October 26, 2009

ኢህአዴግና የሃይማኖት ፖለቲካ

(በየማነ ናግሽ)
(Reporter:Oct.25/2009):-ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ እዚህም እዝያም የሃይማኖት ግጭቶች ተከሰቱ ሲባል መስማት የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ የሃይማኖት አባቶች ያለ አንዳች ልዩነት የእያንዳንዳቸው ሃይማኖት አቋም ሰላምን መስበክ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ በበኩሉ በሃይማኖት ሽፋን የሚነሱ እነዚህ ግጭቶች መንስኤ ሃይማኖቶች ውስጥ ተወሽቀው በሽፋንነት የሚጠቀሙ ፖለቲከኞች እንዳሉ ይፈርጃል፡፡ የአክራሪነት አስተሳሰብም ከኪራይ ሰብሳቢነት ነጥሎ ማየት እንደማይቻል ይገልፃል፡፡ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፣ ኢህአዴግ የሚጠቀምበት አንዱ የማሸማቀቂያ መንገድ መሆኑን በመግለፅ፣ “ፍረጃውን” ያስተባብላሉ፡፡

ሥልጣን ላይ ያለው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ፣ በቅርቡ ከፍተኛ ትኩረት እሰጣችኋለሁ ከሚላቸው አጀንዳዎች መካከል የሃይማኖት ጉዳይ ዋነኛ እየሆነ መጥቷል፡፡ በየሁለት ወሩ ለህትመት የሚበቃው የድርጅቱ የንድፈ ሃሳብ መፅሄት በተከታታይ ሰፊ ትንታኔ ከሰጠባቸው ጉዳዮች የሃይማኖት ግጭቶችና አክራሪነት ይገኝበታል፡፡ በቅርቡ የወጣው 2ኛ ዓመት ቅፅ 2 ሐምሌ - ነሐሴ 2001 “አዲስ ራዕይ” መጽሔት፣ ከአመራር መተካካተ ቀጥሎ ሰፊ ትንታኔ የተሰጠበት ጉዳይ “የሃይማኖት አክራሪነት”ን ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከዚህ በፊት ባወጣው “አዲስ ራዕይ” መጽሔትም የሃይማኖት ግጭቶች መንስኤና ተያያዥ ጉዳዮች ተንትኗል፡፡

ኢሕአዴግ በሃይማኖት ሽፋን እየተነሱ የሚገኙ ግጭቶች እያሳሰበው እንደሆነ ለጉዳዩ ከሰጠው ሰፊ ሽፋንና ትንታኔ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ገዢው ፓርቲ በተለይ በምርጫ 97 ተሸነፉ የሚላቸውና ሌላ አማራጭ ፈልገዋል የሚላቸው ተቃዋሚዎች “የከሰሩ ፖለቲከኞች” ብሎ የሚጠራቸው ሲሆን፣ የሃይማኖት ሽፋን በመጠቀም ግጭቶች እየቀሰቀሱ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ እነዚህ በተለይ በእስልምናና በክርስትና ሃይማኖት ተወሽቀው ግጭት እይቀሰቀሱ ነው ያላቸው ፖለቲከኞች ለግጭቶቹ መነሻ ዋነኞች መሆናቸው የወነጀለ ሲሆን፣ አሁን ያለው ስርዓትና ራሳቸው ሃይማኖቶች የመከባበርና የመቻቻል እንጂ የግጭት ምንጭ እንዳልሆኑ መንደርደሪያውን ያስቀምጣል፡፡ ተቃዋሚዎች ግን ውንጀላውን አይቀበሉትም፡፡ ይልቁንስ ይህንን ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎችን የማሸማቀቅ ተግባር እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

