September 28, 2009

የሰሞኑ የዜና ርዕስ የሆኑት አባ ሰረቀ ማን ናቸው? በአሜሪካ ምን ምን ሲሰሩ ኖሩ?

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 27/2009)፦
ሰሞኑን በማኀበረ ቅዱሳንና በጠቅላይ ቤተ ክህነት አንድ መምሪያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ፈንድቶ መውጣቱንና መንግሥትን ማሳተፉን ከሰማን ወዲህ ስማቸውን በጉልህ መስማት ከጀመርናቸው ሰዎች መካከል አንደኛውና ግንባር ቀደሙ ሰሜን አሜሪካ የነበሩትና በደንብ የምናውቃቸው “አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል” ናቸው። ስለዚህ ይህ ጽሑፍ ስለኚሁ ሰው የአሜሪካ ቆይታ እውነተኛ እማኝነት ይሰጣል። ቤተ ክርስቲያናችንን የሚመሯትና ነገ ጳጳስ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት እኚህ ሰው ምን ዓይነት ሰው እንደሆኑ ያብራራል።

አባ ሰረቀ የዛሬ 15 ዓመት አካባቢ ወደ አሜሪካ ሲመጡ ለመጀመሪያ ጊዜ የሄዱት ወደ ሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ነበር። በዚያም አባ ኃ/ሥላሴ ከተባሉ አባት ጋር የጻድቁን የአቡነ አረጋዊን ቤተ ክርስቲያን ማገልገል ጀምረው ነበር። ይሁን እንጂ አባ ሰረቀ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የሄዱበት አካባቢ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን ሰላም በማወክና በመበጥበጥ የታወቁ እንደመሆናቸው አቡነ አረጋዊንም ወዲያውኑ መበጥበጥ ጀመሩ። የአቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያንን ቦርድ በመቅረብ “መቀደስና ማገልገል የምፈልገው በትግርኛ ቋንቋ ብቻ ነው” ማለት ጀመሩ። በዚህም የዘወትር አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ግዕዝንና አማርኛን ዜሮ አደረጓቸው። ቦርዱን በመጠምዘዝና በማሳመን በትግርኛ ብቻ እንዲቀደስ ለማድረግም ችለው ነበር።

በዚህ መልክ ከ6-8 ወራት ከቆዩ በኋላ በቦርዱ አባላት መካከል እንደገና ጥርጥር፣ አለመግባባትና ልዩነት በመፍጠር ለመክፈል ሞከሩ። ወደ ትግርኛ የቀየሩት ቅዳሴ አላዋጣ ሲላቸው ወይም “ስልታዊ ለውጥ” ማድረግ ሲፈልጉ እንደገና “ወደ አማርኛና ግዕዝ” መመለስ ፈለጉ። በዚህ ጊዜ ቦርዱ እምቢ አለ። “ለምን መጀመሪያ ወደ ትግርኛ ወሰዱን ለምን ይመልሱናል? እኛ የእርስዎ መጫወቻ አይደለንም። ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችን አባላት ለምደውታል” ብለው እምቢ አሉ።

አባ ሰረቀ ይህ አልሳካላቸው ሲል ዲሲ አካባቢ ከሚገኘው የመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ተጋጭተው የወጡ የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን በማስተባበር “ቤተ ክርስቲያን ለመክፈት” ተስማሙ። ይህ ከመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የወጣው ቡድን ያን ጊዜ የአሜሪካ ሀ/ስብከት አሁን የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ ማትያስን በማነጋገር “በትግርኛ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥበት ቤተ ክርስቲያን ለመክፈት” ሞክረው ሳይሳካላቸው የቀሩ እንደነበሩ ጉዳዩን የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ። እናም በሎስ አንጀለስ አቡረ አረጋዊ ያልተሳካላቸው አባ ሰረቀ ቨርጂኒያ ሌላ የአቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን “ከፈቱ”። የሎስ አንጀለስ ምዕመናንን ያሳሳቱት ሳይበቃ የቨርጂኒያዎችንም አጭበርብረው በዘረኛ መንፈሳቸው የዋኃኑን አጠመዷቸው። ትናንትና አባ ሰረቀ “የከፈቱት አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን” ዛሬ ደግሞ አባ ኃ/ሚካኤልን የመሰሉ መናፍቅ መነኩሴ አቅፎ ይዟል። (አስተዳዳሪው ቀሲስ ተከስተ የተባሉ ወጣት ቄስ ናቸው)። አባ ኃ/ሚካኤል ከአባ ሰረቀ ሚሽን ተቀብለው ወደ አሜሪካ የመጡ መሆናቸው በስፋት ይነገራል፤ ይታወቃልም።

አባ ሰረቀ ወደ ቨርጂኒያ እንደመጡ የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስን በመቃወም ማስተማር ጀመሩ። ብፁዕ አቡነ ማትያስን ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው ጵጵስናንና ፕትርክናን በመቃወም “ጳጳስም፣ ፓትርያርክም አያስፈልግም” እያሉ ዐውደ ምሕረቱን ከያዙ ጀምሮ በትግርኛ ብቻ በመቀደስና ማስተማር ክፍፍልን መዝራት ጀመሩ። “ጳጳስ አያስፈልግም አዲስ ቤተ ክርስቲያን ለመክፈት ከሆነ እኔ ራሴ ‘መባረክ’ና መክፈት እችላለሁ” ማለት ጀመሩ። በዚህ የተጀመረው ልዩነት ሰፍቶ አቡነ አረጋዊን ራሱን ለሁለት ለመከፈል አበቁት።

ከዚያም የቤተ ክርስቲያኑን ስምና ንብረት በመውሰድ ጥለው ወደ አሌክሳንደሪያ (ቨርጂኒያ) ሄዱ። በዚያው ስም አቡነ አረጋዊ ብለው በመሰየም “አዲስ ቤተ ክርስቲያን ከፈቱ”። በአባ ሰረቀ ጎትጓችነት ተታለው ከመድኃኔዓለም ወጥተው የነበሩትም ምእመናን ልዩነታቸው በማቻቻል ከቀደመው ቤተ ክርስቲያናቸው ጋር ታረቁ። ይሁን እንጂ አባ ሰረቀ ንብረታቸውን በሙሉ ዘርፈው እንደወጡ እንዲቀሩ አልፈቀዱላቸውም። የሕግ ዕውቀት ያላቸው ሰው በማነጋገርና ርዳታ በማግኘት አባ ሰረቀን ሕግ ፊት አቆሟቸው። አባ ሰረቀም የወሰዱትን ሀብትና ስም በሙሉ በግድ ለመመለስ ተገደዱ። በሕግ ፊት የተዋረዱት አባ ሰረቀም አቡነ አረጋዊን አስረክበው ሲያበቁ በቅ/ጊዮርጊስ ስም “አዲስ ቤተ ክርስቲያን በቨርጂኒያ ከፈቱ”። ይህ ቤተ ክርስቲያን ዛሬም በቨርጂኒያ እንደሚገኝ ይታወቃል።

አባ ሰረቀ በዚህ መልክ ቤተ ክርስቲያንን ሲከፋፍሉና ሲያዋርዱ ቆይተው ጊዜ እየተቀየረ ሲሄድ “ጳጳስ የመሆን ሌላ ጾር ሲነሣባቸው” በፊት “አያስፈልግም” ሲሉት የነበረውን “ጵጵስና፣ ፕትርክና እና ቅዱስ ሲኖዶስ” ሸውደው “እጅ ሰጥተው” የአቡነ ጳውሎስ ጋሻ ጃግሬ ሆነው ወደ ኢትዮጵያ ገቡ። አባ ሰረቀ የዲሲና አካባቢው ማህበረ ካህናት ጉባዔ አባል በነበሩባቸው ዘመናት ሁሉ እያጥላሉ ሲሳደቡ የነበሩትን ፓትርያርክ “ካለ እርስዎ ሰው የለም፣ ቅዱስ የለም” ብለው ጫማ ስመው የመምሪያ ኃላፊነት ሽልማት ተሰጣቸው። ይሁን እንጂ ሲጓጉለት የነበረው ጵጰስና ሳይሳካላቸው ቀረ። የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑ ብፁዓን አባቶች “እንዲህ ዓይነቱን ወንበዴ፣ ቤተ ክርስቲያንን ሲያሰቃይ የኖረ ሰው እንዴት ጵጵስና እንሾመዋለን” በማለታቸው ሳይሳካ ቆይቶ ነበር። ውስጥ አዋቂዎች እንደሚናገሩት ከሆነ በመጪው ጥቅምት በሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ጵጵስና እንዲሾሙ ይቀርባሉ ከሚባሉት አባቶች መካከል አንደኛው እኚሁ ዘረኛ መነኩሴ አባ ሰረቀ ብርሃን እንደሚሆኑ ታውቋል።

አይ ዘመን፤ የሚገርመው እኚህኑ አባ ሰረቀን ዛሬ እሑድ በተላለፈው የሀገር ፍቅር ሬዲዮ ላይ ድምጻቸውን ሰማነው። ያውም የቤተ ክርስቲያን “ጠበቃና ተቆርቋሪ” ሆነው። አይ ቤተ ክርስቲያን!!! መከራሽ አያልቅ!!!
ቸር ወሬ ያሰማን
(http://www.addisadmass.com/news/news_item.asp?NewsID=1462)

ቤተ ክርስቲያናችንን እየተፈታተናት ያለው ከሁለቱ የመንግሥት አካላት የትኛው ነው?

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 27/2009)፦ ከዚህ በታች ያለው ጽሑፍ ሪፖርተር ጋዜጣ በዛሬ እሑድ እትሙ ካተመው ርዕሰ አንቀጽ የተወሰደ ነው።
(ሪፖርተር ጋዜጣ SUNDAY, 27 SEPTEMBER 2009)፦ በአሁኑ ጊዜ ገዢው ፓርቲ ሁለት ዓይነት አካላት ይዞ እየተጓዘ ነው፡፡ አሁንም ለሕዝብ ብለው ለመሰዋዕትነት የተዘጋጁ አሉ፡፡ በተፃራሪው ደግሞ ለአገርና ለሕዝብ ደንታ የሌላቸው ለፍትሕና ለዴሞክራሲ አለርጂክ የሆኑ መፈክራቸው "የትም ፍጪው ጥቅማ ጥቅሙን አምጪው" የሆኑም አሉ፡፡

የሚያሳስበው ሁለት አይነት መሆናቸው ብቻ ሳይሆን አሉታዊው በአዎንታዊው ላይ፣ እኩዩ በሰናዩ ላይ የበላይነት እየያዘ መምጣቱ ነው፡፡ ያለው ሁኔታ እንዴት ነው ነገሩ? የሚል ስጋት እያስከተለ መምጣቱ ነው፡፡ በአንፃራዊነት የተሻለ ጊዜ ነው በሚባልበት ወቅት እንደዚህ ያለ አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት ቢመጣ ለአገር ይቆማሉ ወይ? የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው፡፡
ጋዜጣው እንዳተተው ከሆነ መንግሥት በሁለት አካላት መካከል “ዥዋ ዥዌ” እያለ መሆኑን “በጥቁርና በነጭ” በግልጽ አስቀምጦታል። ነገሩ እኛንም በጣም አስገረመን፣ ጥያቄም እንድንጠይቅ አደረገን። የአባቶችን ቤቶች የሰበረው ወይም ሲሰበር ዝም ያለው የትኛው ቡድን ነው? ቅዱስ ሲኖዶስ በነጻ እንዳይንቀሳቀስ የሚያስፈራራው የትኛው ቡድን ነው? ወዘተ ወዘተ …

September 27, 2009

የደመራ በዓል በአዲስ አበባ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 26/2009)፦ የ2002 ዓ.ም የደመራ በዓል ዛሬ በደማቅ ሁኔታ ሲከበር በቤተ ክርስቲያን ያለው ትርምስ ምዕመናኑን አበሳጭቶ ያስነሣ ይሆናል ተብሎ የተፈራው ብጥብጥ በእግዚአብሔር ችርነትና በክርስቲያኑ ሕዝብ ጨዋነት ሳይሰማና ሳይታይ በሰላም አልፏል።

የመስቀል አደባባይና አካባቢው በዓሉን ለማክበር በመጣ ሕዝበ ክርስቲያን ከአፍ እስከ ገደፉ ጢም ብሎ እጅግ በሚያምር መልኩ ተከብሮ አምሽቷል። በዚሁ በዓል ላይ ቃለ ምዕዳን ያሰሙት ቅዱስ ፓትርያርኩ “ወጣቱ ለልማት እንዲነሣ” ጥሪ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ቅዱስነታቸውን አሁን በቤተ ክርስቲያን ስላለው ሁኔታ ምንም የጠቀሱት ነገር የለም።

ይህንን ታላቅ በዓል በሰላም እንዲከበር ያደረገ አምላካችን እግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰው፤ አሜን።
ቸር ወሬ ያሰማን።

September 26, 2009

ማኅበሩን ለሚያውቁት ሁሉ

(አድማሱ ነኝ)
በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆች የሕዝብም ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ፥ ኢየሱስንም በተንኰል ሊያስይዙት ሊገድሉትም ተማከሩ፥

