September 23, 2009

የአማኙ ጥያቄ ይህ አልነበረም

(ከዮፍታሔ)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
(ሰፕቴምበር 23/2009):- ውድ ወገኖቼ፦ በመጀመሪያ በዚህ ነገር ብዙዎቻችን ብዙም እንደማንርበሽ ነው የሚገባኝ ምክንያቱም የ97 ቱን ምርጫ ተከትሎ በመጣው ግርግር ቤተ ክርስቲያንን መጠጊያ ለማድረግ ወደ ቅጽሯ የተሰደደውን ወጣት እንዴት አድርገው አሳልፈው እንደሰጡት ገና የፈሰሰው ደም ከአደደባባዩ ላይ በቅጡ አልደረቀምና ነው። ይህ የአሁኑ ደግሞ ሁለተኛ ሽያጭ መሆኑ ነው። ምን ያህል የመንግስትን ቀልብ እንደሳበላቸው ባላውቅም፣ መንግስትም ያቀረቡለትን የፈጠራ ክስ በምን አይነት ሁኔታ እንዳየው ለኔ ግልጽ ባይሆንልኝም ማህበሩን ግን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለመኮርከም ወደኋላ ግን አይልም። አባቶች ብለን የክርስቶስን በግ ጠባቂዎች (ኖላዊ አባግዕ) ተብለው የተሰየሙት መነኮሳቱና ባለ አስኬማዎቹ አባቶች ትውልዱን ወደ ሞት ሊነዳ በሚችል ኃላፊነት በጎደለውና በስግብግብነት መንፈስ ለአለሙ ፍርድ ቤት ከሰው ለፍርድ አቁመውታል። በክርስትና ህይወቴ እንደዚህች ቀን ያፈርኩበትና ሆዴ የተረበሸበት ቀን አላስታውስም። በአባ ሠረቀ በጣም አፍሬያለሁ። እነዚህን ከሳሾች የዚህን ማህበር ያህል ምን እንደሰሩ ብንጠይቃቸው መልካም ነበር።

የአማኙ ጥያቄ ይህ አልነበረም ። የእኛ ጥያቄ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የሰፈነዉ የዘር አሰራር ተነቅሎ ይውጣ ነው ያልነው የቤተ ክርስቲያንቱ ሃብቷና ገንዘቧ ለእምነቷ ማስፋፊያ ይዋል ነው ጥያቄያችን የግለሰቦች ሃብት ማድለቢያ አይሁን ነበር ጥያቄው የአስተዳደራዊው ስራ ከግለሰቦች ተጽዕኖ ይዉጣ ነበር ያልነው ይህ ጥያቄያችን ወደ ፊትም ይኖራል መልስ እስከያገኝ ድረስ።

በጣም ያስደነገጠኝ በቅዱስነታቸው የተነበበው መግለጫ አይሉት ማዘዣ ነው።ለመሆኑ ይህ ሽፍጥ ከተዘፈቁበት ውጣ ውረድ ፋታ ያሰጠኛል ብለው ይሆን ? ማህበሩ የፖለቲካ አዝማሚያ ስላሉት ጉዳይ ለሚነሳው ጥያቄ መልስ የምንፈልገው ከፓትርያርካችን ሳይሆን ከዘመኑ ተዋናይ ከአባ ሠረቀ ነው። ለመሆኑ የየትኛው የፖለቲካ ድርጅት ደጋፊ ነው?
ከአባ ጳውሎስ ንግግር በጣም ያመመኝ ማህበሩ በቤተ ክርስትያን አስተዳደር ውስጥ የመግባት አዝማሚያ ያሳያል ነው ያሉን ለመሆኑ የግል ቤት ነው ብሎ የነገረዎት ማነው ወይስ የእንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተውበታል ይህን ስላሉስ እኛ አያገባንም እንደፈለጉ ያድርጉት ብሎ አይኑን ከቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ የሚያነሳ አለ ብለው አስበው ይሆን እንዴ። ይህ ከሆነ አላማዎት አባቴ ይሙቱ ሞኝ ነዎት።