ኢሕአዴግ የሃይማኖት አክራሪነት ከሰላምና ልማት ማስፈን አንፃር የተመለከተበት ሁኔታ አለ፡፡ በተለይ ከዴሞክራሲ አንፃር የሃይማኖት ነፃነት፣ የሃይማኖት እኩልነት፣ የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት ከኢፌዲሪ ህገመንግሥትና ከስርዓቱ አንፃር ሰፊ ትንታኔ ሰጥቶበታል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተከታይ ብዛትም ሆነ በአመጣጣቸው ግንባር ቀደም ሚጠቀሱት የእስልምናና የክርስትና እምነት መካከል የሚፈጠረው ግጭት፣ ብዙዎችን ያሳስባል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተለመደና አዲስ ክስተት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መምጣት መንግሥት፣ ሕዝብንና ምሁራንን እያነጋገረ ነው፡፡ አንዳንድ ምሁራን በግጭቶቹ መነሻ ጥናት በማቅረብ መፍትሄ ይሆናል ያሉትን እየጠቆሙ ነው፡፡ ሕዝቡም በተለያዩ አጋጣሚዎች እነዚህ ግጭቶች የጥቂቶች አጀንዳ እንደሆነ ሲገልፅ በስፋት ይስተዋላል፡፡ የሃይማኖት አባቶችም ቢሆኑ፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ ሃይማኖትን መሰረት አድርገው የሚነሱ ግጭቶች ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ እንደሆኑ ይገልፃሉ፡፡ በየፈርጃቸው ሰላምንና ፍቅርን ይሰብካሉ፡፡ የእያንዳንዱ ሃይማኖት ተከታዮችም ግጭት ቀስቃሾቹን ለሕግ እንዲቀርቡ ሲጠይቁ ይስተዋላሉ፡፡ ታዲያ የሃይማኖት ግጭቶች መንስኤ ምንና ማን ይሆን?

መንግሥታት ስልጣናቸውን ከሃይማኖት የመነጨ አድርገው በሚሰብኩበት ወቅት፣ አንድን ሃይማኖት (ከመንግሥት ጋር የተጠጋው) በሌሎች ላይ የበላይ ሆኖ ሌሎችን ሲጨቆን የነበረበት ሁኔታ ሩቅ አይደለም፡፡ በአሁኑ ዘመን ግን በአብዛኛው የዓለም መንግሥታት የሚከተሉት መርህ ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩበት አንዱ በሌላው ላይ ጣልቃ የማይገቡበት ሴኩላር መንግሥት (Secularism) እየተባለ የሚጠራው ነው፡፡ ኢትዮጵያም ውስጥ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በተዋረድ የመጣው ስርወ መንግሥት እስከ አፄ ኃ/ሥላሴ ዘመን ሃይማኖትና መንግሥት የተደባለቁበት ሁኔታ ስለነበር፣ ክርስትና (ኦርቶዶክስ) እምነት የበላይ የሆነበትና ሌሎች በእኩል የማይታዩበት ሁኔታ ነበር፡፡ በደርግም ጊዜ መንግሥትና ሃይማኖት እንዲለያዩ ቢደረግም፣ ሃይማኖቶች እንደፈለጉ በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት ማዕቀፍ አልነበረም፡፡

ኢሕአዴግ ባስፀደቀው የኢፌዲሪ ህገመንግሥት፣ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ እንዲሆኑ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ማንኛውም ሰው እምነቱ በነፃነትና በእኩልነት እንዲተገብርና እንዲያስፋፋ የሚፈቅድ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ ታሪክ በሕዝቡ መካከል የነበረው የመቻቻልና የእርስ በርስ መከባበር የሚያደፈርስ ግጭቶች እየታዩ ነው፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲ ስለ አክራሪነት

ኢህአዴግ እንደሚለው፣ የሃይማኖት አክራሪነት የተለያዩ ወገኖች በተለያየ መመዘኛ ቢያዩትም፣ ድርጅቱ ከራሱ ስርዓት አንፃር ይመለከተዋል፡፡ “የዴሞክራሲ ስርዓታችን ሁሉም ዜጎች የእምነት ነፃነት እንዳላቸው ያስቀምጣል፡፡ ዜጎች የራሳቸውን የእምነት ነፃነት ማስከበር ይችሉ ዘንድ የሌላውን የእምነት ነፃነት መከበር እንዳለበት ያስቀምጣሉ፡፡ አክራሪነት የምንለው ይህንን መሠረታዊ የዴሞክራሲ መርህ በሃይማኖት ሽፋን መቃወም ነው” ይላል፡፡