ይህ ቃል ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ቃሉን ልብ ብለን ስንመረምረው የካህናት አለቆቹም ሆኑ ባለስልጣናቱ ጌታችንን ለመክሰሰ የተነሱት በተንኮል ነው፡፡ ሃሳባቸውም መክሰስ ብቻ ሳይሆን መግደልም ጭምር ነበር፡፡ ባለስልጣናቱና ካህናቱ ጌታችንን የከሰሱት በብዙ ቢሆንም ጠቅልለን ስናያቸው ግን ሁለት ዋና ዋና ክሶች ነበሩ፡፡ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ይላል፤ የአይሁድ ንጉስ ነኝ ይላል፤ ለቄሳር ግብር አትክፈሉ ይላል እና የመሳሰሉት ነበሩ፡፡

ይቀርቡ ከነበሩት ክሶች አንዳንዶቹ የሀሰት ክሶች ሲሆኑ፡ ለምሳሌም ለቄሳር ግብር አትክፈሉ አለ የሚለውን የመሳሰሉት ሌሎቹ ደግሞ ካለመረዳት የሚነሱ ነበሩ፡፡ ወደዝርዝሩ አልገባም፡፡ ዛሬ ይህንን ለመጻፍ የተነሳሁት ሰሞኑን በማኅበረ ቅዱሳንና በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ መካከል ያለውን አለመግባባት በተመለከተ በመንበረ ፓተርያርኩ የተደረገውን ስብሰባ የተመለከተ ዜና አይቼ በማዘኔ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን የማውቀው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኜ ጊቢ ጉባዬ ስከታተል ጀምሮ ነው፡፡ አገልግሎቱን አና ጥንካሬውን እረዳለሁ፡፡ የማኅበሩ አባል ሆኜ ለማገልገል ካንዴም ሁለቴ ተመዝግቤ በተለያዩ ምክንያቶች ሳልገፋበት ቀርቻለሁ፡፡ እነዚህ አጋጣሚዎችና የሕትመት ውጤቶቹ ሐመርና ስምዐ ጽድቅ መጽሐፍቶቹ ዐውደ ርዕዮቹ እና ሌሎች አገልግሎቶቹን በሚገባ ለማወቅ እድሉን ስለሰጡኝ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ተከሶ ሳየው አዘንኩ፡፡ እናም ይህችን አጭር መልዕክት ማኅበሩን ለሚያውቁት ሁሉ ለመጻፍ ተነሳሁ፡፡

ሶስና በክፉ የርኩሰት ስራቸው አልተባበርም ባለቻቸው ጊዜ በሃይማኖትም በዓላማም የማይመሳሰሉ ሁለቱ ረበናት ከሰዋት በፍርድ አደባባይ ቆማ ሲያዩ ንጽህናዋን የሚያውቁ ሁሉ አለቀሱላት ተብሎ እንደተጻፈ ዛሬም ስለቤተክርስቲያንና ቤተክርስቲያንን በፍጹም ፍቅር በማገልገላቸው ለሚከሰሱ እና ለሚንገላቱ ሌላ ነገር ማድረግ ባንችል ቢያነስ እናልቅስላቸው፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን ጸጥ የሚደርግላትን እንደ ነቢዩ ዳንኤል ያለ እውነትን በጥበብ የሚገልጽ አስኪያስነሳልን ድረስ ወደ ርሱ በጸሎት ማሳሰባችንን ቸል አንበል፡፡
ለማኀበሩ አባላትም እነደ ታናሽ ወንድም በርቱ ከፊት ይልቅ ጸንታችሁ ቁሙ ብዬ በትህትና መልዕክቴን ለማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡ የመንግሰት የደህንነት ባለስልጣናትን ይዘው ሊያስፈራሩ የሚፈልጉትን ስታዩ አትደንግጡ ይልቁንም ከኛ ጋር ያለው ከነሱ ጋር ካለው ይበልጣል ብላችሁ ተጽናኑ፡፡ በጊቢ ጉባዬ በኩል ላለፋችሁ የማኅበሩ አባላት ወይም እንደኔ ዛሬ የማኅበሩ አባል ያልሆናችሁ በምርቃታችን ጊዜ የተሰጠንን ስጦታ አስታውሱት- መስቀሉን ማለቴ ነው፡፡ ብዙ ሚስጥር ያለው ነገር መሆኑን እያደር እንረዳዋለን፡፡ እኔ አስካሁን ከአንገቴ አልለየሁትም ሺዎች ደግሞ በልባቸው አትመው እንደያዙት አምናለሁ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጌታው የሚበልጥ ሎሌ የለም ብሎ እንዳስተማረን ሰድበውት ከሆነ ሰትሰደቡ አይክፋችሁ ከስሰውት ከሆነ በሀሰት ብትከሰሱ አትረበሹ በአጋንንት አለቃ ሰይጣንን ያስወጣል ብለውት ከሆነ ማኅበረ ሰይጣን ብለው ቢጠሩአችሁ አትደነቁ፡፡
አምላከ ቅዱሳን ሁላችንንም በይቅርታውና በምህረቱ ይጎብኘን፡፡

Professor Discusses the Presence of Christianity in Ethiopia

Matthew Usdin
Source: media.www.maroon-news.com
Issue date: 9/24/09
On Thursday, September 17, a large group of students and professors crammed into the Robert Ho Lecture Room in Lawrence Hall as Assistant Professor of History Tsega Etefa continued a mini lecture series, titled "Reflections of Ethiopian Orthodoxy." Specifically, Etefa, a native of Ethiopia, spoke on "The Origin and Expansion of Orthodox Christianity in Ethiopia."

The talk, which was one of several campus wide events that has contributed to Colgate's inaugural Diversity Week, was well received by students and professors alike.

"It was interesting to hear such an informative talk about something that is completely foreign to many of us here at Colgate," junior Mike Naughton said. "It was also an incredible experience to hear Professor Etefa talk about an issue that he has had personal experience with."

The talk focused on the longtime presence of Orthodox Christianity in the East African nation. Etefa explained that Christianity originally came to Ethiopia as early as the 4th century CE. According to the legend, the church was established when two Christians named Frumentios and Aidesios were kidnapped on the Red Sea and taken to Aksum, Ethiopia's capital at the time. Because the two boys were educated, they were soon installed as private tutors to the royal family. It was at this point that the boys taught the king's children the fundamentals of the Christian faith.

Throughout the next century, the religion gradually spread through traditionally pagan areas. Largely because of the arrival of the "Nine Saints," a group of men who traveled from Asia Minor and translated the Bible into the local language, the spread of the religion was extensive.

While the early arrival of Christianity is noteworthy, the ability of the religion to maintain itself in a region of the world that has largely been marked by the presence of Islamic and Pagan beliefs, shocked many students.

"It was pretty surprising to hear that Christianity has existed in that area of the world for so long," senior Alex Gardner said. "The first religion that comes to mind in that region is usually Islam. Professor Etefa proved that wasn't the case at all."

After tracing the presence of the religion throughout the nation's history, the talk concluded with a discussion of Orthodox Christianity's current role in Ethiopia. Within Ethiopia's current population of 68 million, over 58 percent adhere to Christian beliefs, with over 40 percent practicing Christian orthodoxy.

A reception in the Longyear Museum of Anthropology directly followed the talk. On display in the Museum was an array of highly ornamental Ethiopian religious objects of personal devotion.

September 25, 2009

ስለ “ጥንተ አብሶ ጉዳይ” የተዘጋጀ ጽሑፍ

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 25/2009)፦
በካንሳስ ሲቲ ካንሳስ የምትገኘዉ "የደብረ ሣህል መድኀኔዓለም" የኢ/ኦ/ተ/ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በነገረ ሃይማኖት ምክንያት ያላትን ጥያቄ ወደ ኮፕት ቤተ ክርስቲያን ማመልከቻ ማስገባቷን፣ ማመልከቻውም መልስ ይዞ በመምጣቱ ስብሰባ መጥራቷን” መዘገባችን ይታወሳል። ይህ ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ነገረ-ሃይማኖት አስተምህሮ ውጪ የሆነውና “እመቤታችን ጥንተ አብሶ አለባት” የሚለው ጥያቄ ከግብጽ ፓትርያርክ ተልከው መጡ በተባሉ ኤርትራዊ ጳጳስ “ትክክል ነው፤ እመቤታችን ጥንተ አብሶ አለባት” መባሉ ከተዘገበ ወዲህ ይህንን የሚቃወም የተለያየ አስተያየት በመደመጥ ላይ ነው።
To the editor of DejeSelam blog,
First, I greet you by saying Happy Ethiopian New year (Enqutatash).
Please find attached an ARTICLE which would be of interest to fellow Ethiopians. I will be most obliged if you can post it on your website.
Kind Regards,
M G Selassie


ማኅበረ ቅዱሳን ስለራሱ ምን እያለ ነው?

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 25/2009)፦ ስለማኅበረ ቅዱሳን ሌሎች የሚናገሩት እንዳለ ሆኖ ራሱ ማኅበሩ ስለራሱ የሚለውን ለመመልከት ወደ ድረ ገጻቸው ጎራ ስንል ከዚህ በታች ያለውንና ከማኅበሩ ሰብሳቢ ከቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ሥዩም ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ አገኘን። ደጀ ሰላማውያን ቢያነቡት መልካም ነው ብለን ስላሰብን ከረዥሙ-ባጭሩ የተወሰኑ ጥያቄዎችንና መልሶቻቸውን እዚህ ለጥፈነዋል።
ቸር ወሬ ያሰማን
አሜን
+++++++
«ማኅበረ ቅዱሳን ለሁሉም ግልጽ አሠራር አለው»
በዲ/ን ማለደ ዋስይሁንና ሻምበል ጥላሁን
ስለማኅበረ ቅዱሳን ከተለያዩ አካላት የተለያዩ ጥያቄዎች እየተነሡ ናቸው፡፡ እነዚህ ማኅበሩ ላይ የሚነሡት ጥያቄዎች አንዳንዶቹ ማኅበሩን በትክክል ባለመገንዘብ በየዋህነት የሚነሡ ጥያቄዎች ሲሆኑ፤ አንዳንዶቹ ግን ማኅበረ ቅዱሳንን በተዛባ ሥዕል በመሣል ኅብረተሰቡ ውስጥ የተሳሳተ አመለካከት ለማስቀመጥ የሚሞክሩ ናቸው፡፡ እነዚህን የተዛቡ አመለካከቶች ለማጥራት፣ ማኅበሩን ባለማወቅ ከአንዳንዶች በየዋህነት ለሚነሡ ጥያቄዎችም ትክክለኛውን መልስ ለመስጠት እንዲሁም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የማኅበሩን አቋም መግለጽ በማስፈለጉ ከማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ሥዩም ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ ተከታተሉን፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- በቅርቡ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ በተከሰተው ችግር ማኅበረ ቅዱሳን ምን አቋም አለው? የብፁዓን አባቶችን የመደብደብ ሙከራ አስመልክቶ ምን ይላል? በአጠቃላይ በችግሩ ዙሪያ ያለው አቋም ምንድነው?

ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም፡- ማኅበረ ቅዱሳን የተፈጠረውን ነገር አስመልክቶ በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 16ኛ ዓመት ቁጥር 182 ላይ አቋሙን ግልጽ አድርጎ አስቀምጧል፡፡ አሁን በአጭሩ ለመድገም ያህል ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሁሉም መገዛት እንዳለበት ማኅበረ ቅዱሳን ያምናል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሚመራው አካል ነው፡፡ ስለዚህ ለዚህ አካል ውሳኔ ሁሉም የመገዛት ግዴታ አለበት፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ለዚህ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጉዳዮች ለሚወስነው አካል ይሠራል፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን በቤተ ክርስቲያን የተከሰተውን ችግር ቅዱስ ሲኖዶስ ሳይከፋፈል በጥልቀት ተወያይቶ ይፈታል የሚል እምነት ማኅበረ ቅዱሳን አለው፡፡

የብፁዓን አባቶችን ቤት መደብደብና ዛቻ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ልዕልና የደፈረ አሳፋሪ ድር ጊት ነው፡፡ በእውነት ማኅበረ ቅዱሳን እንደሌሎች ማኅበራትና ምእመናን በሁኔታው በእጅጉ አዝኗል፡፡ ድርጊቱም አሳፋሪና አስነዋሪ እንደሆነ በልሳኖቹ ሐመርና ስምዐ ጽድቅ በመዘገብ የጉዳዩን አሳፋሪነት አሳውቋል፡፡ ጉዳዩንም እየተከታተለው ነው፡፡ መንግሥት ይሄንን አሳፋሪ ድርጊት ተከታትሎ ውሳኔ ይሰጣል የሚል እምነት አለን፡፡ በመንግሥት በኩል ስለ ጉዳዩ የሚገለጸውንም ውጤት እንደሁሉም ክርስቲያን በጉጉት እየጠበቀ ነው፡፡

ወደ መጨረሻው ጥያቄ መልስ ስመጣ ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ስለተከሰተው ችግር ያለው አቋም ሲጠቀልል ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና የበላይነት ሁሉም መገዛት አለበት፡፡ ችግሩም በቅዱስ ስኖዶስ ይፈታል ብሎም ያምናል፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- የፖለቲካ አቋምን በተመለከተስ?

ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ- ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የእኛ ማኅበር ሃይማኖታዊ አገልግሎት ለመስጠት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ስር የተቋቋመ የአገልግሎት ማኅበር ነው፡፡ ስለዚህ ማኅበሩ እንደ ተቋም የሚሰጠውም አገልግሎት ሃይማኖታዊ ነው፡፡ ለየትኛውም የፖለቲካ ዓይነትና አደረጃጀት የሚያግዝ /የሚሠራ/ እንዲሆን መቼም ቢሆን ፍላጐቱ የለንም፡፡ በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ አምስት እንደተቀመጠው «ማኅበሩ በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት አይኖረውም» ይላል፡፡ የዚህን አንቀጽ ይዘት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል በማኅበሩ ያሉ የተወሰኑ አካላት በሓላፊነት ላይ እያሉ የማንኛውም የፖለቲካ አባል እንዳይሆኑ በ1998 ዓ.ም የሥራ አመራር ጉባኤያችን ወስኗል፡፡ በውሳኔውም መሠረት የሥራ አመራር ጉባኤ አባላት፣ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት፣ የማኅበሩ መደበኛ መምህራን፣ የኤዲቶሪያል ቦርድ ጽ/ቤት አባላት፣ የኦዲትና ኤንስፔክሽን አገልግሎት ጽ/ቤት አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ የማዕከላት ሰብሳቢዎች በሓላፊነት ላይ ያሉ መደበኛ አገልጋዮች የማንኛውም የፖለቲካ ¬ፓርቲ አባል አይሆኑም፡፡

ይህ ማለት ግን ¬ለፖለቲከኞች በማኅበሩ የማገልገል ዕድል አይኖራቸውም ማለት አይደለም፡፡ ለፖለቲካ ዓላማቸው ማኅበሩን መጠቀም ግን አይችሉም፡፡ ስለዚህ የትኛውንም የማኅበሩን አባል በግሉ የ«ሀ» ወይም የ«ለ» ¬ፓርቲ ደጋፊ፣ አባል ወይም አመራር እንዲሆን ወይም እዳይሆን ምንም ዓይነት ተቋማዊ ተጽዕኖ በማኅበሩ የሚፈጠርበት ዕድል የለም፡፡ ይህ ግን ሀገርን በመገንባት ረገድ ለአጠቃላዩ ማኅበረሰብ ትርጉም ያለው ልማታዊ ተግባራትን የማከናውን ዓላማና እንቅስቃሴ የለውም ማለት አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ያላት የሀገራዊ ልማት ተሳትፎ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቀጣይነት እንዲኖረው ክርስቲያን ምሁራንና ወጣቶች ባላቸው አቅም ሁሉ ይሳተፋሉ፡፡ የልማት ተሳትፎአቸው ለሀገርና ለትውልድ እንዲጠቅም፣ ቤተክርስቲያንም ያላትን ድርሻ እድትወጣ በማሰብ ነው፡፡ ብዙዎቹ ልማታዊ ተግባሮቻችን ደግሞ በቀጥታ የቤተክርስቲያናችንን ጥቅም የሚያስጠብቁ በመሆናቸው እንቅስቃሴያችን ለሌላ ትርጉም በሚጋለጥ መልኩ የሚደረግ ነው የሚል እምነት የለንም፡፡

በእርግጥ እንደተባለው በሀገር ውስጥም በውጪም በ¬ፖለቲካ ወገንተኝነት ማኅበሩን ለማማት የሚፈለጉ ወገኖች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ በጣም የሚገርመው ግን የሚሰጡት አስተያየቶች የተዘበራረቁ መሆናቸው በራሳቸው መሠረት የሌላቸው አስተያየቶች መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ በሀገር ውስጥ ያለው ማኅበሩ የ«ሀ» ፖርቲ ደጋፊ ነው ሲል በውጪ ሀገር ያሉ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ የ«ለ» ፖርቲ ደጋፊ ነው እያሉ ተጨባጭነት የሌለውና ምናልባትም የማኅበራችን አባላት በሆኑ የአንዳንድ ግለሰቦች ተሳትፎን መነሻ አድርጐ የሚሰጥ ሚዛናዊ ያልሆነ ድምዳሜ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ማኅበራችን ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው መተዳደሪያ ደንብ ላይ ተመርኩዞ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ባለው የፖለቲካ ሥርዓት ከሚቋቋመው መንግሥት ጋር መሥራት ሃይማኖታዊም ሕገ መንግሥታዊም ግዴታው ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ማኅበሩ እንደተቋም የትኛውንም የፖለቲካ አስተሳሰብ /Ideology/ በመደገፍ ወይም በመቃውም ከፖርቲዎች ጋር ግንኙነት ስለሌለው /ስለማይኖረው/ ለማንም ስጋት ወይም ዕድል ልንሆን አንችልም፡፡ በዚህ ደረጃ ፈርጆን የሚነሣ አካል ካለ ግን ለመፈረጅ ያበቁትን የመረጃ ምንጮች እንዲመረምር በዚሁ አጋጣሚ ሳልጠቁም አላልፍም፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ማኅበረ ቅዱሳን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ጋር ያለው ግንኙነት የሻከረ ነው፤ ማኅበሩም ለመምሪያው ለመታዘዝ ፈቃደኛ አይደለም የሚሉ አስተያየቶችም አሉ፡፡ እርስዎ እንደ ሰብሳቢ ምን ይላሉ?

ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ፡- ማኅበረ ቅዱሳን ሕገ ቤተክርስቲያን የቤተ ክርስቲያኒቱም ደንብና መመሪያዎች እንዲጠበቁ በጸኑ የሚሠራ ማኅበር ነው፡፡ ይህ ዋነኛ አጀንዳ ያለው አካል የማደራጃ መምሪያውን አሠራር ጠብቆ አይንቀሳቀስም ከተባለ -ራዶክስ /መጣረስ/ ይፈጥራል፡፡ ማኅበሩ በመምሪያው የአሠራር ሥርዓት ላይ ችግር የመፍጠር ፍላጐትም ሥልጣንም የለውም ነገር ግን መምሪያውን ከሚመሩት ግለሰብ ዓላማና አቅም ላይ ግን ጥያቄ አለው፡፡ መከሩ ብዙ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት በሆኑበት ቤተክርስቲያን ውስጥ ለአገልግሎት የተሰማሩ ማኅበራት እና ሰንበት ት/ቤቶችን በመምራት ረገድ የሚከተሉት የራሳቸው ፖሊሲ እንደተመሪ /ባለድርሻ/ ምቹ አይደለም፡፡ ማኅበሩ ላይ አሉ የሚሏቸውን ችግሮች በውይይትና በክርስቲያናዊ የምክክር ሥርዓት ከመፈጸም ይልቅ በግልጽና በስውር የማኅበሩን ስም ማጥፋትን ሥራዬ ብለው ይዘዋል፡፡ የተለያዩ አካላትም በማኅበሩ ላይ የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው ያላ ሠለሰ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ማኅበሩ ችግር አለበት፤ ለመምሪያውም አይታዘዝም... ወዘተ የሚለውን የራሳቸውን ሓሳብ መነሻ አድርገው የሚጽፏቸውን ደብዳቤዎች ምስክር እያደረጉ መናፍቃን ደግሞ በመጻሕፍት አሳትመው ሲሰድቡን እያየን ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን እያየን ማኅበረ ቅዱሳንን ከሚጠሉ መናፍቃን ጋር እርሳቸው ተመጋግበው እየሠሩ ነው ላለማለት ዋስትና አይሰጥም፡፡ የማኅበሩ አሠራር ችግር አለበት ብለው ቢያስቡ እንኳን ከሠሯቸው በጐ ተግባራት፣ የወጣት ምሁራን ክርስቲያኖች እንቅስቃሴን አስፈላጊነትና አሁን ቤተክርስቲያን ከአጽራረ ቤተ ክርስተያን በኩል እየደረሰበት ካለው ፈተና አንጻር በስብከተ ወንጌል ረገድ ያለውን ርምጃ በመመልከት ችግሮቹን ከሚመለከታቸው ከተለያዩ አካላት ጋር ተግባብቶ በመፍታት ግልጽ አሠራር ማስፈን ይገባቸው ነበር፡፡ ያንን አላደረጉም፡፡ ስለዚህ በአንዳንድ ማኅበሩ የአሠራር ችግሮች እንዳሉበት ለመምሪያውም እንደማይታዘዝ አድርጐ በማናፈስ ሺሕዎች የተሰለፉለትን ቤተክርስቲያን የመጠበቅ ተልእኮ ማነቆ እንዲያጋጥመው እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በግለሰቡ ተልእኮ ላይ ማኅበሩ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ሆኗል፡፡ ማኅበሩ ለ17 ዓመታት ከተለያዩ መምሪያ ሓላፊዎች ጋር በምክክር ሠርቷል፡፡ ውጤትም ማስመዝገብ ችሏል፡፡ እኛ ጥያቄያችን ዛሬ እርሳቸው ያገኙት አዲስ ነገር ምንድነው የሚል ነው፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- የመምሪያው ዋነኛ ጥያቄ የማኅበሩን ገንዘብና ንብረት ኦዲት በመደረጉ ጉዳይ ነው፡፡ ማኅበሩ በዚህ ላይ ያለው አቋም ምን ስልሆነ ነው ችግሮች የተፈጠሩት?

ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ- ማኅበራችን ለአገልግሎት የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ገንዘብ በሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር ካሉ ከማኅበሩ አባላት የሚያገኘው በማኅበሩ የውስጥ ኦዲተሮች የሚሠሩት ሪፖርት ተአማኒነት ስላለውና የሚታዩ ውጤታማ ክንውኖችን መሠረት አድርጐ ነው፡፡ የኦዲት ሪፖርቱ የማይታመንና ግልጽነት የጎደለው ከሆነና ሥራችንም በጎና ውጤታማ ባይሆን ለቀጣዩ ተግባሮቻችን የሚሆን የገንዘብ መዋጮን መሰብሰብ ባልቻልን ነበር፡፡ ስለዚህ አባላቱ መዝናናት ሳያምራቸው በመጠን እየኖሩ ለቤተ ክርስቲያን ከሚከፈሉት ዓሥራት በኩራት ተጨማሪ ለማኅበሩ አገልግሎት የሚሰጡትን ገንዘብ፣ ጊዜና ንብረት በአግባቡ መያዝ የእያንዳንዱ አባል ሓላፊነት ያለባቸው አካላት ሁሉ ግዴታ ነው፡፡ ለዚህ ዋስትና የሚሰጠው ደግሞ የኦዲት ሥራው ነው፡፡ ስለዚህ የኦዲት ሥራን ለማኅበራችን ደኅንነት እንደ አንድ ግብ የምናስብ ነን፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስ «ስለዚህ ለጋስ ስጦታ ማንም እንዳይነቅፋችሁ ተጠንቀቁ» ያለውን ቃሉን ሁሌ እናስባለን፡፡ ስለዚህ በየጊዜው የኦዲት ሥራዎች የውስጥ ኦዲተሮቻችን ይደረጋሉ፡፡ ያንን አለማድረጋችን ከማደራጃ መምሪያው ይልቅ የሚጐዳው ማኅበሩን ስለሆነ ስለነገሩን ሳይሆን ስለሚያስፈልገን መቼም ቢሆን እናደርገዋለን፡፡ ማኅበሩ በጠቅላላ ጉባኤው የቤተክርስቲያን መምሪያ ሓላፊዎች ባሉበት የሂሳብ ሪፖርት ያቀርባል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤውም ሆነ የሚመለከተው አካል የሂሳብ ሪፖርቱ አላረካኝም በውጪ ኦዲተር ይቀርብ ብሎን አያውቅም፡፡ ጥያቄው ከቀረበ ምንግዜም ማድረግ ይቻላል፡፡

አሁን ግን የተሻለ አደረጃጀትና ሰፊ አገልግሎት በሀገር ውስጥና በውጪም መስጠት ስንጀምር መምሪያው በማኅበሩ አገልግሎት የማይደሰቱ ግለሰቦች እና አካላት ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ መገኘቱ በእጅጉ ያሳስበናል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የመመሪያ ሓላፊው የእኛን ስም ለማጥፋት በመ ጠመዳቸውና ጊዜያቸውን ለዚያ እየሠው በመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሰ/ት/ቤቶች ከመምሪያው የሚፈልጉትን ያህል ድጋፍ ለማግኘታቸው ከፍተኛ ጥርጣሬ አለን፡፡ ከሁሉ በላይ ሊያሰጨንቀን የሚገባ የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት እንጂ ሌላ አልነበርም በእኛ በኩል ግን የሚጠበቅብንን በማድረግ መልካም ግንኙነት እንዲኖረን ሁሌም እንሻለን፡፡ ችግራችንም ከመዋቅሩ /ከመምሪያው/ ጋር ሳይሆን ከመምሪያው ሓላፊ ጋር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
(ሙሉውን ቃለ ምልልስ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ)

ይህ ሰው (አባ ሰረቀ) ማን ነው?

