ አባቶች ላይ የተጀመረው የስም ማጥፋት ዘመቻ ተጧጡፏል። ራሱን የፓትርያርኩ ሕጋዊ ወኪል ነኝ የሚለውና ከዚህ በፊት በጥንቆላ ሥራ ላይ ተሰማርቶ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ሲነግድ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ሕጋዊ ክስ አቅርበው ሥራውን ያቆሙበት “ጌታቸው ዶኒ” (አሁን ቄስ ነኝ ባይ) በተባለው ሰው በተጻፈና ትናንት ለሕትመት በበቃ “መሰናዘሪያ” በተሰኘ የአዲስ አበባ ጋዜጣ ላይ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልና ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጥቃቱ ዒላማ ሆነዋል። ይኸው ግለሰብ ከዚህ በፊት “ኢትዮ-ቻነል” በተባለ ጋዜጣ ላይ አባቶችን የሚያብጠለጥል፣ ፓትርያርኩ ተጠሪነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ መሆን የለበትም ቅ/ሲኖዶስ ለፓትርያርኩ ተጠሪ መሆን አለበት የሚል ጽሑፍ ያወጣ መሆኑ ይታወሳል። ግለሰቡ የቤተ ክርስቲአንን ችግር በማጣመም “መፈንቅለ ፓትርያርክ ሊደረግ ነው፤ ማህበረ ቅዱሳን ፓትርያርኩን ሊገለብጥ ሲል ተያዘ” ማለቱም ታውቋል።
በሌላም ነገ በሚጀመረው በዚሁ ጉባዔ ላይ የማህበረ ቅዱሳን ጉዳይ ይነሣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከጉባዔው የተወሰኑ ቀናት ቀድሞ አባ ሰረቀ ብርሃን የተባሉት የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ሃላፊ የጻፉት ማህበረ ቅዱሳንን የተመለከተ ደብዳቤ ለሰበካ ጉባዔ ስብሰባ ለመጡት አባቶች መታደሉ ታውቋል። የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ስለ ማህበረ ቅዱሳን የተደረገው ስብሰባ ውጤት ይዟል የተባለው ይኸው ደብዳቤ በዋና ሥራ አስኪያጁ በብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ፊርማ እንዲወጣ ሲጠበቅ ብፁዕነታቸው “ስብሰባውን አላምንበትም፤ ደብዳቤውንም አልጽፍም” በማለታቸው አባ ሰረቀ እንደጻፉ ታውቋል። ከደብዳቤው በተጨማሪም የስበሰባው ቃለ ጉባዔ ነው የተባለና በዕለቱ የተገኙ አባቶች የፈረሙበት ወረቀት ተያይዞ የቀረበ ሲሆን ስለ ጉዳዩ አስተያየታቸው እንዲሰጡ የተጠየቁ ስብሰባው ላይ የተካፈሉ አባቶች ግን ቃለ ጉባዔው ላይ አለመፈረማቸውን፣ የሆነ ሰው የነርሱን ፊርማ አስመስሉ መፈረሙን ተናግረዋል። ጉዳዩንም በቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ በቁጭት ተናግረዋል። “ይህንን ሁሉ የሚያደርገው ሰረቀ ነው፤ እንዴት ፊርማችንን አስመስሎ ይፈርማል” ማለታቸውንም ምንጮቻችን ገልጸዋል።

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)