August 6, 2009

"ቅኔ የአብነት ትምህርቱ ፍልስፍና መሠረት": ማኅበረ ቅዱሳን ያዘጋጀው የቅኔ ዐውደ ጥናት

• ስለቅኔ ታሪካዊ አመጣጥና ትርጓሜ የመምህራኑና የተማሪዎቹን ሕይወትን የሚዳስስ ዘጋቢ ፊልምም ተመረቀ
"ቅኔ የአብነት ትምህርቱ ፍልስፍና መሠረት"
(በሔኖክ ያሬድ)
(ሪፖርተር ጋዜጣ: 05 AUGUST 2009):-የቅኔና የግእዝ ትምህርት ከዘመኑ ጋር ማደግና መስፋፋት ሲገባው እድገቱ እየተገታ በመምጣቱ የከፍተኛ ትምህርትና የቤተ ክህነት የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ፡፡
ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 25 ቀን 2001 ዓ.ም. በማኅበረ ቅዱሳን አዘጋጅነት በተካሄደው ዐውደ ጥናት ላይ እንደተመለከተው፣ በተለይ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የአገሪቱ ጥንታዊ ትምህርት ከዘመኑ ጋር ማደግና መስፋፋት ሲገባው እድገቱ እየተገታ መጥቷል፡፡

በተለይ የፍልስፍና፣ የሒሳብና የሥነ ከዋክብት ትምህርቶች እንደሌሎቹ አገሮች ለትውልድ ሳይተላለፉ ጉባኤዎቹ የታጠፉበት ዘመን ላይ ተደርሷል፡፡


"ቅኔ የአብነት ትምህርቱ ፍልስፍና መሠረት" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ዐውደ ጥናት የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም እንደተናገሩት፣ የአብነት (ቆሎ) ትምህርት ቤቶች ከእምነት ተቋምነታቸው ባሻገር የሀገሪቱ የትምህርት፣ የፍልስፍና፣ የሥነ ጥበብ፣ የሥነ ሕንፃና የሥነ ጽሑፍ ተቋማት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

የቅኔ ትምህርት ሃይማኖትን፣ የሀገር ታሪክን፣ የቀድሞ አባቶችና የአሁን ዘመን ሊቃውንት ፍልስፍናና ጥበብ፣ ማኅበራዊ ሒስ የተላለፈበት የዕውቀት ዘርፍ ቢሆንም ተገቢ ትኩረት ባለማግኘቱ እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡

በቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ አገላለጽ፣ የቅኔ ትምህርት የውጭ ሀገር ምሁራን ለጥናትና ምርምር ሲረባረቡበት በኢትዮጵያ በኩል የተሰጠው ትኩረት ግን አናሳ በመሆኑ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ "ቅኔ የግእዝ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ" በሚል ርእስ ጥናት ያቀረቡት ዶክተር ሥርግው ገላው፣ በቅኔ፣ ታሪክ እንደሚጠናበት፣ እንደሚዘከርበትና እንደሚጠበቅበት፣ ከፍተኛ ጥበብ ያለውና ልዩ የአገላለጽ ስልት በየዘመናቱ እያሳየ መሆኑን፣ በአሁን ዘመን ግን የኅብረተሰቡ ድጋፍ በመቋረጡ የቅኔ ትምህርት ቤቶች እያሽቆለቆሉ መምጣታቸው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ቀደም ሲል የነበረውን ደረጃ አጥቶ እየተዘጋ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግእዝ ቋንቋንና ቅኔውን አስተባብሮ በ24 የግንኙነት ጊዜ (ክሬዲት ሀወርስ) ትምህርት ይሰጥበት የነበረበት ሁኔታ አሁን በሁለት የግንኙነት ጊዜ መገደቡና በሥነ ትምህርት ኮሌጅም ግእዝ ከሥርዓተ ትምህርቱ እንዲወጣ መደረጉን ዶ/ር ሥርግው ጠቁመዋል፡፡ ሌሎች ሀገሮች ዘመናዊ ትምህርትን በራሳቸው ነባር ትምህርት ላይ ተመሥርተው መገንባታቸው ለስርፀትም ሆነ ለስኬት እንዳበቃቸው ያመለከቱት ዶ/ር ሥርግው፣ በኢትዮጵያ ግን የረዥም ጊዜ የአገሪቱን የትምህርትና የጥናት ሂደት ወደ ኋላ መጣሉ አግባብ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ትምህርት ኮሌጅ ቀደም ሲል የተቀረጸው ለአማርኛና ትግርኛ ተማሪዎች ይሰጥ የነበረው የግእዝ ትምህርት፣ ክፍሉ ለምን እንዳስወገደው ግልጽ አይደለም ያሉት መምህሩ፣ የውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ለግእዝ የሰጡትን ትልቅ አክብሮት ያህል ሊነፈገው እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡

"በግእዝ ሥነ ጽሑፍ ላይ በአብዛኛው የሠሩትና ታሪካችንን የሚያስተምሩን የውጮቹ ናቸው፡፡ ከእኛው ግእዝ ወስደው ግእዙንና ታሪካችንን አጥንተው ነው የሚያስተምሩን፡፡ እኛ ግን በተገላቢጦሹ የምንማርበት አንዳችም ምክንያት ያልታየን ግእዝን ለመረዳት ስላልቻልን ነው" ብለዋል፡፡

ቅኔና ሥነ ቃል

ቅኔ በግጥም የሚሰጥ ራሱን የቻለ የትምህርት ዓይነት ነው፡፡ የራሱ ሕግጋትም አሉት፡፡ ሰዎች በሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ክስተቶች፣ ሐዘን ይሁን ደስታ ሁሉንም የሚያሳዩበት የጥበብ ዘርፍ ነው፡፡