Dejeselamoch,
Who is Aba Sereke? Please post an article about him and what he did to our church, if you get information.
September 22, 2009
++++++++++++++++++++++++++++
(ከዘመቻ)
(September 25, 2009)አንድ ደጀ ሰላማዊ “አባ ሰረቀ የሚባለው ስው ማነው? ይህን ያህልስ ማቅን ለማጥፋት ታጥቆ የተነሳበትስ ዓላማው ምንድር ነው?” ሲል መጠየቁን መነሻ አድርጌ የህሊና የውልደት ስብራት ስለገጠመው አባ ሰረቀ (ስም ግብርን ይመራዋል እንዲሉ በ“ሠ” ስሙን አለመጣፌን ልብ ይሉዋል) ማንነት ጥቂት ለማለት ፈለግሁ።

ለነገሩ ይህን ያህል አጀንዳ ሊሆን የሚገባው ሰው እንኳን አልነበረም። አባ ጳውሎስ እንደ ጫማ ውስጥ ጠጠር እየቆረቆረ ዘወትር እረፍት የሚነሳቸውን ማኅበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ “ሳልጠራው አቤት ሳልከው ወዴት የሚል፣ ህሊናውን የተነሳ ሰው ፈልጉልኝ” ብለው ወዳጆቻቸውን፣ (መቼም የልብ ወዳጅ እንደሌላቸው የታወቀ ነው፣ እንደ ንጉሴ ያሉ ጥቅመኞች ያሉትን ለማለት ነው) አደራ ባሉት መሰረት ግዕዛን ከሌላቸው እንስሳት የሚመደብ፣ እውነትን እንኳን በተግባር በስም እንኳን የማያውቃት፣ የሥልጣን ጥም ያናወዘው፣ በፍቅረ ነዋይ ልቡ የታወረ፣ አባ ሰረቀ በመብራት ተፈልጎ ተገኘ። አባ ጳውሎስም “ልቤ በሰረቀ ጸና” አሉ።

በእርሱም ልባቸውን አኖሩ። ማኅበረ ቅዱሳንን ባልዋለበት እንደዋለ አድርጎ እንዲከስ ግዳጅ ተጣለበት። ከላባው አባ ላይ ታች ማለቱን ተያያዘው። የማኅበሩን በጎ ስም የሚያጠፋ የሥድብ መጥሀፍ አጻፈና በውድቅት ሌሊት በገንዘብ የገዛቸው ግብር አበሮቹ ፖስተሩን ሲለጥፉ ሁሉ በፖሊስ አስከመያዝ ደርሰዋል። ዳሩ ግን ውሎው ከኢሕአድግ ባለስልጣኖች ጋር የሆነው አባ ሰረቀ ማህበሩን የቅንጅት ቀኝ እጅ እንደሆነና በሚድያዎቹም የሚያስተላልፋቸው መልእክቶች ምእመኑ በመንግስት ላይ እንዲነሳ የሚያደርጉ እንደሁኑ አቀረበ (ለምሳሌ በጅማውና በኢሊባቡር በክርስቲያኖች ላይ የደረሰውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን ውድመት መግለጹን) ።

በተለያዩ ግዜያት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በአክራሪ ሙስሊሞች አማካይነት የደረሱትን ጭፍጨፋዎች፣ አባ ጳውሎስና መሰሎቻቸው እፍን አድርገው ልክ እንደ ተረቱ “አትናገሩ ጅቡ እኔን እየበላኝ ነው” እንደሚለው ገዳማውያኑ አባቶች እየተገደሉ፣ ክርስቲያኖች ከነ ማተባቸው እየታረዱ፣ አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ፣ እነ አባ ጳውሎስ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ አድርገው የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች ደም ለስልጣናቸው ማቆያ ገፈራ አድርገው ሲያቀርቡ ኖረዋል።

ዛሬም አይናቸውን በጨው አጥበው የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር እንደለመዱት መሬት ላይ ጥለው ሄሮድሳውያን ጌቶቻቸው ሲረጋግጡት ዓለም ሁሉ እንዲያይና ቤተ ክርስቲያኒቱን መሳቅያ መሳለቂያ እንዲያደርጋት ሲያደርጉ በቴሌቪዥን መስኮት ለማየት በቃን። በሲኖዶስ መንበር ላይ ቄሳሮች ተሰይመው ሲዳኙ ለማየት በቃን በአባ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና ምን ያልታየ ጉድ አለ የቤተ ክርስቲያኒቱን እድገት የማይሻውና ሰበባሰበብ እየፈለገ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያጣጥላት የኢሃድግ መንግስት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከመናፍቃንና ከአክራሪዎች ወከባ ይታደጋት ዘንድ እግዚአብሄር ያቆመውን ማኅበር በማፍረስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማዳከም በያዘው ስትራቴጂ መሰረት አስቀድሞ በአባ ጳውሎስ አቀነባባሪነት በአባ ሰረቀ ተላላኪነት የተዘጋጀው ትርኢት መድረኩ ላይ እሰከሚገኙ ድረስ ተሳታፊዎቹ እንኩዋን አያውቁም ነበር። አስቀድሞ የተቀነባበረው ቅንብር በህሊና አልባው በመነኩሴ አምሳል በተሰረው ሮቦት በአባ ሰረቀ ቀርቦ በፖለቲካው አጋፋሪ መመሪያ ሰጪነት በአባ ጳውሎስ አሳራጊነት የትርኢቱ ፍጣሜ ሆነ።

በጠቅላላው አባ ሰረቀ ማለት አባ ጳውሎስ ሰራሽ ሮቦት ነው፤ አልቦ ኅሊና።

September 23, 2009

“የማኅበረ ቅዱሳን አመስራረትና ሥራው ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ያጠፉአችሁ ዘንድ አይቻላችውም” (ሐዋ 5 ፣ 38)

(ከሰንደቅ ዓላማ/ SendekAlama)
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 23/2009):- «ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።» (ሐዋ 5 ፣ 38)

በብላቴ በረሃ መልካም ጥንስስን ጠንስሶ፣ ከቡቄሳ ተራራና ከኬስፓኖቿ እሳት አውጥቶ፣ ከሞርቾ የእግር ጉዞ የጥይት እራትነት ጠብቆ፣ ከፊሉን በአዋሳ በኩል ወደ መሃል አገር ልኮ፣ ከፊሉን በኬንያ አድአ የስደተኛ ካምፕ ጠልሎ ለትልቅና ለተመረጠ ሥራ ታናናሾችን ያጨ እግዚአብሔር ባለፉት ሃያ ዓመታት ያደረገውን ጥበቃ ዛሬም ከማኀበሩና ከአገልግሎቱ ጋር እንደሚያደርግ እምነቴ ነው።

ማኀበሩ በቡቃያነት ዘመኑ ያፈራውን መልካም ፍሬ አይተው ሊመሩትና ሊያግዙት «እኛንም አባል አድርጉን» ያሉ ታላላቅ አባቶች የነበሩትን ያህል፤ እንዲሁ በስሜት ብቻ «ከዛሬ ጀምሮ እኔም አባል ነኝ» ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ በያኔ ሥራው ብዙዎች ተደስተውበት «እደግ እደግ» ብለውት ነበር። ማኅበረ ቅዱሳን አራሚዎችና ዘሪዎች ባነሱበትና ባንቀላፉበት ወቅት ለስራ ተመርጠው ነበርና ቤተ ክርስቲያኒቱ ባላት መዋቅር ልትደርስበት ያልቻላቻችውን ቦታዎች ሁሉ በማዳረስ፣ የመናፍቃን ጎራ ሆኖ እንደ ጭልፊት ትውልዱን ሲጨልፉበት የነበረውን ዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ሐዋርያዊት የአባቶቻችን ሃይማኖት የሚሰበክባት እንድትሆን በማድረግ፤ ብዙ እጂግ ብዙ የተፈቱ ቤተ እግዚአብሔሮች እንዲከፈቱ ያሉትም እንዲበረቱ በማደረግ፣ ወጣቱ ትውልድ ከአባቶቹ እምነት ጋር መልሶ እንዲተዋወቅ በማደረግ ታላቅ ድርሻን የተወጣና ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገሪቱ ባለውለታ ማኅበር ነው።

የማኅበሩ የአገልግሎት አድማስ አየስፋ ሲመጣና ከአባላቱ በአንደኛው መኖሪያ ቤት ክትት ብለው ያልቁ የነበሩ ፈቃደኛ አባላቱ ስድሳና መቶ አፍርተው በመላ ሃገሪቱ የአባቶቻቸው ልጆች ሆነው ሲገኙ ብዙዎች የተደሰቱትን ያህል ማኅበሩ የእግር እሳት ሆኖባቸው እርሱን ለማጥፋት ሥራዬ ብለው ቆርጠው የተነሱም ነበሩ። ከውስጥም ከውጭም። « ሀገር ሲያረጅ እምቧጮ ያበቅላል » እንዲሉ በአሁኑ ስዓት ማኅበሩ ከተጋረጠበት ፈተናዎች መካከል ከባዱና ዋነኛው በአንድ አውድማ ለመሰማራት ቤተ ክርስቲያን «ልጆቼ» ብላ ለስራ ያሰማራቻቸው የገዛ ልጆቹአ ጋር ያለው ፈተናው ነው። በዚህ ሃያ አመት ውስጥ የታየው « ቤተ እግዚአብሔርን ማገልገል» እየተረሳ መጥቶ «በቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት መተዳደር» እየጎላ መምጣት ማህበሩ በፈቃደኛነትና በነጻ ለሚሰጠው አግልግሎት አንድ ተጨማሪ ስውር የፈተና ጎራ ሆኖበታል። ይህ አካሄድና ሁኔታ ግን ለማኅበሩ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን በጥቅሉ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐይማኖት በማንነቷ መቀጠልና አለመቀጠል ጋር ቀጥታ ትያያዥነት ያለው ጉዳይ ነው። አባቶቻችን አገልግሎትን በአገልግሎትነቱ ንጽህና ጠብቀውት ሰለነበር በመንፈሳዊ ኩራት «የሰጠኸኝን ሰጠሁህ» ብለውን ሲይልፉ የአሁኑ ትውልድ ግን «መተዳደሪያዬና እንጀራዬ» ብሉ የያዘውን ክህነት ለማስጠበቅ ብቻ በእውር ድንብር ሲጓዝ «ያልተሰጠውን ለተተኪው ትውልድ የሚስጥ» አሳዛኝ ትውልድ የመሆን እጣ ከፊቱ ተጋርጧል።

መንግሥትም ማኅበሩን በዐይነ ቁራኛ መከታተል የጀመረው ዛሬ ሳይሆን ገና ከጥንስሱ ቢሆንም የውስጥ አርበኛ ሆነው ማኅበሩን ሲከታተሉ የነበሩ የማኅበሩ አባላት «እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትም እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት» ስላሉ ለጊዜው ፋታ ያገኘ ቢሆንም የ 1997 ምርጫ እንደማንኛውም የህብረተሰብ አካል ሁሉ ማኅበሩን ክፉኛ ፈተና ውስት ጨምሮት ሄዷል። መንግስትም የበቀል አርጩሜውን በፍርሃትና በጭፍን ከሰነዘረባቸው መካከል ማኀበሩና አባላቱ እንደሆኑ ሁሉም ያውቀዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ማኅበሩን አሳልፎ ለመንግሥት አለሰጠም ነበር። እጅግ ብዙ በጣም ብዙ ጊዜ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቢሮ በአሰራር ሂደት አቤቱታ አቅራቢነትም ሆነ በመልስ ሰጪነት የተገኙ የማኅበሩ አባላት « በማኅበሩ አሰራርና አካሄድ ካልተደሰቱና በየፊናው የሚወራው ወሬ ዕውነት ነው ብለው ካመኑና ለቤተ ክርስቲያንም ይህ መሆኑ ይጠቅማታል ካሉ ማኅበሩን ያፍርሱት እኛም እንበተናል» የሚል የጠራ ኃሳብ ማህበሩ ባቀረበበት ወቅት እንኩዋን ማህበሩ ቢበተን አባላቱ በግል የሚያጡት ስጋዊ ጥቅም እንደሌለ ቤተ ክርስቲያን ግን በናኅበሩ መኖር እነደምትጠቅም በግልጽ ያዬት ፓትርያርኩ ወደ አዕምሮአቸው በቶሎ ይመለሱ ነበር። የአሁኑ ግን ለየት ያለ ነው። ተሰላፊዎቹ የበዙበት፣ መንግስት ለ2002 ምርጫ በፍርሃት የሚያቸውን አካሎች የሚያጠፋበት ወይንም ቅስም የሚሰብርበት፣ የፓትርያርኩ የመንግሥት ቀኝ እጅነት በቅዱስ ሲኖዶሱ እጂግ የዘገየ እርምጃ ፈተና ውስጥ የወደቅበት በመሆኑ ፓትርያርኩ ማኅበሩን አሳልፈው የሰጡበት አሳዛኝና አሳፋሪ የታሪክ ጊዜ ደረስን።

