September 5, 2009

መንግሥት ሆይ እጅህን ከቤተ ክርስቲያን ላይ አንሣ!!!!!!!!

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 4/2009)፦ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ሆና ቢያንስ እስከ 1966 አብዮት እንደመዝለቋ ከመንግሥት ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ ማወቃችን አሁን ላለችበትም ሆነ ነገ ለምትኖርበት ሁኔታ ዕውቀታችንና ግንዛቤያችን እንዲጨምር ያደርገናል። መንግሥትና ሃይማኖት ተለያዩ እስከተባለበት ዘመን ድረስ “ቤተ መንግሥቱና ቤተ ክህነቱ” የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆኖ ኖሯል። ቤተ ክህነቱ ምንም እንኳን “ነጻ” የሆነ ቢመስልም በቤተ መንግሥቱ ቁጥጥር ሥር እንደነበር ይታወቃል። ኮሚኒስቶቹም ሥልጣን ላይ ከወጡ በሁዋላ “በፈጣሪ አናምንም” ቢሉም “በፈጣሪ የምታምነውን ቤተ ክርስቲያን” ለመልቀቅ አልፈቀዱም። በዚህም መሠረት ደርጎች የጠቅላይ ቤተ ክህነትን ሥራ አስኪያጅ እየሾሙ ከመላካቸውም በላይ በተለይም በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የነበረውን ርስታችንን ከቤተ ክህነቱ ጋር በጋራ ያስተዳድሩ ነበር። ከዚህም በላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለተወረሱባት ንብረቶች ማካካሻ እንዲሆን ዓመታዊ በጀትም ይቆርጡላት ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢሕአዴግ መንግሥት መጣና እንደገና “መንግሥትና ሃይማኖት ተለያይተዋል” ሲባል አዲስ ምዕራፍ ተጀመረ።

