October 12, 2009

ብፁዕ አቡነ ማትያስ ቀጣዩ አቡነ ሳሙኤል እንዳይሆኑ!!!! የወ/ሮ እጅጋየሁ (ኤልዛቤል) ተልእኮ በቅድስት ሀገር በኢየሩሳሌም


(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 12/2009)
የሚከተለው ዜና ከቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የተገኘ መረጃ ነው። ዝግጅቱን አሰናድተው የላኩልንን ደጀ-ሰላማውያን (ለተ ገብርኤል፡ ተክለ ገብርኤል እና ገብረ ማርያም) ከልብ እናመሰግናለን። የቤተ ክርስቲያን አምላክ በበረከቱ አይለያችሁ እንላለን።
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን
++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ውድ አንባብያን
በቅድሚያ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ያስገደደን ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ በአባቶች ላይ የሚደረጉ የሐሰት ውንጀላዎች በወ/ሮ እጅጋየሁ የሚቀነባበሩ መሆናቸውን በመስማታችን ፣ ይህም ብፁዕ አቡነ ማትያስ ቀጣዩ ወንጀል የሚፈለግላቸው አባት እንዳይሆኑ የሚል ስጋት ስለፈጠረብን የሚመለከተው ሁሉ (ብፁዕ አቡነ ማትያስን ጨምሮ) ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ለማሳሰብና ሌሎችም ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማስገንዘብ ነዉ፡፡ በማስከተልም ዝርዝር ሐሳቡን በአጭሩ እናቀርባለን፡፡
በቅድሚያ ባለፈው የግንቦት ሲኖዶስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ እንዲሁ መጠነኛ ክስ ገጥሟቸዉ ነበር፡፡ መነሻ ምክንያቱ እማሆይ ሰብለ ተብለዉ የሚታወቁ መነኩሲት በተለያዩ የሥነ ምግባር ችግሮች በገዳሙ ዉስጥ በተለያዩ ጊዜያት ማስጠንቀቂያና ምክር ሲሰጣት ልትትረም ባለመቻልዋ ትውጣ የሚል ውሳኔ እየተወሰነ እንታገሳት በሚል አየታለፈች ስትኖር ከርማ። በመጨረሻ ሰኔ ወር 2000 ዓ.ም. መነኮሳቱ በአንድነት ትዕግሥት ሊያስተምራት ስላልቻለ ትውጣ በማለት ይወስናሉ፡፡ በዚህም ወቅት እንደ መነኩሴ ስርዓት ንሰሃ ስጡኝ በድያለሁ እንደማለት ተነስታ ሔደች ግን ጥር 2001 ገደማ ተመልሳ በመምጣት አስገቡኝ በማለቷ ገዳሙ አትገቢም ሲላት ወደ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳዉሎስ አመልከታ አስገቧት የሚል ትዕዛዝ መስጠታቸዉና፡፡ ገዳሙ በህጉ መሰረት አስፈላጊውን ሁሉ እንዳደረገ በመግለፅ ብፁዕነታቸዉ ገዳሙ ችግር ሁኖበት ይህን እንደወሰነ እንዲረዱለት በማስረጃ ጭምር ጥያቄዉን ያቀርባል።ይህ እንዳልተሳካ ያወቀችዉ እማሆይ ሰብለ ጉዳዩን እስራኤል ፍርድቤት ታቀርባለች።በዚህ ክስ የተከሰሱት፡
1. በኢየሩሳሌም ኢትዮጵያ ኦ.ተ. ቤተ ክርስቲያን
2. ብፁዕ አቡነ ማትያስ
3. መጋቢ አባ ብርሃነ መስቀል ናቸው፡፡
በዚህ መሀል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳዉሎስ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው በማስፈራራት ጭምር ለማስገባት ቢሞክሩም መነኮሳቱ መረጃቸውን አቅርበው ይፍረዱን በማለታቸዉ ተመልሰው ሂደዋል። በዚህ ምክንያት ጉዳዩ ለሲኖዶስ ቀረበ። በሲኖዶስም ላይ ብፁዕ አቡነ ማትያስ እማሆይ ሰብለ ከእሳቸዉ በፊት በነበሩ አምስት ጳጳሳት ማስጠንቀቅያ እንደተፃፉባትና ገዳሙ ከብዙ ትዕግስት በኁላ ይህንን እንደወሰነ በመግለጻቸዉ። ሲኖዶሱ ቀድሞዉን ይህ ጉዳይ እንዴት ከሊቀ ጳጳስ አልፎ እዚህ ደረሰ ብሎ ሲጠይቅ- እሱማ አቡነ ማትያስ አስተዳደር ስለማይችሉ ነው።መረጃዉ ደግሞ የገዳሙ መነኮሳት የተፈራረሙበት ደብዳቤ አለላችሁ በማለት ሰያቀርቡ። ብፁዕ አቡነ ማትያስ ካልጠበቁት የተቀነባበረ ክስ ተፋጠጡ።ይሁን እንጂ ይጣራልኝ በማለታተዉ የገዳሙ ጽ/ቤት ተጠይቆ ስለተባለዉ ክስ ምንም እንድማያዉቅ በመግለፁና እነኛ ስማቸዉ የተጠቀሰዉ መነኮሳት ነገሩ ዉሸት መሆኑን በደብዳቤ በማረጋገጣቸዉ፡ 51 ጳጳሳት እማሆይ ሰብለ ወደ ኢትዮጵያ እንድትመለስ በመወሰን ተፈራርምው ደብዳቤ ይልካሉ።