ውድ በሰሜን አሜሪካ የምትኖሩ የዚህች መከረኛ ቤተ ክርስትያን እድምተኞች እንግዲህ ባለፉት ሁለት እና ከዛም በላይ ሳምንታቶች ባንዳው ንጉሴ በጦር እንደተወጋ ተኩላ ሲያጓጉር የነበረበት ዋነኛ ምክንያት ይሄና ይሄ ብቻ ነው። ክፍያው ተጠናቆ ይከፈለው አይከፈለው ግን ለጊዜው በእንጥል ይቆየን።
ግን እኮ የእኛ ጥያቄ አሁንም ይህ አይደለም የሲኖዶስ ህግ ይከበር ነው ያልነው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተሰገሰጉት ሌቦች፣ የቅርጽ ዘራፊዎች፣ የቤተ ክርስቲያኒቷን ንብረት እንደ ራሳችው ንብረት ከሚግጧት ደሟን ከሚመጧት ደም መጣጮች ትንጻ ነው ያልነው ። ለዚህ ጥያቅያችን ከሆነ የትናንትናው ትያትር እንደ መልስ የቀረበልን ጥያቄውና መልሱ በጣም የተራራቀ ነው የማይገናኝ ፍየል ቦሌ ቅዥምዥም ጉለሌ እንደሚባለው አይነት ማለት ነው።
አሁን የሚጠበቀው የጥቅምት ጉባዔ እየተቃረበ ነው። ታድያ የእኛስ ድርሻ ምን መሆን እንዳለበት ካሁኑ ማወቅ አለብን። ለአባቶች ከመጸለይ ጀምሮ በአላማቸው ጸንተው እንዲተጉ እየደወልን ከጎናቸው መሆናችንን መግለጽ ያስፈልገናል። እዚህ በገለልተኛ ነን ስም የሚያደናገሩትን አብያተ ክርስቲያናት አቋማቸውን በትክክል እንዲያስረዱ ምዕመናኑ መጠየቅ አለባቸው።ይህ አባ ሠረቀ ከአዲስ አበባ ሆነው በሪሞት የሚያንቀሳቅሱትን የቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተ ክርስቲያንንም ይጨምራል።

የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላት ስራችሁ ከስማችሁጋራ ብዙም አይገናኝም ገንዝብ እያወጣችሁ ለአድባራትና ለገዳማት የምትሰሩት ስራ እንዳለ ሆኖ፣ ከአገር ቤት ከየመጣችሁበት ቀዬ ካሉት የመንፈስ ወንድሞቻችሁ ሁኔታው ካመቻችሁ በኢንተርኔት ካልተቻለ በደብዳቤ መረጃ መለዋወጥ መቻል አለብን። እዚህ ያለነው በተሻለ መልኩ የመረጃ ምንጭ አለን። ካለዚያ እሁድን ጠብቆ መዘመርና አመት እየጠበቁ በየስቴቱ ጊዜንና ገንዘብን መስዋዕት አድርጎ መሰብሰቡ ለለውጥ ካልሆነ ከእረፍት ጊዜ ማሳለፊያነቱ እምብዛም አይዘል።

6 comments:

Anonymous said...

WHO IS ABA SEREKE:
Dear Dejeselamawuyan,
When I read Yoftahe's comment, I also feel bad... But the question is who is Aba Sereke...
Aba Sereke was in US at LOs Angeles Kidist selassie church as a head before the current head, Ababa Haile selassie Amedu.

Aba Sereke was with Aba Tekeste who first go to another state as Abab Serereke enforced him to go.

Then Aba Sereke took the ' Tabot' and other albasat's and money from the church and flew to another state.
During that time, Abune Matiyas, who is now living in Israel beged him to return the stuffs and the Tabot, he rejected that and start a new life ....
Now Aba Sereke is acting as he is the side of church. Please ask old members of Kidistselassie church of Los Angels. THey will tell you who he is...
Yih Yemekera zemen newuna tegiten Eniseliy.

Anonymous said...

በስመ ሥላሴ

« ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።» ሐዋ 5 ፣ 38

በብላቴ በረሃ መልካም ጥንስስን ጠንስሶ፣ ከቡቄሳ ተራራና ከኬስፓኖቿ እሳት አውጥቶ፣ ከሞርቾ የእግር ጉዞ የጥይት እራትነት ጠብቆ፣ ከፊሉን በአዋሳ በኩል ወደ መሃል አገር ልኮ፣ ከፊሉን በኬንያ አድአ የስደተኛ ካምፕ ጠልሎ ለትልቅና ለተመረጠ ሥራ ታናናሾችን ያጨ እግዚአብሔር ባለፉት ሃያ ዓመታት ያደረገውን ጥበቃ ዛሬም ከማኀበሩና ከአገልግሎቱ ጋር እንደሚያደርግ እምነቴ ነው።