ኢሕአዴግ ይህ የአክራሪነት አመለካከት በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ የሚታይ እንደሆነ፣ በአንድ ሃይማኖት ውስጥም የተለየ አመለካከት ባላቸው ላይ አክራሪነት በተግባር እንደሚታይ ይናገራል፡፡ “አክራሪነት በአንድና ሁለት ሃይማኖቶች ብቻ ያልታጠረና አንዱ መሠረታዊ መገለጫው የራሱን የእምነት ነፃነት የሌላን ዜጋ የእምነት ነፃነትን በመሸራረፍ በማፈንና በማንቋሸሽ ለማስከበር የሚደረግ መሆኑ ነው፡፡ ይህ አመለካከት በሃይማኖት ሽፋን የሚካሄድ ፀረ ዴሞክራሲ ነው” ይላል፡፡

ይህ በሁሉም ኃይማኖቶች ተከታዮች የሚፈፀም ፀረ ዴሞክራሲ አመለካከት እንደሆነ ሲያስረዳ፣ ..ጥቂት ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች እንደ ድሮው ሁሉ ኦርቶዶክስ ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት እንዲሆን፣ ከሌሎች የተለየ መብትና ጥቅም እንዲኖረው ይመኛሉ፡፡ . . . በሌላ በኩል አንዳንድ ሙስሊሞች የሃይማኖት ብዙኅነት ባለበት አገር እነሱም እስልምና ነው ብለው ያመኑበት መመሪያ በመንግሥትና በመንግሥት ተቋሞች አማካኝነት እንዲፈፀም፣ እስልምና የመንግሥት ሃይማኖት እንዲሆን ሲከጅሉ ይታያሉ.. በማለት በተለያየ ደረጃም ቢሆን “የአክራሪነት ዝንባሌ የተጠናወታቸው” የሁሉም ሃይማኖቶች አባላት እንዳሉ ይገልፃል፡፡

አክራሪነት - ኪራይ ሰብሳቢነትና የ..ከሰሩ ፖለቲከኞች..

ኢሕአዴግ እያንዳንዱ ሃይማኖቶች ውስጥ አሉት ካላቸው የአክራሪነት አመለካከቶች በተጨማሪ፣ የአክራሪነት ምንጭ ያላቸው ሃይሎች መኖራቸውን ይገልፃል፡፡ ድርጅቱ በዋናነት በኢትዮጵያ ለሃይማኖት አክራሪነት ምንጮች የሚላቸው የታሪክ ቅሪትና ዓለም ዓቀፉ የአክራሪነት ዘመቻ ናቸው፡፡ ድርጅቱ እነዚህ ምንጮች በኢትዮጵያ ተፅዕኖ የሚያሳድሩበት ሁኔታ፣ እነዚህ የአክራሪነት አመለካከቶች ሊያስተናግድና ሊቀበል የሚችል የፖለቲካ ሁኔታና የፖለቲካ ሃይሎች መኖራቸውን ያምናል፡፡

ኢሕአዴግ በዚህ የአክራሪነት አመለካከት ምቹ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ድህነትና ኋላ ቀርነት በግንባር ቀደምትነት ይጠቅሳል፡፡ ይህንን የሚያስረዳውም፣ በቅረቡ በአዲስ አበባ በርካታ ሕዝብ ለችግር የተጋለጠበት የአተት በሽታ “አለመማርና ኋላ ቀርነት” የወለደው እንደሆነ፣ በጠበል ቦታዎች የሆነውን በመግለፅ ነው፡፡ ሁኔታው በማንም ሌላ ሰው ላይ ቀጥተኛ ጉዳት ባያደርስም፣ ጠበሉ የታጠቡ ሰዎች ያስከተለባቸው የአተት በሽታ እንደመፈወስ መመልከታቸው ኋላ ቀርነትና አለመሰልጠን ..ከአክራሪ አመለካከት.. ጋር እንዴት ሊዛመዱ እንደሚችሉ ድርጅቱ ተመልክቷል፡፡

እንደ ገዥው ፓርቲ ትንታኔ፣ ድህነትና ኋላ ቀርነት ግን የአክራሪነት አመለካከቶች እንዲስፋፉ ይፈቅድ እንደሆነ እንጂ የአክራሪነት እንቅስቃሴ መፍጠር አይችሉም፡፡ ድርጅቱ አገሪቱ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ያላትን የታሪክ ቅሪትና ዓለም አቀፍ አክራሪነት የሚያራግቡ የፖለቲካ ሃይሎች ናቸው ሲል በተቃዋሚዎች ላይ ጣቱን ይቀስራል፡፡

