September 26, 2009

ማኅበሩን ለሚያውቁት ሁሉ

(አድማሱ ነኝ)
በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆች የሕዝብም ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ፥ ኢየሱስንም በተንኰል ሊያስይዙት ሊገድሉትም ተማከሩ፥

ይህ ቃል ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ቃሉን ልብ ብለን ስንመረምረው የካህናት አለቆቹም ሆኑ ባለስልጣናቱ ጌታችንን ለመክሰሰ የተነሱት በተንኮል ነው፡፡ ሃሳባቸውም መክሰስ ብቻ ሳይሆን መግደልም ጭምር ነበር፡፡ ባለስልጣናቱና ካህናቱ ጌታችንን የከሰሱት በብዙ ቢሆንም ጠቅልለን ስናያቸው ግን ሁለት ዋና ዋና ክሶች ነበሩ፡፡ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ይላል፤ የአይሁድ ንጉስ ነኝ ይላል፤ ለቄሳር ግብር አትክፈሉ ይላል እና የመሳሰሉት ነበሩ፡፡

ይቀርቡ ከነበሩት ክሶች አንዳንዶቹ የሀሰት ክሶች ሲሆኑ፡ ለምሳሌም ለቄሳር ግብር አትክፈሉ አለ የሚለውን የመሳሰሉት ሌሎቹ ደግሞ ካለመረዳት የሚነሱ ነበሩ፡፡ ወደዝርዝሩ አልገባም፡፡ ዛሬ ይህንን ለመጻፍ የተነሳሁት ሰሞኑን በማኅበረ ቅዱሳንና በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ መካከል ያለውን አለመግባባት በተመለከተ በመንበረ ፓተርያርኩ የተደረገውን ስብሰባ የተመለከተ ዜና አይቼ በማዘኔ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን የማውቀው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኜ ጊቢ ጉባዬ ስከታተል ጀምሮ ነው፡፡ አገልግሎቱን አና ጥንካሬውን እረዳለሁ፡፡ የማኅበሩ አባል ሆኜ ለማገልገል ካንዴም ሁለቴ ተመዝግቤ በተለያዩ ምክንያቶች ሳልገፋበት ቀርቻለሁ፡፡ እነዚህ አጋጣሚዎችና የሕትመት ውጤቶቹ ሐመርና ስምዐ ጽድቅ መጽሐፍቶቹ ዐውደ ርዕዮቹ እና ሌሎች አገልግሎቶቹን በሚገባ ለማወቅ እድሉን ስለሰጡኝ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ተከሶ ሳየው አዘንኩ፡፡ እናም ይህችን አጭር መልዕክት ማኅበሩን ለሚያውቁት ሁሉ ለመጻፍ ተነሳሁ፡፡

ሶስና በክፉ የርኩሰት ስራቸው አልተባበርም ባለቻቸው ጊዜ በሃይማኖትም በዓላማም የማይመሳሰሉ ሁለቱ ረበናት ከሰዋት በፍርድ አደባባይ ቆማ ሲያዩ ንጽህናዋን የሚያውቁ ሁሉ አለቀሱላት ተብሎ እንደተጻፈ ዛሬም ስለቤተክርስቲያንና ቤተክርስቲያንን በፍጹም ፍቅር በማገልገላቸው ለሚከሰሱ እና ለሚንገላቱ ሌላ ነገር ማድረግ ባንችል ቢያነስ እናልቅስላቸው፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን ጸጥ የሚደርግላትን እንደ ነቢዩ ዳንኤል ያለ እውነትን በጥበብ የሚገልጽ አስኪያስነሳልን ድረስ ወደ ርሱ በጸሎት ማሳሰባችንን ቸል አንበል፡፡
ለማኀበሩ አባላትም እነደ ታናሽ ወንድም በርቱ ከፊት ይልቅ ጸንታችሁ ቁሙ ብዬ በትህትና መልዕክቴን ለማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡ የመንግሰት የደህንነት ባለስልጣናትን ይዘው ሊያስፈራሩ የሚፈልጉትን ስታዩ አትደንግጡ ይልቁንም ከኛ ጋር ያለው ከነሱ ጋር ካለው ይበልጣል ብላችሁ ተጽናኑ፡፡ በጊቢ ጉባዬ በኩል ላለፋችሁ የማኅበሩ አባላት ወይም እንደኔ ዛሬ የማኅበሩ አባል ያልሆናችሁ በምርቃታችን ጊዜ የተሰጠንን ስጦታ አስታውሱት- መስቀሉን ማለቴ ነው፡፡ ብዙ ሚስጥር ያለው ነገር መሆኑን እያደር እንረዳዋለን፡፡ እኔ አስካሁን ከአንገቴ አልለየሁትም ሺዎች ደግሞ በልባቸው አትመው እንደያዙት አምናለሁ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጌታው የሚበልጥ ሎሌ የለም ብሎ እንዳስተማረን ሰድበውት ከሆነ ሰትሰደቡ አይክፋችሁ ከስሰውት ከሆነ በሀሰት ብትከሰሱ አትረበሹ በአጋንንት አለቃ ሰይጣንን ያስወጣል ብለውት ከሆነ ማኅበረ ሰይጣን ብለው ቢጠሩአችሁ አትደነቁ፡፡
አምላከ ቅዱሳን ሁላችንንም በይቅርታውና በምህረቱ ይጎብኘን፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)