October 13, 2009

(ሰበር ዜና)፦ የፓትርያርኩ የወንድም ልጅ በፖሊስ ታሰረ

(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 13/2009)፦ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባዔ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊነት ሥልጣን ተሰጥቶት የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ ሲዘርፍ የነበረውና የማፊያውን ቡድን የሚመራው የቅዱስ ፓትርያርኩ የወንድም ልጅ “ሊቀ ኀሩያን” ያሬድ ከበደው በፖሊስ ቁጥጥር ስም መዋሉ ተሰማ።

አጎቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ወደ መንበረ ፕትርክናው ከወጡ ወዲህ በቤተ ክህነቱ በተለያዩ ሥፍራዎች በመመደብ ወደር የሌለው ዝርፊያ ሲፈጽም የነበረው ያሬድ ከበደው በአሁኑ ወቅት የሚሊዮኖች ብር ባለቤት (ሚሊዬኔር) ሲሆን በአንድ ወቅት በተለያዩ የሥራ መደቦች ሁለት ደሞዝ ይበላ የነበረበት ጊዜ እንደነበር ምንጮቻችን አብራርተዋል። የሚያስገርመው ይህንን ሁሉ ዝርፊያ የፈጸመ ወንጀለኛ “ሊቀ ኀሩያን” ተብሎ (የምርጮች ሁሉ የበላይ/አለቃ?? መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ) ታላቁን የሰበካ ጉባዔ መምሪያ እንዲመራ መመደቡ ነው። ለቤተ ክርስቲያን ምንም የማይገዳቸውና ዘመዶቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ አልቅት በመሰግሰግ የእናት ቤተ ክርስቲያንን ደም የሚያስመጥጡት ቅዱስ ፓትርያርኩ መሬት እየከዳቸው መሔድ ከጀመረበት ካለፈው የግንቦት ወር የቅ/ሲኖዶስ ጉባዔ ወዲህ የዘመዶቻቸው ዓይን ያወጣ ዝርፊያ ታሪክ አደባባይ መዋል ጀምሯል።

አሁን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚገኘው ያሬድ ባለፈው ቅዳሜ አካባቢ በፖሊስ ከተያዘ በኋላ ዛሬ ማክሰኞ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ጉዳዩ በተለዋጭ ለፊታችን ሐሙስ በመቀጠሩ ወደ ማረፊያ ቤት ተመልሶ እንደገባ ታውቋል። በብፁዓን አባቶች መኖሪያ ቤት ድብደባ፣ በቤተ ክርስቲያን ሀብት ዝርፊያና በሌሎች የተለያዩ ወንጀሎቹ የሚታወቀው ያሬድ የተያዘው በየትኛው ወንጀል እንደሆነ ለጊዜው ለማወቅ አልቻልንም። ፖሊስ ባለፈው ጊዜ የፓትርያርኩን አቡነ ቀሲስ አባ ዕንቁ ባሕርይንም ለተወሰኑ ቀናት ከያዘ በኋላ መልቀቁ ይታወሳል።
ፖሊስ ወንጀለኞቹ እነማን እንደሆኑ ቢረዳም እየያዘ የሚለቃቸው ምናልባት በቀጭኑ ሽቦ ሌላ ትዕዛዝ እየደረሰው ሳይሆን እንዳልቀረ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። ቤተ ክህነት የምትመራው በጠቅላይ ቤተ ክህነትና በቅዱስ ሲኖዶስ እስከማይመስል ድረስ የመንግሥት ታላላቅ ሚኒስትሮች በይፋ በቤተ ክህነቱ ጉዳይ እየገቡ መሆናቸው ይታወቃል። በተለይም የመንግሥት የደህንነት ጉዳዮች ሚኒስትርና የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካሪ አቶ ዓባይ ፀሐዬ በሚያሳዩት ጠባይ በርግጥም እነ ያሬድ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ይዋሉ እንጂ ነገ “በሉ ልቀቁት” ሳይባል እንደማይቀር ይገመታል።
በብፁዓን አባቶች መኖሪያ ቤት አደጋ ድራማውን የሰራው የማፊያው ቡድን ተራ የማፊያ ቡድን ሳይሆን የመንግሥት የደህንነት ኃይሎችን ያቀፈ አንድ ግብረ ኃይል መሆኑ ይፋ እየወጣ ከመጣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ለምን እነዚህን ወንጀለኞች በመደገፍ እንደቆመ ግራ የሚያጋባ ነገር ሆኗል። ይህ የመንግሥት አቋም ይሁን ወይም የጥቅም ተካፋይ የሆኑ ጥቂት ኃላፊዎች ይሁን ምንም መረጃ ማግኘት አልተቻለም።
ፖሊስ ለይስሙላ የሀገርና የሕዝብ ደህንነትን የሚያስጠብቅ መስሎ ቢታይም በተለይም ቤተ ክርስቲያናችንን በተመለከተ ሥልጣኑን ይዞ የሚያንቀሳቅሰው ደህንነቱ ነው። አባ ዕንቁ ባሕርይ የተፈቱት፣ ፓትርያርኩ የሚያስፈራሩበት፣ አባ ሰረቀ ብርሃንን (የሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ኃላፊ)፣ ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃን (የጠ/ቤ ክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ) እና መጋቤ ካህናት ኃ/ሥላሴን (የካህናት መምሪያ ኃላፊ) የመሳሰሉ ካድሬዎች እንደፈለጋቸው የሚፈነጩት ይህንኑ የደህንነቱን ክፍል በመያዛቸው እንደሆነ ይነገራል። ስለዚህ የያሬድም መያዝ ምናልባት ነገሩ ያልገባው ፖሊስ ሳያውቀው ያደረገው እንጂ ደህንነቱ ግን እንደማይፈልግ ምንጮቻችን በእርግጠኝነት ይናገራሉ። ሁሉንም ጊዜው ሲደርስ የምንመለከተው ይሆናል።
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)