“በአገራችን የአክራሪነት አደጋ ቀላል ተደርጎ የማይወሰድበት ደረጃ ላይ የደረሰው ይህንኑ በማራገብ የፖለቲካ አላማቸውን ለማራመድ የሚፈልጉ የጥፋትና የኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች ስላሉ ነው” የሚለው ኢሕአዴግ፣ አንዳንድ ዓማፂ ሃይሎች በተለይ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ያካሂዱታል ያለው የጥፋት ሥራ በመግለጫነት ያስቀምጣል፡፡ አገር ውስጥ ያሉት ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ፣ ህጋዊና ህገወጥ ተግባራትን እያጣመሩ ይህንን አመለካከት ከማራገብ ወደ ኋላ አይሉም ይላል፡፡

ኢሕአዴግ እንደሚለው ተቃዋሚዎች ህብረተሰቡ በጥፋት መንገድ ለመምራት፣ ሁለት መንገድ ይጠቀማሉ፣ ብሔርና ሃይማኖት፡፡ በአሁኑ ወቅት የብሔር ጥያቄ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እልባት ያገኘ በመሆኑ፣ ሃይማኖትን በሽፋን ለመጠቀም በአማራጭነት እንደሚጠቀሙበት ይወነጅላል፡፡ “ዋናው መሳሪያቸው ትምክህተኝነትና ጠባብነት በማራገብ በብሔር ጥያቄ ዙሪያ ለመፍጠር የሚሞክሩት የጥፋት እንቅስቃሴ ቢሆንም ሃይማኖትንም በመሳሪያነት ከመጠቀም አልቦዘኑም”፡፡

ኢሕአዴግ ቀደም ብሎም እንዳለው “የከሰሩ ፖለቲከኞች” የሚላቸው “ህጋዊና ህገወጥ” መንገድ እያጣቀሱ የሃይማኖት አክራሪነት ያራግባሉ የሚላቸው ተቃዋሚ ወገኖች እነማን እንደሆኑ ተጨባጭ ምሳሌ ባያቀርብም፣ የኤርትራ መንግሥት ጀሌዎች የሚላቸው እንደ ኦነግ የመሳሰሉ ሃይሎች ግን ይጠቅሳል፡፡ በተለይ ሃዋርጂያ የተባለው የእስልምና አክራሪ ቡድን አባላት አብዛኛዎቹ የኦነግ አባላት የነበሩና በምህረት የተፈቱ እንደሚገኙባቸው ይጠቁማል፡፡ ገዥው ፓርቲ እንደሚለው፣ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ውስጥ ትርምስ ለመፍጠርና ከሌሎች ተከታዮች ጋር ግጭት ለመቀስቀስ የሚሞክሩት የደርግና የተለያዩ የትምክህት ሃይሎች ቅሪቶችም አሉ፡፡ “ከ97 ምርጫ በኋላ አንዳንድ በአሜሪካ የሚገኙ ጳጳሳት ቅንጅት በመራው ሰልፍ ላይ የሃይማኖት አባትነት ካባቸውን እንደለበሱ ከመሰለፍም አልፈው አስተባባሪ ሆነው መታየታቸው በቂ ማረጋገጫ ነው” ይላል፡፡ አንዳንዱም የገንዘብ ምንጭ አድርገው ይጠቀሙበታል የሚለው ኢሕአዴግ፣ “የሃይማኖት አክራሪነትና ኪራይ ሰብሳቢነት በአገራችን ያላቸው የማይነጣጠል ትስስር” መገንዘብ የአክራሪነት ባህሪና ገፅታ ለመረዳት ያስችላል የሚል እምነት አለው፡፡

በእርግጥ፣ ኢሕአዴግ እንደሚለው ተቃዋሚዎች በሃይማኖት ግጭት እናተርፋለን ብለው ያስባሉ? ወይስ ገዥው ፓርቲ ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ተቃዋሚዎችን እየፈረጀና እየነጠለ ይሆን? በትክክል በእንደዚህ ዓይነት ወንጀል የተሰማሩ ተቃዋሚዎችስ ሕግ ፊት መቅረብ የለባቸውም? ተቃዋሚዎችስ በሃይማኖትም ሆነ በብሔር ሽፋን ግጭት እንዳይቀሰቀስ ምን ያህል ጥንቃቄ ያደርጋሉ? የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች በጉዳዩ ላይ ሊነሱ የሚችሉ ናቸው፡፡

