September 18, 2009

መንበረ ፓትርያርኩ ከሩብ ሚሊዮን ብር በላይ ለደመራ መደበEthiopia Zare (ኀሙስ መስከረም 7 ቀን 2001 ዓ.ም. September 17, 2009)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የፊታችን መስከረም 16 ቀን 2002 ዓ.ም. ለሚከበረው የደመራ በዓል ከሩብ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አፀደቀ። የወጪው መብዛት ምዕመናኑን አሳዝኗል።

ለፖሊስ ባንድ አባላት 28 ሺህ ብር፣ ለአራት ትራፊክ ፖሊሶች አንድ ሺህ ብር፣ ለሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ትርዒት አገልግሎት የሚውል የማቴሪያል መግዣ ሁለት መቶ ሺህ (200000) ብር እና ለ56 አሠልጣኞች 25200 ብር፤ በድምሩ ሁለት መቶ ሃምሳ አራት ሺህ ሁለት መቶ (254200) ብር ወጪ እንዲደረግ መጽደቁን ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በአባ ይስኃቅ ተፈርሞ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ከተላከው ደብዳቤ ለመረዳት ችለናል።


ነኀሴ 29 ቀን 2001 ዓ.ም. የተፃፈው ይኸው ደብዳቤ የመስቀል በዓል አዘጋጅ ዓቢይ ኮሚቴ ከገንዘብ አሰባሳቢ ንዑስ ኮሚቴ የቀረበለትን መግለጫ ተቀብሎ ነኀሴ 22 ቀን 2001 ዓ.ም. ማጽደቁን ያትታል። የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሆኑት በአባ ይስኃቅ ፊርማና ማኅተም የወጣውና በቀጥታ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በቁጥር 5258/290/2001 የወጣው ደብዳቤ፤ በግልባጭ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣ ለሂሳብና በጀት መምሪያ፣ ለቁጥጥር አገልግሎት መምሪያ፣ ለበዓል አዘጋጅ ዓቢይ ኮሚቴ፣ ለፀጥታና ሥነሥርዓት አሰባሳቢ ንዑስ ኮሚቴ እና ለሰንበት ት/ቤት ያሬዳዊ
መዝሙርና ትርዒት ዝግጅት ንዑስ ኮሚቴ ደርሷቸዋል።

ይህንን ከሩብ ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ወጪ በርካታ የኦርቶዶክስ ምዕመናንን እንዳሳዘነ የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢዎች ከየሥፍራው (ከሀገር ቤት እና ከሀገር ውጪ) ያሰባሰቡት መረጃ ያስረዳል። ምዕመናን “ፓትርያርኩ ተጠያቂነት በሌለበትና ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ገንዘብ እያባከኑ ነው ለሚባለው ይህ አንዱ ማረጋገጫ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

ለበዓል የሚወጣው ወጪ ያሳዘናቸው ምዕመናን በርካታ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ የተገደዱ መሆናቸውን ለመረዳት ችለናል። ከእነዚህም ውስጥ “አቡነ ሳሙኤልን በአዲስ አበባ ከነበራቸው ሥልጣን ፓትርያርኩ ያነሷቸው እንዲህ ላለው የገንዘብ ብክነት ያመቻቸው ዘንድ ነው ወይ?”፣ “ገንዘቡ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ለምን አይውልም?”፣ … የሚሉ ይገኙበታል።

እንዲህ ያለውን የገንዘብ አወጣጥና አሠራርን አጥብቀው የሚቃወሙትና ሥርዓት ለማስያዝ የሚጥሩ አባቶች በየጊዜው በተደራጀ ኃይል ጥቃት ሲፈፀምባቸው መቆየቱን ያስታወሱ አንድ ምዕመን፤ “ይሄ የኦርቶዶክስ ምዕመናን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጉዳይ ሊሆን ይገባዋል፤ ሁሉም ዜጋ በያለበት ኃይማኖት ውስጥ ሆኖ እንዲህ ላሉት በኃይማኖት አባትነት ሥም ለሚፈፀሙና የሞራል ጥያቄ ሊያስነሱ የሚችሉ ሥርዓት አልባ አካሄዶችን ማውገዝና መከላከል ይገባቸዋል” ብለዋል።

ከዚህ በተቃራኒው ሃሳባቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ የገለጹ ምዕመናን ደግሞ፤ የገንዘቡ መጠን የበዛ ቢመስልም በሀገር ውስጥ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ለማያያዝ ሞክረዋል። ከጠቅላላ ወጪው ውስጥ ሁለት መቶ ሺህ (200000) ብሩ ለሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ትርዒት አገልግሎት ለሚውል ቁሳቁስ መግዣ መዋሉን ግምት ውስጥ በማስገባት፤ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ቢያንስ ከ300 % (ሦስት እጥፍ) የኑሮ ውድነት በመከሰቱ በአንፃራዊነት ወጪው ብዙ አይደለም ሲሉ እነዚሁ ምዕመናን ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልፀዋል።

3 comments:

yophtahe said...

ውድ አንባብያን፦

የመስቀል በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ከምታከብራቸው ታላላቅ በዓላቶች ውስጥ ከመጀመሪው ረድፍ የሚሰለፍ በዓላችን ስለሆነና ፣ የውጭ ሃገር ዜጎችም ይህንን ታላቅ የደመራ በዓል ትዕይንት ለመመልከት እና በየመቅረጸ ምስላቸው ቀርጸው ለማስቀረት ስለሚሹ በዓሉ በደመቀ ሁኔታ ቢከበር የሚያስከፋ አይሆንም ። ችግሩ የበዓሉ አከባበር ሳይሆን የተመደበው ገንዘብ በትትክል ተፈላጊው ቦታ ላይ ይውላል ወይ ነው ጥያቄው?የማፍያው እጅ ካለበት ግን ይህ የተነገረን ገንዘብ እራሱ የመጠኑ ትክክለኛነት ራሱ ያጠራጥራል።

የዋጋውን ግሽበት ፣የኢኮኖሚውን ሁኔታም ሳይዘነጋ ማለቴ ነው።


መሆን ያለበት በዓሉ የራሳችን ነዉና በተውኅቦ እንዲያልፍ ሁላችንም የበኩላችንን እናድርግ። ስለ ወጭው ግን የበአል ዝግጅት ክፍሉ ከበዓሉ በኋላ ለህዝቡ አግባብ ባለው መንገድ ቢያሳውቅ የሰለጠነ አካሄድ ይሆናል።

መልካም የደመራ በዓል ለመላው የተዋህዶ አማኞች።

Unknown said...

Surprising to hear such amount of money for not morthan 3 or 4 hour cermoney thinking being in a shoe of Ethiopian poor people...
mtm from NL

Anonymous said...

ገንዘቡ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ለምን አይውልም?

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)