October 2, 2009

አለቃ አያሌው ታምሩ መስከረም 21 ቀን 1990 ዓ.ም ምን ብለው ነበር?

(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 1/2009)፦ የሚከተለው ምንባብ የተወሰደው ከታላቁ ሊቅ ከአለቃ አያሌው ታምሩ ድረ ገጽ (http://www.aleqayalewtamiru.org/) ላይ ነው። የተናገሩበት ዕለት ዛሬ፣ በታሪክ አንጻርም እርሳቸው በትንቢት መነጽር ዛሬን ያዩ ይመስል የሚገርም አንድነት አለው።“በእነ አባ ጳውሎስ በኩል የሚደረገው የደም ማፍሰስ፥ ሰዎችን ማሳሰር፥ ማስደብደብ፥ የገንዘብ ምዝበራ እየተስፋፋ መሄዱ ግልጽ ከመሆኑም በላይ … አሁን የአዲስ አበባ ምእመናን ከቀሳውስትና ከአለቆች፥ ከካህናትና ከጳጳሳት፥ ከፓትርያርኩም ጋር ሆነው በእግዚአብሔር ላይ ዐምፀዋል። ገዳዮች እየገደሉ፥ አስገዳዮች እያስገደሉ፥ ደብዳቢዎች እየደበደቡ፥ አስደብዳቢዎች እያስደበደቡ፥ አሳሪዎች እያሰሩ፥ አሳሳሪዎች እያሳሰፉ፥ ገንዘብ መዝባሪዎች እየመዘበሩ፥ አስመዝባሪዎች እያስመዘበሩ ይህን ሁሉ እያሉ መከላከል ሲቻላቸው የማይከላከሉ፥ መናገር ሲገባቸው ዝም የሚሉ፤ ያለዚያም ርቀው መመልከት፥ ከደም ማኅበር መለየት ሲገባቸው ተቀላቅለው የሚያፌዙ ሁሉ ከታላቁ ፈራጅ ከኀያሉ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አምላክ ፍርዳቸውን ይቀበላሉ። ስለዚህ ምእመናን ተጠንቀቁ። «ከርኩሳን ተለዩ፤ ወደ ርኩሳን አትቅረቡ፤ ከመካከላቸው ውጡ፤ እኔ አባት እሆናችሁአለሁ፤» ብሏል እግዚአብሔር። ይህ የእግዚአብሔር ዐዋጅ ነው። ጆሮ ያለው ይስማ።”

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
«የታሪክ ውንብድና ቢቆም መልካም ነው።»
(ኢትኦጵ መስከረም 21 ቀን 1990 ዓ ም)
ኢትዮጵያውያን ምእመናን! ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የሚሄደው የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ሕይወት አሳዛኝ ሁኔታ ላይ የደረሰ ይመስላል። ሰዎች በሚሠሩት ክፉ ነገር እየጨመሩ መሄዳቸውን፥ አንጠጠትም ማለታቸውን፥ ከሰው ዐልፈው እግዚአብሔርን ወደ መጋፋት መድረሳቸውን ሲያስረዳ፤ «ወኀለፈ እምትዕቢት ልቦሙ። ኀለዩ ወነበቡ ከንቶ። ወነበቡ ዐመፃ ውስተ አርያም። ወአንበሩ ውስተ ሰማይ አፉሆሙ። ወአንሶሰወ ውስተ ምድር ልሳኖሙ።» «ልባቸው ከትዕቢት ዐለፈ፤ ዐስበው ከንቱ ነገርን ተናገሩ፤ በአርያም ዐመፅ ተናገሩ፤ አፋቸውን በሰማይ አኖሩ፤ ምላሳቸውም በምድር ላይ ተመላለሰ፤» ይላል። (መዝ፤ ፸፪፥ ፯ - ፲።) በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያን ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወት የማይገመግም የሰው ዘር በሩቅም በቅርብም ያለ አይመስለኝም። ይልቁንም መንፈሳዊው ክፍል ከቀን ወደ ቀን ጉዳቱ እየጨመረ መሄዱ ግልጽ እየሆነ ነው። በተለይም የኢትዮጵያ መገናኛ ድርጅት የሃይማኖት ፌዴሬሽን ለማቋቋም ሲዳዳው ይታያል። ይህንንም ያሰኘኝ በዓል በመጣ ቍጥር የማይገናኙትን ለማገናኘት፥ የማይተባበሩትን ለማስተባበር፥ የማይዋሐዱትን ለማዋሐድ የሚደረገውን ዝግጅት እየተመለከትኩ ነው።