ከሳምንታት በፊት በሰጡት መግለጫቸው « ልማት፣ ሰላምና መረጋጋት» የምትል ሐረግ በማስገባት «እኔ ከመንግሥት ወገን ነኝ» ለማለት የሞከሩት ፓትርያርኩ አሁን ደግሞ «ማኅበሩ በፖለቲካና በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጣልቃ የመግባት አዝማሚያውን እንዲያቆም» በማለት ከማይክራፎኑ ጀርባና ከፓትርያርኩ ፊት ሌላ ተናጋሪ አንደበት ያለ እስኪመስል ድረስ ከእርሳቸው የማይጠበቅ ኃይለ ቃል ተናገረው ራሳቸውን ዳግም አቀለሉ። ኦዲት እንዲደረግ የተባለውም የማኀበሩ ሂሳብ ምናለ በቶሎ በቶሎ አድርገው ቢጨርሱትና ቢያሳውቁን፤ እንደ ዛሬው በመግለጫቸው አያካትቱትም እንጂ የማህበሩ ሥራዎች የሚተነተኑበት መልካም አጋጣሚ ይሆን ነበር ግን ምን ያደርጋል ክስን እንጂ ውጤቱን ስለማይናገሩ ውዥንብሩን ብቻ ነዝተውት ይቀራሉ።

በአንድ በኩል የፖለቲካ ተቃዋሚው ጎራ « ለሀገሩ ደንታ የሌለውና ወደ ቤተ ክርስቲያን እንጂ ወደ ስብሰባ አዳራሽ መውጣት የማይወድ ተልካሻ ተውልድን ማኅበረ ቅዱሳን እያፈራ ነው» በማለት በአገርም በውጪም ያሉ «አንቱ» የተባሉ «ፖለቲከኞች» ማኅበሩን ሌትተቀን ይከሳሉ፤ በሌላ በኩል « አህዳዊ አመለካከት ያላቸውና የተቃዋሚዎች ጎራ ሆነዋል» እያለ መንግሥት ማኅበሩን ይከሳል።

በግንባር ሆናችሁ እሳቱን ለምትጋፈጡ ወንድሞችን እህቶች መድኃኔአለም ብርታቱን ይስጣችሁ። የዚህ የማኅበረ ቅዱሳን አመስራረትና ሥራው ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ያጠፉአችሁ ዘንድ አይቻላችውም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ሲጣሉ ምናልባት ይገኙ ይሆናልና።»

“የማኀበረ ቅዱሳንን አገልግሎት ማደናቀፍ የሀገሪቱን የሃይማኖቶች ሚዛን ያዛባል” የሃይማኖት አጥኚ

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 23/2009)፦ መንግሥት ማኀበረ ቅዱሳንን በተመለከተ የሚወስደው ማንኛውም እርምጃ በኢትዮጵያ ያለውን የሃይማኖቶች ሚዛን እንደሚያዛባው አንድ የሃይማኖት አጥኚ ገለፁ።

ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት እኚኹ ባለሙያ ከፕሮቴስታንቶችና ከሙስሊሞች እንቅስቃሴ አኳያ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሁን ካለችበት አሳዛኝ ሁኔታ በባሰ ችግር ውስጥ እንዳትገባ የረዳት ማኀበረ ቅዱሳን መሆኑን ጠቅሰው የማኀበሩ አገልግሎት ላይ ሳንካ መፍጠር በእምነቶች መካከል ያለውን ሚዛናዊነት በማይጠበቅ መልኩ ስለሚያዛባው ለወደፊቱ በሀገሪቱ ውስጥ ትልቅ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል አብራርተዋል።


ጉዳዩ የአንድ መምሪያና አንድ ማኀበር ሆኖ ሳለ ቅዱስ ሲኖዶስና ቋሚው ሲኖዶስ ወይም የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባዔ ሳያውቀው ታላላቅ የመንግሥት ባለሥልጣናትን መጋበዝ ያስፈለገበት ሁኔታ ግልጽ እንዳልሆነላቸው የገለፁት እኚሁ ባለሙያ ለጊዜያዊ ጥቅም ተብሎ የሚወሰድ እርምጃ ትልቅ መዘዝ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል አስረድተዋል። ጉዳዩ የአንድ ማኀበር ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፣ ሀገሪቱ ካለችበት ጂኦ-ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ስብጥር ጋርም ተያይዞ መመርመር አለበት ያሉት ባለሙያ ከሶማሊያ የወቅቱ ሁኔታ፣ ከኤርትራ፣ ጂቡቲና ሱዳን የእምነት ይዘትና ዓለማቀፋዊ የአክራሪነት አደጋ ጋር መመዘን እንዳለበት አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በገጠማት የአስተዳደር ችግር ቅዱስ ሲኖዶሷ ራሱ ፈተና ውስጥ በመግባቱ ራሱ ሊመለከተውና ሊፈታው ይገባ የነበረው እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ በሙሉ ወደ ውጪ አካላት እየተገፈተረ “ኑና ዳኙን” መባሉ እንዳስገረማቸው ባለሙያው አትተዋል።

የአማኙ ጥያቄ ይህ አልነበረም

(ከዮፍታሔ)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
(ሰፕቴምበር 23/2009):- ውድ ወገኖቼ፦ በመጀመሪያ በዚህ ነገር ብዙዎቻችን ብዙም እንደማንርበሽ ነው የሚገባኝ ምክንያቱም የ97 ቱን ምርጫ ተከትሎ በመጣው ግርግር ቤተ ክርስቲያንን መጠጊያ ለማድረግ ወደ ቅጽሯ የተሰደደውን ወጣት እንዴት አድርገው አሳልፈው እንደሰጡት ገና የፈሰሰው ደም ከአደደባባዩ ላይ በቅጡ አልደረቀምና ነው። ይህ የአሁኑ ደግሞ ሁለተኛ ሽያጭ መሆኑ ነው። ምን ያህል የመንግስትን ቀልብ እንደሳበላቸው ባላውቅም፣ መንግስትም ያቀረቡለትን የፈጠራ ክስ በምን አይነት ሁኔታ እንዳየው ለኔ ግልጽ ባይሆንልኝም ማህበሩን ግን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለመኮርከም ወደኋላ ግን አይልም። አባቶች ብለን የክርስቶስን በግ ጠባቂዎች (ኖላዊ አባግዕ) ተብለው የተሰየሙት መነኮሳቱና ባለ አስኬማዎቹ አባቶች ትውልዱን ወደ ሞት ሊነዳ በሚችል ኃላፊነት በጎደለውና በስግብግብነት መንፈስ ለአለሙ ፍርድ ቤት ከሰው ለፍርድ አቁመውታል። በክርስትና ህይወቴ እንደዚህች ቀን ያፈርኩበትና ሆዴ የተረበሸበት ቀን አላስታውስም። በአባ ሠረቀ በጣም አፍሬያለሁ። እነዚህን ከሳሾች የዚህን ማህበር ያህል ምን እንደሰሩ ብንጠይቃቸው መልካም ነበር።

የአማኙ ጥያቄ ይህ አልነበረም ። የእኛ ጥያቄ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የሰፈነዉ የዘር አሰራር ተነቅሎ ይውጣ ነው ያልነው የቤተ ክርስቲያንቱ ሃብቷና ገንዘቧ ለእምነቷ ማስፋፊያ ይዋል ነው ጥያቄያችን የግለሰቦች ሃብት ማድለቢያ አይሁን ነበር ጥያቄው የአስተዳደራዊው ስራ ከግለሰቦች ተጽዕኖ ይዉጣ ነበር ያልነው ይህ ጥያቄያችን ወደ ፊትም ይኖራል መልስ እስከያገኝ ድረስ።

በጣም ያስደነገጠኝ በቅዱስነታቸው የተነበበው መግለጫ አይሉት ማዘዣ ነው።ለመሆኑ ይህ ሽፍጥ ከተዘፈቁበት ውጣ ውረድ ፋታ ያሰጠኛል ብለው ይሆን ? ማህበሩ የፖለቲካ አዝማሚያ ስላሉት ጉዳይ ለሚነሳው ጥያቄ መልስ የምንፈልገው ከፓትርያርካችን ሳይሆን ከዘመኑ ተዋናይ ከአባ ሠረቀ ነው። ለመሆኑ የየትኛው የፖለቲካ ድርጅት ደጋፊ ነው?
ከአባ ጳውሎስ ንግግር በጣም ያመመኝ ማህበሩ በቤተ ክርስትያን አስተዳደር ውስጥ የመግባት አዝማሚያ ያሳያል ነው ያሉን ለመሆኑ የግል ቤት ነው ብሎ የነገረዎት ማነው ወይስ የእንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተውበታል ይህን ስላሉስ እኛ አያገባንም እንደፈለጉ ያድርጉት ብሎ አይኑን ከቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ የሚያነሳ አለ ብለው አስበው ይሆን እንዴ። ይህ ከሆነ አላማዎት አባቴ ይሙቱ ሞኝ ነዎት።

ውድ በሰሜን አሜሪካ የምትኖሩ የዚህች መከረኛ ቤተ ክርስትያን እድምተኞች እንግዲህ ባለፉት ሁለት እና ከዛም በላይ ሳምንታቶች ባንዳው ንጉሴ በጦር እንደተወጋ ተኩላ ሲያጓጉር የነበረበት ዋነኛ ምክንያት ይሄና ይሄ ብቻ ነው። ክፍያው ተጠናቆ ይከፈለው አይከፈለው ግን ለጊዜው በእንጥል ይቆየን።
ግን እኮ የእኛ ጥያቄ አሁንም ይህ አይደለም የሲኖዶስ ህግ ይከበር ነው ያልነው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተሰገሰጉት ሌቦች፣ የቅርጽ ዘራፊዎች፣ የቤተ ክርስቲያኒቷን ንብረት እንደ ራሳችው ንብረት ከሚግጧት ደሟን ከሚመጧት ደም መጣጮች ትንጻ ነው ያልነው ። ለዚህ ጥያቅያችን ከሆነ የትናንትናው ትያትር እንደ መልስ የቀረበልን ጥያቄውና መልሱ በጣም የተራራቀ ነው የማይገናኝ ፍየል ቦሌ ቅዥምዥም ጉለሌ እንደሚባለው አይነት ማለት ነው።
አሁን የሚጠበቀው የጥቅምት ጉባዔ እየተቃረበ ነው። ታድያ የእኛስ ድርሻ ምን መሆን እንዳለበት ካሁኑ ማወቅ አለብን። ለአባቶች ከመጸለይ ጀምሮ በአላማቸው ጸንተው እንዲተጉ እየደወልን ከጎናቸው መሆናችንን መግለጽ ያስፈልገናል። እዚህ በገለልተኛ ነን ስም የሚያደናገሩትን አብያተ ክርስቲያናት አቋማቸውን በትክክል እንዲያስረዱ ምዕመናኑ መጠየቅ አለባቸው።ይህ አባ ሠረቀ ከአዲስ አበባ ሆነው በሪሞት የሚያንቀሳቅሱትን የቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተ ክርስቲያንንም ይጨምራል።

የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላት ስራችሁ ከስማችሁጋራ ብዙም አይገናኝም ገንዝብ እያወጣችሁ ለአድባራትና ለገዳማት የምትሰሩት ስራ እንዳለ ሆኖ፣ ከአገር ቤት ከየመጣችሁበት ቀዬ ካሉት የመንፈስ ወንድሞቻችሁ ሁኔታው ካመቻችሁ በኢንተርኔት ካልተቻለ በደብዳቤ መረጃ መለዋወጥ መቻል አለብን። እዚህ ያለነው በተሻለ መልኩ የመረጃ ምንጭ አለን። ካለዚያ እሁድን ጠብቆ መዘመርና አመት እየጠበቁ በየስቴቱ ጊዜንና ገንዘብን መስዋዕት አድርጎ መሰብሰቡ ለለውጥ ካልሆነ ከእረፍት ጊዜ ማሳለፊያነቱ እምብዛም አይዘል።

የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያና ማኅበረ ቅዱሳንን የተመለከተ ውይይት ተካሄደ

• ችግሩ ካልተፈታ “መንግሥት እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል” (አባይ ፀሐዬ)፤
• ማኅበረ ቅዱሳን “በፖለቲካና በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ የመግባት አዝማሚያ አሳይቷል” (አቡነ ጳውሎስ)

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 22/2009)፦ በማኅበረ ቅዱሳን እና በሰንበት ት/ቤቶች መምሪያ ሃላፊ በአባ ሰረቀ ወልደ ሳሙኤል መካከል የነበረው የረዥም ጊዜ አለመግባባት ፈንድቶ መውጣቱ ተሰማ (ዘገባውን ለመመልከት ይህንን ይጫኑ)።። ለዓመታት ውስጥ ለውስጥ ሲጋጋም የነበረው አለመግባባት ቅዱስ ፓትርያርኩና የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ይፋ ሲሆን እንደተነገረው ከሆነ “ማኅበሩ መመሪያዎችን ይጥሳል፣ በቤተ ክርስቲያንና በፖለቲካ የመግባት አዝማሚያ” ያሳያል ተብሏል። በሁለቱ መካከል “ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የተደረገ የውይይት መድረክ” መሆኑን የዘገበው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቅዱስ ፓትርያርኩን፣ የተወሰኑ ብፁዓን አባቶችን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ የመምሪያውን ባልደረቦችና የማህበሩን ሃላፊዎች ምስል አሳይቷል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻ ከተናገሩት ላይ ቀንጭቦ ያቀረበው ይኸው ዘገባ የማኅበሩ ንብረት ኦዲት እንዲደረግ፣ በሁለቱም በኩል ደንቦች እንዲከበሩ፣ “ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና በፖለቲካ ውስጥ ለመግባት የሚያሳየውን አዝማሚያ” እንዲያቆም ያሳስባል። ይኸው “አዝማሚያ” ምን እንደሆነ ግን ዘገባው አላብራራም። በዚሁ ውይይት ወቅት የተገኙት የመንግሥት ባለሥልጣናት ያለው ችግር እንዲፈታ ያሳሰቡ ሲሆን ችግሩ የማይፈታ ከሆነ ግን “መንግሥት ጣልቃ በመግባት እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል” ብለዋል። ይህ “ጣልቃ መግባት” ግን ምን ማለት እንደሆነ ለጊዜው አልተብራራም።

ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ አግኝቶ የሚንቀሳቀስና በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች፣ ኮሌጆች፣ ኢኒስቲቲዉቶች ውስጥ የሚማሩ ኦርቶዶክሳውያንን ነገረ-ሃይማኖት የሚያስተምር፣ በገዳማትና አድባራት ድጋፍ የሚያደርግ ማኅበር መሆኑ ይታወቃል። ዛሬው ስብሰባና ውጤት ምንነትን በተመለከተ ቀጣይ ዝግጅቶችን እናቀርባለን።

September 21, 2009

አዲሱ ዓመት ለቤተ ክርስቲያን አዲስ የአገልግሎት ዘመን ወይስ ሌላ የንትርክ ዓመት? (ክፍል አንድ)

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 20/2009)
የተወደዳችሁ ደጀ-ሰላማውያን፤ እንኳን ለአዲሱ ዓመት ሁለተኛ ሳምንት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ። በአዲሱ ዓመት ስለ ቤተ ክርስቲያናችን የምናደርገውን ውይይት፣ ምክክርና እንቅስቃሴ የበለጠ እንቀጥልበታለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በተለይም በዚህ በአዲስ ዓመት ቤተ ክርስቲያናችን ገብታበት ከነበረው መቀመቅ የመውጣት እንቅስቃሴ (በ2001 ዓ.ም የተጀመረውን) ቀጥላ ወደተሻለ የአገልግሎት ደረጃ ትሸጋገራለች ብለን እንጠብቃለን።ለዚህም እግዚአብሔር አምላክ ይጨመርበት ዘነድ ጸሎታችንና ምኞታችን ነው።

ይሁን እንጂ አሁን በምናየው ሁኔታ ብሩህ ዘመን ይመጣል ከማለት ይልቅ የጨለማው ክፍል የበለጠ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በተጨባጭ እየታዘብን ነው። ቅዱስነታቸው ራሳቸው በአዲስ ዓመት ቃለ ምዕዳናቸው ላይ እንደተናገሩት ራሳቸው ሕገ ቤተ ክርስቲያንን መጣሳቸውን እንደ መልካም ነገር በመቁጠር ይህንን የተቃወሙትን ብጹዓን አባቶች “ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የጣሱ” አድርገው አቅርበዋቸዋል። ይህም በመጪው የጥቅምት የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ለሕገ ቤተ ክርስቲያን እንደማይገዙ ከወዲሁ አመላክተዋል።
በተጨማሪም ለቀ ካህነና ጌታቸው ዶኒ የተባሉ እና ራሳቸውን “የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሕጋዊ ወኪል” ነኝ የሚሉ ግለሰብ “ኢትዮ-ቻነል” ለተባለ ጋዜጣ በጻፉት ጽሑፍ ፓትርያርኩ ለቅ/ሲኖዶስ ተጠሪ አለመሆናቸውን አበክረው በማብራራት ይልቁንም ቅ/ሲኖዶሱ ራሱ ተጠሪነቱ ለፓትርያርኩ መሆን እንዳለበት አትተዋል። ፀሐፊው በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ምንም የሥራ ድርሻ እንደሌላቸው የቤተ ክህነት ምንጮቻችን የገለፁልን ሲሆን “የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሕጋዊ ወኪል” ብለው ስለራሳቸው የገለፀበት ምክንያቱ ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ጋር ባላቸው ፀብ እርሳቸውን ለመቃወም የተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ በመመረጣቸው እንደሆነ ምንጮቻችን ገልጸውልናል።

ሊቀ ካህናት ጌታቸው “ጻፉት” ተብሎ “ጋዜጣ ላይ የወጣው ጽሑፍ የርሳቸው የአእምሮ ውጤት አይደለም” ያሉት ምንጮቻን ቅዱስ ፓትርያርኩ ራሳቸው ሥልጣናቸውን ለማጠናከርና ቅ/ሲኖዶሱን ለማዳከም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አካል ነው ብለዋል። በተለይም በቡድን ጽሑፎችን በመጻፍ፣ ክሶችን በማሰናዳት፣ በሬዲዮ በመናገር ብፁዓን አባቶችንና ለቤተ ክርስቲያን የሚቆሮቆሩ አካላትን አፋቸውን ለማዘጋት የሚያደርጉት ርብርብ አካል ነው ተብሏል።

ይህንን ሁሉ ስንመዝነው ይህ ዓመት ወደ በጎው ያደላ ይሆን የሚለውን ፍላጎታችንን ይጫነዋል። እንደተመለከትነው ለቅ/ሲኖዶሱ ልንጽፈው ይገባ የነበረውን “ፔቲሽን” እንኳን ሳናጠናቅቅ ጥቅምት “ደረስኩ ደረስኩ” እያለ ነው። በዚህ ዳተኝነታችን ላይ የማፊያዎቹ ቡድን ግን ቀን ከሌሊት ቤተ ክርስቲያንን እየዘረፈና አበውን እያዋረደ፣ ስብከተ ወንጌልን እየገደለና ምእመናንን እየበተነ፣ በዘመድ አዝማድ እየተቀጠረና ሊቃውንቱን እያባረረ በመዝለቅ ላይ ነው። የመጨረሻው ዕድል ቅ/ሲኖዶሱ ጀምሮት የነበረው እንቅስቃሴ ተግባራዊ ማድረግ ነበር።፡እርሱም ቢሆን በራቸው ሲሰበርባቸው፣ ማስፈራሪያ ሲደርሳቸውና መንግሥትም በውስጡ የተደበቀውን ሃይል ሳያወጣ (ፖሊስም ወነጀለኞችን ሳይዝ በመቅረቱ፣ ወይም አውቆ ዝም በማለቱ) ደኀንነቱ የማፊያ ተግባር ሲሠራ ዝም በማለቱ ብፁዓን አባቶች ተደፋፍረው ይናገራሉ ለማለት አያስችልም። እግዚአብሔር መፍትሔውን እንደሚያመጣ እያመንን እኛም የአቅማችንን “ማናገርም ብቻ ቢሆን እንኳን” ከመናገር ዝም ማለት የለብንም።

ታዲያ ምን ይሻላል? (ይቀጥላል)

September 18, 2009

መንበረ ፓትርያርኩ ከሩብ ሚሊዮን ብር በላይ ለደመራ መደበEthiopia Zare (ኀሙስ መስከረም 7 ቀን 2001 ዓ.ም. September 17, 2009)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የፊታችን መስከረም 16 ቀን 2002 ዓ.ም. ለሚከበረው የደመራ በዓል ከሩብ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አፀደቀ። የወጪው መብዛት ምዕመናኑን አሳዝኗል።

ለፖሊስ ባንድ አባላት 28 ሺህ ብር፣ ለአራት ትራፊክ ፖሊሶች አንድ ሺህ ብር፣ ለሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ትርዒት አገልግሎት የሚውል የማቴሪያል መግዣ ሁለት መቶ ሺህ (200000) ብር እና ለ56 አሠልጣኞች 25200 ብር፤ በድምሩ ሁለት መቶ ሃምሳ አራት ሺህ ሁለት መቶ (254200) ብር ወጪ እንዲደረግ መጽደቁን ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በአባ ይስኃቅ ተፈርሞ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ከተላከው ደብዳቤ ለመረዳት ችለናል።


ነኀሴ 29 ቀን 2001 ዓ.ም. የተፃፈው ይኸው ደብዳቤ የመስቀል በዓል አዘጋጅ ዓቢይ ኮሚቴ ከገንዘብ አሰባሳቢ ንዑስ ኮሚቴ የቀረበለትን መግለጫ ተቀብሎ ነኀሴ 22 ቀን 2001 ዓ.ም. ማጽደቁን ያትታል። የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሆኑት በአባ ይስኃቅ ፊርማና ማኅተም የወጣውና በቀጥታ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በቁጥር 5258/290/2001 የወጣው ደብዳቤ፤ በግልባጭ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣ ለሂሳብና በጀት መምሪያ፣ ለቁጥጥር አገልግሎት መምሪያ፣ ለበዓል አዘጋጅ ዓቢይ ኮሚቴ፣ ለፀጥታና ሥነሥርዓት አሰባሳቢ ንዑስ ኮሚቴ እና ለሰንበት ት/ቤት ያሬዳዊ
መዝሙርና ትርዒት ዝግጅት ንዑስ ኮሚቴ ደርሷቸዋል።

ይህንን ከሩብ ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ወጪ በርካታ የኦርቶዶክስ ምዕመናንን እንዳሳዘነ የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢዎች ከየሥፍራው (ከሀገር ቤት እና ከሀገር ውጪ) ያሰባሰቡት መረጃ ያስረዳል። ምዕመናን “ፓትርያርኩ ተጠያቂነት በሌለበትና ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ገንዘብ እያባከኑ ነው ለሚባለው ይህ አንዱ ማረጋገጫ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

ለበዓል የሚወጣው ወጪ ያሳዘናቸው ምዕመናን በርካታ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ የተገደዱ መሆናቸውን ለመረዳት ችለናል። ከእነዚህም ውስጥ “አቡነ ሳሙኤልን በአዲስ አበባ ከነበራቸው ሥልጣን ፓትርያርኩ ያነሷቸው እንዲህ ላለው የገንዘብ ብክነት ያመቻቸው ዘንድ ነው ወይ?”፣ “ገንዘቡ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ለምን አይውልም?”፣ … የሚሉ ይገኙበታል።

እንዲህ ያለውን የገንዘብ አወጣጥና አሠራርን አጥብቀው የሚቃወሙትና ሥርዓት ለማስያዝ የሚጥሩ አባቶች በየጊዜው በተደራጀ ኃይል ጥቃት ሲፈፀምባቸው መቆየቱን ያስታወሱ አንድ ምዕመን፤ “ይሄ የኦርቶዶክስ ምዕመናን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጉዳይ ሊሆን ይገባዋል፤ ሁሉም ዜጋ በያለበት ኃይማኖት ውስጥ ሆኖ እንዲህ ላሉት በኃይማኖት አባትነት ሥም ለሚፈፀሙና የሞራል ጥያቄ ሊያስነሱ የሚችሉ ሥርዓት አልባ አካሄዶችን ማውገዝና መከላከል ይገባቸዋል” ብለዋል።

ከዚህ በተቃራኒው ሃሳባቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ የገለጹ ምዕመናን ደግሞ፤ የገንዘቡ መጠን የበዛ ቢመስልም በሀገር ውስጥ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ለማያያዝ ሞክረዋል። ከጠቅላላ ወጪው ውስጥ ሁለት መቶ ሺህ (200000) ብሩ ለሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ትርዒት አገልግሎት ለሚውል ቁሳቁስ መግዣ መዋሉን ግምት ውስጥ በማስገባት፤ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ቢያንስ ከ300 % (ሦስት እጥፍ) የኑሮ ውድነት በመከሰቱ በአንፃራዊነት ወጪው ብዙ አይደለም ሲሉ እነዚሁ ምዕመናን ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልፀዋል።

September 13, 2009

History of Ethiopian Church Presence in Jerusalem

Above photo: Ethiopian monks on the roof of Christianity’s holiest shrine in Jerusalem (Creative Commons Attribution).
Tadias Magazine
Saturday, April 25, 2009
New York (Tadias) - The following piece was first published on the print issue of Tadias Magazine in the context of the July 2002 brawl that erupted on the roof of Christianity’s most holy place between Ethiopian and Egyptian monks.

“Eleven monks were treated in hospital after a fight broke out for control of the roof of the Church of the Holy Sepulchre in Jerusalem, the traditional site of Jesus’s crucifixion, burial and resurrection”, wrote Alan Philps, a Jerusalem based reporter for the Daily Telegraph.
“The fracas involved monks from the Ethiopian Orthodox church and the Coptic church of Egypt, who have been vying for control of the rooftop for centuries.”
(To read more click: History of Ethiopian Church Presence in Jerusalem)
Posted using ShareThis

September 12, 2009

ብፁዕ አቡነ አብርሃም ያስተላለፉት ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የአዲስ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉት ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ
(Click HERE to view in Youtube).


 

September 8, 2009

መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች "ሠራተኛ" ናቸው አይደሉም?