ኢሕአዴግና ደርግ “መንግሥትና ሃይማኖት ተለያይተዋል” ሲሉ የወሰዱት መፍትሔ የተለያየ ነው። ደርግ ግልጽ የሆነውን ቁጥጥሩን ሳያላላ ሲቀጥል ኢሕአዴግ ግን በድብቅ ነገር ግን በጥልቀት መቆጣጠሩን ተያይዞታል። ደርግ ፓትርያርክ መሾሙን ሳይክድ፣ ሥራ አስኪያጅ መላኩን ሳያቋርጥ፣ መንግሥት በቤተ ክህነቱ አሠራር የሚገባበት ቦታ ላይ ያለማመንታት እየገባ ሲያስኬድ ኢሕአዴግ ግን “በቤተ ክህነቱ ሥራ ጣልቃ አልገባም/ አልገባሁም” እያለ ነገር ግን ሰላዮቹ ቤተ ክህነቱን ተቆጣጥረውታል፣ ፓትርያርኩም በመንግሥት ወገንተኝነታቸው እየተመኩ የአንድ ሰው አስተዳደርን አሰልጥነውታል።
ኢሕአዴግ ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ከፈጸማቸው የተሳሳቱ አካሄዶች መካከል ዋነኛውና አሁንም ካልተሻሻለ ሌላ ውድቀት የሚያመጣው ፓትርያርኩ፣ ልክ እንደ ካቶሊክ ፓፓ፣ አይነኬ ያውም ፈላጭ ቆራጭ እንዲሆኑ ማድረጉ ነው። የቀድሞዎቹም ፓትርያርኮች ጽኑዕ ሥልጣን እንዳላቸው ቢታወቅም እንደ አባ ጳውሎስ ዘመን ግን ፍፁም መረን የወጣ ሥራ ሠርተው አያውቁም። ለዚህ የአባ ጳውሎስ መረን መውጣት ዋነኛ ተጠያቂው መንግሥት ነው። አንደኛ ከመጠን ያለፈ ጀሌ የስለላ ሰዎች በቤተ ክህነቱ ግቢና አሠራር ውስጥ ሰግስጓል። በዘራቸው ብቻ የሚመኩ፣ ከክርስቶስ መንግሥት ይልቅ ለዚህ መንግሥት ጥብቅና የቆሙ፣ ምንም ነገር ከመሥራታቸው በፊት አገልግሎቱን በፖለቲካ አንድምታ መፈተሽ የሚፈልጉ፣ ቤተ ክህነቱን እንደ ፓርቲው አንድ አካል እንጂ እንደ እግዚአብሔር መሥሪያ ቤት የማይመለከቱ፣ ከክህነታቸው ይልቅ የፓርቲ አባልነታቸውን የሚያደንቁ፣ ከአበው ትዕዛዝ ከመቀበል ይልቅ ባላቸው የመንግሥት ወገንተኝነት ትከሻቸውን የሚያሳብጡ ሰዎች ቤተ ክህነቱን እንዲቆጣጠሩት ያደረገው መንግሥት ራሱ ነው። በየአህጉረ ስብከቱ ከጳጳሳቱና ከሥራ አስኪያጆቹ እኩል የፓርቲው ሰዎች ተሠማርተዋል። “የነፍጠኛ ቤተ ክርስቲያን” በሚለው የነአቶ ተፈራ ዋልዋ መመሪያ መሠረት “ነፍጠኖች ሊያንሠራሩባት” የሚችሉባት ቦታ ቤተ ክርስቲያን ሆና በመቆጠሯ የስለላው መዋቅር በጥልቀት እንዲገባ ሆኗል። አሁን በቤተ ክህነቱ ውስጥ፣ በተለይም በፓትርያርኩና በቅዱስ ሲኖዶሱ መካከል ለተፈጠረው ችግር መንስዔው ይኼው 17 ዓመት ሙሉ የተጠራቀመው ሕገ ወጥ አሠራር ነው። ዛሬ የፓትርያርኩ ዘመዶችና ወገኖች እንዲሁም የማፊያው ቡድን አባላት ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመለከቷት እንደ ግል ንብረታቸውና እንደ ቤተሰብ ሀብት ነው።
መንግሥት ይህንን ቅጥ ያጣ ግንኙነት መለወጥ እንዳለበት ግልጽ ቢሆንም አሁን በሚታየው ሁኔታ ይህንን የመለወጥ ፍላጎት ያለው አይመስልም። ፓትርያርኩን የሚመለከታቸው የቤተ ክህነቱን ቁጥጥር በእርሱ ሥር የመሆን/አለመሆኑ ምልክት አድርጎ ስለሆነ የእርሳቸው ሥልጣን መገደብ የኢሕአዴግ ሥልጣን መገደብ አድርጎ ይወስደዋል። እርሳቸው ላይ የሚመጣ ማንኛውም ነገር “በራሱ ላይ የመጣ” ይመስለዋል። የወንበራቸው መነቃነቅ “የአንድ የነፍጠኛ ጳጳስ መምጣት” አድርጎ ይቆጥረዋል። ለኢሕአዴግ ማንኛውም ሰው የሚመዘነው ባለው የፖለቲካ አቋም ብቻ እና ብቻ እንጂ በሃይማኖቱ ወይም በዜግነቱ አይደለም። ምእመን ሆነ ካህን፣ ጳጳስ ሆነ ፓትርያርክ የመንግሥት ደጋፊ ከሆነ ተቀባይነት አለው አለበለዚያ ግን ማንም አይፈልገውም።
መንግሥት የተበላሸ አመለካከቱን በቅዱስ ሲኖዶሱና በፓትርያርኩ መካከል በተፈጠረው ችግር ወቅት በግልጽ አሳይቷል። የመንግሥት የስለላው አካላት የሆኑ ነገር ግን በማፊያው ብር የሰከሩና የመንግሥትን መዋቅር የሚጠቀሙ ሰዎች የአባቶችን በር መሰባበራቸውን፣ አንዳንድ ብፁዓን አባቶችን አፍነው ወስደው ማስፈራራታቸውን፣ አሁንም በየጳጳሳቱ ዘንድ እየቀረቡ “ወየውላችሁ” እንደሚሉ አሳማኝ ማስረጃዎች በማግኘት ላይ ነን። እስካሁን ድረስ መንግሥት በመንግሥትነቱ በዚህ ጉዳይ ውስጥ አልገባም ብለን ያመንን ቢሆንም አሁን የሚታየው አካሄድ ግን መንግሥት የፓትርያርክ ጳውሎስን ወገን በመደገፍ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከችግሯ ለመውጣት በማድረግ ላይ ያለችውን ሙከራ በማደናቀፍ ላይ መሆኑን እየተመለከትን ነው። ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በደህንነት ሃይሎች ታፍነው ተወስደው ማስፈራራትና ማዋከብ ደርሶባቸው ሳለ እስካሁን ማንም ተጠያቂ አልሆነም። የአባቶች ቤቶች በሃይል ተደብድበው ተሰባብረው ሳለ ወንጀለኛው እስካሁን አልተያዘም። ፓትርያርኩ ከቅ/ሲኖዶስ በላይ መሆናቸውን በተግባር እያሳዩ፣ ከቤተ ክርስቲያን በወጣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ወንጀለኞች እንደፈለጉ እየፏነኑ መንግሥት “ዓይኔን ግንባር ያድርገው ፣ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ” እያለ ነው።
በርግጥ በዚህ ሁሉ ነገር መንግሥትስ ቢሆን “ፖለቲካዬን ይጠቅመዋል” ብሎ ያስባል ማለት ነው? መንግሥት ከሚጠላባቸው ነገሮች አንዱ ፓትርያርክ ጳውሎስና የተበላሸ ማንነታቸው መሆኑን አልተረዳም? እርሳቸውን ማስተካከል ከሕዝብ መታረቅ መሆኑንስ አልተገነዘበም? ፓትርያርኩ መንግሥት ላይ ኪሳራ ከማምጣታቸው በስተቀር በረዥም ጊዜ ካየነው ጥቅማቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ቤተ ክርስቲያኒቱ ግን ትልቅ ስብራት እየገጠማት ነው። ከዚህ ስብራቷ ለማገገም የአንድ ትውልድ ዕድሜ ሊጠይቅ ይችላል። ምንኩስና ተበላሽቷል፣ ክህነት ረክሷል፣ ጵጵስና ክብር አጥቷል፣ ሊቃውንቱ የትም ወድቀዋል፣ አባቶች ሳይሆኑ ደንደሳም ወይዘሮዎች ቤተ ክህነቱን ተቆጣጥረውታል፣ የቤ ክርስቲያን ገንዘብ የማንም መጫወቻ ሆኗል፣ ምእመናን እረኛ አጥተዋል። ለዚህ ሁሉ ዋነኛው ምክንያት ፓትርያርክ ጳውሎስ ናቸው። ለእርሳቸው መከታ ሆኖ ያስጠቃን ደግሞ መንግሥት ነው። ስለዚህ “ይበቃል” እንላለን። እጅህን ከቤተ ክርስቲያን ላይ አንሣ!!!!!!!!
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)