እስከ ፳ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ፥ እስከ ለውጡ ድረስም ማለት ይቻላል በኢትዮጵያ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በቀር ብሔራዊ መንፈሳዊ ክብረ በዓል የነበረው የሃይማኖት ክፍል አልነበረም። «ሃይማኖት የግል ነው፤ አገር የጋራ ነው፤» የሚለው ዐዋጅ ከታወጀ ወዲህም እንኳ ቢሆን «የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በዓል» እየተባለ ይነገር ነበር እንጂ በዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል እንደ ታየው ያለ መልክ ያልለየ ድብልቅልቅ ያለ አነጋገር አልነበረም። በክርስትናው ዘርፍ በኩልም የካቶሊክና የፕሮቴስታንት ተወካዮች የላኪዎቻቸውን ሥርዐት ጠብቀው የዘመን መለወጫን፥ ልደቱንም ፋሲካውንም የሚያከብሩ ከላኪዎቻቸው ጋር እንጂ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር የበዓል ኅብረት አልነበራቸውም። አሁን ግን በየቀኑ፥ በየበዓሉ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሪ ስም ከተጠራ የካቶሊክና የፕሮቴስታንት ስም ዐብሮ ይቀርባል። ባለፉት የትንሣኤ፥ የዘመን መለወጫ፥ የመስቀል በዓላት አከባበር ከኢትዮጵያ መገናኛ ድርጅት የሰማነው፥ ያነበብነው፥ ያየነውም ይኸው ነው። አንድነቱ የለም እንጂ ካለ፥ እውነቱ የለም እንጂ የሚኖር ከሆነ አልቃወምም። ግን አንድ ሰው እግዚአብሔርን ለማታለል፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማሳሳት የሚያደርገው ከሆነ የኢትዮጵያ መገናኛ ድርጅትም ሆነ ሦስቱ የሃይማኖት ክፍሎች ማለት ኦርቶዶክስ፥ ካቶሊክና ፕሮቴስታንት ሥርየት የሌለው በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚፈጽሙት በደል ነው ማለት ይቻላል።
የመስቀል በዓል አከባበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከካቶሊክና ከፕሮቴስታንት በፊት የተቀበለችው ነው። ኢትዮጵያ ታሪክን የተመረኮዙ ታላላቅ መንፈሳውያን፥ ብሔራውያን በዓላት አሏት።
ሀ፤ የዘመን መለወጫ መስከረም ፩ ቀን፤ ከማየ አይኅ በፊት የነበረ ጥንተ ፍጥረት፥ ጥንተ ብርሃን፥ ጥንተ ዕለት ሲሆን በኖኅ ዘመንም ለሰው ዘር ተሐድሶ ጥንት፥ በብሉይ ኪዳንም በዓለ መጥቅዕ ተብሎ ሲከበር፥ ሥርዐተ ቤተ እግዚአብሔር ሲታወጅበት የኖረ፤ በሐዲስ ኪዳንም ቅዱስ ዮሐንስ የሚለውን ስም ጨምሮ በቤተ ክርስቲያን የታወቀ፤ ጌታችንም በናዝሬት ምኵራብ የተናገረው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፬ ቍጥር ፲፰ - ፳ እንደ ተገለጠው ትንቢተ ኢሳይያስን ጠቅሶ የራሱን ዐዋጅ የገለጠበት በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ዓመተ ምሕረትን ከዓመተ ዓለም፥ ትንቢትን ከስብከት አስተባብረው ያደረጉበት ርእሰ ዐውደ ዓመት ነው።