በዓማፂነት እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ሃይሎች መንግሥት እንደሚለው ሁሉ ከደሙ ንፁህ ናቸው ማለት ይከብዳል፡፡ በተለያዩ መንገዶች የኢትዮጵያን አንድነት ለማተራመስ ሌት ተቀን ደፋ ቀና ከሚለው የኤርትራ መንግሥት ጋር ..እጅና ጓንት.. ሆነው የሚሰሩ ወገኖች የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማራመድ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴና ከሚያወጡዋቸው መግለጫዎች መገንዘብ እንደሚቻል ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ በአገር ውስጥ በህጋዊነት የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ግን “አጠቃላይ ፍረጃ” ይሉታል፡፡

አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፣ ኢሕአዴግ በአገር ውስጥ በሚፈጠር ማንኛውም ጥፋትና ችግር በእነሱ ላይ ማላከክ ይወዳል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን ከሚጠቡበት መንገድ አንዱ እንደሆነና ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች ከሕዝብ ለመነጠል፣ ለማጥቃትና ለማሸማቀቅ እንደሚጠቀምበትም ይገልፃሉ፡፡ “ይህንን ግን ለችግሩ መፍትሄ አይሆንም” ይላሉ፡፡

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ሃይሉ አርአያ፣ “የሃይማኖት የአክራሪነት አመለካከት ምንጭ የ፣ከሰሩ ፖለቲከኞች፣ ናቸው” የሚለውን የኢሕአዴግ ፍረጃ “ራሱ የከሰረ አመለካከት” ይሉታል፡፡ ዶ/ር ሃይሉ ለሪፖርተር እንደገለፁት፣ “ኢሕአዴግ ራሱ የፈጠረውን ችግር መፍታት ሲያቅተው በእኛ ላይ ማላከክ አመሉ ነው” ያሉ ሲሆን በገዢነት ደረጃ እንዲህ የዘቀጠ አስተሳሰብ ማራመዱ አሳፋሪ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ ለሃይማኖት መከባበር እንጂ ለግጭት ምክንያት የምንሆንበት ምንድን ነው? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው፣ ይህንን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ ኢሕአዴግ ማንኛውም ዓይነት ችግር ሲፈጠር በጉዳዩ ላይ ከማተኮር ይልቅ “እገሌ ያለው ነው፣ እገሌ ያስተጋባው ነው” በማለት በተቃዋሚዎች ላይ ጣቱን ይቀስራል ብለዋል ለሪፖርተር፡፡ እንዲያውም፣ የሕዝቡ የአስተሳሰብ ንቃተ ህሊና ዝቅ አድርጎ የመመልከት ውጤት መሆኑን ይናገራሉ አቶ ገብሩ፡፡ “ሕዝቡ የቧንቧ ውሃ አይደለም፡፡ በተወሰኑ ቡድኖች አመለካከት ብቻ የሚነዳ”፡፡ በሃይማኖትም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች የሚነሱ ግጭቶች የራሳቸው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መነሻ እንደሚኖራቸው ገልፀው፣ ያንን ከስርዓቱ አንፃር ከመፈተሽ ይልቅ ተቃዋሚዎች የፈጠሩት ችግር ነው ማለት በራሱ መፍትሄ አይሆንም ይላሉ፡፡ “ስልጣንን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ መኖር የሚፈልግ ነው ግጭቶች እያባባሰ የሚንቀሳቀስ”ም ይላሉ፡፡ አቶ ገብሩ፣ በሃይማኖት ዙሪያ ግጭት የሚቀሰቅስ ወገን አይተውም ሰምተውም እንደማያውቁ ገልፀው፣ “ይሄ የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የሕግም ጥያቄ ነው፡፡ እንዲህ ያደረገ አካል ካለ ሕግ ፊት መቅረብ ይኖርበታል” ይላሉ፡፡

