August 16, 2009

የቅዱስ ሲኖዶስ ሥራ አስፈጻሚ ሥራውን እንዲቀጥል፣ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዲወጣ፣ እኛም የበኩላችንን እናድርግ

ደጀ ሰላም “እነዚህን አበው በስልክም በሰውም ማግኘትና ማነጋገር አለብን፣ ‘አይዟችሁ፣ በርቱ’ ማለት አለብን” ብላ ታምናለች!!!

(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 16/2009) ያለፈው የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ለጥቅምት ካደረ ወዲህ አጀንዳው መቀዝቀዝ የጀመረ ይመስላል። አንዳንዶች ተስፋ በመቁረጥ፣ አባቶች ላይም ጥርጣሬያቸውን በማስፋት እንዲያውም የሃይማኖቱን ነገር ችላ እስከማለት ደርሰዋል ይባላል። የማፊያው ቡድን ብቻ የያዘውን ይዞ “ጥቅምት እንዳትመጣ ባይጸልዪም” ያኔም ቢሆን ጥቅሙን ሳያስነካ፣ ወንበሩን ሳያስደፍር፣ ዝርፊያውን ለመቀጠል ቀንተሌት እየሠራ ነው። ሕብረትም አለው። ሕብረት የሌለውና አሰባሳቢ ያጣው ለቤተ ክርስቲያን የሚያስበው ወገን ነው። ከዚያውም ቢሆን አንዳንዱ “የአባቶችን ገመና አትግለጡ” እያለ ስለ ማፊያው ቡድን እንዳይወራ በጥቅሳጥቅስ ያስፈራራል። ሌላው ደግሞ እኔን ካልነኩኝ እግዜር በፈቀደው ቀን ይፍታው ብሎ መሽጓል። አንዳንዱ ደግሞ ሲያመቸው ከመዘመርና “ሆ” ከማለት ውጪ ነገሩንም ከመጀመሪያው አልሰማውም።

ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሣሣን ምክንያቱ ግን ቅዱስ ሲኖዶስ የመረጠውና ሰባት ብፁዓን አባቶች ያቀፈው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሥራውን የማቆሙ ጉዳይ ነው። ቅዱስ ፓትርያርኩ እንደተናገሩት አንዳንድ የኮሚቴው አባላት የሆኑ አባቶች ራሳቸውን ከኮሚቴው ማግለላቸውን ተናግረዋል። አንዳንዶችም “አንሠራም” ባይሉም እየሠሩ አይደለም። በጠቅላላው ኮሚቴው ማንም “ፈርሰሃል፣ ተበትነሃል” ሳይለው በራሱ ጊዜ እየፈረሰ ነው ወይም ፈርሷል። የቅዱስ ሲኖዶስን እንቅስቃሴ የሚጠላው ክፍል የሚፈልገው ይኽንን ነበር፤ እየሆነለት ነው። እና ሁላችንም እንዲህ ቁጭ ብለን ጥቅምት ትድረስ?
ደጀ ሰላም አንድ ሐሳብ ለመጠቆም ትፈልጋለች። የዚህ ኮሚቴ አባላት ሆኑ አባቶች የተሰጣቸውን ሥራ ሳይሠሩ ማለፍ እንደሌለባቸው ማሳሰብ አለብን ብላ ታምናለች። በርግጥ የነዚህ ብፁዓን አበው ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን ባለፈው ተመልክተናል። ከዚህ በኋላም እንዲህ ዓይነቱ አደጋ እንደማይደርስ ማረጋገጫ መስጠት ባይቻልም መንግሥት ግን ዝም ብሎ ያያል ብላ አታምንም ደጀ ሰላም። አሁን ውይይቱ “መንግሥት ይጠብቃቸዋል ወይስ አይጠብቃቸውም?” የሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ሳይሆን መንግሥት ጠበቃቸውም አልጠበቃቸው አባቶቻችን ግን የጀመሩትን ሥራ አንድ ደረጃ ማስኬድና ለወከላቸው ቅዱስ ሲኖዶስ መልሱን ማቅረብ አለባቸው እንጂ ጥቅምት ላይ ሲገናኙ “ችግር ስለገጠመን ሳንሠራው ቀረን” ማለት ያለባቸው አይመስላትም-ደጀ ሰላም። ለታሪክም ጥሩ አይደለም። በር ሰባሪ ሥራ እንዳይሠራ ማድረግ ከቻለ ነገር ተበላሸ ማለት ነው።
ስለዚህ እነዚህን አበው በስልክም በሰውም ማግኘትና ማነጋገር አለብን፣ “አይዟችሁ፣ በርቱ” ማለት አለብን ብላ ታምናለች -ደጀ ሰላም!!! የኮሚቴው አባላት አባቶች የሚከተሉት ናቸው።
1. ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ (የኮሚቴው ሊቀመንበር)፣
2. ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል (የኮሚቴው ፀሐፊ)፣
3. ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ (አባል)፣
4. ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ (አባል)፣
5. ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ (አባል)፣
6. ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል (አባል)፣
7. ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ (አባል) (ደሴ ላይ ባለው ችግር ምክንያት ከመጀመሪያውኑ በኮሚቴው ውስጥ አልተሳተፉም) ናቸው።
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)