ማኀበሩ በቡቃያነት ዘመኑ ያፈራውን መልካም ፍሬ አይተው ሊመሩትና ሊያግዙት «እኛንም አባል አድርጉን» ያሉ ታላላቅ አባቶች የነበሩትን ያህል፤ እንዲሁ በስሜት ብቻ «ከዛሬ ጀምሮ እኔም አባል ነኝ» ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ በያኔ ሥራው ብዙዎች ተደስተውበት «እደግ እደግ» ብለውት ነበር። ማኅበረ ቅዱሳን አራሚዎችና ዘሪዎች ባነሱበትና ባንቀላፉበት ወቅት ለስራ ተመርጠው ነበርና ቤተ ክርስቲያኒቱ ባላት መዋቅር ልትደርስበት ያልቻላቻችውን ቦታዎች ሁሉ በማዳረስ፣ የመናፍቃን ጎራ ሆኖ እንደ ጭልፊት ትውልዱን ሲጨልፉበት የነበረውን ዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ሐዋርያዊት የአባቶቻችን ሃይማኖት የሚሰበክባት እንድትሆን በማድረግ፤ ብዙ እጂግ ብዙ የተፈቱ ቤተ እግዚአብሔሮች እንዲከፈቱ ያሉትም እንዲበረቱ በማደረግ፣ ወጣቱ ትውልድ ከአባቶቹ እምነት ጋር መልሶ እንዲተዋወቅ በማደረግ ታላቅ ድርሻን የተወጣና ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገሪቱ ባለውለታ ማኅበር ነው።

የማኅበሩ የአገልግሎት አድማስ አየስፋ ሲመጣና ከአባላቱ በአንደኛው መኖሪያ ቤት ክትት ብለው ያልቁ የነበሩ ፈቃደኛ አባላቱ ስድሳና መቶ አፍርተው በመላ ሃገሪቱ የአባቶቻቸው ልጆች ሆነው ሲገኙ ብዙዎች የተደሰቱትን ያህል ማኅበሩ የእግር እሳት ሆኖባቸው እርሱን ለማጥፋት ሥራዬ ብለው ቆርጠው የተነሱም ነበሩ። ከውስጥም ከውጭም። « ሀገር ሲያረጅ እምቧጮ ያበቅላል » እንዲሉ በአሁኑ ስዓት ማኅበሩ ከተጋረጠበት ፈተናዎች መካከል ከባዱና ዋነኛው በአንድ አውድማ ለመሰማራት ቤተ ክርስቲያን «ልጆቼ» ብላ ለስራ ያሰማራቻቸው የገዛ ልጆቹአ ጋር ያለው ፈተናው ነው። በዚህ ሃያ አመት ውስጥ የታየው « ቤተ እግዚአብሔርን ማገልገል» እየተረሳ መጥቶ «በቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት መተዳደር» እየጎላ መምጣት ማህበሩ በፈቃደኛነትና በነጻ ለሚሰጠው አግልግሎት አንድ ተጨማሪ ስውር የፈተና ጎራ ሆኖበታል። ይህ አካሄድና ሁኔታ ግን ለማኅበሩ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን በጥቅሉ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐይማኖት በማንነቷ መቀጠልና አለመቀጠል ጋር ቀጥታ ትያያዥነት ያለው ጉዳይ ነው። አባቶቻችን አገልግሎትን በአገልግሎትነቱ ንጽህና ጠብቀውት ሰለነበር በመንፈሳዊ ኩራት «የሰጠኸኝን ሰጠሁህ» ብለውን ሲይልፉ የአሁኑ ትውልድ ግን «መተዳደሪያዬና እንጀራዬ» ብሉ የያዘውን ክህነት ለማስጠበቅ ብቻ በእውር ድንብር ሲጓዝ «ያልተሰጠውን ለተተኪው ትውልድ የሚስጥ» አሳዛኝ ትውልድ የመሆን እጣ ከፊቱ ተጋርጧል።