ነገር ግን እማሆይ ሰብለ የሲኖዶሱን ውሳኔ ቸል በማለት የፍርድቤት ሙግትዋን ቀጠለች፡፡ በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ክሷን ዉድቅ አደረገባት።
በዚህ ወቅት እማሆይ ሰብለ ገዳሙ ግቢ ገብታ ለወራት አልወጣም ብላ ስታስቸግር ቆይታ በመጨረሻ በፖሊስ ከገዳሙ በነሐሴ ወር 2001 ዓ.ም. ወጣች።

ነገር ግን እማሆይ ሰብለ አሁንም እዚሁ እስራኣኤል ዉስጥ መኖሯንና እንደገና የጥቅምት ሲኖዶስን እንደምትጠብቅ በመስማታችን አቡነ ማትያስ ከግንቦት ሲኖዶስ የባሰ ዱብዳ ሊገጥማቸዉ እንደሚችል መገመታችን አልቀረም፡፡ ይህን ግምታችንን ደግሞ ክብደት የሰጡት ሁለት ነገሮች ተከስተዋል፡፡

1. ባለፉት ሁለት ወራት ዉስጥ የአባቶችን ስም የሚያጠፉ ፅሁፎች በዕብራይስጥ ቁንቐ በሚታተሙ ጋዜጦች መዉጣታቸዉና እነኝህም ፅሁፎች እማሆይ ሰብለ ከገዳሙ አባላት ዉስጥ ለዝሙት ተጠይቃ እምቢ በማለቷ እንደ ተባረረች የሚያትቱ መሆናቸዉ፡፡

2. የወ/ሮ እጅጋየሁ ለኢየሩሳሌም ድርጅት ስራ ሽፋን መምጣትና ከእማሆይ ሰብለ ጋር ስትወጣ ስትገባ መታየት

የአቡነ ማትያስ የክስ ውንጀላዎች እየተቀናበረ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋታችንን አጠንክሮታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አቡነ ማትያስ በግልፅ በሲኖዶስ በተከሰተው ነገር ላይ ማለትም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳዉሎስ ላይ ያቀረቡት ግልፅ ተቃውሞ ቀጣዩአቡነ ሳሙኤል እንዲሆኑና የወ/ሮ እጅጋየሁ እኩይ ወጥመድ ዉስጥ እንዳስገባቸው ለማመን ተገደነል። በመሆኑም
1. ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ አቡነ ማትያስ የሚቀርብለት ክስ ቢኖር በጥንቃቄ እንዲመረምር ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡ በተጨማሪም እማሆይ ሰብለን መልሶ ማስገባት ከተፈጠረው ችግር አንፃር ለገዳሙ ደህንነት ጠንቅ ይሆናል ብለን ስለምንገምትና በተለይም ደግሞ ለገዳሙ ተቆርቁረው የተናገሩ አባቶችን ለአደጋ ሊያጋልጥ ስለሚችል በኣግባቡ አንዲጤን ስንል በትህትና እንጠይቃለን፡፡
2. የገዳሙ አባቶችም ይህንን ጥቆማ በጥንቃቄ እንዲመረምሩትና በስማቸው እንዳይነገድ አንዲከላከሉ
3. ምዕመናን ይህ ክስ ቢከሰት እንዳይወናበዱ ከዚህ በተጨማሪም በሌላ ቦታ የሚኖሩም ምዕመናን ለየሀገረ ስብከቶቻቸዉ ሊቃነ ጳጳሳት ማሳሰቢያችንን እንዲያደርሱልን እንማጸናለን፡፡
እግዚአብሔር ይስጥልን

ለተ ገብርኤል፡ ተክለ ገብርኤል እና ገብረ ማርያም


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)