ኢሕአዴግ የሃይማኖት አክራሪነት አመለካከት ከኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ከኋላ ቀርነት የሚያይዘው ሲሆን፣ እንደ መንግሥትም እንደ ድርጅትም በተደራጀ መልኩ የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ እንዲህ ዓይነት አመለካከቶች በሕግም ሆነ በፖለቲካ እታገላቸዋለሁኝ ይላል፡፡ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው እነዚህ አመለካከቶችና ግጭቶች አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታ የፈጠራቸው በመሆኑ፣ መንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ ጣት ከመቀሰር ፖሊሲውና ችግሩ ላይ እንዲያተኩር ያሳስባሉ፡፡ የሃይማኖት አባቶች የሚሰብኩት ሰላም የሚደነቅ ቢሆንም፣ በሃይማኖት ተቋማት የሚሰራጩ አንዱ በሌላው ላይ ያነጣጠሩ አንዳንድ ጽሑፎች መታረም እንዳለባቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡


3 comments:

Anonymous said...

ያበየን ወደእመየ!!!

Anonymous said...

"ያብዬን፡ወደ፡እምዬ"እንደሚባለው፡ነው።

በአገራችን፡ኢትዮጵያ፡ውስጥ፡ይህን፡የጥላቻና፡የጥ
ፋት፡እሳት፡ማን፡እንደለኮሰው፣የማንን፡አጀንዳ፡ተ
ደግፎ፡እንደገባና፡አሁንም፡በነማን፡እንደሚስፋፋ፡
የታወቀ፡ጉዳይ፡ነው።

እንዲህም፡አርጎ፡"አዲስ፡ራዕይ፡"የለ!
በርግጥ፡የኢትዮጵያን፡ሕዝብ፣በተለይም፡ተዋህ
ዶ-ኦርቶዶክሱን፡ለይቶ፡ለማጥቃትና፡ለማስጠቃ
ት፡የማይመለስ፡ኃይል፡ሥልጣኑን፡በመያዙ፣ተግ
ራኝ፡ወዲህ፡በአገራችን፡ታይቶም፡ተሰምቶም፡ያል
ታወቀ፡አክራሪ፡እስልምና፡እየፈጸመ፡ያለውን፡ግድ
ያና፡ጥፋት፡ሁሉም፡የሚያውቀው፡ነው።

ተገዳዮችና፡ተፈናቃዮችም፡የተዋህዶ፡ክርስቲያ
ናት፡መሆኑንስ፡ማን፡አጣው?የተቃጠሉትና፡የተ
ዘረፉት፡አድባራትስ፡ያልታወቁ፡ሆኖ፡ነው?በለው፡
ይህን፡ነፍጠኛ፡እያሉ፡መነኮሳትን፡ጭምር፡ያስገደ
ሉት፡እነ፡አቶ፡ታምራት፡ላይኔና፣አዲሱ፡ለገሠ፡አል
ነበሩም?!

ይህ፡ሁሉ፡ግፍ፡ሲፈጸምብን፡ጆሮ፡ዳብ፡ብለው፡ቤ
ተክህነትን፡በዓመፅና፡በዝምድና፡በአገር፡ልጅነት፡
አፍነው፡የያዟት፡ሰዎችስ፡ምን፡አደረጉ?ዛሬስ፡ም
ን፡እያደረጉ፡ነው?ኢልዛቤልስ፡ብቅ፡ያለችው፡
ብቻዋን፡ይሆን፡እንዴ?

ጳጳሳት፡እየተደበደቡና፡በማስጠንቀቂያ፡እንዲሠ
ሩ፡የሚደረገውስ፡በማን፡ሆነና፡ነው?የሲኖዶስን፡ስ
ብሰባ፡ያስደፈረውና፡ደፍረውስ፡የገቡት፣ትዕዛዝም፡
በመስጠት፡ላይ፡ያሉት፡እነማን፡ናቸው?ከነማንስ፡
ወግነው፡ነው፡እንዲህ፡ያለ፡ጥቃት፡በተዋሕዶ-ኢት
ዮጵያ፡ላይ፡የሚፈጽሙት?

ለመሆኑ፡አሁንስ፡ይህ፡የጥፋት፡ፖለቲካ፡መነጥራቸ
ው፡ከዘርና፡ከመንደር፡ባሻገር፡ይመለከታል?የመመ
ልከትስ፡ፍላጎት፡አለው?ዓመታት፡እየተከታተሉ፡አ
ለፉኮ፡ዛሬ፡ይሻላቸው፡ይሆን፡ነገ፡ስንል!