መንግሥትም ማኅበሩን በዐይነ ቁራኛ መከታተል የጀመረው ዛሬ ሳይሆን ገና ከጥንስሱ ቢሆንም የውስጥ አርበኛ ሆነው ማኅበሩን ሲከታተሉ የነበሩ የማኅበሩ አባላት «እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትም እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት» ስላሉ ለጊዜው ፋታ ያገኘ ቢሆንም የ 1997 ምርጫ እንደማንኛውም የህብረተሰብ አካል ሁሉ ማኅበሩን ክፉኛ ፈተና ውስት ጨምሮት ሄዷል። መንግስትም የበቀል አርጩሜውን በፍርሃትና በጭፍን ከሰነዘረባቸው መካከል ማኀበሩና አባላቱ እንደሆኑ ሁሉም ያውቀዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ማኅበሩን አሳልፎ ለመንግሥት አለሰጠም ነበር። እጅግ ብዙ በጣም ብዙ ጊዜ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቢሮ በአሰራር ሂደት አቤቱታ አቅራቢነትም ሆነ በመልስ ሰጪነት የተገኙ የማኅበሩ አባላት « በማኅበሩ አሰራርና አካሄድ ካልተደሰቱና በየፊናው የሚወራው ወሬ ዕውነት ነው ብለው ካመኑና ለቤተ ክርስቲያንም ይህ መሆኑ ይጠቅማታል ካሉ ማኅበሩን ያፍርሱት እኛም እንበተናል» የሚል የጠራ ኃሳብ ማህበሩ ባቀረበበት ወቅት እንኩዋን ማህበሩ ቢበተን አባላቱ በግል የሚያጡት ስጋዊ ጥቅም እንደሌለ ቤተ ክርስቲያን ግን በናኅበሩ መኖር እነደምትጠቅም በግልጽ ያዬት ፓትርያርኩ ወደ አዕምሮአቸው በቶሎ ይመለሱ ነበር። የአሁኑ ግን ለየት ያለ ነው። ተሰላፊዎቹ የበዙበት፣ መንግስት ለ2002 ምርጫ በፍርሃት የሚያቸውን አካሎች የሚያጠፋበት ወይንም ቅስም የሚሰብርበት፣ የፓትርያርኩ የመንግሥት ቀኝ እጅነት በቅዱስ ሲኖዶሱ እጂግ የዘገየ እርምጃ ፈተና ውስጥ የወደቅበት በመሆኑ ፓትርያርኩ ማኅበሩን አሳልፈው የሰጡበት አሳዛኝና አሳፋሪ የታሪክ ጊዜ ደረስን።

ከሳምንታት በፊት በሰጡት መግለጫቸው « ልማት፣ ሰላምና መረጋጋት» የምትል ሐረግ በማስገባት «እኔ ከመንግሥት ወገን ነኝ» ለማለት የሞከሩት ፓትርያርኩ አሁን ደግሞ «ማኅበሩ በፖለቲካና በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጣልቃ የመግባት አዝማሚያውን እንዲያቆም» በማለት ከማይክራፎኑ ጀርባና ከፓትርያርኩ ፊት ሌላ ተናጋሪ አንደበት ያለ እስኪመስል ድረስ ከእርሳቸው የማይጠበቅ ኃይለ ቃል ተናገረው ራሳቸውን ዳግም አቀለሉ። ኦዲት እንዲደረግ የተባለውም የማኀበሩ ሂሳብ ምናለ በቶሎ በቶሎ አድርገው ቢጨርሱትና ቢያሳውቁን፤ እንደ ዛሬው በመግለጫቸው አያካትቱትም እንጂ የማህበሩ ሥራዎች የሚተነተኑበት መልካም አጋጣሚ ይሆን ነበር ግን ምን ያደርጋል ክስን እንጂ ውጤቱን ስለማይናገሩ ውዥንብሩን ብቻ ነዝተውት ይቀራሉ።

በአንድ በኩል የፖለቲካ ተቃዋሚው ጎራ « ለሀገሩ ደንታ የሌለውና ወደ ቤተ ክርስቲያን እንጂ ወደ ስብሰባ አዳራሽ መውጣት የማይወድ ተልካሻ ተውልድን ማኅበረ ቅዱሳን እያፈራ ነው» በማለት በአገርም በውጪም ያሉ «አንቱ» የተባሉ «ፖለቲከኞች» ማኅበሩን ሌትተቀን ይከሳሉ፤ በሌላ በኩል « አህዳዊ አመለካከት ያላቸውና የተቃዋሚዎች ጎራ ሆነዋል» እያለ መንግሥት ማኅበሩን ይከሳል።

በግንባር ሆናችሁ እሳቱን ለምትጋፈጡ ወንድሞችን እህቶች መድኃኔአለም ብርታቱን ይስጣችሁ። የዚህ የማኅበረ ቅዱሳን አመስራረትና ሥራው ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ያጠፉአችሁ ዘንድ አይቻላችውም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ሲጣሉ ምናልባት ይገኙ ይሆናልና።»

SendekAlama

Anonymous said...

Kal-hiwot yasemaln wendem Sendek Alama M Kudesanen ye-Kedewsan Amelak Egzabehar Yetbekeln Amen.


G/Egzabehar The Canada

Anonymous said...

http://mkorms.blogspot.com/

Anonymous said...

http://mkorms.blogspot.com/

Wolede Tekelehaimanot said...

ደጀ ሰላማላውያን !ፉከራ ብቻውን ለውጤት አያበቃም የመጣውን ፈተነና ለማለፍ እንድንችል አለም አቀፍ የጸሎት መርኃ-ግብር ቢታወጅ መልካም ነው !

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)