ለ፤ በዓለ መስቀል፤ ይህ በዓል በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ ፳፫ በተገለጠው የበዓላት ዝርዝር መግለጫ መሠረት እንደ ዕብራውያን አቆጣጠር በ፯ኛው ወር ከ፲፭ኛው ቀን ጀምሮ፥ እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ከመስከረም ፲፯ እስከ ፳፩ በብሉይ ኪዳን ሥርዐት ሲከበር የኖረ በዓል ሲሆን ጌታችን በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፯ እንደ ተገለጠው በሳምንቱ የበዓላት ዕለታት በበዓሉ እየተዘዋወረ ትምህርት የሰጠበት ሲሆን በእሱ ትምህርት በበዓሉ ላይ ከነበሩት ሰዎች አነጋገር እንደምንመለከተው ነገረ መስቀልን የሚመለከት በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ይህንን በብሉይ ኪዳን በዓል ላይ አጽንተው በዓለ መስቀልን መሥርተውበታል። ታሪኩ፤ «ወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ።» «ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፤» በሚለው ትንቢት መምሪያ የብሉይ ኪዳን በዓል የተስፋ መሠረት የንግሥት ዕሌኒን ታሪክ የተስፋ ፍጻሜ መግለጫ ያደረገ ስለ ሆነ በዓሉ በቤተ ክርስቲያን የሳምንት በዓል ነው። በቤተ ክርስቲያን ስያሜው ዘመነ መስቀል ይባላል። በዓሉ ባለ ደመራ፥ ችቦው ባለ ጣምራ ነው። አበውን ከውሉድ፥ ብሉይ ኪዳንን ከሐዲስ ኪዳን፥ ተስፋን ከእውነት፥ መሠረትን ከፍጻሜ ያጣመረ ነው። በዓሉ ዕፀ መስቀሉን ብቻ ሳይሆን የክርስቶስን ነገረ መስቀሉን አጠቃለን የምናይበት ነው። ሌሎችም አሉ። ግን ለጊዜው ወደ ዕለቱ ታሪክ እመለሳለሁ።
እንግዲህ የዚህ በዓል አመሠራረቱ፥ መንፈሳዊነቱ፥ ብሔራዊነቱ፥ ጥንታዊነቱ እንዲህ ሲሆን መስከረም ፲፮ እና መስከረም ፲፯ ቀን ፲፱፻፺ የተፈጸመው የበዓል አከባበር በምኑም በምኑም ከማንኛውም ክፍል በታየው ሁሉ የበዓለ መስቀልን ክብር፥ ምስጢር፥ ኢትዮጵያዊነት፥ ብሔራዊነት፥ መንፈሳዊነት የጠበቀ አልነበረም። ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወገን መሪዎች ነን ከሚሉት የተላለፈው የተቀጸል ጽጌን የዐፄ መስቀልን ታሪክ የተመረኮዘ በአንድ በኩል የስሕተት፥ በሌላ በኩል የናፍቆትና የስስት፥ የጌጥ፥ የዘፈን ወዳድነት፥ የአድር ባይነት ጠባይ የታየበት ትረካ፤ እንዲሁም በልብ የሌለውን ዕርቀ ሰላም መክፈቻ አድርጎ በጥቁሮች ስብሰባ ላይ ጉራን ለመንዛት የተማሩ መስሎ በመታየት ኢትዮጵያዊ ማለት ጥቁር ማለት ነው ስለዚህ የዓለም ጥቁሮች በዓል ነው ተብሎ ከላይኛው ወገን የተተረከው ትረካ ራስን የመዘንጋት በተለይም ሞኙ አባ ገ የተቀጸል ጽጌን የአጤ መስቀልን በዓል ከጥንታዊ ነገሥታት ታሪክ አዛምደው ከመስቀል በዓል ጋር አንድ ለማድረግ ሞክረዋል። አንደኛው አለማወቅ፥ አለመማር ነው። ሁለተኛው ብልጣብልጥነት ነው። የተቀጸል ጽጌ በዓል ከጥንቱ ከመሠረቱ የኢትዮጵያ ቅዱሳን ነገሥታት ክረምቱን አስፈጽሞ ከፀሓዩ ከአበባው ዘመን ላደረሳቸው አምላክ ምስጋና የሚያቀርቡበት ነው። ቤተ ክርስቲያንም ምእመናን ልጆቿን እንኳን አደረሳችሁ የምትልበት ሲሆን ሲከበር የኖረውም መስከረም ፳፭ ቀን ነው።