Sunday, 06 September 2009
(Reporter): የአሰሪና የሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 የተፈፃሚነት ወሰን በዚያው ሕግ አንቀጽ 3"2) ስር የተዘረዘሩትን እንደማይሸፍን ይደነግጋል፡፡ የዚህ የተለያየ የፖሊሲ ምክንያት አለው፡፡ ይህ አዋጅ በተለይ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3"ለ) ስር የሃይማኖት ወይም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሚመሰርቱት የስራ ግንኙነቶች ላይ ሕጉ ተፈጻሚ እንዳይሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ሊወስን ይችላል ይላል፡፡


በአዲስ አበባ የሚገኙ የሥራ ክርክር ችሎቶችን የማየት እድል ያጋጠመው ሰው ልብ እንደሚያደርገው የማይናቅ ቁጥር ያላቸው "መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡ" ከሃይማኖት ድርጅት የሥራ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ክስ መስርተው ሲመላለሱ ልብ ማለቱ አይቀርም፡፡

ጉዳዩ የሚቀርብላቸው ፍርድ ቤቶች እንዲህ ያሉትን ሰዎች ክስ ጉዳይ በአዋጁ የሚሸፍን አይደለም በማለት እየወሰኑ ነው፡፡ ለዚህ መነሻ የሆነው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሰሚ ችሎት በመ. ቁጥር 18419 ግንቦት 4 ቀን የሰጠው በሌሎች በየትኛውም ደረጃ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች አስገዳጅነት ያለው ውሳኔ ነው፡፡ ውሳኔውን እንዳለ አቅርበነዋል፡፡
የሰበር መ/ቁ. 18419

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ግንቦት 4/1998
ፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት
ዳኞች፡- 1. አቶ መንበረፀሐይ ታደሰ
2. አቶ ዓብዱልቃድር መሐመድ
3. አቶ ጌታቸው ምህረቱ
4. አቶ መስፍን እቁበዮናስ
5. ወ/ት ሂሩት መለሠ
አመልካች፡- ሐመረወርቅ ቅ/ማርያም ቤ/ክርስቲያን ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት

መልስ ሰጭዎች፡- 1. ዲያቆን ምህረት ብርሃን
2. አጋፋሪ አብርሃም ታደሰ
3. ዲያቆን አስራት ወ/ትንሣይ
4. ዲያቆን ገዛኸኝ ከበደ
5. ዲያቆን ስመኘው ግርማይ
6. ዲያቆን ዓለማየሁ ሞገስ

ፍርድ

ጉዳዩ ለዚህ ችሎት የቀረበው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መልስ ሰጪዎች በአመልካች ቤተክርስቲያን ውስጥ መንፈሣዊ አገልግሎት ተቀጥረን ስናገለግል ከቆየን በኋላ አመልካች ሕገወጥ በሆነ መንገድ ከሥራ ያሰናበተን በመሆኑ ወደ ሥራ እንድንመለስ ይወሰንልን በሚል ባቀረቡት ክስ የአዋጅ ቁ. 42/85 ድንጋጌዎችን ተፈፃሚ በማድረግ ስንብቱ ሕገወጥ ነው በማለት መልስ ሰጭዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ የሰጠውና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያፀናው ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሞበታል በሚል አመልካች የሰበር አቤቱታ በማቅረቡ ነው፡፡ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት መልስ ሰጭዎች የአመልካች አቤቱታ ደርሷቸው መልስ የሰጡ ሲሆን አመልካችም የመልስ መልስ እንዲያቀርብ ተደርጓል፡፡

በጉዳዩ በዚህ ችሎት መታየት ያለበት የሕግ ነጥብ በአዋጅ ቁ.42/85 አንቀጽ 3"3""ለ) መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊያወጣው የሚችለው ደንብ የኃይማኖት ተቋማት መንፈሣዊ አገልግሎት ከሚሰጡ ሠራተኞቻቸው ጋር ያላቸውን የሥራ ግንኙነቶችም ሊጨምር ይችላል? ወይስ አይችልም? የሚለው በመሆኑ ችሎቱም ነጥቡን መርምሯል፡፡ አንቀጽ ቁ42/85 በአዋጅ ቁጥር 377/96 የተሻረ ቢሆንም ነጥቡን በሚመለከት ሁለቱ አዋጆች አንድ ዓይነት ድንጋጌዎች የያዙ በመሆኑ ችሎቱ የአዋጅ ቁ.42/85 ድንጋጌዎች መሠረት አድርጎ በተጠቀሰው ነጥብ ላይ የሚሰጠው የሕግ ትርጉም ለአዋጅ ቁ.377/96 ድንጋጌዎች አግባብነት ያለው ነው፡፡

ይህ ችሎት በዚህ ጉዳይ የሕግ ትርጉም ለሚሰጥበት ከላይ ለተመለከተው ነጥብ ቀጥተኛ አግባብነት ያለው የአዋጅ ቁ.42/85 አንቀጽ 3 ነው፡፡ ይኸው አንቀጽ አዋጁ በንዑስ አንቀጽ 2 ከተመለከቱት በቅጥር ላይ ከተመሰረተ የሥራ ግንኙነት ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ የኃይማኖት ተቋማት መንፈሣዊ ተግባር ከሚያከናውኑ ሠራተኞች ጋር ያላቸው የሥራ ግንኙነት አዋጁ ተፈፃሚ እንደማይሆንባቸው በአንቀጽ 3"2) ከተዘረዘሩት የሥራ ግንኙነቶች ውስጥ የተካተተ ሲሆን ይልቁንም የአዋጁ አንቀጽ 3"3""ለ) የኃይማኖት ወይም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሚመሰረቱት የሥራ ግንኙነቶች ላይ አዋጁ ተፈጻሚ እንደማይሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ሊወስን ይችላል በሚል ይደነግጋል፡፡ የስር ፍ/ቤት ጉዳዩን በአዋጅ ቁ.42/85 መሠረት ለማየት ውሣኔ የሰጠው በአንቀጽ 3"3""ለ) መሠረት የተጠቀሱት ድርጅቶች በሚመሰርቱት የሥራ ግንኙነት አዋጁ ተፈፃሚ እንዳይሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እስካላወጣ ድረስ ድርጅቶቹ በሚመሰርቱት የሥራ ግንኙነቶች ላይም አዋጁ ተፈጻሚ ይሆናል የሚል ነው፡፡ ይህም በስር ፍርድ ቤት ለአንቀጽ 3"3""ለ) የተሰጠው ትርጓሜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኃይማኖት ድርጅቶች መንፈሣዊ አገልግሎት ከሚሰጡ ሠራተኞቻቸው ጋር ባላቸው የሥራ ግንኙነቶች ላይ የአዋጅ ቁ.42/85 ተፈፃሚ እንዳይሆን በደንብ ሊወስን ይችላል የሚል ድምዳሜን መሠረት ያደረገ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ አተረጓጎም የሕጉን መንፈስ ተከትሎ የተሰጠ መሆን አለመሆኑን ለመመርመር የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ የሚሸፍናቸውን የሥራ ግንኙነት ጉዳዮች መመልከት የግድ ይላል፡፡

የአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ የሥራ ውል ስለሚመሰረትበት ሁኔታ የሥራ ውሉ ስለሚቆይበት ጊዜ፤ የሠራተኛውና የአሠሪው መብትና ግዴታ የሥራ ግንኙነት ስለሚቋረጥባቸው ውስን ሁኔታዎች፣ የሥራ ውሉ ሕጋዊ ወይም ሕገወጥ በሆነ መንገድ በሚቋረጥበት ጊዜ ስለሚከተሉ ውጤቶች የሚደነግጉ ድንጋጌዎች የያዘ ሆኖ ይታያል፡፡ በአጠቃላይ ሕጉ ከአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን በአንዳንድ ሁኔታዎች ከሚያጋጥሙ ልዩ ጉዳዮች በቀር አካቶ የያዘ መሆኑን መረዳት ይችላል፡፡

ከላይ የተመለከቱት ከአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ነጥቦች መንፈሣዊ አገልግሎትን በሚመለከት የኃይማኖት ተቋማት በሚመሠርቷቸው የሥራ ግንኙነቶች ውስጥም የሚነሱ ቢሆንም በሌሎች የሥራ ግንኙነቶች ከሚያጋጥሙበት አኳኋን ለየት ባለ መንገድ የሚያጋጥሙ ሁኔታዎችም አሉ፡፡ ምክንያቱም በአንድ የኃይማኖት ተቋም ውስጥ ሊመሰረት የሚችል የተለያየ የሥራ ግንኙነት በመኖሩ ነው፡፡ በአንድ በኩል የሚሠጡት አገልግሎት ድርጅቱ ከሚከተለው እምነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለውና ከእምነቱ ጋር ተነጥሎ ሊታይ የማይችል ሠራተኛን፤ እንደ ቄስ፣ ካህን፣ ዲያቆን ወዘተ. ያሉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሚሠጡት አገልግሎት ከእምነቱ ጋር ያልተቆራኘ እንደ ሂሣብ ሠራተኛ የንብረት ክፍል ሠራተኛ የስታትስቲክስ ሠራተኛ ወዘተ. አሉ፡፡ በመሆኑም የሃይማኖት ሥራውን ከሚሠሩት ሠራተኞች ጋር የሚነሣው የአሠሪና ሠራተኛ ሁኔታ ከሌሎቹ ሠራተኞች ጋር ከሚነሳው የተለየ ነው፡፡ ቀጥተኛ የሃይማኖቱን ወይም መንፈሣዊ ሥራ የሚሠሩትን ሠራተኞች ስንመለከት የሥራቸው ፀባይ የኃይማኖት ተቋሙ ከሚከተለው እምነት የሚመነጭና ከእምነቱ ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው በመሆኑ መንፈሣዊ አገልግሎቱን ለመስጠት ብቁ ሆኖ ለመገኘት መሟላት የሚገባቸው ነገሮች ለምን ያህል ጊዜ አገልግሎቱ ላይ መቆየት እንደሚችል የኃይማኖቱ እና የመንፈሣዊ አገልግሎት ሠጪው መብትና ግዴታ አገልጋዩ መንፈሣዊ አገልግሎቱን እየሰጠ እንዲቀጥል የሚያደርጉ ሁኔታዎች አገልጋዩ አግባብ ባልሆነ መንገድ አገልግሎቱን እንዳይሰጥ በተደረገ ጊዜ የሚከተሉት ሁኔታዎች እና ሌሎች በሥራ ግንኙነቱ ሊነሱ የሚችሉ ጉዳዮች እያንዳንዱ የኃይማኖት ተቋም ከሚከተለው እምነት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ የመንፈሣዊ ሥራ ግንኙነቱ የሚያስነሳቸው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳዮች ከእምነቱ ተነጥለው የሚታዩ ባለመሆናቸው በሥራ ግንኙነቱ ውስጥ ጣልቃ መግባቱ በእምነት ውስጥ ጣልቃ መግባትን ያስከትላል፡፡

በሌላ በኩል ግን ከእምነቱ ጋር ተያያዥነት ያለውን ሥራ የሚሰሩ ሠራተኞች ከድርጅቱ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ሊያስነሳ የሚችለው ጉዳዩ ከእምነቱ ጋር የማይያያዝና ይልቁንም በማንኛውም የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ከሚነሱ ሁኔታዎች የተለየ አይደለም፡፡

ከላይ እንደተመለከተው የመንፈሣዊ የሥራ ግንኙነቱ የሚያስነሳቸው ሁኔታዎች ከሃይማኖቱ ተነጣጥለው ሊታዩ የማይችሉ በመሆናቸው የሥር ፍርድ ቤት ለተጠቀሰው አንቀጽ በሰጠው ትርጉም የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመንፈሣዊ ሥራ ግንኙነትን በሚመለከት ሕግ የሚያወጣ ከሆነ በኃይማኖት ጉዳዮችም ጣልቃ መግባቱ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11 "መንግሥትና ኃይማኖት የተለያዩ ናቸው፤ መንግሥት በኃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ አይገባም" በማለት ከተደነገገው ጋር የሚጋጭ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሃይማኖቱን ሥራ ከሚሰሩት ሠራተኞች ውጪ ያሉና በሃይማኖት ተቋም ከሚሰሩ ሠራተኞች ጋር ያለው የሥራ ግንኙነት የሚያስነሳው ጉዳይ ሌላው የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ከሚያስነሳው ጋር ተመሣሣይ በመሆኑ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአ.ቁ.42/85 አንቀጽ 3"3""ለ) መሠረት ሊያወጣ የሚችለው ደንብ እነዚህን ሠራተኛን በተመለከተ እንጂ መንፈሣዊ አገልግሎት ለመስጠት ከኃይማኖት ተቋማት ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት የሚጨምር ሊሆን አይችልም፡፡

በመሆኑም ደንቡ እስካልወጣ ድረስ የአዋጅ ቁጥር 42/85 በመንፈሣዊ የሥራ ግንኙነቶች ላይም ተፈፃሚ ይሆናል የሚለው ትርጉም የሕግ መሠረት የሌለው ይሆናል፡፡

ከፍ ሲል በተዘረዘሩት ምክንያቶችም ማንኛውም የሥራ ክርክር ሰሚ አካላት መንፈሣዊ የሥራ ግንኙነቶች ተመስርቶ የሚነሱ ክርክሮች በአ/ቁ 42/85 መሠረት አይቶ ለመወሰን ሥልጣን የሌላቸው ሲሆን ክርክሮቹ የኃይማኖት ተቋማቱ በሚኖራቸው አለመግባባቶች በሚፈቱበት መንገድ የሚታዩ ናቸው፡፡ ይህ ችሎትም የስር ፍርድ ቤት በዚህ ጉዳይ በታየው የሕግ ነጥብ የሰጠው የሕግ ትርጉም መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝቶታል፡፡

ውሣኔ

1/ የፌ/መ/ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ. 13549 ህዳር 24 ቀን 1997 የሰጠው ውሣኔና የፌ/ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 35562 ጥር 17 ቀን 1997 ዓ.ም. የሰጠው ትእዛዝ ተሽሯል፡፡

2/ ግራ ቀኙ ወጪና ኪሣራቸውን የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ይመለስ
የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

September 7, 2009

የማፊያው ቡድን ከአቡነ አብርሃም ጋር “ሰላም” አወረደ ወይስ የስልት ለውጥ?

