October 7, 2009

“መንግሥትን የጋበዘው ማኀበረ ቅዱሳን ነው” የሚለው የአባ ሰረቀ “የአብዬን ወደ እምዬ” (“Blame-Game”) ጨዋታ

(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 6/2009)፦ በቤተ ክህነቱ ስብሰባ የመንግሥት ባለሥልጣናትን የጋበዘው ማኀበረ ቅዱሳን ነው ሲሉ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ከሰሱ።

“ውይይቱ የተካሔደው በማደራጃ መምሪያው ጥያቄ ሳይሆን ማኀበሩ በደብዳቤ ለቅዱስ ፓትርያርኩ እና ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለውይይት በጠየቁት መሠረት ነው” ያሉት የመምሪያ ኃላፊው አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ናቸው። ኃላፊው ቅዳሜ ታትሞ ከወጣው “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ቤተ ክህነት የራሱን የውስጥ ጉዳይ መከወን እየተሳነው መምጣቱ የበለጠ በግልጽ በወጣበት በሰሞኑ ውዝግብ ችግሩን ለማድበስበስ ጥፋቱን ወደ ማኀበረ ቅዱሳን ለማሸጋገር ሲሞክሩ ተስተውለዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ መልስ እንዲሰጡ የተጠየቁት የማኀበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም በበኩላቸው “የውይይቱ አጀንዳ ምን እንደሆነ እንኳን አናውቅም ነበር። በቦታው ደርሰን ጸሎት ከተደረገ በኋላ ፕሮግራም ሲታደል ነው የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያው ኃላፊ ስለ ማህበሩ ጉዳይ ሪፖርት እንደሚያቀርቡና ማህበሩ መልስ እንደሚጠበቅበት የተረዳነው። ስብሰባው በእና ጠያቂነት ተጠርቶ ቢሆን ኖሮ አቤቱታችንን የምናቀርበው እኛ ነበርን።፡ወይም የቀረበብንን አቤቱታ አስቀድመን ብናውቅ ኖሮ መልስ ይዘን እንቀርብ ነበር። ነገር ግን እኛ ስንቀርብ ከማስታወሻ ደብተር ውጭ የያዝነው ነገር አልነበረም” ሲሉ ክሱን በመቃወም መልሰዋል።
“የአባ ሰረቀ ዘዴ ምን ሊሆን ይችላል፣ ለምን ጉዳዩን ወደ ማኀበረ ቅዱሳን መገልበጥ ፈለጉ? ያዋጣቸዋል ወይ” ስንል የጠየቅናቸው ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ደጀ-ሰላማውያን እንዳሉት ከሆነ ጉዳዩ የዛሬ ዓመት (2001 ዓ.ም ጥምቀት ማግሥት) ከተከናወነ ድርጊት ጋር ሳይገናኝ እንዳልቀረ ጠርጥረዋል። ጉዳዩ “ደጀ ሰላም” የዘገበችበትና ቅዱስ ሲኖዶስን ለማነጋገር በመጡ በመንግሥት ባለሥልጣናትና በብፁዓን አባቶች መካከል የተፈጠረውን ግብግብ ተከትሎ የተነሣ እንደነበር እነዚሁ ሰዎች ይናገራሉ።

“በወቅቱ ‘በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አክራሪዎች አሉ፣ ሙስሊሞችን የሚያስቸግሩ፣ አውጥታችሁ ስጡን፣ አለበለዚያ…” እያሉ ለማስፈራራት የሞከሩትን ባለሥልጣናት በመጋፈጥ “እኛው በተጎዳን፣ እኛው ምእመናችን በተጨፈጨፈ እንዴት እንዲህ እንባላለን፤ ለመሆኑ ይኼ መንግሥት ከቤተ ክርስቲያንን ለምን እንዲህ ያደርጋታል?” ብለው አባቶች በድፍረት በመናገራቸው መንግሥት መደናገጡ ይታወሳል። በወቅቱ በስብሰባው ላይ የተገኙት አቶ አባይ ፀሐዬ “አክራሪው ማኀበረ ቅዱሳን ነው” በማለት ሲናገሩ አባቶችም “የማኀበረ ቅዱሳን አባላት አክራሪዎች አይደሉም፤ ልጆቻችን ናቸው። እነርሱን አሳልፈን አንሰጥም” ይላሉ። ከዚህ ስብሰባ በኋላ በታላላቅ የመንግሥት ባለሥልጣናት “አክራሪ” የተባለው ማኀበረ ቅዱሳን ስለ ጉዳዩ መረዳት እንደሚፈልግ፣ ይህ ስምም ሊሰጠው እንደማይገባ ለቅዱስ ፓትርያርኩና ለሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ በማስገባት ተቃውሞውን ይገልጻል። እናም አባ ሰረቀ ያንን የ2001 ዓ.ም የጥምቀት ማግስት ሁኔታ በመመርኮዝ ሳይሆን አይቀርም “እኛ አልጠራናቸውም ማኀበረ ቅዱሳን ነው” በማለት ለማጨበርበር የሞከሩት”
ሲሉ አብራርተዋል - ደጀ ሰላማውያኑ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በውጪው ሀገር (በዳያስጶራ) ባለው ኤሊት (ምሁር) ዘንድ “የወያኔ ጉዳይ አስፈጻሚ፣ የአቡነ ጳውሎስ ወኪል” እየተባለ ሲታማ የነበረው ማኀበረ ቅዱሳሰን በሰሞኑ ውዝግብ እስካሁን ሲቀርብበት የነበረው ክስና ወቀሳ ትክክል እንዳልነበረ ማረጋገጫ እንደሆነለት ምንጮቻችን እየዘገቡ ነው። በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ የሚገኙ “ደጀ ሰላማውያን” ያለውን ድባብ ተመልክተው እንዳስተነተኑት ከሆነ ማኀበረ ቅዱሳን ፖለቲካ ውስጥ እንዳለበት በመናገር ብዙ የፖለቲካ ትርፍ ሲያገኙ በነበሩት የማኀበረ ቅዱሳን ተቃዋሚዎች ዘንድ ሐፍረት መፈጠሩን፣ ነገሩን በመመልከት ብቻ ዳር ቆመው በሚመለከቱት ዘንድ ደግሞ ማኀበሩ ትክክለኛ የቤተ ክርስቲያን አካል በመሆኑ ላይ እምነት ማሳደሩን ተመልክተዋል። በሀገር ውስጥ ያለውን በተመለከቱት ”ደጀ ሰላማውያን” ዘገባ መሠረት ጉዳዩ ማኀበረ ቅዱሳንን በሕዝቡ የበለጠ እንዲወደድ እንዳደረገው ተጠቅሷል።
የአዲስ አድማስን ቃለ ምልልስ ለማንበብ ይህንን ttp://www.addisadmass.com/Yesemonun/news_item.asp?NewsID=279 ይጫኑ
ቸር ወሬ ያሰማን፣
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)