ከሃይማኖታዊ ይዘት ባሻገር የአገሪቱ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችም በቅኔ ይዳሰሳሉ፡፡ ዶ/ር ሥርግው ባቀረቡት ጥናት ላይ በምሳሌነት እንደጠቆሙት፣ በመካከለኛው ዘመን ሰምና ወርቅ የሌለው ደረቅ ቅኔ ታሪክ ተመዝግቦበታል፡፡

በ16ኛው ምእት ዓመት ግራኝ አህመድ የተነሳበት ጊዜ ነበር፡፡ ማዕከላዊ መንግሥቱን ይመሩ የነበሩት አፄ ልብነድንግል ግራኝ አህመድ በሚያሳድዳቸው ጊዜ፣ ለሠራዊታቸውና ለሕዝባቸው መልዕክት ያስተላለፉት በቅኔ ነበር፡፡

ዓይነቱ "ደረቅ ቅኔ" የተሰኘውም እንደ ዛሬ ዘመን ግጥሞች ሰምና ወርቅ የሌለው በመሆኑ ነው፡፡ "ስለ እናንተ የታመመውና የሞተውን ስሙን አትካዱ፡፡ ኢአማኒ ቢማርካችሁ፣ ሰይፍም ቢያሰቃያችሁ፣ የግፉ ዋጋ ወደ ፊት ይጠብቃችኋልና ስሙን አትካዱ" የሚል ነበር፡፡

ቅኔዎች ለይዘታቸው ማጠናከሪያ ከሚጠቀሱት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሌሎች ታሪካዊ ድርሳኖች ሌላም ሥነ ቃልን የሚጠቀሙም ሞልተዋል፡፡

ሊቃውንቱ፣ ኅብረተሰቡ የቅኔን መንገድ በቅርበት እንዲያውቅ ለማድረግ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍቱ ሌላ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚዘወተሩ ሥነ ቃሎችን (ተረትና ምሳሌዎችን) በቅኔዎቻቸው ያስገቡ ነበር፡፡

"ቅዱሳት መጻሕፍቱን የሚያውቁት ሁሉም አይደሉም፡፡ ሥነ ቃልን ሁሉም ያውቀዋል፤ ሰው ግእዙን ከቻለና አካሄዱን ከተረዳ ከሥነ ቃሉ በመነሳት ብዙ ሰዎችን ማሰልጠን ይቻላል፡፡" የሚሉት ዶ/ር ሥርግው ለማሳያነት የሚከተለውን ጠቅሰዋል፡፡

ዐፄ ምኒልክ ወራሪውን የኢጣሊያ ሠራዊት ለማስወገድ ወደ ዓድዋ ሲዘምቱ ወሎ ውስጥ እረፍት አድርገው ነበር፡፡ በእንግድነት ካደሩበት ቤት ሲወጡ ለባለቤቱ ሴት አገልጋይ (አመት) ሰጥተው ነበር የሄዱት፡፡ ድል አድርገው ሲመለሱ ያገኟቸው ባለቤቱ ሌላ ሴት አገልጋይ ጨምሩልኝ ለማለት ቅኔውን ተቀኙ፡፡

" ምኒልክ ሠዊት ዘትፈሪ ምእተ
ድግመኒ ዐመተ ዐመተ፡፡"
(መቶ መቶ የምታፈራው ምኒልክ እሸት
ዓመት ዓመት ድገመኝ)

የእሸት ወቅት ደርሶ እሸቱ ከተበላ በኋላ "ዓመት ዓመት ድገመኝ" የሚሰኝ አባባል አለ፡፡ ይህን ብሂል ባለቅኔው ይዞ በአፄ ምኒልክ ከደረሰለት በረከት ጋር አያይዞ አቀረበው፡፡ (ዐመት በዓይኑ ዐ ሲነበብ ዘመንን፣ በአሌፉ "አ" ሲነበብ ደግሞ ሴት አገልጋይ ማለት ነው"፡፡

በዐውደ ጥናቱ፣ ስለ ቅኔ አገልግሎትና ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ማብራሪያ በሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሳን መምህር ደሴ ቀለብ አገላለጽ፣ በርካታ ሊቃውንት ያፈራው፣ ቀደም ሲል ከተማሪው ብዛት የተነሳ በትልቅ ገበያ የሚመሰለው የዋሸራ ቅድስት ማርያም የቅኔ ማስመስከሪያ ጉባኤ ቤት፣ ዛሬ በጣት የሚቆጠሩ ተማሪዎች ብቻ ቀርተውታል፡፡ በአሁን ሰዓት አሉ የሚባሉ ጥቂት የቅኔ ትምህርት ቤቶች ይህ እጣ ፈንታ ሳይደርስባቸው ሕዝቡና የሚመለከታቸው ተቋማት ምንነቱንና ጠቀሜታውን ተገንዝቦ እንዲንከባከባቸውና እንዲጠብቃቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በዐውደ ጥናቱ ላይም ስለቅኔ ታሪካዊ አመጣጥና ትርጓሜ የመምህራኑና የተማሪዎቹን ሕይወትን የሚዳስስ ዘጋቢ ፊልምም ተመርቋል፡፡

ፊልሙ የቅኔ ትምህርት ለሃይማኖት መጎልበት፣ ከሥነ ጽሑፍና ከትርጓሜ መስፋፋት አኳያ ያለውን ድርሻ የሚዘግብና ስመጥር የቅኔ ሊቃውንትና ትምህርት ቤቶችን የሚያስተዋውቅ ነው፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)