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 7/2009)፦
የማፊያው ሬዲዮ ጣቢያ “ሀገር ፍቅር ሬዲዮ” የማህበረ ቅዱሳን ጳጳስ ሲላቸው የነበራቸውን ብፁዕ አቡነ አብርሃምን “ብፁዕ አባታችን፣ የእናት ቤተ ክርስቲያናችን እውነተኛ አባት” ሲላቸው አምሽቷል። አቶ ንጉሴ ወ/ማርያም እንዲህ ዓይነቱን የልብ ለውጥ ለምን እንዳመጣ ለጊዜው ግልጽ አይደለም። ስትራቴጂክ (የስልት) ለውጥ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት ወደፊት የምንደርስበት ይሆናል።

ንጉሴ ትናንት የተናገረውን ዛሬ የማይደግም መሆኑ ይታወቃል። ሐሳቡን የሚቀያይረው ከሁዋላ ሆነው በገንዘባቸው የሚዘውሩት አጉራሾቹ “ጃስ” ሲሉት ነው። ይኼ የቁልቢን ብር/ ገንዘብ (ጉቦ) እየበላ የሚጮኽብን ጅብ በአንድ ሳምንት ጊዜ ተገልብጦ አቡነ አብርሃምን ያንቆለጳጰሰበት ምክንያት ይመረመራል።
ቸር ወሬ ያሰማን
አሜን

September 5, 2009

መንግሥት ሆይ እጅህን ከቤተ ክርስቲያን ላይ አንሣ!!!!!!!!

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 4/2009)፦ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ሆና ቢያንስ እስከ 1966 አብዮት እንደመዝለቋ ከመንግሥት ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ ማወቃችን አሁን ላለችበትም ሆነ ነገ ለምትኖርበት ሁኔታ ዕውቀታችንና ግንዛቤያችን እንዲጨምር ያደርገናል። መንግሥትና ሃይማኖት ተለያዩ እስከተባለበት ዘመን ድረስ “ቤተ መንግሥቱና ቤተ ክህነቱ” የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆኖ ኖሯል። ቤተ ክህነቱ ምንም እንኳን “ነጻ” የሆነ ቢመስልም በቤተ መንግሥቱ ቁጥጥር ሥር እንደነበር ይታወቃል። ኮሚኒስቶቹም ሥልጣን ላይ ከወጡ በሁዋላ “በፈጣሪ አናምንም” ቢሉም “በፈጣሪ የምታምነውን ቤተ ክርስቲያን” ለመልቀቅ አልፈቀዱም። በዚህም መሠረት ደርጎች የጠቅላይ ቤተ ክህነትን ሥራ አስኪያጅ እየሾሙ ከመላካቸውም በላይ በተለይም በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የነበረውን ርስታችንን ከቤተ ክህነቱ ጋር በጋራ ያስተዳድሩ ነበር። ከዚህም በላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለተወረሱባት ንብረቶች ማካካሻ እንዲሆን ዓመታዊ በጀትም ይቆርጡላት ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢሕአዴግ መንግሥት መጣና እንደገና “መንግሥትና ሃይማኖት ተለያይተዋል” ሲባል አዲስ ምዕራፍ ተጀመረ።

ኢሕአዴግና ደርግ “መንግሥትና ሃይማኖት ተለያይተዋል” ሲሉ የወሰዱት መፍትሔ የተለያየ ነው። ደርግ ግልጽ የሆነውን ቁጥጥሩን ሳያላላ ሲቀጥል ኢሕአዴግ ግን በድብቅ ነገር ግን በጥልቀት መቆጣጠሩን ተያይዞታል። ደርግ ፓትርያርክ መሾሙን ሳይክድ፣ ሥራ አስኪያጅ መላኩን ሳያቋርጥ፣ መንግሥት በቤተ ክህነቱ አሠራር የሚገባበት ቦታ ላይ ያለማመንታት እየገባ ሲያስኬድ ኢሕአዴግ ግን “በቤተ ክህነቱ ሥራ ጣልቃ አልገባም/ አልገባሁም” እያለ ነገር ግን ሰላዮቹ ቤተ ክህነቱን ተቆጣጥረውታል፣ ፓትርያርኩም በመንግሥት ወገንተኝነታቸው እየተመኩ የአንድ ሰው አስተዳደርን አሰልጥነውታል።
ኢሕአዴግ ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ከፈጸማቸው የተሳሳቱ አካሄዶች መካከል ዋነኛውና አሁንም ካልተሻሻለ ሌላ ውድቀት የሚያመጣው ፓትርያርኩ፣ ልክ እንደ ካቶሊክ ፓፓ፣ አይነኬ ያውም ፈላጭ ቆራጭ እንዲሆኑ ማድረጉ ነው። የቀድሞዎቹም ፓትርያርኮች ጽኑዕ ሥልጣን እንዳላቸው ቢታወቅም እንደ አባ ጳውሎስ ዘመን ግን ፍፁም መረን የወጣ ሥራ ሠርተው አያውቁም። ለዚህ የአባ ጳውሎስ መረን መውጣት ዋነኛ ተጠያቂው መንግሥት ነው። አንደኛ ከመጠን ያለፈ ጀሌ የስለላ ሰዎች በቤተ ክህነቱ ግቢና አሠራር ውስጥ ሰግስጓል። በዘራቸው ብቻ የሚመኩ፣ ከክርስቶስ መንግሥት ይልቅ ለዚህ መንግሥት ጥብቅና የቆሙ፣ ምንም ነገር ከመሥራታቸው በፊት አገልግሎቱን በፖለቲካ አንድምታ መፈተሽ የሚፈልጉ፣ ቤተ ክህነቱን እንደ ፓርቲው አንድ አካል እንጂ እንደ እግዚአብሔር መሥሪያ ቤት የማይመለከቱ፣ ከክህነታቸው ይልቅ የፓርቲ አባልነታቸውን የሚያደንቁ፣ ከአበው ትዕዛዝ ከመቀበል ይልቅ ባላቸው የመንግሥት ወገንተኝነት ትከሻቸውን የሚያሳብጡ ሰዎች ቤተ ክህነቱን እንዲቆጣጠሩት ያደረገው መንግሥት ራሱ ነው። በየአህጉረ ስብከቱ ከጳጳሳቱና ከሥራ አስኪያጆቹ እኩል የፓርቲው ሰዎች ተሠማርተዋል። “የነፍጠኛ ቤተ ክርስቲያን” በሚለው የነአቶ ተፈራ ዋልዋ መመሪያ መሠረት “ነፍጠኖች ሊያንሠራሩባት” የሚችሉባት ቦታ ቤተ ክርስቲያን ሆና በመቆጠሯ የስለላው መዋቅር በጥልቀት እንዲገባ ሆኗል። አሁን በቤተ ክህነቱ ውስጥ፣ በተለይም በፓትርያርኩና በቅዱስ ሲኖዶሱ መካከል ለተፈጠረው ችግር መንስዔው ይኼው 17 ዓመት ሙሉ የተጠራቀመው ሕገ ወጥ አሠራር ነው። ዛሬ የፓትርያርኩ ዘመዶችና ወገኖች እንዲሁም የማፊያው ቡድን አባላት ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመለከቷት እንደ ግል ንብረታቸውና እንደ ቤተሰብ ሀብት ነው።
መንግሥት ይህንን ቅጥ ያጣ ግንኙነት መለወጥ እንዳለበት ግልጽ ቢሆንም አሁን በሚታየው ሁኔታ ይህንን የመለወጥ ፍላጎት ያለው አይመስልም። ፓትርያርኩን የሚመለከታቸው የቤተ ክህነቱን ቁጥጥር በእርሱ ሥር የመሆን/አለመሆኑ ምልክት አድርጎ ስለሆነ የእርሳቸው ሥልጣን መገደብ የኢሕአዴግ ሥልጣን መገደብ አድርጎ ይወስደዋል። እርሳቸው ላይ የሚመጣ ማንኛውም ነገር “በራሱ ላይ የመጣ” ይመስለዋል። የወንበራቸው መነቃነቅ “የአንድ የነፍጠኛ ጳጳስ መምጣት” አድርጎ ይቆጥረዋል። ለኢሕአዴግ ማንኛውም ሰው የሚመዘነው ባለው የፖለቲካ አቋም ብቻ እና ብቻ እንጂ በሃይማኖቱ ወይም በዜግነቱ አይደለም። ምእመን ሆነ ካህን፣ ጳጳስ ሆነ ፓትርያርክ የመንግሥት ደጋፊ ከሆነ ተቀባይነት አለው አለበለዚያ ግን ማንም አይፈልገውም።
መንግሥት የተበላሸ አመለካከቱን በቅዱስ ሲኖዶሱና በፓትርያርኩ መካከል በተፈጠረው ችግር ወቅት በግልጽ አሳይቷል። የመንግሥት የስለላው አካላት የሆኑ ነገር ግን በማፊያው ብር የሰከሩና የመንግሥትን መዋቅር የሚጠቀሙ ሰዎች የአባቶችን በር መሰባበራቸውን፣ አንዳንድ ብፁዓን አባቶችን አፍነው ወስደው ማስፈራራታቸውን፣ አሁንም በየጳጳሳቱ ዘንድ እየቀረቡ “ወየውላችሁ” እንደሚሉ አሳማኝ ማስረጃዎች በማግኘት ላይ ነን። እስካሁን ድረስ መንግሥት በመንግሥትነቱ በዚህ ጉዳይ ውስጥ አልገባም ብለን ያመንን ቢሆንም አሁን የሚታየው አካሄድ ግን መንግሥት የፓትርያርክ ጳውሎስን ወገን በመደገፍ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከችግሯ ለመውጣት በማድረግ ላይ ያለችውን ሙከራ በማደናቀፍ ላይ መሆኑን እየተመለከትን ነው። ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በደህንነት ሃይሎች ታፍነው ተወስደው ማስፈራራትና ማዋከብ ደርሶባቸው ሳለ እስካሁን ማንም ተጠያቂ አልሆነም። የአባቶች ቤቶች በሃይል ተደብድበው ተሰባብረው ሳለ ወንጀለኛው እስካሁን አልተያዘም። ፓትርያርኩ ከቅ/ሲኖዶስ በላይ መሆናቸውን በተግባር እያሳዩ፣ ከቤተ ክርስቲያን በወጣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ወንጀለኞች እንደፈለጉ እየፏነኑ መንግሥት “ዓይኔን ግንባር ያድርገው ፣ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ” እያለ ነው።
በርግጥ በዚህ ሁሉ ነገር መንግሥትስ ቢሆን “ፖለቲካዬን ይጠቅመዋል” ብሎ ያስባል ማለት ነው? መንግሥት ከሚጠላባቸው ነገሮች አንዱ ፓትርያርክ ጳውሎስና የተበላሸ ማንነታቸው መሆኑን አልተረዳም? እርሳቸውን ማስተካከል ከሕዝብ መታረቅ መሆኑንስ አልተገነዘበም? ፓትርያርኩ መንግሥት ላይ ኪሳራ ከማምጣታቸው በስተቀር በረዥም ጊዜ ካየነው ጥቅማቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ቤተ ክርስቲያኒቱ ግን ትልቅ ስብራት እየገጠማት ነው። ከዚህ ስብራቷ ለማገገም የአንድ ትውልድ ዕድሜ ሊጠይቅ ይችላል። ምንኩስና ተበላሽቷል፣ ክህነት ረክሷል፣ ጵጵስና ክብር አጥቷል፣ ሊቃውንቱ የትም ወድቀዋል፣ አባቶች ሳይሆኑ ደንደሳም ወይዘሮዎች ቤተ ክህነቱን ተቆጣጥረውታል፣ የቤ ክርስቲያን ገንዘብ የማንም መጫወቻ ሆኗል፣ ምእመናን እረኛ አጥተዋል። ለዚህ ሁሉ ዋነኛው ምክንያት ፓትርያርክ ጳውሎስ ናቸው። ለእርሳቸው መከታ ሆኖ ያስጠቃን ደግሞ መንግሥት ነው። ስለዚህ “ይበቃል” እንላለን። እጅህን ከቤተ ክርስቲያን ላይ አንሣ!!!!!!!!
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)