ይህም ቀን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባህል ፀአተ ክረምት የክረምት መውጣት ይባላል። ሦስት ወር ክረምት የሚፈጸምበት፥ ዐዲስ የአበባ ዘመን የሚጀመርበት፥ ምድር አትክልትን፥ አዝርዕትን ለብሳ የምትታይበት ጊዜ ነው። በቀድሞው ዘመን እንደ ዛሬ መገናኛ ያልተስፋፋበት በመሆኑ ሕዝቡ ከነገሥታቱ፥ ነገሥታቱ ከሕዝቡ እንደ ልባቸው ሊገናኙ አይችሉም። የአገሪቱ ጥበቃም በዚያው ዐይነት ችግር ነበረበት። ክረምት አልቆ በጋው ሲተካ ግን ሁሉም የአስተዳደር ሥራ በየዘርፉ ሊቀጥል ስለሚችል ሕዝብና ሠራዊቱ ከነገሥታት፥ ነገሥታቱም ከሕዝቡ የሚገናኙበት ስለ ሆነ ሁሉም ከየከረሙበት ተሰባስበው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት ቀን ነበረ። በዚህም ቀን ነገሥታቱ ከሕዝቡ፥ ሕዝቡም ከነገሥታቱ ሲገናኙ የአበባ ገጸ በረከት አቅርበው እንኳን አደረሳችሁ ይባባሉ ነበር። በብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናቱ፥ በሐዲስ ኪዳን ጳጳሱ ለንጉሠ ነገሥቱ እግዚአብሔር ያደረገለትን ቸርነትና በረከት ገልጾ፤ «ተቀጸል ጽጌ ዕገሌ ዐፄጌ፤» «ጃንሆይ! እግዚአብሔር የአበባ አክሊል ያቀዳጅዎ፤» ብሎ የአበባ አክሊል ይደፋለት ነበር፤ የአበባ ገጸ በረከት ያበረክትለት ነበር። እስከ ፲፬ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ድረስ የነበረው ሥርዐት ይህ ነበር። በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የተነሡት ዐፄ ዳዊት ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ለኢየሩሳሌምና ለግብጽ ምእመናን ባሳዩት ዕርዳታ ምእመናን መክረው ከጌታ መስቀል የቀኝ ክንፉን ለኢትዮጵያ በረከት አድርገው ሰጥተዋል። ዐፄ ዳዊትም ግማደ መስቀሉን ተቀብለው ተመልሰው ስናር እንደ ገቡ (መተከል የሚገኝ ሲሆን ሀገረ ዳዊት ይባላል) በድንገት ስለ ሞቱ መስቀሉ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወር ቆይቶ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ግሸን ላይ ዐርፏል።
ወደ ታሪኩ ስንመለስ ዐፄ ዳዊት መስቀሉን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት መስከረም ፲ ቀን ነበር። ቅዱሳን የኢትዮጵያ ነገሥታት ከራሳቸው ክብር ይልቅ የእግዚአብሔርን ክብር ስለሚያስቀድሙ ከአባቶቻቸው ተያይዞ የመጣውን መስከረም ፳፭ ቀን ይከበር የነበረውን የተቀጸል ጽጌ በዓል መስከረም ፲ ቀን እንዲከበር አደረጉ። የጌታ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ በገባበት ቀን ማለት ነው። በዚህም ምክንያት ስሙ አጤ መስቀል ተባለ። አጤ የተሰቀሉበት ሳይሆን ያከበሩት ማለት ነው። ይህም በዓል እስከ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ ሳይለወጥ ኖሯል። ከሃያ ዓመት በላይ ተቋርጦ ከቆየ በኋላ ግን ጉዳዩ የማያገባቸው፥ የውርስም ሕጋዊ መብት የሌላቸው መነኮሳት የዘውድ በዓል ማክበር ከጀመሩ ሦስት ዓመታቸው ነው። በዚህ ምክንያት የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ መመዝበር ከጀመሩ የዚያኑ ያህል ነው። ግን ሞኙ አባ የሚጠይቃቸው ቢያጡ ታሪክ አድርገው ሊያወሩን ይሞክራሉ። ሊቃውንት በሌሉበት እስዎ የዓለም ባለሙያ ሆነው የተገለገሉበት እንጂ ውርሱንም ሆነ ታሪኩን ከበዓለ መስቀል ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። እንዲህ ያለው የታሪክ ውንብድና ቢቆም መልካም ነው። ከሌሎች ወገንም አንዱ፤ «መስቀል ማለት መስቀለኛ ዕንጨት ነው፤» በማለት የሰጠው፥ ሌላኛው የሥጋዊ በዓል አከባበር አስመስሎ የሰጠው አስተያየት ትክክል ካለመሆኑም በላይ፤ ሁለቱም ወገኖች ፩ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ ፩ ቍጥር ፲፰ን ጠቅሰው ሊያስተላልፉ የሞከሩት አነጋገር ዐብረው ካስተላለፉት ጋራ የማይስማማ ከመሆኑም በላይ ከበዓሉ ጋር ምንም ዐይነት ልምድ የሌላቸው፥ ለበዓሉ ባዕድ መሆናቸውን በግልጥ ያሳያል። ይህን ያህል ርቀት ያለበትን ነገር የኢትዮጵያ መገናኛ ድርጅት የዕገሌ ቤተ ክርስቲያን ማለት የኦርቶዶክስ፥ የካቶሊክና የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ተወካይ እያለ ያስተላለፈው ነጎዳ ፈሩን የሳተ ነው። ዐዲሶቹ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ቤተ ክርስቲያንን የካዱ ናቸው። ካቶሊክና ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን የሚባሉትም የኢትዮጵያን ነባር ሃይማኖት ነቅፈው የራሳቸውን ሚስዮናዊ ተልዕኮ አስፋፊዎች ናቸው እንጂ የኢትዮጵያ አይደሉም። በዓሉም የኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያን እንጂ የአውሮፓ ወይም የአሜሪካ፥ የአውሮፓውያንና የአሜሪካውያን ጉዳይ አይደለም። ነገሩ እንዲህ ሆኖ ሳለ በልዩ ልዩ የሃይማኖት ክፍል ስም ከእውነቱ ዐልፈው በሐሰት ኅብረት፥ በወሬ ጥምረት ሕዝቡን ለማሳሳት መሞከር ከትዕቢት ማለፍ ነው።
በብሉይ ኪዳን፥ በሐዲስ ኪዳን ከተሰበከው ከክርስቶስ ሃይማኖት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እበልጣለሁ፥ እውነቱም እኔ የያዝኩት ሃይማኖት ነው የሚል ካለ ዐደባባይ እንውጣና፥ መድረክ ይከፈትና በታሪክ፥ በመጻሕፍት ምስክርነት፥ በመንፈስ ቅዱስ ዳኝነት እንነጋገር። ከአባቶቼ እኔ ብቻየን ቀርቼአለሁ። እንዲህ ስል እግዚአብሔር ለነቢዩ ኤልያስ የተናገረውን አልረሳውም። ብዙ ኦርቶዶክሳውያን እንዳሉ እንደሚኖሩም አምናለሁ። እስካሁን ከእኔ ጋር የተጋለጠ ግን የለም። ወደፊት የሚመጣ ዐብሮኝ የሚሰለፍ ካለም ደስ ይለኛል። እስከዚያው ድረስ ግን ቤተ ክርስቲያናቸውን የካዱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጊዜው መሪዎች፥ ልዩ ልዩ የባዕድ ሃይማኖት አራማጅ ክፍሎች በክርስትና ስም በማስመሰል በኢትዮጵያ የሚያስተላልፉት እውነት አይደለምና ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ሃይማኖታችሁን፥ ባህላችሁን፥ ሥርዐታችሁን በጥንቃቄ ጠብቁ። እኔ እንደምመለከተው ከሆነ ሁሉም በየራሳቸው ሕዝቡን ለማታለል፥ ለማሳሳት የሚያደርጉት ሁሉ ቅዱስ ጳውሎስ፤ «የክርስቶስ የመስቀሉ ነገር በጥፉዎች ዘንድ ስንፍና ነው፤» ሲል የጻፈው ሊፈጸምባቸው ይመስለኛል። ጌታ፤ «ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ያሳተ ይፈረድበታል፤» ያለው እንዲፈጸምባቸው እንደ ሆነ ነው እንጂ ይህን ያህል የሚቅበዘበዙት ሌላ ጥቅም ሊያገኙ አይመስለኝም። ካቶሊክም ፕሮቴስታንትም በመስቀል አያምኑም፤ በመስቀል አይባርኩም፥ አይባረኩም። ካቶሊካውያን በመስቀሉ የጌታን መልክ የመሰለ ቅርጽ ደርበው ነው መስቀል የሚያደርጉት፤ በመስቀል ግን አይባርኩም፥ አይባረኩም። ፕሮቴስታንቶች ግን ጨርሶ መስቀልን አይቀበሉም፤ «የአባት ገዳይ፤» እያሉ ያሾፋሉ። አምናና ዘንድሮ በደመራው በዓል ላይ ሲበተን ከነበረው ወረቀት እንዲህ ዐይነት ስሜት እንደ ነበረ ብዙዎች ይመሰክራሉ። በዚህም ልዩ ልዩ የሃይማኖት ክፍሎች የያዛችሁት እውነት ከሆነ መድረክ ይከፈት፤ እንነጋገርበት። አለዚያ ሕዝቡን አታሳስቱ። ይፈረድባችሁአል። የኢትዮጵያ መገናኛ ድርጅትም ሃይማኖትን ከፖለቲካ ማጎዳኘቱ ቢቀር ጥሩ ነው። ምእመናን ግን ከሁሉም ተጠንቀቁ።
ምእመናን! ሰዎች ያሉትን ቢሉ፥ ያደረጉትን ቢያደርጉ፥ የእናንተ የሆነውን እውነቱን እንዳታዩ በብዙ ግርዶሽ ዐይናችሁን ለመጨፈን ብትሞክሩም እግዚአብሔር ግን የዘመኑ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች፥ ሌሎችም የቤተ ክርስቲያን ተቃዋሚዎች በተጓዳኝ የሚያወሩት እውነት አለመሆኑን እያረጋገጠ እየመሰከረ ነው።
ካለፈው ዓመት ጀምሮ በእነ አባ ጳውሎስ በኩል የሚደረገው የደም ማፍሰስ፥ ሰዎችን ማሳሰር፥ ማስደብደብ፥ የገንዘብ ምዝበራ እየተስፋፋ መሄዱ ግልጽ ከመሆኑም በላይ ባለፈው ዓመት ዘንድሮም በየቤተ ክርስቲያናቱ በር ላይ ይደረግ የነበረውን ደመራ ከልክለው፥ የምእመናንን ጸሎት አግደው፥ የእግዚአብሔርን ክብር ተጋፍተው ሕዝበ ክርስቲያኑ በሙሉ እሳቸው ካሉበት ዐደባባይ በግዴታ እንዲሰበሰብና እሳቸውን እንዲያከብር፥ እንዲያመልክ በማስገደዳቸው እነሱ የሚያሳርጉትን ዕጣን የተጠየፈ የባቢሎንን ግንብ ባፈረሰበት ሥልጣኑ ድንኳናቸውን እንዳፈረሰውና የሥራቸውን ከንቱነት እንዳጋለጠ አይታችሁአል። የቀረበው ቀርቦ የዐይን ምስክር ሲሆን ለራቀውም የቴሌቪዥን ድርጅት መስክሮለታል። እዚህ ላይ አንድ ነገር ላስታውስ። እላይ ማጎዳኘቱ ይቅር ብዬአለሁ። ለበዓሉ አከባበር መደበኞች አስመስሎ ማቅረብ ይቅር እላለሁ እንጂ ያየውን አይመስክር አይደለም የምለው። የሆነውን፥ ያየውን፥ የሰማውን ለማንም ድጋፍ ሳይሰጥ ቢመሰክር አያስወቅስም። የእውነት ምስክር ነውና። እኔ የምፈልገው እውነት ይናገር ነው። አሁን የአዲስ አበባ ምእመናን ከቀሳውስትና ከአለቆች፥ ከካህናትና ከጳጳሳት፥ ከፓትርያርኩም ጋር ሆነው በእግዚአብሔር ላይ ዐምፀዋል። ገዳዮች እየገደሉ፥ አስገዳዮች እያስገደሉ፥ ደብዳቢዎች እየደበደቡ፥ አስደብዳቢዎች እያስደበደቡ፥ አሳሪዎች እያሰሩ፥ አሳሳሪዎች እያሳሰፉ፥ ገንዘብ መዝባሪዎች እየመዘበሩ፥ አስመዝባሪዎች እያስመዘበሩ ይህን ሁሉ እያሉ መከላከል ሲቻላቸው የማይከላከሉ፥ መናገር ሲገባቸው ዝም የሚሉ፤ ያለዚያም ርቀው መመልከት፥ ከደም ማኅበር መለየት ሲገባቸው ተቀላቅለው የሚያፌዙ ሁሉ ከታላቁ ፈራጅ ከኀያሉ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አምላክ ፍርዳቸውን ይቀበላሉ። ስለዚህ ምእመናን ተጠንቀቁ። «ከርኩሳን ተለዩ፤ ወደ ርኩሳን አትቅረቡ፤ ከመካከላቸው ውጡ፤ እኔ አባት እሆናችሁአለሁ፤» ብሏል እግዚአብሔር። ይህ የእግዚአብሔር ዐዋጅ ነው። ጆሮ ያለው ይስማ።
ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን። አሜን።»
አለቃ አያሌው ታምሩ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጉባኤ ዋና ሰብሳቢ።

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)