ውጤቱ፡ግን፡የተተከለባቸው፡ዓመፅ፡ሰውን፡ከመና
ቅ፡አልፎ፡እግዚአብሄርንም፡ወደ፡መጋፋቱ፡አድርሷ
ቸዋል።እንደገቡስ፡ራሳቸውን፡"ተራሮችን፡ያንቀጠ
ቀጠ፤ትውልድ፡"በማለት፡መጪውን፡ሥራቸውን፡
ጠቁመውን፡አልነበረም?የተረዳ፡ተረድቶታል።

ኢትዮጵያ፡አገራችን፡ታላቅ፡ፈተና፡ተደቅኖባታል።
ከሁላችሁም፡የበለጠ፤እኔ፡አውቃለሁ፤እኔ፡ያልኩት
ን፡ብቻ፡መቀበል፡አለባችሁ፡የሚል፡እግዚአብሄርን
ም፡የደፈረ፡የጥፋት፡ሥራዓት፡ጫንቃችን፡ላይ፡እን
ደወደቀ፡ከተረዳን፡ቆይተናል!


አቶ፡ተፈራ፡ዋልዋ፡ተዋህዶ፡ኦርቶዶክስ፡ቤተ፡ክር
ስቲያናችንን፡"የትምክህተኞች፡መሸሸጊያ፡"በማ
ለት፡መመታት፡እንደሚገባት፡ተከታዮቻቸውን፡
ያዘጋጁበት፡ጊዜ፡ሰንበትበት፡ብሏል።

እኛስ፡ስለሃይማኖታችን፡ተሰደብን፣ተንገላታን፣ተገ
ደልን፤እየተገደልንም፡ነው።እንዲያው፡ለነገሩ፡የኒ
ህ፡ሰዎች፡ሃይማኖት፡ማን፡ይሆን፡ስሙ?!

የዛሬው፡የ"አዲስ፡ራዕይ፡"ዘመቻም፡ሊደንቀን፡አይ
ገባም።ምስጢሩ፡ጉዳዩን፡ከሥሩ፡መረዳቱ፡ላይ፡ነው!

ሰማያትንና፡ምድርርን፣በውስጧም፡ያሉትን፡ተራ
ራዎችና፣ሌሎችም፡የሚታዩና፡የማይታዩ፡ፍጥረታ
ትን፡የፈጠረው፡የተዋሕዶ፡አምላካችን፣ፈጣሪያችን፡
ከመጣብን፡የጥፋት፡ርኩሰት፡ውድመት፡ያድነን!

የሰማዕታቱ፡የቅዱስ፡እስጢፋኖስና፡የአቡነ፡ጴጥሮ
ስ፡አምላክ፡ብርታቱንና፡ጽንዓቱን፡ያድለን።አሜን!

እግዚአብሔር፡ስለ፡ቅድስት፡ቤተክርስቲያኑ፡መገፋ
ትና፡በሕዝበ፡ክርስቲያኑ፡ላይ፡የሚፈጸመውን፡ዓመ
ፅ፡ሁሉ፡ይመለከታል።

የፍርድ፡ጊዜውም፡ስለ፡ተቃረበ፡አንደናገጥ!በእም
ነትና፡በጸሎት፡እንበርታ፤እንትጋም!

ክርስትናችን፡የመስቀል፡መንገድ፡ስለሆነች፡መከራ
ው፡ሊደርስ፡ግድ፡እንደሆነ፡በማወቅ፣በትዋሕዶ፡ጸን
ተን፡ለመድሃኒታችን፡እግዚእነ፡ኢየሱስ፡ክርስቶስ፡
ፍርድ፡እንዘጋጅ!

እግዚኦ፡መሐረነ፡ክርስቶስ!
በእንተ፡እግዝእትነ፡ማርያም፡
መሐረነ፡ክርስቶስ!

አሜን፤አሜን፤አሜን።


ሰይፈ፡ገብርኤል።

bili said...

ውሀ እና መብራት በበቂ ሁኔታ በሌለባት አዲስ አበባ አተት ሲነሳ የሆቴሎች የተበላሸ አገልግሎት መስጠት ነው ተባልን ፡ ዛሬ ደግሞ ለዝመናት ሲፈውስ የኖረ ጠበል ወቸ ጉድ ወይ መቆሚያ ማጣት !!!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)